Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡  ጦርነቱ ያስከተለው ውድመት በክልሉም ሆነ በአገር ደረጃ ከፍተኛ የሚባል ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አድርሷል፡፡ በትግራይ ክልል በተለያዩ ዘርፎች ዕድገት ይታይባቸው የነበሩ ቢዝነሶች ቁልቁል እንዲወርዱ አድርጓል፡፡ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ጦርነት ባይኖርም በጦርነቱ የወደመውን ኢኮኖሚና መሠረተ ልማት ወደነበረበት ለመመለስ ብዙ ሥራ ይጠይቃል፡፡ አሁን ችግሩን ለማቃለል ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ከጉዳቱ ስፋት አንፃር ስብራቱን በቶሎ ለመጠገን እየተቻለ አይደለም፡፡ የሰሜኑ ጦርነት በዋናነት የትግራይ ክልልን በቀዳሚነት የሚጠቅስ ቢሆንም፣ አጎራባች ክልሎችንም በእጅጉ ጎድቷል፡፡ በትግራይ ክልል የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር የሰላም ስምምነቱ ከተደረገም በኋላ የተጎዳውን ኢኮኖሚ ወደነበረበት ለመመለስ አሁንም ብዙ ሀብትና ጉልበት የሚፈልግ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡ በክልሉ የደረሰውን ጉዳትና መፍትሔዎችን ያመላከተ አንድ የዳሰሳ ጥናት፣ ከሥራ ውጪ የሆኑ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችንና ቢዝነሶችን ወደ ሥራ ለመመለስ በልዩ ሁኔታ የተለያዩ ዕርምጃዎች የሚያስፈልጉ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ መንግሥት ፖለቲካዊ ውሳኔ ጭምር በመውሰድ ችግሩን ለመፍታት ካልተቻለ፣ ከዚህ በኋላ የበለጠ ችግር ሊከተል እንደሚችልም የቀረበው ጥናት ያመለክታል፡፡ በቅርቡ ይፋ የተደረገውን ይህንን ጥናት በዋናነት ያስተባበሩትና ጥናቱንም ያቀረቡት የፋይናንስ ባለሙያው አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ በጥናቱ ዙሪያና አሁን አለ የሚባለው የክልሉ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ላይ ዳዊት ታዬ ከእሳቸው ጋር ያደረገው አጭር ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡ 

ሪፖርተር፡- በሰሜን ኢትዮጵያ በተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ በተለይ በትግራይ ክልል የደረሰውን ውድመት በተመለከተ አንድ ጥናት አቅርባችሁ ይፋ አድርጋችኋል፡፡ የጥናታችሁ አጠቃላይ ይዘት ምን ነበር? ምንስ አመለከተ?

አትክልቲ (ዶ/ር)፡- ከፊል ጥናት ነው ያደረግነው፡፡ ምክንያቱም ሙሉ ጥናት ለማድረግ ራሱን የቻለ ሰፊ ሥራ ይጠይቃል፡፡ በመንግሥትም ሆነ በሌላ አካል ጥልቅ ጥናት የሚፈልግ ነው፡፡ እኛ የተወሰነ ጉዳይ ላይ ጥናት አድርገን ከተለያየ ቦታ ዳታ ወስደን የሠራነው ነው፡፡ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ያለውን ችግር ሊያሳይ የሚችል ነው፡፡ ለምሳሌ ከአሁን በፊት በክልሉ ያለው ኢኮኖሚ ምን ነበር በተለይ ከጦርነቱ በፊት የነበረው ይዘት ምን ይመስል ነበር? ከሚለው ተነስተን ነው ጥናታችንን ያደረግነው፡፡ ችግሩ በብዛት ጎልቶ የታየባቸው የትኞቹ ናቸው? የሚለውን ዓይተናል፡፡ የጎላ ችግር ታይቶባቸዋል የተባሉ የኢኮኖሚ ዘርፎችንም በጥናቱ ለማካተት ተሞክሯል፡፡ ለምሳሌ በ2011/12 ዓ.ም. የክልሉን የግብርና ምርታማነትን የተመለከተውን ዳታ ወስደን ስናይ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ተመጣጣኝ የሆነ የልማት ሥራ የሚታዩበት ክልል እንደነበር መረዳት ይቻላል፡፡ በእርሻ፣ በኢንዱስትሪ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ አምራች ዘርፎች ሰፋፊ ሥራዎች የነበሩበት ክልል እንደነበር መረጃው ያሳያል፡፡ በቱሪዝም ዘርፍም ዕድገት እያሳየ መጓዙን ያገኘናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እንዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎች ደግሞ በክልሉ የነበረውን የደኅንነት ምጣኔን ከጊዜ ወደ ጊዜ በእጅጉ እንዲቀንስ አድርገው ነበር፡፡  እ.ኤ.አ. የ1991 የዓለም ባንክ ሪፖርት እንደሚያሳየው የትግራይ ክልል የድህነት መጠን ወለሉ 65 በመቶ ነበር፡፡ ይኸው የዓለም ባንክ ሪፖርት ወለል ምጣኔው ወደ 27 በመቶ እንደወረደ ያሳያል፡፡ አሁን ግን እንደገና የድህነት ወለሉ ሽቅብ የወጣበት ሁኔታ መከሰቱን ጥናታችን አሳይቶናል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በክልሉ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች የነበሩ እንቅስቃሴዎች በጦርነቱ ምክንያት በመገታታቸው ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ጦርነት ምን ያህል ጎጂ ስለመሆኑና ጉዳቱን መልሶ ለማከም በክልሉ የደረሰው ከፍተኛ ውድመት እንደ ማሳያ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በዳሰሳ ጥናታችሁ ጦርነቱ ምን ያህል ጉዳት አድርሷል ብላችሁ ታምናላችሁ? አኃዛዊ መረጃዎችስ ምን አሳዩዋችሁ?

አትክልቲ (ዶ/ር)፡- ይህ በፌዴራል መንግሥትም ሆነ በሌሎች አካላት እንደተገለጸው ጉዳቱ የገዘፈ ስለመሆኑ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ የእርሻ ዘርፉን ለብቻው ነጥለህ ስታይ፣ በአሁን ወቅት በክልል የእርሻ ሥራ እየተሠራ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ለዚህ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው በአነስተኛ መሬት ላይ ያርሱ የነበሩ አርሶ አደሮች አብዛኞቹ በጦርነቱ ምክንያት የእርሻ መሣሪያቸውን አጥተዋል፡፡ ሞፈርና ቀንበርን ጨምሮ ሌሎች መሣሪያዎቻቸው እጃቸው ላይ የለም፣ በመሆኑም እያረሱ አልነበሩም፡፡ ይህ ለምርት መቀነስ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ የግብርና ቢሮ ጥናትም ያሳየን ለእርሻ ሥራው መስተጓጎሉን፣ አሁንም ብዙዎች ወደ እርሻው ያልተመለሱባቸውን በርካታ ምክንያቶች ዘርዝሯል፡፡ ሌላው ቀርቶ ለግብርና ዘርፍ አጋዥ ይሆናሉ ተብለው የተሠሩ የግብርና ማሠልጠኛዎች፣ የግብዓት አቅራቢዎች፣ የግብዓት መቆጣጠሪያና የፀረ ተባይ መቆጣጠሪያ በሙሉ ከሥራ ውጭ ሆነዋል፡፡ ዘመናዊ ግብርናን ለማስፋት ተብለው እየቀረቡ የነበሩ ትራክተሮች፣ ኮምባይነሮችና የመሳሰሉት በጦርነቱ ምክንያት እስከ 81 በመቶ የሚሆኑት ወድመዋል፡፡ ስለዚህ የግብርናው ዘርፍ በእጅጉ ተጎድቷል፡፡ አርሶ አደሩ አሁንም ወደ እርሻው አልተመለሰም፡፡ በቅርቡ የወጣው የኦቻ ሪፖርት እንደሚያሳየው 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑት ተፈናቅለዋል፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች ምርት ላይ ሳይሆኑ ተረጂ ሆነዋል፡፡ ስለዚህ ጦርነቱ በክልሉ ምርትና ምርታማነት ላይ በከፍተኛ ጎድቷል፡፡ 

ሪፖርተር፡- እነዚህ አርሶ አደሮች አሁንም ወደ እርሻቸው አልተመለሱም ማለት ነው?

አትክልቲ (ዶ/ር)፡- አልተመለሱም፣ በመንግሥት ደረጃ ግን እየተነጋገሩበት ነው፡፡ የተፈናቀለው ሕዝብ በአብዛኛው አልተመለሰም፡፡ ተረጂ ሆኖ በተለያዩ ቤተሰቦቹና በትምህርት ቤት አካባቢ ተጠልሎ ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- የእርሻ ሥራው የለም ማለት ይቻላል? አንዳንድ እንቅስቃሴዎች እየታዩ ነውና ሙሉ ለሙሉ እንዴት የለም ሊባል ይችላል?

አትክልቲ (ዶ/ር)፡- እርሻው አለ፣ እየተሠራ ያለው ግን በተወሰነ አካባቢ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ከምዕራብ ትግራይና ራያ አካባቢ የተፈናቀሉት ተመልሰው እያረሱ አይደለም፡፡ ከእነዚህ አካባቢዎች ውጪ በአብዛኛው ይታረሱ የነበሩ መሬቶች እየታረሱ አይደለም፡፡ ስለዚህ ችግሩ የከፋ ነው፡፡ ስለዚህ ሌላ ከጦርነቱ በኋላ ደግሞ ድርቅ ተከሰተ፡፡ ሊያመርቱ ይችሉ የነበሩ አካባቢዎችም ድርቁ በበቂ እንዳያመርቱ ስላደረገው እንደገና ለከፍተኛ ችግር እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል፡፡ በቅርቡ የወጣ ሪፖርትም ወደ 1.8 ሚሊዮን የሚሆን የክልሉ ሕዝብ ተረጂ ሆኗል፡፡ ይህን ያህል ተረጂ ካለ እርሻው መዳከሙን ነው የሚያሳየው፡፡ የኮሜርሻል እርሻ ይካሄድባቸው የነበሩ አካባቢዎች በሙሉ ሥራ ላይ አይደሉም፡፡ አሁን ገና በተወሰነ ደረጃ ሥራ ለመጀመር እየተንቀሳቀሱ ካሉት ውጪ የሚታይ ነገር የለም፡፡ ስለዚህ በዚህ አካባቢ ያለውን ችግር በጥልቀት አጥንቶ የመፍትሔ ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልተደረገ ችግሩ እየተወሳሰበ ነው የሚሄደው፡፡ በተለይ ከአሁን በኋላ በጣም እየተለጠጠ የሚሄድበት አንዱና ትልቁ ምክንያት ጦርነቱ የፈጠረው በከፍተኛ ደረጃ የሥራ አጦች ቁጥር በመጨመሩ ነው፡፡ የሥራ አጥ መብዛት የበለጠ አለመረጋጋት እየፈጠረ ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ሊኖር የሚችለው አለመረጋጋት ደግሞ ሊፈጥረው የሚችለውን ችግር ለመፍታት ፈጣን ዕርምጃ ያስፈልጋል፡፡  

ሪፖርተር፡- የክልሉ ኢኮኖሚ በመጎዳቱ በአገር ደረጃም ጉዳት እንዳስከተለ ስለሚታመን፣ ክልሉ ለአጠቃላይ አገራዊ ምርት (ጂዲፒ) የነበረው አስተዋጽኦ ምን ያህል ነበር? አሁንስ?

አትክልቲ (ዶ/ር)፡- ደረጃውን ለማየት ሞክረን ነበር፡፡ ይህንን በተጨባጭ መረጃ ደግፎ የጠራ መልስ ለማግኘት ራሱን የቻለ ቢሮ ተቋቁሟል፡፡ ቢሮው ይህንን ዳሰሳ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ጂዲፒ የእርሻው፣ የኢንዱስትሪው፣ የጥቃቅንና አነስተኛው፣ የቱሪዝምና የሁሉም ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ውጤት ነው፡፡ እነዚህ ተደምረው ነው ጂዲፒውን የሚያሳዩትና አሁን በቁጥር ማስቀመጥ ይቸግራል፡፡ ነገር ግን ቀንሷል ወይም አልቀነስም የሚለውን ለማየት ግን አስቸጋሪ አይደለም፡፡ የክልሉ ኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ስለገባ ዲጂፒው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማድረሱ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል በትግራይ ትልልቅ ኢንተርፕራይዞች ተብለው 45 ኢንዱስትሪዎች ነበሩ፡፡ በመካከለኛ ደረጃ የተመዘገቡ ኢንተርፕራይዞች 891 ነበሩ፡፡ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች 5,525 ነበሩ፡፡ በማይክሮ ደረጃ ደግሞ 73 ሺሕ ነበሩ፡፡ እነዚህ ተቋማት 425 የሚሆኑ የተለያዩ ቢዝነሶች ዓይነቶችን ይሠሩ እንደነበሩ ነው በጥናታችን ወቅት ያገኘነው መረጃ የሚየሳየው፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ (ኢንፖርት ሰብስቲቲውሽን) ምርቶችን ለማምረት ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ይሸጋራሉ ተብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 6,378 ኢንተርፕራይዞችም ዕጣ ተመሳሳይ ነው፡፡ እነዚህ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ ምርቶችን ያመርታሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው ኢንተርፕራይዞች በሙሉ የመንግሥት ድጋፍ ነበራቸው፡፡ አሁን ይህ ድጋፍ የለም፡፡ የገበያ ትስስር፣ የብድር፣ የሥልጠናና የመሳሰሉት ድጋፎች አሁን አለመኖራቸው ተበትነው እንዲቀሩ ስላደረጋቸው ወደ ሥራ ሊገቡ አልቻሉም፡፡

ሪፖርተር፡- ከእነዚህ በርካታ ኢንተርፕራይዞች ውስጥ ከጦርነቱ በኋላ ምን ያህል ወደ ሥራ ገብተዋል ማለት ይቻላል?

አትክልቲ (ዶ/ር)፡- እኔ በተወሰኑ ዘርፎች ላይ ባሰባሰብኩት መረጃ በተለይ ትልቅ ኢንተርፕራይዝ በመባል የሚጠቀሱት መቀሌ ካሉት ከተወሰኑት በስተቀር አብዛኛዎቹ ወደ ሥራ አልገቡም፡፡ ኢንዱስትሪ ዞንና አካባቢ የነበሩት ብዙዎቹ እየሠሩ አይደለም፡፡ አንድ ሁለት የሚሆኑት ባላቸው ግብዓት ሥራ የጀመሩ ቢሆንም ብዙዎቹን ግን ሥራ ማስጀመር አልተቻለም፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ ያልገቡበት ዋነኛ ምክንያት ምንድነው?

አትክልቲ (ዶ/ር)፡- በርካታ ችግሮች ናቸው፡፡ አንደኛው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ በኤፈርት ሥር የነበሩ ኩባንያዎችም ብዙዎቹ ወደ ሥራ አልተመለሱም፡፡ እንደ አልመዳ ጨርቃ ጨርቅና መድኃኒት ማምረቻዎች ሁሉ ወደ ሥራ አልገቡም፡፡ ሌሎች የግለሰብ  ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እየተመለሱ አይደለም፡፡ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ለመሰማራት በግንባታ ሒደት ላይ የነበሩትንም ካየን ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ እነዚህ በጅምር የቀሩ ፕሮጀክቶች በአሁኑ ወቅት ግንባታቸው አልቆ ወደ ሥራ መግባት ነበረባቸው፡፡ ማምረት መጀመር ነበረባቸው፡፡ ለምሳሌ የጠርሙስና ብርጭቆ ፋብሪካ ግንባታው ተጀምሮ ቆሟል፡፡ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው ሲነገርለት የነበረው ግዙፍ የፒቪሲ ፋብሪካ የግንባታ ሥራው ቆሟል፣ ሌሎችም አሉ፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሊባል የሚችለው እጅግ ጥቂት የሚባሉት እየሠሩ ቢሆንም አብዛኛው ግን እንደቆሙ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተ ባካሄዳችሁት ጥናት በተለያዩ ኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ የነበሩና አምራች የሚባሉ ተቋማት መልሰው ወደ ሥራ ያልገቡበት ምክንያት ምን እንደሆነ አላሳየም? ችግሩ የገጠማቸው ባለንብረቶች ምን የሚል ምላሽ ሰጥተዋል?

አትክልቲ (ዶ/ር)፡- ትልቁ ችግር ሆኖ የሚገለጸው ሥራውን ለማስቀጠል የብድር አቅርቦት የለም የሚል ነው፡፡ በሁሉም ቢዝነስ ላይ ያሉ የክልል የግል ዘርፍ ተዋንያን ችግራቸው አድርገው እየገለጹ ያሉት ከብድር አቅርቦት እጥረት ጋር የተያዘ ነው፡፡ በተለይ ጅምር ሥራዎችን ለማስቀጠል ፋይናንስ ሲጠየቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው የ14 በመቶ የብድር ገደብ በምክንያትነት እየቀረበ ብድር ለማግኘት አልተቻለም፡፡ ከዚህም ሌላ ባንኮች የራሳቸው የብድር አስተዳደር ቢኖራቸውም በሚፈለገው መጠን ብድር ለመልቀቅ አልቻሉም፡፡ ያነጋገርናቸው አብዛኞቹ የግሉ ዘርፍ አባላት እንደገለጹት የጠየቁትን ብድር ለማግኘት ወረፋ ጠብቁ እየተባሉ መሆኑን ነው፡፡ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አሁን ብድር እያቀረበ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ እንደ ደደቢት ያሉ ማይክሮ ፋይናንሶችም ውስን ብድር እየቀረቡ ነበር፡፡ እነሱም ቢሆኑ ግን አሁን ያላቸውን ገንዘብ ጨርሰው ተበዳሪዎች ወረፋ ይዘው እንዲጠብቁ ስለተነገራቸው እየጠበቁ ነው፡፡ ሌሎች ባንኮች የጀማመሩዋቸው አንዳንድ ነገሮች ቢኖሩም በቂ ብድር እየቀረበ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ባንኮች ብድር ለመስጠት እየተቸገሩበት ነው ተብሎ ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ ቀደም ብሎ በክልሉ ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች የተሰጠው ብድር ካለመመለስ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች የተሰጠው የብድር መጠን ምን ያህል ነው?

አትክልቲ (ዶ/ር)፡- አዎ፣ ትልቅ ችግር የሆነው ይህ ነው፡፡ ቀደም ብለው የወሰዱት ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር አለ፡፡ የዚህ ብድር አለመከፈል ተጨማሪ ብድር እንዳያገኙ እያደረጋቸው ነው፡፡ በእኛ ጥናት ያገኘነው መረጃ የሰላም ስምምነቱ በተፈጸመበት ወቅት፣ በክልሉ ላሉ ሥራዎች ባንኮች ሰጥተውት የነበረው የብድር መጠን 32 ቢሊዮን ብር አካባቢ ነበር፡፡ ይህ ገንዘብ ለባንኮች አልተመለሰም፡፡ ይህ ብድር በአማካይ የወለድ መጠን በየዓመቱ ወደ ስድስት ቢሊዮን ብር ወለድ እየቆጠረ ነው፡፡ ይህ ተደማምሮ አሁን ከ52 ቢሊዮን ብር በላይ ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህንን ያህል ብድር በክልሉ ካለ ከፍተኛ ጫና አለ ማለት ነው፡፡ ብድሩ ይህን ያህል ደረጃ በመድረሱና ለመመለስ አሁን ያሉበት ተጨባጭ ሁኔታ ፈጽሞ የማይፈቅድላቸው በመሆኑ ተበዳሪዎች ላይ ጫና እየፈጠረ ነው፡፡ ይህንን ጫና ለማቃለል መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጥ በተለያዩ መንገዶች ጥያቄዎች ስለቀረቡ አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ሆኖም ይህ የብድር ጫና ማኅበራዊ ቀውስ እየፈጠረ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ብድሩን ካልመለሱና ተጨማሪ ብድር የማያገኙ ከሆነ መጨረሻው ምንድነው?

አትክልቲ (ዶ/ር)፡- ችግሩ በተለያየ ሁኔታ የሚገለጽ ነው፡፡ ለምሳሌ አዲስ ብድር ማግኘት የቻሉ  ተበዳሪዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የብድር ገደብ ይዟቸዋል፡፡ የቆዩት ቢዝነሶች ደግሞ ተመልሰው ወደ ሥራ እንዳይገቡ ቀድሞ የነበረባቸውን ብድር ባለመክፈላቸው ተጨማሪ ብድር የማግኘት ዕድላቸው ጠቧል፡፡ ይህ ጫና ደግሞ በቀላሉ ወደ ሥራቸው ሊያስገባቸው አይችልም፡፡ በሁሉም ዘርፎች የሚታይ ነውና በልዩ ሁኔታ መፍትሔ ሊሰጠው አልቻለም፡፡ በአጠቃላይ ኢኮኖሚውን ይጎዳዋል፡፡ ቱሪዝምን ነጥለህ ብታየው እንኳን በክልሉ ተስፋ ሰጪ ዘርፍ ነበር፡፡ በ2011 ዓ.ም. ወደ 125 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቶበት ነበር፡፡ እዚህ የደረሰው በየዓመቱ ያልተቋረጠ ዕድገት በማሳየት ነበር፡፡ አሁን ግን ዜሮ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ቢያንስ እንዲህ ያሉ ዘርፎች በቀላሉ ደግፎ ውጤታማ ማድረግ ይቻላል፡፡ ለቱሪዝሙ ማነቆ የሆኑ ነገሮች በቀላሉ ይፈታሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ምክንያቱም አገልግሎት ስለሆነ ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶችና አስጎብኚዎች ሁሉ ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡ ኢኮኖሚውንም ማነቃቃት የሚችልበት ዕድል ይፈጥራል፡፡   

ሪፖርተር፡- በአጠቃላይ ሲታይ ግን በክልሉ የደረሰው ኢኮኖሚያዊ ውድመት በገንዘብ ሲተመን ምን ያህል ይሆናል ተብሎ ይገመታል?

አትክልቲ (ዶ/ር)፡- ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልህ በመንግሥት ጭምር ጥልቅ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ ጉዳቱ ሰፊ ለመሆኑ ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ አሁንም ኢኮኖሚው ተቀዛቅዟል፡፡ በተለይ የሥራ አጡ ቁጥር ተበራክቷል፡፡ የሥራ አጡ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ይህንን ሁሉ ሥራ አጥ ቦታ ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል፡፡ የኑሮ ውድነቱ ላይ የሥራ አጥ ቁጥር መብዛቱ ደግሞ ነገሮችን ያወሳስባል፡፡ ስለዚህ አስፈላጊው ርብርብ ተደርጎ የተጎዱ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ የቆሙ ቢዝነሶችን ወደ ሥራ ማስገባት ካልተቻለ ነገሮች ከባድ መሆናቸው አይቀርም፡፡

ሪፖርተር፡- ጥናቱን ባቀረቡበት ወቅት ከሥራ አጥ ቁጥር መበራከት ጋር በተያያዘ ሲገልጹ አንድ የጠቀሱት ነገር ነበር፡፡ ይህም አሁን በትግራይ ክልል ያለውን ሥራ አጥ አደገኛ የሚያደርገው የተማረና ታጥቆ የነበረ ሥራ አጥ መሆኑ ነው ብለዋል፡፡ እንዲህ ያሉበት ምክንያት ምንድነው?

አትክልቲ (ዶ/ር)፡- አዎ፡፡ አሁን ያለው ሥራ አጥ የተማረ ነው፡፡ ወታደራዊ ትምህርት ያለው፣ የጦር መሣሪያ ታጥቆ የነበረም ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሥራ አጥ ሥራ ፈት ሲሆን ሊያስከትለው የሚችለው ችግር ያሳስባል፡፡ ከአሁን በፊት የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ በጣም ከፍተኛ በነበረበት ወቅት ብዛት ያላቸውና የተማሩ የመንግሥት ሠራተኞችና የፋብሪካ ሠራተኞች ናቸው፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ላይም ያሉት ቢሆኑ የተማሩ ናቸው፡፡ ጦርነቱ ሲመጣ ግን አማራጭ ስላልነበር በቀጥታ ትጥቅ ይዘው ወደ ጦርነቱ ገብተዋል፡፡ ታጥቀው የነበሩ ሰዎች ጦርነቱ ካበቃ በኋላ አንዳንዶቹ በራሳቸው ተመልሰዋል፡፡ በመንግሥት የተቀነሱም አሉ፡፡ ከተመለሱ በኋላ ግን ምንም ሥራ የላቸውም፡፡ እነዚህን ኢኮኖሚው ካልተቀበላቸው እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ክላሽ ብቻ አይደለም የሚያውቁት ታንከኛ የነበሩ ናቸው፡፡ መድፈኛ ናቸው፡፡ የተለያዩ ሚሳይሎች ላይ ሲሠሩ የነበሩ ናቸው፡፡ እንዲህ ያለ የጦር ልምምድ ያለው ሰው ሲመለስ ሥራ አጥ ከሆነ ችግሩ ከፍተኛ ነው፡፡ ተቀጥሮ መሥራት ካልተቻለ ወደ ሌላ አማራጭ ሊሄድ ስለሚችል ውጤቱ መጥፎ ነው ለማለት ነው፡፡ ለክልሉም ሆነ ለአገሪቱ በጣም ከፍተኛ ጥፋት ሊያመጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ወደ ሥራ ለማስገባት የመልሶ ግንባታው ወሳኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ባጠኑት ጥናት አሉ ያሉዋቸውን ችግሮች ከማመላከት ባሻገር፣ መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦችንም ሰንዝረዋልና እንዲህ ያለውን ሥር የሰደደ ችግር ለመፍታት መፍትሔው ምንድነው?

አትክልቲ (ዶ/ር)፡- አሁን መሆን ያለበት መጀመሪያ እስከ 2011 ዓ.ም. ድረስ ሥራ ላይ የነበሩት በሙሉ ወደ ነበሩበት መመለስ ነው፡፡ በእርሻም ሆነ በቢዝነስ ዘርፍ በሙሉ ወደ ነበሩበት የመመለስ ሥራ መከናወን አለበት፡፡ በዚህ ከፍተኛ የሆነ የመልሶ ማቋቋም ሥራ ያስፈልጋል፡፡ ልዩ የሆነ የልማት ፓኬጅ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ የልማት ፓኬጅ የሚተገበሩ ሥራዎች የድህነት ቅነሳን ታሳቢ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ እንዲህ ያለውን ሥራ ከመንግሥት ውጪ ማንም ሊሠራው አይችልም፡፡ የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት ተባብረው ኢኮኖሚውን ማዳን ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህም የፖለቲካ ውሳኔ መወሰን የግድ ነው፡፡ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የፖለቲካ ውሳኔዎች ከሌሉበት በመደበኛው አሠራር መለወጥ አይቻልም፡፡ ከሙስናና ከብልሹ አሠራሮች ነፃ የሆነ  የመልሶ ግንባታ ሊሠራ ይገባል፡፡ በተለይ በቶሎ ወደ ሥራ ሊመለሱ የሚችሉ ዘርፎች ላይ ቅድሚያ በመስጠት ሥራው ቢጀመር ለውጥ ሊመጣ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የቱሪዝም ዘርፉን በቀላሉ ወደ ሥራ ማስገባት ይቻላል፡፡ የአክሱምን አውሮፕላን ማረፊያ ሥራ ማስጀመር ብዛት ያላቸውን ቱሪስቶች መሳብ ያስችላል፡፡ አሁንም ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት ከአዲስ አበባ ብቻ እንዳይመለሱ ማድረግ ይቻላል፡፡ አሁን በትግራይ ያለው ድህነት ሰፊ ነው፡፡ ስለዚህ ድህነት ተኮር የሆኑ ሥራዎች ላይ ለመሥራት የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ትብብር ጭምር የሚጠይቅ ነው፡፡

በተለይ የሥራ አጡን ቁጥር ለመቀነስ ብዙ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ በቅርቡ በአንድ ምሁር ወደ 16 ሺሕ የክልሉ ወጣቶችን ወስዶ ባደረገው ጥናት 81 በመቶ ሥራ አጥ መሆናቸውን አሳይቷል፡፡ ስለዚህ ሥራ አጥነትን ሊቀርፉ የሚችሉ ድህነት ተኮር የሆኑ ሥራዎች ግድ ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻገር ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ የሰላምና ደኅንነት ላይ ችግር የሚያመጡ አንዳንድ የሚታዩ ነገሮች አሉና ይህ እንዳይሠፋ ቀድሞ ሊሠራበት ይገባዋል፡፡ ድህነት ተኮር ሥራዎች ላይ መሥራት ሰላምና ድህነትን ለመጠበቅ ያስችላል፡፡ ይህ አማራጭ የሌለው ነገር ስለሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ መሥራት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ አሁን በትግራይ ያለውን ችግር ለመፍታት ሌላው በብርቱ መታሰብ ያለበት ጉዳይ የብድር ጫናው የሚቃለልበትን መንገድ መፈለግ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ጦርነቱ የፈጠረበት ችግር ሳያንስ የወሰደው ብድር ምን ያስከትልብኝ ይሆን በማለት ጭንቀት ውስጥ ገብቷል፡፡ ንብረቴ በባንክ ይወሰድ ይሆን ይህን እያለ እያፈራ ነው፡፡ ዕዳውን በተመለከተ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት የቆሙትን ቢዝነሶች በመለየት ወደ ሥራ እንዲገቡ ማገዝ የመፍትሔው አንድ አካል ነው፡፡ በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች እየሠሩ ያሉ ብዛት ያላቸው የልማት ሥራዎች በትግራይም እንዲተገበሩ ማድረግንም ይጠይቃል፡፡ በሁለትና በሦስት ዓመታት ውስጥ የታዩ የቴክኖሎጂ ለውጦች ሌሎች ክልሎች እየተጠቀሙባቸው ሲሆን፣ ትግራይ ግን ወደኋላ የቀረ በመሆኑ የመልሶ ግንባታ ሥራው ይህንን ሁሉ ሊያጠቃልል ካልቻለ ትልቅ ክፍተት ይፈጥራል፡፡ ይህንን ሁሉ ነገር ለማድረግ ግን ሁሉንም ነገር ትቶ ወደ ሰላም መመለስ ነው፡፡ የተፈናቀለው መመለስ አለበት፡፡ የሕዝብ ደኅንነት መጠበቅ አለበት፡፡ ወደ ሌላ ግጭት እንዳይገባ ቁርጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ በሆነው ባልሆነው ከመነታረክ ዘላቂ ሰላምና ዘላቂ ልማት የሚያመጡ ሥራዎች ላይ ማተኮር ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በትግራይ ክልል ያሉ ችግሮችን ለማቃለል የቆሙ ቢዝነሶችን ለማስቀጠልም ሆነ ነገሮችን ለማረጋጋት፣ የፌዴራል መንግሥትና የክልሉ መንግሥት በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገር ግን ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ አሁንም መቆራቆሶች ይስተዋላሉ፡፡ ይህ ደግሞ አለመረጋጋትን ሊያስከትልና ሊሠሩ የሚገባቸው ዋና ዋና ጉዳዮችን ሊያሰነካክል ይችላል፡፡ በእርስዎ እምነት እንዲህ ያሉ ነገሮች አያሳስቡም? እንዴትስ መፈታት አለባቸው ብለው ያምናሉ? ግጭትስ እንዳይከሰት መደረግ ያለበትስ  ምንድነው?

አትክልቲ (ዶ/ር)፡- እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ ችግሮችን ስንፈታ የነበርን ነን፡፡ ብዙ የተማሩ ሰዎች አሉ፡፡ ተስማምተን ልንሠራና ልናድግ የምንችልባቸው ብዙ ዕድሎች አሉ፡፡ ስለዚህ በሆነው ባልሆነው ወደ ጥል፣ ወደ ግጭትና ወደ አፍራሽ ነገሮች ከመግባት ሰከን ብሎ በጋራ አገራችንን ወደፊት ሊያራምዳት በሚችሉ ጉዳዮች ላይ መሥራት ግድ ይለናል፡፡ በሰበብ አስባቡ ወደ ጦርነት መግባት አይኖርብንም፡፡ ከዚህ በኋላ ጦርነት ውስጥ መግባት እንደገና የአገሪቱን ጉዳት ማባባስ ነው፡፡ ስለዚህ በሁሉም ወገን ለሰላም ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ማመን ነው፡፡ ሕዝቡን ማክበርና ሊሠሩ የሚገባቸውን ሥራዎች በሚገባላቸው ውለታ መሠረት ከተሠራ ችግሮች በሰላም የማይፈቱበት ምክንያት የለም፡፡ ነገር ግን በሆነው ባልሆነው ነገር ቁርሾ ውስጥ የምንገባ ከሆነ የሕዝቡን ሥቃይ ማባስ ይሆናል፡፡ አገሪቱንም ችግር ውስጥ መክተት ይሆናል፡፡ በሰላም አብሮ ለመሥራት ካልቻልን የእኛን ውድቀት ለሚመኙትም ምቹ እንሆናለን፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት፣ እንዲሁም በየዘርፉ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ ለጋራ ችግሮቻችን የመፍትሔው አካል መሆን አለባቸው፡፡ ለመፍትሔ በትዕግሥት በመነጋገር መሥራት ይገባል፡፡ በየማኅበራዊ ሚዲያው መነቋቆርም ተገቢ አይደለም፡፡ በተለያዩ መንገዶች ወደ ግጭት የሚመሩ ድርጊቶች መቆም ይኖርባቸዋል፡፡ ግጭት ለኢትዮጵያ በፍፁም የሚገባትም የሚያዋጣትም አይደለም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ዘላቂ ጥቅም ያመጣል ብዬ ያሰብኩትን ሥራ ለመተግበር እንደ መሪ መጀመሪያ ቃሌን ማመን አለብኝ›› እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመቀላቀል የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘ 25ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ጉዞው በውጤታማነት ሲራመድ የነበረ ባንክ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት...

‹‹ግጭቶች በሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራዎቻችን ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖና እየተከሰተ ያለውን ሥቃይ እያየን ነው›› ስካት ሆላንደር፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያና የጂቡቲ ዋና...

ከበርካታ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ እንደሆነች ይነገርላታል፡፡ ክፍለ ዘመንን የተሻገረው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ሰሞኑን ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የጀመሩበትን 120ኛ ዓመት ክብረ በዓላቸውን...

‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖሩንን እንቅስቃሴዎች ሊያግዙ የሚችሉ ተቋማት ያስፈልጉናል›› ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር)፣ የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያንና የምሥራቅ አፍሪካን የፋይናንስ ተቋማት መሠረት በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ፣ በበርካታ አጀንዳዎች አማካይነት በተለይ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጎን...