Tuesday, May 28, 2024

በኢትዮጵያና በሶማሊያ ግንኙነት ላይ ሌላ ውጥረት የፈጠረው የፑንትላንድ ጉዳይ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሐሰን ሼክ መሐመድ “ወደ ሌላኛዋ ቤትዎ እንኳን ደህና መጡ” ተብለው በፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ እቅፍ ውስጥ ሲገቡ ታይተዋል፡፡ ሰውዬው ወደ ኬንያ ያቀኑት አንድም ቀጣናዊ አጋር ለመሻት፣ በሌላ በኩልም የሶማሊያን ወቅታዊ ችግር እልባት ለመስጠት እንደሆነ ነው የተነገረው፡፡ በወቅቱ ከፑንትላንድ ራስ ገዝ አስተዳደር ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ውዝግብ ከበድ ያለና ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ማሠለፍ የሚጠይቅ እንደሆነ እንደተረዱ ሲነገር ቆይቷል፡፡ በሌላ በኩል ሶማሌላንድን ማዕከል ያደረገው ከኢትዮጵያ ጋር የፈጠሩት ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብም ሌላው የቤት ሥራቸው መሆኑ ተነግሯል፡፡

በናይሮቢ የቀድሞ የሶማሊያ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን አግኝተው ሲመካከሩ የቆዩት ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ፣ ከፑንትላንድ ጋር የገቡበትን ውጥረት ለማርገብ መፍትሔ ለመፈለግ ስለመጣራቸው ተዘግቧል፡፡ በሌላ በኩል ከኬንያ ፕሬዚዳንት ሩቶ ጋር ቀጣናዊ ውጥረቶችን የተመለከቱ ንግግሮች ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡

ኬንያ ለእንግዳው ጥሩ አቀባበል ነበር ያደረገችው ተብሏል፡፡ በርካታ የዜና ምንጮች የኬንያው ፕሬዚዳንት ሩቶ ሶማሊያን ለከበበው ውጥረት የተሻለ የሚሉትን ሐሳብ ሰጥተዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር የባህር በር ስምምነት እንድታደርግ ኬንያ መጠየቋ ተነግሯል፡፡ ሶማሊያ ለኢትዮጵያ የባህር በር እንድትፈቅድ የሚያደርግ ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር እንድትፈርም ተጠይቃለች፡፡ ኢትዮጵያ ወደብና የባህር ኃይል ሠፈር ለመገንባት የሚያስችል የባህር በር በሶማሊያ መንግሥት በኩል እንዲሰጣት ኬንያ የሶማሊያውን ፕሬዘዳንት ስታግባባ ነበር ተብሏል፡፡ 

ቀጣናውን ወደ መረጋጋት ይመልሳል ብላ ያመነችበትን አዲስ ዕቅድ ኬንያ ስታቀርብ፣  በዕቅዱ መሠረት ሶማሊያና ኢትዮጵያ ከመናቆር ወጥተው በመግባባት መንፈስ የባህር በር ስምምነት እንዲፈራረሙ የሚጠይቅ እንደሆነ ነው የተነገረው፡፡ ኮሪር ሲንጎይ የተባሉት የኬንያ የውጭ ጉዳይ ጸሐፊ ነገሩኝ ብሎ ሮይተርስ ዓርብ ሚያዝያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደዘገበው ከሆነ ቀጣናዊው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ)፣ ሶማሊያንና ኢትዮጵያን የሚያግባባ የባህር በር ስምምነት መቀመር እንደሚችል መመላከቱ ተነግሯል፡፡

የኬንያ ባለሥልጣናት በዚያው በሶማሌላንድ ግዛት ኢትዮጵያ የባህር በሩን እንድታገኝ ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር በቀጥታ በሚካሄድ ስምምነት እንዲፈጸም ነው ያቀዱት። ሶማሊያ ሉዓላዊነቴ ተጣሰ የሚል ስሜት በማታሳድርበት ሁኔታ ጉዳዩ እንዲፈጸም ጠይቀዋል። ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት የፈጠረው ቁርሾም በአዲሱ ስምምነት እንደሚቀረፍ ነው ተስፋ ያደረጉት። የኬንያው ባለሥልጣን ይህን ዕቅድ አገራቸው ለሁለቱም ጎረቤታሞች ማቅረቧን ተናግረዋል፡፡ የኬንያን ሐሳብ እንዲቀበሉት ኢትዮጵያና ሶማሊያ ተጠይቀዋል ያሉት ባለሥልጣኑ፣ በመሪዎቻቸው አማካይነት ፊት ለፊት ተገናኝቶ በገቡበት ውጥረት ዙሪያ እንዲወያዩ የማድረግ ሐሳብም እንደቀረበላቸው ነው የተናገሩት፡፡

ለዚህ የኬንያ ሐሳብ ሶማሊያም ሆነች ኢትዮጵያ ስለሰጡት ምላሽ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ዓርብ ምሽት ድረስ የተባለ ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ ሐሳቡ ተቀባይነት ቢኖረው እንኳን ሶማሌላንድ በዚህ ላይ ሊኖራት የሚችለው አቋምም ከወዲሁ የሚያጠያይቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ባደረገችው ስምምነት የባህር በር ለኢትዮጵያ በመፍቀድ በልዋጩ የሉዓላዊ አገርነት ዕውቅና ከኢትዮጵያ እንደምታገኝ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይህ ከሦስት ወራት በፊት የተፈረመ የመግባቢያ ስምምነት ደግሞ ዝርዝር ቴክኒካዊ ጉዳዮች እየተዘጋጀለት ስለመሆኑና በቅርቡ በሶማሌላንድ ፓርላማም ፀድቆ ለዓለም ይፋ እንደሚሆን ሲነገር ነበር፡፡

በእንግሊዝ የሶማሌላንድ አሊያንስ ማኅበራዊ አንቂና የፖለቲካ ተንታኙ ሻርማርኬ ዓሊ ለአልጄዚራ እንደተናገረው የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን በዚሁ ጉዳይ ስለመጠየቁ ገልጿል፡፡ የመግባቢያ ስምምነቱን ዝርዝር ዕቅዶችና ቴክኒካዊ ጉዳዮች የማዘጋጀቱ ሥራ በአብዛኛው መጠናቀቁን ነግረውኛል ያለው ሸርማርኬ በቅርቡ ይህ ሰነድ ተጠቃሎ በሶማሌላንድ ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚፀድቅ እየተጠበቀ መሆኑን፣ ከአሥር ቀናት በፊት በአልጄዚራ ላይ ተናግሮም ነበር፡፡

ይህ በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ በኩል የመግባቢያ ስምምነቱን ወደ መደበኛ የስምምነት ሰነድነት ለመቀየር የሚደረገው ሥራ በሒደት ላይ እንዳለ ጠቋሚ ሲሆን፣ የመግባቢያ ስምምነቱ ምን ዓይነት ነጥቦችን (ይዘቶች) ይዞ ይመጣል የሚለው ከወዲሁ እያነጋገረ ነው፡፡

ይህ ሥራ ሳይገባደድ ደግሞ ኬንያ አዲስ የስምምነት ሐሳብ ይዛ ብቅ ማለቷ የከዚህ ቀደሙና ሒደቱ በመገባደድ ላይ ያለው የመግባቢያ ስምምነት ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄ እያስነሳ ነው የሚገኘው፡፡ ኢትዮጵያና ሶማሊያ የኬንያን ጥያቄ ተቀብለው አዲስ የባህር በር ስምምነት ወደ መፈራረሙና ወደ መታረቁ የሚገቡ ከሆነ፣ በሶማሌላንድ ዘንድ ክስተቱ የሚፈጥረው ተፅዕኖ የማይተነበይ እንደሚሆን ነው ተንታኞች የሚናገሩት፡፡ ሶማሊያ ኬንያ ባቀረበችው ጥሪ መሠረት በሶማሌላንድ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር የገባችበትን ውጥረት ለማብረድ ብትችል እንኳን የሶማሌላንድን ሉዓላዊ አገር የመሆን ትግልን ግን ማስቆም ትችላለች ወይ የሚለው ጥያቄ በይደር ያለ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሳይቋጭ ደግሞ ከሰሞኑ ሶማሊያ ከፑንትላንድ ጋር የገባችበትን ውጥረት እንዴት ልትፈታው ትችላለች የሚለው ከፍተኛ መነጋገሪያን የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ከሰሞኑ የሶማሊያ ፓርላማ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ማፅደቁ ከባድ ቀውስ ፈጥሯል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያው መፅደቁ በዋናነት ከፑንትላንድ በኩል ከባድ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡

በሶማሊያ እ.ኤ.አ. በ2012 የፀደቀው የሽግግር ጊዜ አስተዳደር ሕገ መንግሥት እንዲሻሻል ዕቅድ ተይዞ ሥራ ከተጀመረ ከራርሟል ነው የሚባለው፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት የአሁኑ የሶማሊያ መሪ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሀመድ በመጀመሪያ ዙር ሥልጣናቸው ወቅት ነበር የፀደቀው፡፡ ያኔ ያፀደቁትን የሽግግር ሕገ መንግሥት አሁን በሁለተኛ ዙር ወደ ሥልጣን ሲመጡ ቋሚ ሕገ መንግሥት አድርገው ሊያፀድቁት ጥረት እያደረጉ ነው የሚል ወቀሳ እየቀረበባቸው ነው፡፡

በሽግግር ጊዜ ሕገ መንግሥት አገራችን እየተመራች ከሚገባው ጊዜ በላይ ቆይታለች፡፡ ከዚህ በላይ ጊዜ መፍጀቱ ትርጉም ስለሌለው በአስቸኳይ ቋሚ ሕገ መንግስት ያስፈልገናል ብለው መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ ይህን የፕሬዚዳንቱን አቋም አንዳንዶች የተቃወሙት ሲሆን ፑንትላንዶች ደግሞ በተለየ ሁኔታ ነው የተቃወሙት፡፡  

የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ኮሚቴውን የሚመሩት ሁሴን አይዶ እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ ለሥስር ዓመታት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል ይላሉ፡፡ በእነዚህ ዓመታት ሦስት ምክር ቤቶች ተመሥርተው የሥራ ጊዜያቸውን እየጨረሱ አልፈዋልም ሲሉ ያክላሉ፡፡ ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ. ከ2023 መገባደጃ ወዲህ ባሉት ጊዜያት ሒደቱ መፋጠኑን አመልክተዋል፡፡ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሥራው በዋናነት አራቱን የሕገ መንግሥት ምዕራፎች ማሻሻል ላይ ትኩረት ማድረጉ የታወቀ ሲሆን፣ ይህም በፍጥነት መሳካቱን ያመላከቱት ሁሴን አይዶ በቀጣይ ከሃይማኖት ጋር የተገናኙ ሦስት የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎችን ለማሻሻል እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ 

ሼክ አደን መሐመድ ኑር ማዶቤ የሶማሊያ ታችኛው ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሲሆኑ፣ የሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ የፀደቀበትን ሒደት ዴሞክራሲያዊና በአብላጫ ድምፅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በላዕላይ ምክር ቤቱ 212 ድምፅ፣ እንዲሁም በታችኛው ምክር ቤት 42 ድምፅ የሕገ መንግሥት ማሻሻያው ማግኘቱን ገልጸው ይህም ሒደቱ በብዙኃን የምክር ቤት አባላት የተደገፈ ስለመሆኑ አመልክተዋል፡፡

የሞቃዲሾ ባለሥልጣናት ይህን ቢሉም የሕገ መንግሥት ማሻሻያው መፅደቅ ከባድ ተቃውሞ ከፑንትላንድ ግዛት አስተዳደር በኩል ፈጥሯል፡፡ የሕገ መንግሥት ማሻሻያውን ማካለብ ለምን አስፈለገ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ሒደቱ የፕሬዚዳንቱን ሥልጣን የበለጠ ለማጠናከር የተደረገ ነው የሚለው ክስና ወቀሳም ተበራክቷል፡፡

የሰሞኑን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተለው ጋዜጠኛ ኢስማኤል ቡርጋቦ ሕገ መንግሥቱ የፀደቀበት ሒደት በአመዛኙ በፕሬዚዳንቱ ግላዊና የፖለቲካ ፍላጎትና ተፅዕኖ የማሳደር ጥረት የተነሳ ነው የሚል ሙግት እንደሚቀርብበት ይናገራል፡፡ “የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ በሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ስም የጎሳ ውክልናን፣ እንዲሁም የግዛት አስተዳደሮችን የፖለቲካ ተፅዕኖ ለመለወጥ እየተንቀሳቀሱ ነው” የሚል ስሞታ ይቀርብባቸዋልም ይላል፡፡  

ፑንትላንዶች ነፃ ሉዓላዊ አገር ለመሆን በይፋ ጥያቄ ያቀረቡበት ሁኔታ እስካሁን የለም፡፡ ከሶማሊያ የመገንጠል ትግል ሲያደርጉ የታዩበት አጋጣሚም አልነበረም፡፡ የአሁኑ የሶማሊያ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ግን ለረጅም ዓመታት የገነቡትን የከፊል ራስ ገዝ ግዛትነት ሥልጣን የሚቀማ ነው ብለው ተቃውመውታል፡፡ በዚህ የተነሳ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያውን ሙሉ ለሙሉ ውድቅ አድርገውታል፡፡ ከሶማሊያ የአንድነት መንግሥት ራሳቸውን ማግለላቸውንም አስታውቀዋል፡፡

የፑንትላንድ ግብርና ሚኒስትር መሐመድ አብዱልቃድር የሕገ መንግሥቱን ማሻሻያ የተጣደፈና የፑንትላንድ አስተዳደር ፍላጎትን ያልተከተለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ያማከረን የለም ሲሉ የተደመጡት መሐመድ፣ “የመንግስት ሥልጣን ክፍፍልን፣ የቢሮዎች ሥልጣንና ኃላፊነትን፣ የፋይናንስ አስተዳደር ጉዳይን፣ የዋና ከተማ ጉዳይን፣ የግዛት አስተዳደርና የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣን ክፍፍል፣ ብሔራዊ የጸጥታ ጥበቃ ጉዳይን፣ የሀብት አሰባሰብና ክፍፍል ጉዳዮችን በሚመለከቱ የሕገ መንግሥት ክፍሎች ላይ የፌዴራል መንግሥቱ የተናጠል የማሻሻያ ዕርምጃ መውሰዱን አንቀበለውም” በማለት ነበር የግዛቱን ተቃውሞ ያስረዱት፡፡ 

ሶማሊያ ወደ ስድስት ግዛቶች አሉኝ ትላለች። ኩፉር ጋልቢድ፣ ቤናዲር፣ ሸበሌ፣ ጋልሙዱግ፣ ፑንትላንድ፣ እንዲሁም ሶማሌላንድ ሉዓላዊ ግዛቶቼ ናቸው ትላለች። ይሁን እንጂ ይህን የማይቀበሉ ግዛቶች አሉ። ለምሳሌ ሶማሌላንድ ነፃ አገር ነኝ የምትል ሲሆን፣ የራሷን ሕገ መንግሥት፣ መንግሥት፣ የመገበያያ ገንዘብ፣ የፀጥታ መዋቅርና የአስተዳደር ተቋማትን ገንብታለች። ሶማሌላንድ የራሷን ሰንደቅ ዓላማ የምታውለበልብ ስትሆን፣ ከተለያዩ አገሮች ጋር ግንኙነት ስታደርግ ብትታይም በዓለም አቀፍ ደረጃ እስካሁን ዕውቅና አላገኘችም። በምርጫ የተመረጠ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት በመገንባቱ ረገድ በአፍሪካ ደረጃም ሶማሌላንድ ጥሩ ስም ብትገነባም፣ ነገር ግን ይህ ሁሉ የሉዓላዊ አገርነት ዕውቅና አላሰጣትም።

ሶማሌላንድ እ.ኤ.አ. ከ2001 ጀምሮ የራሷ ሕገ መንግሥት ሲኖራት፣ ማንም አገር ዕውቅና ባይሰጣትም ነፃ አገር ነኝም ብላለች፡፡ ሶማሌላንዶች የራሳቸውን መገበያያ ገንዘብ፣ መከላከያ፣ መንግሥትና መንግሥታዊ መዋቅር ፈጥረው መኖር ከጀመሩ ከራርመዋል፡፡ ፑንትላንዶች ግን ከዚህ በተለየ ሁኔታ ራሳቸውን የሶማሊያ ፑንትላንድ ግዛት (ዘ ፑንትላንድ ስቴት ኦፍ ሶማሊያ) ብለው ነው የሚጠሩት፡፡ በይፋ ነፃ ሉዓላዊ አገር ነኝ የምትል ባትሆንም በርካታ የራስ ገዝ ነፃነቶች ያሏት ግዛት ናት፡፡

ከአሥር ቀናት በፊት በሶማሊያ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ መፅደቁን ተከትሎ ደግሞ ፑንትላንዶች ከሶማሊያ ጋር አገር ሆነው የመቀጠል ፍላጎት እንደሌላቸው በግልጽ እያንፀባረቁ ነው፡፡ ፑንትላንድ ወደ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት ስትሆን፣ በ1990ዎቹ ሶማሊያ ወደ እርስ በእርስ ግጭት ስትገባ የተፈጠረች ራስ ገዝ ግዛት ናት፡፡

“የሶማሊያ የጎሳ ፖለቲካና የግዛት አስተዳደሮች የፖለቲካ ተክለ ቁመና በመንግሥት ሥልጣን ላይ የሚቀመጡ ሰዎችን የጎሳና የግዛት አስተዳደር መሠረት የተከተለ ነው፤” ይላል ጋዜጠኛ ኢስማኤል የሶማሊያን ፖለቲካ የኃይል አሠላለፍ ሲያስረዳ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ወይም በፕሬዚዳንትነትና በሌላም ቁልፍ የሥልጣን ቦታዎች ከእኛ ወገን የተወከለ አልተመደበም የሚል ቅሬታ ከሁሉም አቅጣጫ የሚንጸባረቅ መሆኑን የገለጸው ጋዜጠኛው፣ አሁንም የተፈጠረው ውዝግብ የዚያ ተያያዥ ውጤት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ “አንድ የግዛት አስተዳደር ወይም አንድ አብላጫ ቁጥር ያለው ጎሳ በመንግሥት ሥልጣን ላይ አልተወከልኩም ባለ ጊዜ ሁሉ በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ሲያምፅ ወይም ዕውቅና አልሰጥም ሲል ማየት የተለመደ ነው፤” በማለትም ያክላል፡፡  

ሶማሊያ ራስ ገዝ ነን ከሚሉ ግዛቶች ጋር ጠብ ውስጥ የገባችው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ነው ይባላል፡፡ እሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚባል ሥልጣን አስወግደዋል ይባላል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳይሾሙ ለረጅም ጊዜ ቆይተዋል የሚል ወቀሳም ይቀርብባቸዋል፡፡ በሶማሌላንድ ጉዳይ የተነሳ ሶማሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ውጥረት ውስጥ እንድትገባ አድርገዋል የሚል ወቀሳም ይሰነዘርባቸዋል፡፡ ይህ ሳያንስ ባለፈው ወር ደግሞ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ አደረጉ መባሉ የሶማሊያን ፖለቲካ አወሳስቦታል እየተባለ ነው፡፡

የፑንትላንድ ባለሥልጣናት ፕሬዚዳንቱ በራሳቸው ጊዜ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን በሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ዕርምጃቸው አጥተዋል በማለትም ይወቅሳሉ፡፡ ፑንትላንድ በጊዜያዊነት ከሶማሊያ መለየቷንና አጠቃላይ ሁሉን አቀፍ ሕዝበ ውሳኔ ተደርጎ ሁሉንም የሚያግባባ መንግሥት እስኪፈጠር ድረስ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ግንኙነት እንደማይኖራት አውጃለች፡፡

የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ውዝግቡ በተባባሰበትና ውጥረቱ ባየለበት ወቅት ደግሞ የፑንትላንድ ባለሥልጣናት ወደ ኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን መላካቸው ይታወሳል፡፡ በፑንትላንድ የፋይናንስ ሚኒስትር መሐመድ ፋራህ መሐመድ የተመራ የልዑካን ቡድን ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ የሞቃዲሾ ባለሥልጣናትን በእጅጉ ነበር ያስቆጣው፡፡

ሶማሌላንድ በራሷ ነፃነት ከኢትዮጵያ ጋር የባህር በር ስምምነት ማድረጓ ክፉኛ ያስቆጣው የፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መንግሥት አሁን ደግሞ ፑንትላንዶች በራሳቸው ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት መጀመራቸው የበለጠ አስቆጥቶታል ነው የተባለው፡፡ በዚህ የተነሳ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ወደ ማቋረጥ መግባታቸውን የሞቃዲሾ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡ በሞቃዲሾ የኢትዮጵያን ኤምባሲ ዘግተው አምባሳደሩን በ72 ሰዓታት እንዲወጡ አዘዋል፡፡ በአዲስ አበባ የነበራቸውን ኤምባሲም ዘግተዋል፡፡ ይህ የሞቃዲሾ ባለሥልጣናት ዕርምጃ ለወራት የዘለቀውን ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ እንዳያባብሰው ተሠግቷል፡፡

ይህን የሚያጠናክር አስተያየት የሚሰጠው ጋዜጠኛ ኢስማኤል ኢትዮጵያ በማንኛውም መንገድ የሐሰን ሼክ መንግሥትን የበለጠ ማስቆጣት እንደምትችል ይገልጻል፡፡ “ሶማሊያ ከሶማሌላንድና ከፑንትላንድ ጋር በተወዛገበች ቁጥር ኢትዮጵያ በሶማሊያ ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የምትችልበት ዕድል ታገኛለች፡፡ ይሁን እንጂ ይህን የሶማሊያን ውስጣዊ ቀውስ ኢትዮጵያ ልጠቀም ካለች ለወደፊቱ አዋጭ አይሆንም፡፡ ለአጭር ጊዜ የሐሰን ሼክ አስተዳደርን ተፅዕኖ ውስጥ መክተት ቢቻልም፣ ነገር ግን ይህ አካሄድ ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም አይበጅም፤” ሲል ነው የተናገረው፡፡

አሁን በሶማሊያ የአልሸባብ ጥቃት መጨመሩ ይነገራል፡፡ በአገሪቱ የሠፈረው ወደ 13 ሺሕ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል (አትሚስ) በቅርቡ ሊወጣ እየተዘጋጀ ነው፡፡ የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግሥት ራሱን አለማጠናከሩ ይነገራል፡፡ ይህ ሳያንስ ደግሞ የተለያዩ ግዛት አስተዳደሮችን ወደ መገንጠል የሚገፋ ዕርምጃ እየወሰደ ይገኛል ይባላል፡፡ ፑንትላንድ ከሶማሊላንድ ጋር የምትጋጭበት ግዛት አለ፡፡ በሁለቱ ግዛቶች መካከል የሚገኘው ኤስኤስሲ ካቱሞ የተባለው አካባቢ በሁለቱ ግዛቶች ይገባኛል ጥያቄ ጦርነት ያስነሳ ውዝግብ ቀስቅሷል፡፡ የቅርብ ጊዜው የላሳኖድ ጦርነት የዚሁ ነፀብራቅ መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህ ሁሉ ያልተፈታ ከባድ የቤት ሥራ ያለባት ሶማሊያ ከጎረቤት ኢትዮጵያ ጋርም ከባድ ቀጣናዊ ውዝግብ ፈጥራ ቆይታለች፡፡

“አሁን ሁሉም ነገር ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ላይ ነው የወደቀው፤” የሚለው ጋዜጠኛ ኢስማኤል፣ በተቻለ መጠን የፑንትላንድ ሰዎችን ማናገርና ማግባባት ከቻሉ ችግሮች ሊፈቱ እንደሚችል ይናገራል፡፡ ይህ የሚሆን ግን እንደማይመስለውና ከኢትዮጵያ ጋርም ሆነ ከሶማሌላንድ ሰዎች ጋር የቀጥታ ግንኙነት ያደርጋሉ የሚል እምነት እንደሌለው ግምቱን አስቀምጧል፡፡

በሶማሌላንድ የወደብ ስምምነት የተቀሰቀሰው የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት መሻከር፣ አሁን ደግሞ ከፑንትላንድ ጋር በተደረገ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተነሳ የበለጠ ተባብሷል፡፡ ጉዳዩ ወዴት ያመራል የሚለው በሒደት ይታያል፡፡         

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -