Tuesday, May 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለውጭ ኢንቨስተሮች ተከልክለው የነበሩ የንግድ ዘርፎች ተፈቀዱ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ከዚህ በፊት ለውጭ ኢንቨስተሮች ተከልክለው የነበሩ ማለትም የወጪና የገቢ ንግድ፣ እንዲሁም የጅምላና የችርቻሮ ንግድ ውስጥ እንዲሳተፉ የሚፈቅድ መመርያ ፀደቀ፡፡

የኢንቨስትመንት ቦርድ ያፀደቀው አዲስ የማስፈጸሚያ መመርያ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የውጭ ኢንቨስተሮች እስካሁን ለአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ተለይተውና ተጠብቀው በቆዩ የንግድ ዘርፎች ላይ ማሻሻያ የሚያደርግ ሲሆን፣ አዲስ እንዲሰማሩበት የተፈቀደላቸውን የንግድ ዓይነት ይዘረዝራል።

በተጨማሪም ተግባራዊ የሚደረጉ አካሄዶችንና በሕግ ሥልጣን የተሰጣቸው የሚመለከታቸው መንግሥት አካላት መመርያውን በማስፈጸም ረገድ የሚኖራቸው ሚናም ተደንግጓል።

በአንድ ዘርፍ ውስጥ ሊሰማራ የሚያመለክት የውጭ ኢንቨስተር አስፈላጊው የሥራ ልምድ፣ አቅም ወይም የገበያ ትስስር ያለው መሆኑን ገምግሞ የንግድም ሆነ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሊሰጥ የሚችለው የኢንቨስትመንት ቦርድ መሆኑ በአዲሱ መመርያ ላይ ተደንግጓል። 

የወጪ ንግድ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለማግኘት እነዚህን ሁኔታዎች ከማሟላት በተጨማሪ በአገሪቱ ሕግ የተደነገገውን የተፈቀደ ትንሹን ካፒታል ማሟላትና ፈቃዱን ከመቀበሉ በፊትም ውል ለመፈጸም መስማማትና መከወን ይጠበቅበታል።

በመመርያው ክፍል ሁለት አንቀፅ አምስት የሰፈሩት ድንጋጌዎች የትኛውም የውጭ አገር ኢንቨስተር በጥሬ ቡና፣ ጫት፣ የቅባት ጥራጥሬዎችና እህሎች፣ የደን ምርቶች፣ የዶሮ ምርቶች፣ ከሕጋዊ ገበያ በተገዙ የቁም ከብት እንዲሁም የቆዳና ሌጦ የወጪ ንግድ ዘርፎች ላይ እንዲሰማራ ይፈቅዳል።

በአንድ ዘርፍ ውስጥ ሊሰማራ የሚያመለክት የውጭ ኢንቨስተር አስፈላጊው የሥራ ልምድ፣ አቅም ወይም የገበያ ትስስር ያለው መሆኑን ገምግሞ የንግድም ሆነ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሊሰጥ የሚችለው የኢንቨስትመንት ቦርድ መሆኑ በአዲሱ መመርያ ላይ ተደንግጓል። 

የወጪ ንግድ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለማግኘት እነዚህን ሁኔታዎች ከማሟላት በተጨማሪ በአገሪቱ ሕግ የተደነገገውን የተፈቀደ ትንሹን ካፒታል ማሟላትና ፈቃዱን ከመቀበሉ በፊትም ውል ለመፈጸም መስማማትና መከወን ይጠበቅበታል።

በመመርያው መግቢያ ላይ የቀረበው ማብራሪያ የአገር ውስጥ አቅም ላይ መሠረቱን የጣለ ዘላቂነት ያለው አገር አቀፍ የኢኮኖሚ ግንባታ ፖሊሲ ተግባራዊነትን ማስቀጠል ያለው አስፈላጊነት ዕውቅና እንደሚሰጠው ተገልጿል።

ከአራት ዓመታት በፊት የፀደቀው የኢንቨስትመንት መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 474/2012 የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ፍትሐዊ ያልሆነ ውድድር እንዳይገጥማቸው፣ በጥራትና በብዛት የመሥራት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ገበያ የእሴት ሰንሰለት የመዋሃድ አቅማቸውን በማሳደግ፣ በሒደትም እሴት የታከሉባቸው ኢንቨስትመንቶችን መፍጠር እንዲችሉ የሚሉ ምክንያቶችን በማቅረብ የተወሰኑ የንግድ ዘርፎችን ከውጭ አገሮች ኢንቨስተሮች ተሳትፎ ከልሎ መቆየቱ ይታወቃል።

በዚህም እስካሁን ድረስ የተወሰኑ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደተቻለ ሲጠቀስ የአገራዊው ፖሊሲ ዓላማ ግን የተጠበቀውን ያህል ስኬት እያስመዘገበ እንዳልሆነም ተጠቅሷል።

ከዚህ ክፍተት ጋር ተያይዞም የፖሊሲው ትግበራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት ዓመታት ለአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ብቻ በተለዩ ልዩ ጥበቃ በተደረገላቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ከአገልግሎት ተደራሽነት፣ ጥራት፣ ቅልጥፍናና ብቃት ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ አልፎም ሕገወጥ እንቅስቃሴዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን የሚያሳዩ  ቅሬታዎች በስፋት ሲቀርቡ መቆየታቸውን ማብራሪያው ይገልጻል።

ከፍትሐዊ የንግድ ውድድር ልምምድ አለመኖርና ከሕግ ማዕቀፍ ክፍተቶች መመንጨታቸው የተጠቀሰ ከትግበራ ጀምሮ የፖሊሲ ዓላማዎቹን ማሳካት መቻል ላይ እንቅፋት ፈጥረዋል በተባሉ በተለዩት የንግድ ዘርፎች ያጋጠሙ ተጨማሪ ችግሮች መለየታቸውም ተጠቅሷል።

በእነዚህ ምክንያቶች መነሻነትም በሥራ ላይ ያለው አገር አቀፍ ፖሊሲ በውጭ ንግድ፣ ወደ አገር ውስጥ ምርቶችን የማስገባት ንግድ ዘርፍ፣ በጅምላና ችርቻሮ የንግድ ዘርፎች ላይ የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮችን ተሳትፎ በማበረታታት፣ አቅም ያላቸውን የውጭ አገሮች ኢንቨስተሮች በመሳብ፣ ቀጣይ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጉላት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች (liberalization measures) ተግባራዊነት ተገማች በሆነ የታለሙ ለውጦችንና ጥቅሞችን የአፈጻጸምና የምዘና ሒደት ወደ መሬት ማውረድ በሚያስችል አዲስ ስልት ወይም አካሄድ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ግንዛቤ ላይ መደረሱም ተገልጿል። 

መመርያው የኢንቨስትመንት ፈቃድ የሚሰጥባቸው ሁኔታዎችንም በግልጽ አስቀምጧል።

በዚህም መሠረት ተቀዳሚው በጥሬ ቡና የወጪ ንግድ ላይ መሰማራት የሚፈልግ ማንኛውም የውጭ ኢንቨስተር በትንሹ በዓመት በአማካይ አሥር ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ መጠን ያለው ጥሬ ቡና ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ከኢትዮጵያ ሲወስድ የቆየና የኢንቨስትመንት ፈቃድ በሚሰጠው ዓመትም የተገለጸውን መጠን ያለው ዶላር ለማስገባት ውል ለመፈጸም መስማማት ይኖርበታል።

በቅባት ጥራጥሬዎች የወጪ ንግድ ላይ መሰማራት የሚፈልግ የውጭ ኢንቨስተር ላለፉት ሦስት ዓመታት ቢያንስ አምስት ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርቱን ከኢትዮጵያ ሲወስድ የቆየና ፈቃዱ በሚሰጠው ዓመትም ቢያንስ የተገለጸውን መጠን ያህል ያለው ዶላር ለማስገባት ስምምነት መፈጸም እንደሚኖርበት ተገልጿል። 

የቅባት እህሎችንና የጫት የውጪ ንግድ ላይ ለመሰማራት ላለፉት ሦስት ዓመታት ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የእያንዳንዳቸው የምርቶቹን መጠን ከኢትዮጵያ ሲወስድ የቆየና በተመሳሳይ ፈቃዱ በሚሰጠው ዓመትም ይህንኑ መጠን ገቢ ለማስገኘት ውል መፈጸም እንደሚኖርበት ተደንግጓል።

ለቆዳና ሌጦ፣ ለደን ምርቶችና ለዶሮ ምርቶች የወጪ ንግድ በተመሳሳይ ዓመታትና የውል ሒደት ውስጥ እንደሚስተናገዱ የተገለጸ ሲሆን በዓመት ቢያንስ 500 ሺሕ ዶላር ይጠበቅበታል። ከቀንድ ከብቶች የወጪ ገበያ ንግድ ጋር ግን በተያያዘ ምንም ዓይነት የተለየ የተቀመጠ ቅድመ ሁኔታ እንደሌለ ተጠቅሷል። 

ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዘ ምንም ዓይነት የንግድ ታሪክ የሌላቸው በወጪ ንግድ ላይ አዲስ መሰማራት የሚፈልጉ የውጭ አገሮች ኢንቨስተሮች ጥሬ ቡና ለመነገድ ቢያንስ 12 ሚሊዮን ዶላር፣ ለቅባት ጥራጥሬዎች 7.5 ሚሊዮን ዶላር ለጫትና የቅባት እህሎች ንግድ 1.5 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በቆዳና ሌጦ፣ በደን ምርቶችና በዶሮ ምርቶች ለመሰማራት 750 ሺሕ ዶላር ማቅረብና የገበያ ትስስር እንዳለው ማረጋገጫ የግዥ ትዕዛዝ ማቅረብ እንደሚኖርበትም ተገልጿል።

ገቢ ንግድን በተመለከተ ግን መመርያው ከአፈር ማዳበሪያና ነዳጅ ውጭ ባሉ የትኛውንም ምርቶች ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ለሚፈልጉ የውጭ አገሮች ኢንቨስተሮች መሳተፍ እንደሚችሉ ደንግጓል።

በጅምላ ንግድ ላይ የሚኖራቸው ተሳትፎም በብቸኝነት የሚከለክለው የአፈር ማዳበሪያን ወደ አገር ውስጥ አስገብቶ መሸጥን ብቻ ሲሆን በችርቻሮ ንግድ ላይ ለማንኛውም የአገር ውስጥ ኢንቨስተር የተፈቀደው የትኛውም ዘርፍ ላይ መሳተፍ እንደሚችሉ ተገልጿል።

ከመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ የተገለጸው መመርያ በኢንቨስትመንት ቦርዱ የበላይ ኃላፊ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ፊርማ የፀደቀ ነው።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች