Wednesday, May 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ተስፋ የተጣለባቸው የንግድ ማዕከላት

የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ተስፋ የተጣለባቸው የንግድ ማዕከላት

ቀን:

ፆም ሲገባ ዋጋቸው ከሚጨምሩ የምግብ ፍጆታዎች ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬ  ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የእንስሳት ተዋጽኦ  ያልተካተተባቸው ምግቦችም  ዋጋቸው አንፃራዊ ጭማሪን አሳይቷል።

በተለይ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጎመን፣ ድንች፣ ቃሪያና ሌሎች በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉ ምግቦች የዋጋ ጭማሪ  ጎልቶ የሚታይባቸው ናቸው።

ዘንድሮ የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮች ፆምና ፀሎታቸው  የገጠመበት ወቅት ነው፡፡ የሁለቱን ትልልቅ አጽዋማት መግባትን ተከትሎ በተለይ በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ሊታይ ይችላል  የሚል ሥጋት ነበረ።

- Advertisement -

ነገር ግን ከታሰበው በተቃራኒው በአትክልት የዋጋ ቅናሽ ተስተውሏል፡፡  ፆም ሲገባ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቲማቲምና ቃሪያ በወቅቱ ከነበረበት ከእጥፍ በላይ  በሚባል ደረጃ ዋጋቸው ቀንሷል፡፡ በኪሎ እስከ ከ90 ብር ገብቶ የነበረው የቲማቲም ዋጋ  ከ10 ብር እስከ 25 ብር በአንድ ጊዜ ሲያሽቆለቁል፣ ከ120ብር እስከ 150 ብር የነበረው ሽንኩርት ከ40 እስከ 60 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ በፆም ወቅት በየምግብ ቤቶች የሚዘወተሩ ምግቦች ምንም ዓይነት የዋጋ  ቅናሽ አልታየባቸውም። ሽሮ በየዓይነትና ሌሎች የፆም ምግቦች እንደየአካባቢው ቢለያይም ከ10 ብር እስከ 40 ብር ጭማሪ አሳይተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ጫና በዘላቂነት  ለመቅረፍ በአምስቱም የከተማዋ መግቢያ በሮች  የገበያ ማዕከላት በመገንባት  ከተለያዩ አካባቢዎች ምርቶችን ለማስገባት ወደ ሥራ ከገባ ወራት ተቆጥረዋል፡፡

ከተገነቡት አምስት የግብርና ምርቶች ማቅረቢያ የገበያ ማዕከላት በአሁኑ ወቅት አገልግሎት መስጠት የጀመሩት የለሚ ኩራ፣ የኮልፌ ቀራኒዮና የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ናቸው፡፡ ቀሪ ሁለት የገበያ ማዕከላት ደግሞ በግንባታ ላይ ናቸው ተብሏል።

በማዕከላቱ የሚገኙ የጅምላና የችርቻሮ መሸጫ መጋዘኖችና መደብሮችን  ለአምራቾች በኪራይ እየተላለፉ ሲሆን፣ አምራቾችም ምርቶቻቸውን ማቅረብ መጀመራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡

አምራቾች ምርታቸውን በስፋት ለተጠቃሚው በሌሎች ገበያዎች ካለው ዋጋ ቀንሰው እያቀረቡ ሲሆን፣ ገዥዎች የሚፈልጉትን በአንድ ቦታ በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከለሚ ኩራ የገበያ ማዕከል ሸምተው ሲወጡ ያገኘናቸው እናቶች እንዳሉት፣ ከማዕከሉ ውጭ ካለው የገበያ ሁኔታ፣ በዋጋም ሆነ በአቅርቦት የተሻለ ነው፡፡

በወቅቱ ሸምተው ከወጡት ውስጥም ውጭ ላይ ከ90 ብር እስከ 95 ብር ይሽጣል ያሉትን ዱቄት በ88 ብር መሸመታቸውን ነግረውናል፡፡ በተመሳሳይ የቲማቲም፣ የጎመን  የሽንኩርት፣ የፓፓያና የድንች ገበያ ከሌላው የተሻለ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በአንድ አካባቢ መገኘቱ፣ ጊዜን የሚቆጥብ መሆኑና ምርቱ ብዙ ንክኪ ሳይበዛበት  ከማሳ በቀጥታ  የገባ መሆኑ  ከዋጋው  መቀነስ በላይ  እንዳስደሰታቸው  ተናግረዋል፡፡ 

ማዕከሉ ሥራ ሲጀምር ከነበረው የዋጋ ተመን በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱና  መርጦ መግዛት አለመቻሉ ማለትም የተበላሸውን ካልተበላሸው፣ ደቃቁን ከትልልቁ ቀላቅሎ መግዛት እንደ ግደታ መወሰዱ ቅር እንዳሰኛቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው ሸማች ናቸው፡፡

ያለው  የዋጋ ልዩነት በጣም ተቀራራቢና  ለትራንስፖርት የሚያወጡትን ገንዘብ  የማይሸፍን በመሆኑ በአቅራቢያቸው የተሻለውንና የመረጡትን ምርት መሸመት  ሳይሻላቸው እንደማይቀር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በማዕከሉ 62 አምራች ማኅበራት የተለያዩ ምርቶችን ይዘው የቀረቡ ሲሆን፣  ከአንዳንድ ችግሮች በቀር ቦታው ለግብይት እንደተመቻቸው ተናግረዋል፡፡

የ200 የገበሬ የማኅበራት ተወካይ አቶ ቶልቻ ንጉሤ፣ በማኅበር ተደራጅተው  ያመረቱትን ጥራጥሬ ይዘው የተገኙ አቅራቢ ናቸው፡፡

ከአዳማ፣ ከሞጆ፣ ከቢሾፍቱና ከሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች ጤፍን ጨምሮ ሌሎች የጥራጥሬ ምርቶችን ወደ ማዕከሉ በማስገባት ለማኅበረሰቡ እያቀረቡ መሆኑን የተናገሩት አቶ ቶልቻ፣ በዚህም በተለዩ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

አቶ ቶልቻ ምርታቸውን በማዕከሉ እየሸጡበት ያለው ዋጋ ከማዕከሉ ውጭ ካለው ገበያ ጋር እያነፃፀሩ ሲናገሩ፣ በኩንታል 15 ሺሕ ብር የሚሸጠውን ነጭ ጤፍ ማኅበሩ 12 ሺሕ 500 ብር፣ በውጭ 12 ሺሕ ብር ይሸጣል ያሉትን ቀይ ጤፍ፣ በ10 ሺሕ  ብር እየሸጡ እንደሚገኙ ተናግረው፣ ማኅበራቸው በኪሎ 88 ብር የሚሸጠውን የቀርሳ ዱቄት በውጭ እስከ 110 ብር  እየተሸጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በሁሉም ጥራጥሬዎች በኪሎ ቢያንስ ከ15 ብር እስከ 20 ብር በኪሎ ቅናሽ መኖሩን ተናግረዋል፡፡

ሸማቾች ቦታውን እየለመዱት በመሆኑ፣ በቀን እስከ 40 ኩንታል ጤፍ ሸጠው  እንደሚውሉ አቶ ቶልቻ ተናግረዋል፡፡

ለዋጋ መቀነሳቸው ዋነኛ ምክንያትም ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት ምርታቸውን በቀጥታ ለተጠቃሚው በማድረሳቸውና ገበያውን ሲያውክ የነበረው አካል እንዲወጣ በመደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አምራቹ ምርቱን ከማሳው በማምጣት ለነጋዴ በሚያስረክብበት ዋጋ  እንደሚሸጡ፣ ሸማቹን ለማለማመድና ደንበኛ ለማፍራት እንዲሁም የማኅበረሰቡን ኑሮ እያናጋ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ካልሆነ በቀር እስካሁን ባለው ግብይት ምንም ዓይነት ትርፍ እንደማያገኙ በቦታው ያሉ አቅራቢዎች ተናግረዋል፡፡

ለምርታቸው ማጓጓዥያና ለቦታ ኪራይ የሚያወጡት ወጪ እየሸጡበት ካለው ዋጋ ጋር እንዳልተመጣጠነላቸው አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል በማዕከሉ የውኃና የመብራት አለመኖር በሥራቸው ላይ ከፍተኛ እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረው፣  የእህል ወፍጮም  በአቅራቢያቸው  ቢተከል ሲሉ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ሰጥተዋል፡፡

የገበያ ማዕከሉ መገንባት በከተማዋ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ ከማዘመኑም ባሻገር ገበያውን ለማረጋጋትና ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓት እንዲፈጠር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው የተናገሩት  የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳነ ሱሌ ናቸው፡፡

በማዕከሉ 212 መጋዘኖች፣ 46 የችርቻሮ መደብሮችና 15 የጅምላ ሱቆች  መኖራቸውን  የተናገሩት አቶ አዳነ፣ ይሁን እንጂ በተሟላ ሁኔታ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለው እንደማያስቡ ገልጸዋል፡፡

ውኃ፣ መብራት፣ መፀዳጃ ቤትና የመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች  ገና ያልተሟሉ በመሆናቸው በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ለመግባት እንዳልቻሉ ተናግረው፣ ነገር ግን  የመብራትና የውኃ መተላለፊያ መስመሮች በመዘርጋታቸው በቅርብ ቀን አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ አብራርተዋል፡፡ 

በእሑድ ገበያ የተጀመረው የገበያ ማረጋጋት ሥራ በሰፊው እንዲተገበር  እየታሰበ ነው ያሉት ኃላፊው፣ አርሶ አደሩ ምርቱን በቀጥታ ለተጠቃሚው በማድረስ፣ ለገበያው አለመረጋጋት ትልቅ ሚና የነበረውን ደላላ ከመካከላቸው እንዲወጣ መደረጉን  ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ አዳነ፣ በከተማው የንግድ ቢሮ የገበያው ሁኔታ እየታየ በየሳምንቱ  የዋጋ ተመን ይደረጋል፡፡ ከማዕከሉ ውጭ ያለው ገበያ ሲጨምርም ሆነ ሲቀንስ የማዕከሉ የግብይት ሁኔታ ሊጨምር ወይም ሊቀንስ የሚችልበት ሁኔታም አለ፡፡ ለሚወጣው የገበያ ተመን ተፈጻሚነትም፣ ንግድ ቢሮ ተቆጣጣሪዎችን መድቦ ይከታተላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...