Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

ቀን:

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች እንደታየው በወርቃማ ዘመንነት ይጠቀሳል፡፡ በሙዚቃው ዓለም ከተከሰቱት ድምፃውያን መካከል በ1960ዎቹ ጎልተው ከታዩት መካከል በ14 ዓመቱ መዝፈን የጀመረው ሙሉቀን መለሰ ይገኝበታል፡፡

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ነፍስ ኄር ሙሉቀን መለሰ

ወደ ዘፈኑ ዓለም የተሳበው በኩር ድምፃዊውን ጥላሁን ገሠሠ አይቶ መሆኑ፣ በምሽት ክለቦችም ሲጫወት የጥላሁንን ዘፈን በመዝፈን እንደነበር በገጸ ታሪኩ ተጠቅሷል፡፡

በወ/ሮ አሰገደች አላምረው ባለቤትነት ይመራ የነበረው ፓትሪስ ሉሙምባ የምሽት ክለብ ዘፋኝነትን አሐዱ ያለው ሙሉቀን፣ በፖሊስ ኦርኬስትራ ሥራውን በመቀጠል ስሙን ያስነሱትን እናቴ ስትወልደኝ መቼ አማከረችኝ፣ ያ ልጅነት በጊዜያቱ፣ እምቧይ ሎሚ መስሎ፣ የዘለዓለም እንቅልፍና ሌሎችንም ተጫውቷል፡፡

- Advertisement -

ታዋቂነትን ያተረፈባቸው በተለይ ሦስቱ ዘፈኖች (እምቧይ ሎሚ መስሎ፣ እናቴ ስትወልደኝ መች አማከረችኝ እና ያ ልጅነት የደረሳቸው ተስፋዬ አበበ ነው፡፡

በፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ ካገለገለ በኋላ እስከ 1970ዎቹ አጋማሽ ድረስ ባሉት ዓመታት ከኢኳተርስ ባንድ፣ ቬኑስ፣ ዳህላክ፣ ኢትዮ ስታር፣ ሮሃ ባንዶች ጋር ተጫውቷል፡፡

የሙሉቀን ዜማዎች የብዙዎችን ቀልብ መያዛቸው አልቀሩም፡፡ ለሙዚቃው መድረክ ያበረከተው አስተዋጽኦም የማይረሳ ነው፡፡ ቀደምት ሥራዎቹ በታዋቂዎቹ በአምሃ ሪከርድስ፣ ፊሊፕስ ኢትዮጵያና ካይፋ ሪከርድስ፣ ታንጎ ሙዚቃ ቤት፣ ሐራምቤ ሙዚቃ ቤት ተሠራጭተዋል፡፡

እንባዬን ጥረጊው፣ ወተቴ ማሬ፣ እቴ እንዴነሽ ገዳዎ፣ ተነሽ ከልቤ ላይ፣ እምቧ በለው፣ እሹሩሩ ካሉት፣ ድንገተኛ ፍቅር፣ አንታረቅም ወይ፣ በምሥጢር ቅበሪኝ፣ ቼ በለው፣ ውቢት፣ ናኑ ናኑ ነይ፣ ነይ ነይ ከሥራዎቹ መካከል ይገኛሉ፡፡

ሙዚቃውን በማቀናበር ረገድ የሚጠቀሱት ዳዊት ይፍሩ፣ ሙላቱ አስታጥቄ፣ ጥላዬ ገብሬና ሌሎችም ናቸው፡፡

‹‹የሙሉቀን ዜማዎች በብዙዎች ልብ የሚዘልቅና ቀልብን የሚገዙ ናቸው፡፡ ለሙዚቃው መድረክ ያበረከተው አስተዋጽኦም የማይረሳ ነው፤›› ያሉት የነገረ ሙዚቃ ልሂቅ ባለሙያ ትምክህት ተፈራ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

የሙሉቀንን ዜና ዕረፍት ተከትሎ ባለሙያዋ እንዳሉት፣ ሙሉቀን መለሰ በችሎታውና በትጋቱ ከኢትዮጵያ የሙዚቃ ከፍታ ጋር ተመሳሳይ ሆኗል፡፡ ሰምሯል፡፡

ከ46 ዓመት በፊት በጌታቸው ተካልኝ ዋና አዘጋጅነት ትወጣ የነበረችው ‹‹ፀደይ›› መጽሔት፣ የሙሉቀን መለሰን ቃለመጠይቅ አውጥታ ነበር፡፡ በ1973 ዓ.ም. ለኪነት ዓምዱ ያነጋገረውም ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር፣ ከድምፃውያን ተጫዋቾች ማንን ታደንቃለህ? ብሎ ጠይቆት የመለሰው እንዲህ ነበር፡-

‹‹ዓለማየሁ እሸቴን። ደረጃው በጣም ከፍተኛ ነው። ካሉን ዘፋኞች ሁሉ የበለጠ የሙዚቃ ዕውቀት አለው። ሁላችንም በዘልማድ የምንዘፍን ሲሆን፣ እሱ ግን ሙዚቃን በማወቅ ከኛ ብልጫ አለው። ፕሮፌሽናል ኢንተርናሽናል (በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለሙያ) ዘፋኝ ያለን እሱ ነው ብዬ የምኮራበት ሰው ነው።

‹‹በድምፅ ደሞ እንደ ምኒልክ ወስናቸው ያለ ዘፋኝ የለንም። የኦፔራ ዘፋኝ ድምፅ ነው ያለው… ጥላሁን፣ ዓለማየሁ፣ ምኒልክ፣ ብዙነሽ፣ ሒሩት፣ መሐሙድ እነዚህን የሚተኩ ድምፃውያን መብቀል አለባቸው። ይኸ የአገሪቱ ኃላፊነት ነው… ይህን ሙያ ሲበዛ ነው የምወደው። በየዕለቱ ይበልጥ እያወቅከው… እየተማርከው ትሄዳለህ። ማቆሚያ የለውም… ሙዚቃን በትምህርት ሳይሆን በልማድ ነው የማውቀው።

ከዘፈኖችህ በጣም የምትወደው የትኞቹን ነው? ብሎ ለጠየቀውም እንዲህ መልሶ ነበር፡፡

‹‹እኩል ነው የማያቸው። ግን … በጣም የሚያረኩኝ … በዜማውና በዘፈኑ … ‹‹ሰውነቷ› እና ‹ሆዴ ነው ጠላትሽ› … እ …… በሙዚቃ ጥራትና ባሠራር ደግሞ፣ ሙላቱ አስታጥቄ ያቀነባበራቸውና ከዳህላክ ባንድ ጋር የዘፈንኳቸው ‹ቼ በለው› እና ‹ውቢት›።››

‹‹ከሻይ ቤት ሀርሞኒካ እስከ ዳህላክ ባንክ›› 17 ዓመታት ከዘለቀው የዓለማዊ ሙዚቃ ጉዞው በኋላ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት ያመራው ሙሉቀን መለሰ፣ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ በመሆን በዘማሪነት ዘልቋል፡፡ የመጀመርያው በካሴት የተሠራጨውም ‹‹የኢየሱስ ወታደር ነኝ›› የሚለው መዝሙሩ ነው፡፡

በጎጃም ጠቅላይ ግዛት እነደድ ወረዳ፣ ዳማ ኪዳነ ምሕረት በምትባል አጥቢያ በ1946 ዓ.ም.  የተወለደው ሙሉቀን፣ የሚጠራው በአሳዳጊ አጎቱ አቶ መለሰ መሆኑን፣ ይሁን እንጂ ወላጅ አባቱ አቶ ታምር ጥሩነህ መሆናቸውን በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር፡፡

ሙሉቀን በሥነ ጥበቡ ዓለም ታምር ሆኖ ከዘለቀ በኋላ ዜና ዕረፍቱ ሚያዝያ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ከአሜሪካ ተሰምቷል፡፡ ሥርዓተ ቀብሩም በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን አማካይነት የጸሎትና የስንብት ፕሮግራም ከተካሄደ በኋላ ሚያዝያ 4 ቀን ተፈጽሟል፡፡

በኵሯ ድምፃዊት አስቴር አወቀ በማኅበራዊ ትስስር ገጿ እንዲህ ከተበች፡፡ ‹‹እጅግ አድርጌ የማከብርህ አርቲስት ሙሉቀን መለሰ፣ ነብስህን እግዚአብሔር በገነት ያኑርልን፡፡ እጅግ በሚአምሩ ሙዚቃዎችህ ሁልጊዜም በልባችን ትኖራለህ፡፡››፡፡ 

አሁንም ትዝታ                   

ነፍስ ኄር ሙሉቀን መለሰ በቀዳሚው የሙዚቃ ምዕራፉ፣ ካይፋ ሪከርድስ ባሳተመለት አልበሙ ላይ ከምስሉ ጋር የተዋደደ ‹‹አሁንም ትዝታ›› የምትል ማሠሪያ አንቀጽ እንዲህ ትነበባለች፡፡

‹‹ትዝታ በሐሳቤ ዓይን ሲንገዋለል በዓይኔ ትይዩ የመጣ እየመሰለኝ የማላየውን እያየሁ አንዴ ፈገግ አንዴ ኮስተር እያልኩ እራሴን በራሴ ሳነጋግር ለኔ የሚታየኝ ለሌላው ስለማይታየው ለኔ የሚሰማኝ ለሌላው ስለማይሰማው ብቻዬን ተነጋግሬ ራሴ ጠይቄ ራሴው መልሼ ለትዝታዬ ትዝታ እፈጥራለሁ፡፡ ትዝታ! ትዝታ! ትዝታ!

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...