Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

ቀን:

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት መኖር የመማር ማስተማር አንዱ ውጤት ነው፡፡ ተማሪዎች ትምህርትን በትምህርት ቤት ‹‹ሀ›› ብለው ሲጀምሩም፣ የማንበብ፣ የመጻፍ፣ የማዳመጥና የመናገር ክህሎት እንዲያዳብሩ ይጠበቃል፡፡ ይህ የወደፊት ትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆን መሠረት ነውና፣ የመማር ማስተማር ሒደቱ እነዚህን መሠረት አድርጎና በግብዓት ታጅቦ የሚከናወን ነው፡፡

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
አቶ ብርሃኑ ግርማ

አንብቦ መረዳት በቅድመ መደበኛና በአንደኛ ደረጃ ትምህርት የሚጠበቅም ነው፡፡ በመላ ኢትዮጵያ የቅድመ መደበኛ ትምህርት አስገዳጅ የሆነው በቅርቡ ቢሆንም፣ በከተሞች በተለይም በግል ትምህርት ቤቶች የቅድመ መደበኛ ትምህርት አዲስ አይደለም፡፡

ሆኖም በታችኛው የክፍል ዕርከን የሚገኙ ተማሪዎች የማንበብ ክህሎት ዛሬም አልተቃናም፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች በተለይም ልዩ ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው ክልሎች የሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አንብቦ የመረዳት ችሎታቸው ፈተና ተጋርጦበታል፡፡

- Advertisement -

እ.ኤ.አ በ1998 በአሜሪካ የተመሠረተውና ከ2002 ጀምሮ በመላ ኢትዮጵያ የልጆች የማንበብ ክህሎትን ለማሳደግ ለመሥራት ዕውቅና አግኝቶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ኢትዮጵያ ሪድስ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት፣ ሚያዝያ 3 እና 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ባዘጋጀው 4ኛው ዓመታዊ የሕፃናት የንባብ ጉባዔ የተነሳውም፣ አብዛኞቹ የሁለተኛና የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ዜሮ አንባቢ ወይም አንድም ቃል ማንበብ የማይችሉ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡

በአገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ የትምህርት ምዘናና ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኢፋ ጉርሙ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የEarly Grade Reading Assessment (EGRA) ኢግራ መሠረታዊ የጥናት መርሆዎችን ተከትሎ በ2023 በብሔራዊ ደረጃ የተደረገ ጥናት ከ2ኛ እና 3ኛ ክፍል ተማሪዎች 56 በመቶ ዜሮ አንባቢዎች ወይም ምንም ማንበብ የማይችሉ ሆነው መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

 

ዓምና ከነበረው 63 ከመቶ ዜሮ አንባቢዎች የዘንድሮው ትንሽ መሻሻል ያሳየ ቢሆንም፣ በ401 ትምህርት ቤቶች፣ በ802 መምህራን እንዲሁም በ16 ሺሕ ተማሪዎች በዘጠኝ ቋንቋዎች ላይ የተሠራው ጥናት፣ የተማሪዎችን የማንበብና የመረዳት ክህሎት ለማሳደግ ብዙ መሥራትን እንደሚጠይቅ ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ኢፈ ጉርሙ (ዶ/ር)

በገጠርና በከተማ በሚማሩ ልጆች መካከል ሰፊ ልዩነት መኖሩን፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በሲዳማ ክልሎች የዜሮ አንባቢዎች ቁጥር እየቀነሰ ሲመጣ፣ በአፋር፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉልና በሶማሌ ክልሎች እንደ ቅደም ተከተላቸው በርካታ ተማሪዎች ማንበብ እንደማይችሉ በጥናቱ መታየቱን ኢፋ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

‹‹ተማሪዎች ያልተሰጣቸውን ከየትም ሊያመጡና ሊማሩ አይችሉም፣ መምህራን ካልሠሩ ተማሪዎች አያውቁም›› ያሉት ኢፋ (ዶ/ር)፣ መምህራን በሚያስተምሩት ትምህርት ሥልጠና ወስደዋል ወይ? ለሚለው 52 በመቶ መምህራን ሥልጠና አለመውሰዳቸውን፣ 70 በመቶ መምህራን ደግሞ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ዙሪያ ሥልጠና እንዳልተሰጣቸው በጥናቱ መታየቱን ጠቁመዋል፡፡

በአብዛኛው ለተማሪዎች የንባብም ሆነ በተለይ የቅድመ መደበኛ ትምህርት መጽሐፍ አለመኖርና አለመዳረስ፣ የማንበቢያ ቦታ አለመኖር፣ የቤተ መጻሕፍት እጥረትና ለቅድመ መደበኛና ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚመጥኑ የንባብ መጻሕፍት አለመገኘት ችግሩ እንዲባባስ ካደረጉ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡

የሚታየውን የንባብ ተደራሽነት በተለይም የሕፃናት የንባብ አቅምን ለማሻሻልና በኢትዮጵያ የሚታየውን ሁሉ ወደተቃና መስመር ይዞ ለመሄድ ሕፃናት ላይ መሥራት ወሳኝ ነው ያሉት በትምህርት ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ አቶ መዝገቡ ባያዝን ናቸው፡፡

ከዚህ ቀደም ሦስተኛ ክፍል ከደረሱ ተማሪዎች አብዛኞቹ ማንበብ አለመቻላቸው በጥናት በመታየቱና የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ችግሩን ለመቅረፍ መሠረት የሚጣልበት በመሆኑ፣ በሁሉም አካባቢዎች እንዲጀመር ተደርጓል ብለዋል፡፡

ሆኖም የቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት በባህሪው የተለየ በመሆኑ የመምህራንና የመጻሕፍት ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ፣ መጻሕፍት አትሞ ለሁሉም ሕፃናት ማዳረስ ችግር መሆኑን፣ ይህንን ለመቅረፍ ከአጋር ድርጅቶች ጋር እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2000 ጀምሮ የተሠሩ ጥናቶች የንባብ ክህሎት እየቀነሰ መምጣቱን እንደሚያሳዩ፣ ‹‹ልጆች አያነቡም እያልን ልጆችን እየወቀስን ነበር፡፡ ግን የሚነበብ መጻሕፍትና ቦታ አዘጋጅተናል ወይ?›› ሲሉ የጠየቁት አቶ መዝገቡ፣ ትውልዱ የሚያነበውና የሚያነብበት ቦታ ካገኘ እንደሚያነብ በአብረሆት ቤተ መጻሕፍት ለማንበብ የሚመጡ ተማሪዎችን ለአብነት በመጥቀስ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሪድስ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ግርማ በበኩላቸው፣ ንባብን ባህል በማድረግ ዙሪያ የሚሠራው ኢትዮጵያ ሪድስ፣ የቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን የንባብ ክህሎት ለማሳደግ፣ የማኅበረሰብ ቤተ መጻሕፍት በመገንባትና የትምህርት ቤቶችን ቤተ መጻሕፍት በማሻሻል እየሠራ እንደሚገኝ አስታውሰዋል፡፡

በአፍ መፍቻ ቋንቋ የተጻፉ መጻሕፍት የማግኘት ችግር የሁሉም ትምህርት ቤቶች መሆኑን በመግለጽም፣ ኢትዮጵያ ሪድስ ችግሩን ለማቃለል ባህል የጠበቁ መጻሕፍትን ከውጭ በማስመጣት፣ በአገር ውስጥ ጥሩ መጻሕፍት የተባሉትን በመግዛት እንዲሁም ድርጅቱ እያሳተመ እንደሚያሠራጭ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ከ2000 ወዲህ በየሁለት ዓመቱ የተማሪዎች የማንበብ ክህሎት ላይ ጥናት ይሠራል፡፡ በየጊዜው የተሠሩ ጥናቶችም ተመሳሳይ ችግሮች አሳይተዋል፡፡ ምክረ ሐሳብም ተሰጥቷል፡፡ ይህ ምን መፍትሔ አመጣ ስንል ለኢፋ (ዶ/ር) ጥያቄ አቅርበን ነበር፡፡

እንደ ኢፋ (ዶ/ር)፣ አሁን የተሠራው ጥናት ቀደም ሲል ከነበረውና በሰባት ቋንቋዎች ብቻ ሲሠራ ከነበረው በሁለት ቋንቋዎች  ጨምሮ በዘጠኝ ቋንቋዎች ላይ ነው፡፡

ከዚህ በፊት በደህና ደረጃ ይገኙ በነበሩት የአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይና ሌሎች በኢኮኖሚ የተሻሉ ክልሎች ላይ የተሠሩ ጥናቶች የተሻለ ውጤት ያሳዩ ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉልና ሶማሌ ተካተዋል፡፡ የእነዚህ የዜሮ አንባቢ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ፣ አጠቃላይ ውጤቱን ያጎለዋል፡፡ በመሆኑም የጥናቱ ውጤት በሁሉም ክልል ችግሩን ለመቅረፍ አልተሠራም ለማለት እንዳልሆነ፣ የቀደሙት ጥናቶች ለሚመለከታቸው አካላት ከተሰጡ በኋላ የተሻለ እንቅስቃሴ መኖሩን ተናግረዋል፡፡

በአንድ ጊዜ ውጤቱን መለወጥ ከባድ መሆኑን፣ በሒደት መለወጥ እንደሚቻል፣ ከባለፈው ጥናት የአሁኑ የዜሮ አንባቢ ቁጥር ላይ በትንሽም ቢሆን መቀነስ ማሳየቱን፣ ከ63 በመቶ ዜሮ አንባቢ ወደ 56 ዜሮ አንባቢ መውረድ መቻሉ ችግሩን ለመቅረፍ እንቅስቃሴ መኖሩን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

አሠራሩ በዚሁ ከቀጠለና የሚመለከተው ሁሉ የእኔ ሥራ ነው ብሎ ከወሰደው፣ የንባብ ክህሎትን ብሎም የትምህርት ጥራትን እናሻሽላለን የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

‹‹12ኛ ክፍል ላይ የተመዘገበውን አስደንጋጭ ውጤት ለመለወጥ መሥሪያው ቦታ ቅድመ መደበኛ ላይ ነው›› ያሉት ኢፋ (ዶ/ር) ችግሮቹ ከመምህራን ሥልጠና ጋር የሚያያዙ መሆኑን፣ ንባብን በእውነት እያስተማሩ ነው ወይ? ብሎ መጠየቅ እንደሚያስፈልግ፣ አብዛኛው መምህር የሚጠቀመው የማስተማር ዘዴ መምህሩ ሲጽፍ ተማሪ መገልበጥ መሆኑ መስተካከል እንደሚገባው አክለዋል፡፡

ተማሪዎች ክፍል ውስጥ እንዲያነቡ ማለማመድን ጨምሮ ግብዓት ላይ ያለውን ከፍተኛ ችግር መቅረፍ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

ጥናቱን ለመሥራት መረጃ ሲሰበሰብ በግጭት ምክንያት ተደራሽ መሆን ያልቻሉ አካባቢዎች እንዳልተካተቱ፣ የትግራይ ክልል በአሁኑም ባለፈውም አለመካተቱ፣ የጥናቱ ውስንነት ግጭት ያለባቸው አካባቢዎች ትኩረት እንደሚሹ ገልጸዋል፡፡

ቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ ተማሪዎች ፊደል እንዲለዩ፣ ለገጠር ተማሪዎች ትኩረት እንዲሰጥ፣ ልጆች ቤት ውስጥም ለማንበቢያ በቂ ጊዜ እንዲያገኙና ወላጅ እንዲተባበር የሚሉት ኢፋ (ዶ/ር) በምክረ ሐሳባቸው ካነሷቸው ነጥቦች ይገኙበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...