Tuesday, May 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በግብርና ምርቶች ብክነት በዓመት ከ474 ቢሊዮን ብር በላይ እየታጣ መሆኑ ተነገረ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግብርና ሚኒስቴር አዲስ ያስተዋወቀው የግብርና ምርቶች አስተዳደርና አመራር ስትራቴጂ፣ በኢትዮጵያ በየዓመቱ 474.67 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የምርቶች ብክነት መኖሩን አመላከተ፡፡

ሚኒስቴሩ ከዚህ ቀደም ብክነትን ለማስቀረት ሲሠራበት የቆየው ስትራቴጂ እህልና ጥራጥሬ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ሲሆን፣ አዲሱ ስትራቴጂ ተጨማሪ ሁለት ዘርፎችን አካቷል። 

ከተያዘው ዓመት ጀምሮ ለተከታታይ ሰባት ዓመታት የሚተገበረው ስትራቴጂ በእንስሳትና የእንስሳት ተዋፅኦ፣ በጥራጥሬ፣ በዕፅዋትና በሰብል ምርቶች በዓመት 46 ሚሊዮን ሕዝብ ሊመግብ የሚችል ምግብ እያባከነ መሆኑን ያስረዳል። 

በየዓመቱ 161.74 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የሥጋና ወተት ምርቶች ብክነት እያጋጠመ መሆኑንና 312.93 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬዎች፣ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች እየባከኑ መሆኑ ተገልጿል። 

እነዚህ የግብርና ምርቶች በከፍተኛ መጠን በቀላሉ የመበላሸት ይዘት ያላቸው መሆኑን የሚገልጸው የሚኒስቴሩ የስትራቴጂ ሰነድ የአገሪቱን የምግብ ዋስትናና ሥነ ምግብ ሥርዓት ደኅንነት ከማረጋገጥ፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች ቀጣይነት ያለው ጥሬ ዕቃዎች ከማቅረብ፣ የወጪ ንግድን ከማበረታታት፣ የሥራ ዕድል ከማሳደግና ሁሉን አቀፍ የሆነ አገራዊ የልማት ስትራቴጂ ከመከተል አንፃር የግብርና ምርቶች ብክነት አስተዳደር ጉዳይ ችላ ተብሎ የቆየ መሆኑንም ያስረዳል። 

የግብርና ምርቶቹ ብክነት ከምርት እስከ ገበያ ትስስር ውስጥ የዘለቀ እንደሆነም ተነግሯል። 

እንደ ስትራቴጂው ማብራሪያ እያጋጠመ ያለው ብክነት የምርት ሒደት የሚያቀላጥፉ ግብዓቶችን፣ ማለትም ምርጥ ዘር፣ ውኃ፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ የግብርና ኬሚካሎች፣ መሬት፣ የእንስሳት መኖ፣ እንዲሁም የእንስሳት መድኃኒቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ካለመቻል እንደሆነ ተጠቅሷል። 

ባለፉት ዓመታት ለግብርና ምርት ጥቅም ላይ የሚውሉ የኬሚካል ማዳበሪያዎች፣ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች፣ የእንስሳት መድኃኒቶች፣ የግብርና መሣሪያዎች መለዋወጫዎችና ሌሎችም ለእርሻ ሥራ ላይ የሚውሉ ቁሳቁሶች በውጭ ምንዛሪ ተገዝተው እንደሚገቡ፣ በምርቶች ብክነት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እየታጣ መሆኑ አንድ ማሳያ ነው ተብሏል። 

አነስተኛ መጠን ያላቸው መሬት የሚያለሙ አርሶ አደሮች ምርት ከሰበሰቡ በኋላ ይዘው በማቆየት የሚያጋጥም ኪሳራና ብክነትን ሽሽት የግብርና ውጤቶቻቸውን ለነጋዴዎች በዝቅተኛ ዋጋ ለመሸጥ እየተገደዱ መሆናቸውን፣ በሌላ በኩል ግን በእርሻ ወራት የሚያስፈልጓቸውን ግብዓቶች የምግብ ደኅንነታቸውን መጠበቅ እንኳን በማያስችላቸው ከፍተኛ ዋጋ ለመግዛት እየተገደዱ እንደሆኑ ተገልጿል። 

የዚህም ውጤት አርሶ አደሮቹ እያጋጠማቸው ያለው የገንዘብ ዕጦት በገጠር አካባቢዎች ያለውን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ አለመቻል 80 በመቶ እንዳደረሰው፣ የሚኒስቴሩ ስትራቴጂካዊ ሰንድ ያብራራል፡፡

ይህም ከከተማው 20 በመቶ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አለመቻል ጋር ሲነፃፀር፣ በብክነቱ ከፍተኛ ተጎጂው አምራቹ እንደሆነ ይጠቁማል። 

አዲሱ የሰባት ዓመት ስትራቴጂ ስድስት ዋና ዋና ግቦች ያሉት ሲሆን፣ ለማስፈጸም ከ14.3 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግም ተገልጿል። 

በ2016 ዓ.ም. 1.52 ቢሊዮን ብር፣ በመጪው ዓመት 2.56 ቢሊዮን ብር፣ በ2018 ዓ.ም. 1.98 ቢሊዮን ብር፣ በተከታዩ ዓመት 2.3 ቢሊዮን ብር በጀት እንደሚፈለግ፣ በስትራቴጂው ትግበራ መዝጊያ ዓመት 1.91 ቢሊዮን ብር በጀት ይጠይቃል ተብሏል። 

በጀቱን ከመንግሥት ካዝና ጨምሮ ከግሉ ዘርፍ፣ ከዓለም አቀፍ አጋር አካላትና ከግል በጎ ፈቃደኞች ለማሟላት ሲታሰብ ገንዘቡን በዋናነት የሚያንቀሳቅሰው የግብርና ሚኒስቴር እንደሆነ የቀረበው ማብራሪያ ይገልጻል። 

የበጀቱ ከፍተኛው ክፍል 5.9 ቢሊዮን ብር አምራቾች የግብርና ምርቶችን ብክነት ለማስቀረት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ለማድረግ ለሚሰጡ ሥልጠናዎች፣ የጥናትና የምርምር ሥራዎች፣ ለአዳዲስ ግኝቶች ትግበራ፣ እንዲሁም የኤክስቴንሽን ፕሮግራሞችን ለማስጀመርና ለማስፋፋት ጥቅም ላይ ይውላል ተብሏል። 

ሁለተኛው ከፍተኛ በጀት 5.3 ቢሊዮን ብር የተመደበው በተለይ አነስተኛ እርሻዎች ላሏቸው አርሷ አደሮች እህል ማከማቻ የሚያገለግሉ ደረጃቸውን የጠበቁ መጋዘኖች ለመገንባት፣ ምርት ከአምራቾች እስከ ተጠቃሚው እስኪደርስ ድረስ እንዲባክን ሁኔታዎችን የሚያባብሱ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የመጋዘን አያያዝ ሁኔታዎች፣ መንገዶች፣ የትራንስፖርት ሒደቶችና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማት እንቅፋቶችን ለመቅረፍ የሚቀረፁ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ እንደሚውል ተገልጿል። 

በዚህ ዓላማ ሥር  በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያሉ የቀዝቃዛና የደረቅ መጋዘኖችን አሠራር አቅም ለማሳደግና አዳዲስ ለመገንባት፣ አገር አቀፍ የእህልና የጥራጥሬ መጋዘን ለመገንባት፣ የግብርና ምርቶች ብክነት የሚያግዙ መሳሪያዎች ሥልጠና የሚሰጥባቸውና የጥገና አገልግልግሎቶች የሚቀርቡባቸው ማዕከላት ግንባታ ለማካሄድ የሚያካትት ነው ተብሏል። 

የግብርና ንግድና የምርት ማቀነባበር ሥራ ላይ ለተሰማሩ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና ለመደገፍ 1.76 ቢሊዮን ብር ላይ ይውላል ተብሏል። 

ለግብርና ምርቶች ብክነት ቅነሳ በዘርፉ ውስጥ ያለውን የበጀት ሁኔታና ኢንቨስትመንት ለማሻሻል 520 ሚሊዮን ብር፣ የዘርፉ ተቋማትን ለመገንባትና ለማጠናከር፣ እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ያለውን የተቀናጀ ትብብር ለማጎልበት 440 ሚሊዮን ብር፣ በተጨማሪም የሕግ ማዕቀፎችን ለመቅረፅና ለማጠናከር 300 ሚሊዮን ብር በጀት እንደሚያስፈልግ ተብራርቷል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች