Tuesday, May 28, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር ፀባዮች የታደለች አገር መሆኗ ብዙ የተባለበት ነው፡፡ እነዚህን በረከቶች አቀናጅቶ መሥራት የሚያስችሉ በርካታ ዕድሎችና አማራጮች እያሉ ግን፣ የአገሪቱ ጊዜና ሀብት እየባከነ ያለው ፈፅሞ ጥቅም ለሌላቸው አጥፊና አውዳሚ ጉዳዮች ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በሁሉም ነገሮች መስማማት ቢያቅታቸው እንኳ፣ በብሔራዊ ወሳኝ ጉዳዮቻቸው ላይ በምንም ምክንያት ጎራ ለይተው መጠማመድና መጠፋፋት አይገባቸውም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ትልቁና መሠረታዊ የሆነው ችግር መነሻና መድረሻቸው አጥፊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ጊዜና ሀብት ማባከን ነው፡፡ ለመግለጽ የሚያዳግት አስመራሪ የድህነት አረንቋ ውስጥ በምትገኝ አገር፣ ሁሉም ነገር የንትርክ አጀንዳ መሆኑ ከመግረም አልፎ ያስቆጫል፡፡

ዓለም ዘመን አፈራሽ በሆኑ ቴክኖሎጂዎች አማካይነት እጅግ አስደማሚ የዕድገት ትሩፋቶችን በሚያጣጥምበት በዚህ ጊዜ፣ ከአገር አቅም በላይ የሆኑ ግጭቶችና ጦርነቶች በተለያዩ ሥፍራዎች ይካሄዳሉ፡፡ እነዚህ ግጭቶችና ጦርነቶች ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ እያደረሱ የአገሪቱ ገጽታ እየተበላሸ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት ቅኝ አገዛዝን አልቀበልም ብላ በአውሮፓ ኮሎኒያሊስት ኃይል ላይ አንፀባራቂ ድል የተቀዳጀች፣ በዚህ ወሳኝ ድል ምክንያትም ለአፍሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ተምሳሌት የሆነች፣ ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ምሥረታ ምክንያት የነበረችና በዓለም አደባባይ ክብሯን ያስጠበቀች እንደነበረች አይዘነጋም፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ የክብር ማማ ላይ ያወረዳት ግን የገዛ ልጆቿ አለመስማማት ነው፡፡ ልጆቿ ልዩነቶችን አክብረው በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መስማማት ሲገባቸው፣ እርስ በርስ እንደ ጠላት እየተያዩ በጭካኔ መፋጀታቸው አሁንም ቀጥሏል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖር የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ የሚለመንላቸው በግጭትና በድርቅ የተጠቁ ወገኖች ከሃያ ሚሊዮን በላይ እንደሆኑም በተለያዩ ጊዜያት ተነግሯል፡፡ መካከለኛ ገቢ የነበራቸው ወደ ደሃ ተርታ፣ ደሃ ተርታ ውስጥ የነበሩት ደግሞ የደሃ ደሃ እየተባሉ እንደሆነም በስፋት እየተሰማ ነው፡፡ በከተሞች የሚኖሩ ዜጎች በከፍተኛ የኑሮ ውድነት እየተሰቃዩ ሲሆኑ፣ በቂ መጠለያና አገልግሎቶችን ለማግኘት እየተፈተኑ ነው፡፡ በአርብቶ አደርነትና በግብርና የሚተዳደሩ አብዛኞቹ ወገኖች ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡ በሰው ኃይልና በተፈጥሮ ፀጋዎች የታደለች አገር ውስጥ እንዲህ ዓይነት እንቆቅልሽ ለዘመናት መቀጠሉ ያሳቅቃል፡፡ ለአገር ልማትና ለሕዝብ ኑሮ ዕድገት ቢተኮርና የማይረቡ አጀንዳዎች ወደ ጎን ቢገፉ፣ ይህ ሁሉ ሥቃይና መከራ አይደርስም ነበር፡፡

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ እያለፈችበት ላለው ችግርና ሰቆቃ በርካታ ምክንያቶችና ዕሳቤዎች ቢኖሩም፣ በአመዛኙ ጉዳት እያደረሱ ያሉት ግን ለሕዝብ ምንም ፋይዳ የሌላቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ተጠቃሽ የሚሆነው ለሥልጣን የሚደረገው ፉክክር ጤናማና ሰላማዊ አለመሆኑ ነው፡፡ ወደ ሥልጣነ መንበሩ የሚያነጣጥሩት የሁሉም ጎራ ተወካዮች ዓይኖች የሚያማትሩት፣ ከሕጋዊና ከሰላማዊ መንገድ ይልቅ የጉልበቱን አማራጭ ነው፡፡ ለስሙ ያህል ምርጫ ቢካሄድም ሒደቱ በአመዛኙ ከሕግ በተቃራኒ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ አንዱ ሌላኛውን በሐሳብ በልጦ የሕዝብ ልብ ከመማረክ ይልቅ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ሒደቱን ያውካል፡፡ ገዥው አካል ከሥልጣኑ ላለመነቅነቅ ቅድመ ምርጫ ጊዜያትን በማወክ፣ ተፎካካሪዎችም ከእጅ አይሻል ዶማ ሆነው ስለሚቀርቡ ንትርክ በመፍጠር ችግር መፍጠራቸው የተለመደ ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሒደት ያተረፈው ጥላቻና ጭቅጭቅ ብቻ ነው፡፡

በሕግና በሥርዓት ለመመራት በሁሉም ወገኖች ዘንድ ፈቃደኝነት ቢኖር ግን የሚከበረው የሕዝብ ድምፅ ነው፡፡ ያለፈው አገራዊ ምርጫ በአንፃራዊነት መልካም ምልክት አሳይቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ከምርጫው በኋላ ባሉት ዓመታት የታዩት ውዝግቦች፣ ንትርኮች፣ ግጭቶችና አውዳሚ ጦርነቶች ለኢትዮጵያም ሆነ ለሕዝቧ ያስከተሉት መዘዝ ከባድ ዋጋ እየተከፈለበት ነው፡፡ ለአገር ልማትና ለሕዝብ ኑሮ ዕድገት መዋል የሚገባው ጊዜና ሀብት ብቻ ሳይሆን፣ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ጭምር በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወቱን እያጣበት ነው፡፡ ማንኛውም የፖለቲካ ዓላማ የዜጎችን በሕይወት የመኖርና አካላዊ መብት ማስከበር መሆን ሲገባው፣ በገዛ አገር ተስፋ ለመቁረጥና ራስን ለስደት ማነሳሳት ሲውል መጪው ጊዜ ያስፈራል፡፡ ኢትዮጵያን ከገባችበት ቀውስ ውስጥ ለማውጣት የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ጠፍቶ፣ ሁሉም ባሻው ጎዳና የሚነጉድ ከሆነ አያዋጣም፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት አልፎ ሂያጅ በሆኑ አጀንዳዎች ከላይ እስከ ታች በመጠለፍ በርካታ ወርቃማ ዕድሎች አምልጠዋል፡፡ በተለይ በዚህ ችግር የሚወቀሱት ምሁራንና ልሂቃን ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ጊዜያቸውን ለአገር ጥቅም ምንም ፋይዳ በሌላቸው አጀንዳዎች አጥፍተዋል፡፡ ከአንድ ሥፍራ የተለቀቀ አጀንዳ በወጉ ሳይብላላና ለምን እንደተሰነዘረ ሳይታወቅ፣ በሌላ አዲስ አጀንዳ በመጠለፍ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ የሚያባክኑት ጊዜ ሊሰማቸው አልቻለም፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ፣ በማኅበራዊና በመሳሰሉት ፖሊሲ ነክ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር ጠቃሚ ሐሳቦች ማፍለቅ አልቻሉም፡፡ ይልቁንም በተለመዱት የጎራ ፖለቲካ ስንጥቆች ውስጥ ዘው እያሉ እየገቡ እሳት መጫር ነው የለመዱት፡፡ እሳቱ ግን ከአንዱ ወደ ሌላው እየተዛመተ አገር እያቃጠለ ነው፡፡ ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ሲባል ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስብ! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ያቀረቡት መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰማ

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞው የውኃ ሀብት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለዘመኑ በማይመጥን ዕሳቤ አገር ማተራመስ ይብቃ!

ዘመኑ እጅግ ድንቅ የሚባሉ የሥልጣኔ ትሩፋቶችን በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች እያቋደሰ ነው፡፡ ለልማትና ለዕድገት የሚማስኑ የኑሮን ጫና ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በስፋት ሲጠቀሙ፣ ያላደላቸው ደግሞ እርስ...

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...