Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?›› ይላል ጋቢና የተሰየመ ጎልማሳ። ‹‹ቀን ምን አለበት ቤንዚን ወይም ናፍጣ አይፈልግ። እኛ ነን እንጂ ሄድ ቆም እያልን የተቸገርነው…›› አለ መጠጥ ያለ ጉንጩን እየፈተገ ሾፌራችን። ‹‹እስኪ ምንድነው ችግሩ?›› ጠየቀች ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየመች ወይዘሮ። ‹‹ዝናብ…›› አለ ወያላው ነገር ባዘለ ድምፀት። መጨረሻ ወንበር የተሰየመች የቀይ ብስል፣ ‹‹ለመሆኑ እናንተ ነዳጅ ከየት ቀድታችሁ ነው?›› ብላ ጨዋታውን ተቀላቀለች። ‹‹ጂቡቲ የጣለ ኃይለኛ ዝናብ ነው ይላሉ የአቅርቦት እጥረቱን የፈጠረው…›› ብሎ ወያላው አንጠልጥሎ የተወውን መረጃ ደመደመው። ‹‹እንሄዳለን ወይስ አንሄድም? ወሬ ነው ነዳጅ ነው ያጠረህ ሾፌር? ለምን አንንቀሳቀስም?›› ባዩ ቶሎ ተቆጪ ደግሞ ከመሀል ወንበር አንባረቀ። ‹‹ቆይ ትንሽ ይሙላ…›› አለው ወያላው። ‹‹አሥራ ሁለት ሰዎች ጭነሃል፣ በቃ ግባና ዝጋው…›› ቁጣው ጨመረ ሰውዬው። ‹‹ምን አዳረቀህ ልጄ? በቃ እኮ ነገረህ፣ ጎድለናል ተብለናል ጎድለናል ነው። እሱ ሞልታችኋል እስኪለን ዝም አትልም? በገዛ እጃችን ያለ አቅም ግንባታ ተዋልደን ተዋልደን በዝተን የጎደልን እኛ። ተወው እስኪ…›› ብለው አዛውንቱ በምፀት ተናገሩ። ለነዳጅ እጥረት መንስዔ የሆነብን ዝናብ ዕውን ከመሬት ነው ከሰማይ ነው አያስብልም ታዲያ!

ጉዟችን ተጀምሯል። ሾፌሩ ቀልቡን ሰብስቦ ያዳምጥ ይመስል ሬዲዮኑን ከጣቢያ ወደ ጣቢያ ይፈትሻል። ጣቢያው ሁሉ በአሸሼ ገዳሜ የተከበበ ነው። ወይዘሮዋ ድንገት፣ ‹‹ይገርማል እኮ…›› ትላለች። ‹‹ምኑ?›› ትላታለች ከጎኗ። ‹‹እንዲያው የእኛ ነገር ልማትና ራዕይ አንጋራም እያልን ዛሬ ማን እንደሚያዛልቅና እንደማያዛልቅ አየን…›› አለቻት በደፈናው። ‹‹አልገባኝም?›› ስትላት፣ ‹‹ይኼው እኔ በኮሪደር ልማት መርሐ ግብሩ ከዚያ አስቀያሚ ሠፈር ወጥቼ የኮንዶሚኒየም ቤት ባለቤት ሆንኩ፡፡ እዚያ ለመኖር የሚያሰቅቅ ሠፈር ውስጥ ሃያ ዓመት ሙሉ በኪራይ ስኖር የረባ መኝታ ቤት፣ መታጠቢያ፣ መፀዳጃ፣ ኩሽና፣ ብቻ ምን አለፋሽ ለኑሮ የሚመች ነገር አላውቅም ነበር፡፡ ኑሮ ምን እንደሚመስል አሁን ገና አየሁት ለማለት ነው…›› አለቻት። ‹‹ልክ ነው የታገሰ ከሚስቱ ይወልዳል ነው የሚባለው…›› ሲል አንዱ ከአጠገቧ፣ ‹‹እሱ እንደ ትዳሩ ሁኔታ ይወሰናል…›› ባዩ መጨረሻ ወንበር ጥጉን ይዞ የተቀመጠ ጎልማሳ ነው። ‹‹ምን ማለት ነው?›› አንድ አዛውንት ጠየቁት። ‹‹የሰከነና ችኩል አንድ ነው እንዴ አባታችን?›› ሲላቸው፣ ‹‹ወደን መሰለህ ግራ የምንጋባው?›› አሉት አቀርቅረው። ያሰኛል!

ወያላው ገንዘቡን በንቃት ይሰበስባል። መጨረሻ ወንበር ያለው ተሳፋሪ አጠገቡ የተሰየመችውን ወጣት በፌስታል የተቋጠረ አረንጓዴ ቅጠል አውጥቶ እያሳያት፣ ‹‹እስቲ እንቃመስ…›› ይላታል። ‹‹ኧረ በስመአብ በል፣ ካልጠፋ ነገር ጫት ልቃም? አንተ ለምትቅመውም ይሰቀጥጠኛል፡፡ ባለፈው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለጫት ያሉትን ብትሰማ ራስህን ትጠላ ነበር…›› አለችው፡፡ ‹‹እሳቸውማ እኔንና ቢጤዎቼን ልካችንን ነው የነገሩን፡፡ ታዲያ አሁን ምን ልጋብዝሽ የእኔ ቆንጆ? ሰው ባለው ነው…›› አላት። ‹‹ባይሆን የኩዳዴ ፆም እስኪያልፍ ምናለበት ብትተወው?›› አለችው በቀናነት ከሥጋው አልፋ ለነፍሱ የተጨነቀች ትመስላለች። ከሾፌሩ ጀርባ ያለው መቀመጫ የተሰየመ ጎረምሳ፣ ‹‹እንዴ ይኼም እኮ ጎመን በይው አልተቀቀለም እንጂ…›› ይላታል። ‹‹ኧረ ይቅር ይበልህ…›› ብላ ልትዘጋው ስትል፣ ‹‹ጎመንም ጫትም፣ አበባም ሱፍም ይብቀሉ ያለው አምላክ ነው። ቆይ ሰው ምንድነው ችግሩ? ያለ መፈራረጅ መኖር አንችልም በቃ? ሰው ላይ ለመፍረድ አንደኞች። በፍትሕ ዕጦት ተሰቃይቶ ሰው በቁሙ ማቆ ሲሞት ያላየን ያልሰማን መሆን። ምንድነን ግን እኛ?›› እያለ ከመሀል ሌላው ተፈላሰፈ፡፡ አዛውንቱ ጉሮሮአቸውን እየሞረዱ፣ ‹‹እናንተ ሰዎች አገር ፈርሳ እንደገና እየተሠራች እያያችሁ ራሳችሁን መለወጥ ሲገባችሁ፣ ወጣትነታችሁን ለዚህ የማይረባ ቅጠል አሳልፋችሁ ሰጥታችሁ ለምን እንደምትሰቃዩ ይጨንቀኛል…›› ብለው አሁንም አቀረቀሩ፡፡ እውነታቸውን ነው!

ጉዟችን ቀጥሏል። መጨረሻ ወንበር ላይ ከተቀመጡት ወጣቶች በወዲያ በኩል በሾፌሩ ትይዩ ጥጉን ይዞ የተቀመጠ ተሳፋሪ ደግሞ በስልኩ ይነጋገራል። ‹‹እንዴት ነሽ? ደህና ነሽልኝ? ወይ አትጋበዥ ወይ አትጋብዥ? ቆይ ግን አንቺ ምን ይሻልሻል?›› ይላል። ሌላ ነገር ያወራል ስንለው አሁንም፣ ‹‹ወይ አትጋበዥ? ወይ አትጋብዥ…›› ይላታል። ይህንኑ ሦስት አራት ጊዜ ደጋገመው። ‹‹ለካ የአንዳንዱ ሰው ስልክ የሚሠራው በንፋስ ነው…›› ብሎ አንዱ አሽሟጠጠ። ‹‹ሥራ የፈታ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል ሲባል አልሰማህም መሰል…›› ትላለች ሌላዋ። ‹‹እኔ የምለው ጎበዝ በረባ ባረባው ቴሌ የሚያንጋጋብንን ‹ቴክስት ሜሴጅ› ማስቆም የሚቻለው እንዴት ነው?›› ጎልማሳው ይጠይቃል። ‹‹ቆይ እስኪ ተረጋጉ፣ አንድ ነገር አንድ ጊዜ ነው መከወን የሚቻለው። መጀመሪያ ሃምሳ ቢሊዮን ብር ያስፈልገዋል የተባለው ህዳሴ ግድብ ይጠናቀቅ፣ ከዚያ በሥልጣኔ ወደፊት እየገሰገሰ ስላለው ሀብታሙ ቴሌ እንነጋገራለን…›› ብለው አዛውንቱ ጨዋታው ላይ ተሳታፊ መሆን ጀመሩ። ‹‹ቆይ ግን አንቺ አትጋብዥ ወይ አትጋበዥ?›› ባለስልኩ ሞዛዛ ወቀሳውን ደገመው። ‹‹ኤጭ ምንድነው ይኼ ሰውዬ ወይ አይጋብዘን ወይ አያስጋብዘን አደረቀን እኮ ባዶ ሆዳችንን…›› ብላ ያቺ የቀይ ዳማ ስትናገር ጋባዥና ተጋባዥ፣ ጉዳይና ባለጉዳይ፣ ሸማችና ኑሮ ያልተገናኙበት ዘመን…›› ብሎ ጎልማሳው ጠቀሳት። ተረብ ተጀመረ!

ያ ቅጠል ቀንጣሹ ተሳፋሪ በበኩሉ፣ ‹‹አልሰማችሁም እንዴ?›› ብሎ ጣልቃ የገባው ይኼኔ ነው። ‹ምኑን?› አልነው አንድ ላይ። ‹‹በአለቀ ሰዓት የአሸናፊነትና የአቻናነት ጎል እየተቆጠረ መሆኑን?›› ብሎ አፈጠጠብን። ‹ምንድነው የሚያወራው?› ተባብለን ሳንጨርስ፣ ‹‹ተስፋ አለመቁረጥ ነው፣ ልክ እንደ ቻምፒዮንስ ሊግ ተፋላሚዎች የባከነውን ሰዓት ጨምረን ከታገልን ከመመራት ወደ መምራት የምንሸጋገርባቸው ጊዜያት ይመጣሉ። ጋባዥና ተጋባዥ፣ ጉዳይና ባለጉዳይ የሚገናኝበት ዘመን ቅርብ ነው…›› ብሎ በደፈናው ማውራት ሲጀምር፣ ‹‹እንዴት እባክህ፣ ቅጠሉ ነው ወይስ አንተ ነህ ትንተናውን የምታንደቀድቁብን፡፡ ልክ እንደ ትንቢት ተናጋሪ ተብዬዎች አንተም በአንዴ ከዓለማዊነት ወደ መንፈሳዊነት ተቀይረህ ግራ አጋባኸን እኮ፡፡ ለማንኛውም ምርቃና በሚሉት ነገር አለመወሰድህ መልካም ነው…›› የምትለው ወይዘሮዋ ናት፡፡ በባከነ ሰዓት ባክኖ የማይቀር ምንኛ ዕድለኛ ነው!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ረዥሙ ጉዟችን ሊገባደድ ጥቂት ቀርቶታል። ‹‹አሁንስ ልቤን ስብር የሚያደርገው የሰው ልጅ እንደ ዋዛ በወጣበት መቅረቱ ነው…›› ትላለች ወጣቷ የወይዘሮዋን ዓይን ዓይን እያየች። ‹‹መቼስ ምን ይደረጋል? የሰው ልጅ እኮ ጭካኔ ከሚባለው ሰይጣናዊ ድርጊት ጋር ሲቆራኝ ንፁኃን በየመንገዱ እንደ መፋቂያ እንጨት ይቆረጣሉ፡፡ መልካም ሰው ከራሱ፣ ከቤተሰቡ፣ ከዘመዱና ከማኅበረሰቡ አልፎ ለእንስሳትና ለዕፅዋት ሲጨነቅ ትታዘቢያለሽ። አሁን ግን አስፈሪ ጊዜ ውስጥ ነን…›› ብላ ወይዘሮዋ ተናገረች፡፡ ‹‹እውነትሽን ነው ልጄ፣ ፈጣሪ ይቅር ይበለን እንጂ የአንዱ መራብ ለሌላው መጥገብ፣ የአንዱ እንግልት ለሌላው ምቾት፣ የአንዱ ሞት ለሌላው ሕይወት እንደማይሆን ተገንዝበን እርስ በርስ ብንተዛዘን ጥሩ ነበር፡፡ ዳሩ ጭካኔ በዝቶ የሰው ልጅ እንደ ዱር አውሬ ታድኖ ሲገደል ያሳዝናል፡፡ በተለይ ለእኛ ሃይማኖቶች ጉልህ ተፅዕኖ በሚያሳድሩብን ኢትዮጵያውያን ውስጥ ጭካኔ ሲበዛ መቅሰፍት የሚመጣብን ይመስለኛል…›› ብለው ለሦስተኛ ጊዜ ሲያቀረቅሩ አብረናቸው አቀረቀርን፡፡ አንገትን ያስቀረቅራል!

‹‹እውነት ነው። ጠረፍ በሆኑ አካባቢዎች ዘመናዊነት፣ ከተሜነት፣ ንቃት፣ ግብረ ገብነት፣ ትምህርትና ሌሎች ገና ብዙ ስለሚቀሩ በሰዎች መካከል በተለያዩ ምክንያቶች ግጭቶች ቢከሰቱ አይገርምም። ግን እኔን የገረመኝ በየቴሌቪዥንና በየሬዲዮ ጣቢያው የአየር ሰዓቱን ተቆጣጥረው ግራ ሲያጋቡን የሚውሉ ጉዳዮቻችን ነገር ነው…›› አለ ጎልማሳው። ‹‹እኛማ ሕይወታችንን በማይገልጹ ተከታታይ ድራማዎችና ቅንጡ ማስታወቂያዎች አየሩን አጨናንቀውታል…›› ሲለው አንዱ፣ ‹‹በርካቶች ታግተዋል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ብሮች ለማስለቀቂያ ተጠይቀውባቸዋል…›› ይሉና ‹አቅም የሌላቸውን ብቻ ሳይሆን የከፈሉትን ጭምር ይገድሏቸዋል መባሉ ችግሩን በጣም የከፋ ያደርገዋል› አለ አንዱ በቀደም። ኧረ ሰው ለምንስ ይታገታል ለምንስ ይሞታል?›› እያለ ሳለ ወያላው፣ ‹‹መጨረሻ…›› ብሎ በሩን ከፈተው። ቃሊቲ ደርሰናል። አዛውንቱ ቀድመውን እየወረዱ፣ ‹‹ኤጭ አሁንስ በአንድ በኩል እጥረት በዛ ስንል በሌላ በኩል ውጥረት ይጠብቀናል…›› እያሉ አጉተመተሙ። ነገራችን ሁሉ እሳቸው እንዳሉት እጥረትና ውጥረት ብቻ ይሁን? መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት