Tuesday, May 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የገቢና የወጪ ንግድን ጨምሮ በጅምላና በችርቻሮ የሚሳተፉ የውጭ ባለሀብቶች የሚያሟሉት የካፒታል መጠን ይፋ ተደረገ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ሰባት ተቋማት የተካተቱበት ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ይደራጃል ተብሏል

ከዚህ ቀደም ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ በነበሩ በገቢ፣ በወጪ፣ በጅምላና በችርቻሮ ንግድ እንዲሳተፉ የሚያደርግ መመርያ ከፀደቀ በኋላ ሊያሟሉት የሚገባ የካፒታል መጠን ይፋ ተደረገ፡፡ ባለሀብቶቹ እንደሚሰማሩበት ዘርፍ ከ500 ሺሕ ዶላር እስከ አሥር ሚሊዮን ዶላር የካፒታል መጠን እንዲኖራቸው ይጠበቃል፡፡

የኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሐሙስ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በአራቱ ዘርፎች የውጭ ባለሀብቶች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ በመመርያ ቁጥር 10001/2016 ዓ.ም. በኢንቨስትመንት ቦርድ መፅደቁን፣ በመመርያው ውስጥ የተቀመጡ መሥፈርቶችን ያሟሉ የውጭ ባለሀብቶች ፈቃድ እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ዓመታት በመንግሥት ተይዘው የነበሩ ዘርፎችን ሙሉ በሙሉና በከፊል ወደ ግሉ ዘርፍ የማዞር ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን የገለጹት የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነሯ ወ/ሮ ሃና አርዓያ ሥላሴ፣ ይህም መመርያ የእነዚህ ሥራዎች አንድ አካል ነው ብለዋል፡፡

መመርያው ሲዘጋጅ ለአንድ ዓመት ያህል ጥናት እንደተደረገበት፣ ዘርፎቹ ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ተደርገው በመቆየታቸውም የገበያ ውድድሩን ገድቦት ቆይቷል ተብሏል፡፡ መመርያው ተግባራዊ ሲደረግ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ትርፍ ላይ ጫና እንደሚኖረው፣ በሌላ በኩል የሸቀጦች ዋጋ እንደሚቀንስና የመንግሥት ገቢ ጭማሪ እንዲያሳይ እንደሚያግዝ ተነግሯል፡፡

ከአራቱ ዘርፎች የወጪ ንግድ አንዱ ሲሆን፣ በዚህ ዘርፍ ውስጥ በጥሬ ቡና ወጪ ንግድ ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ የውጭ ባለሀብቶች ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ቢያንስ አሥር ሚሊዮን ዶላር የምርት ግዥ ከኢትዮጵያ ሲፈጽሙ የቆዩ መሆን እንዳለባቸው፣ ፈቃድ በወሰዱ የመጀመሪያ ዓመት ላይም የአሥር ሚሊዮን ዶላር ግዥ ውል ሊያከናውኑ ይገባል ተብሏል፡፡

የቅባት እህል ወጪ ንግድን በተመለከተ ባለፉት ሦስት ዓመታት ቢያንስ የአምስት ሚሊዮን ዶላር ግዥ ሲያከናውኑ የቆዩ፣ ፈቃድ ሲወስዱም የአምስት ሚሊዮን ዶላር የግዥ ውል መፈጸም የሚችሉ መሆን እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡ በጫትና በጥራጥሬ የወጪ ንግድ ለመሠማራት ቢያንስ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ግዥ ሲያከናውኑ የቆዩና የግዥ ውል የሚገቡ መሆን እንደሚገባቸው ተመልክቷል፡፡ 

ቆዳና ሌጦ፣ የደን ውጤቶችና ዶሮ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚፈልጉ የውጭ ባለሀብቶች 500 ሺሕ ዶላር ግዥ ያከናወኑና ውል የሚገቡ መሆን አለባቸው ተብሏል፡፡ በቁም እንስሳት የወጪ ንግድ መሠማራት ለሚፈልጉ የውጭ ባለሀብቶች በዘርፉ ያለው አፈጻጸም ዝቅተኛ በመሆኑ የግዥ ታሪክም ሆነ የግዥ ውል መፈጸም እንደማይጠበቅባቸው ተገልጿል፡፡

በወጪ ንግድ የሚሳተፍ ማንኛውም የውጭ ባለሀብት የተረጋገጠ ገበያ ሊኖረው እንደሚገባ፣ በዓመት ቢያንስ አምስት ሚሊዮን ዶላር የግዥ ውል ማቅረብ የሚችል መሆን እንደሚኖርበት ተጠቁሟል፡፡

ከማዳበሪያና ከነዳጅ ውጪ በገቢ ንግድ መሠማራት የሚፈልግ የውጭ ባለሀብት ፈቃድ መውሰድ የሚችል ሲሆን፣ አምራች አልያም የአምራች ተወካይ መሆን እንደሚኖርበትና ቢያንስ የአሥር ሚሊዮን ዶላር ገቢ ዕቃ በየዓመቱ ለማስመጣት ዕቅድ ሊያቀርብ ይገባል ተብሏል፡፡ 

የጅምላ ንግድን በተመለከተ ከማዳበሪያ ውጪ ባሉ ሁሉም የጅምላ ንግዶች መሳተፍ እንደሚቻል በመመርያው የተገለጸ ሲሆን፣ በየችርቻሮ ንግድ ግን በሁሉም ምርቶች መሳተፍ እንደሚችሉ ተመላክቷል፡፡

በችርቻሮ ንግድ ፈቃድ ለመውሰድም የንግድ ማዕከሉ ቢያንስ 2‚000 ካሬ የመሸጫ ቦታ ላይ ሊያርፍ እንደሚገባና በሦስት ዓመት ውስጥም አምስት ሱፐር ማርኬቶችን መክፈት እንደሚያስፈልግ፣ ፈቃድ ለመውሰድ ደግሞ ቢያንስ ሁለት ሱፐርማርኬቶች መክፈት የግድ ነው ተብሏል፡፡

መመርያው ወደፊት ተግባራዊ ሲደረግ በነበር የንግድ ሕጎች ላይ ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚቻል፣ አዳዲስ ሕጎችን ማውጣት ካስፈለገም ሊወጡ እንደሚችሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ አቶ እንዳለው መኮንን ገልጸው፣ በሁሉም ዘርፎች ቁጥጥር እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

የቁጥጥር ሥራውን ለማከናወን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የጉምሩክ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ያካተተ ኮሚቴ ይደራጃል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች