Wednesday, May 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየባህርና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ክፍያ አንፈጽምም ያሉ የመንግሥት ተቋማትን እንዲያግባባለት ለፓርላማው ጥያቄ አቀረበ

የባህርና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ክፍያ አንፈጽምም ያሉ የመንግሥት ተቋማትን እንዲያግባባለት ለፓርላማው ጥያቄ አቀረበ

ቀን:

  • ዋና ኦዲተር ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ አለመሰብሰቡን አስታውቋል
  • የቀድሞው ሜቴክ የአሁኑ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ያለበትን ዕዳ መክፈል አይችልም ተብሏል

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርትና የየብስ ወደቦች አገልግሎት የሰጣቸው የመንግሥት ተቋማት ያለባቸውን ክፍያ ባለመፈጸማቸው፣ ፓርላማው እንዲያግባባለት ትብብር ጠየቀ፡፡

ድርጅቱ ጥያቄውን ያቀረበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. የ2014/15 በጀት ዓመት፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በድርጅቱ ላይ ያቀረበውን የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት መነሻ በማድረግ ውይይት ሲደረግ ነው፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) ከኮሚቴው ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ‹‹ፓርላማው ጉዳዩን ዓይቶ ቢያግዘን በጣም አስፈላጊ ነው፣ ዕገዛ እንፈልጋለን፡፡ በተለይ በመንግሥት ድርጅቶች ላይ ያለን ተሰብሳቢ ሒሳብ በጊዜ እንዲከፈለን ፓርላማው የማወያየትና የማቀራረብ ሥራ እንዲያከናውን እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡

- Advertisement -

ከግል ድርጅቶች ያልተሰበሰበ ክፍያ አለመኖሩን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ለተሰጣቸው አገልግሎት ክፍያ ካልፈጸሙ የመንግሥት ተቋማት መካከል የቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የአሁኑ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ፣ የስኳር ኮርፖሬሽን፣ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ዝግጁነት ኮሚሽን፣ የትምህርት ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚገኙበት አስረድተዋል፡፡

ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በተሰጠው የዱቤ አገልግሎት የትራንዚት 83 ሚሊዮን ብር፣ የዲሜሬጅ 507 ሚሊዮን ብርና 209 ሺሕ ዶላር፣ የባህር ማጓጓዣ 169 ሚሊዮን ብርና 19.3 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ አለበት ተብሏል፡፡ ዕዳው በአጠቃላይ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ታውቋል፡፡  

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ለብሔራዊ አደጋ ሥጋት ኮሚሽን ለባህር ማጓጓዣ 22 ሚሊዮን ዶላር፣ ለዴሜሬጅ 3.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ለትራንዚት አገልግሎት 136 ሚሊዮን ብር ዋና ዋናዎቹ መሆናቸው ተገልጿል፡፡  

ከመንግሥት ተቋማት በተጨማሪም ለቦንድ መጋዘንና ለኢንዳስትሪ ፓርክ የሚያጓጉዙ ድርጅቶች ኦዲት እስከተከናወነበት ቀን ድረስ ያልከፈሉት 3.9 ሚሊዮን ዶላር የባህር ማጓጓዣ ክፍያ የወደብ ክሪላንስ አንድ ሚሊዮን ዶላር፣ የየብስ ትራንስፖርት ክፍያ 28 ሚሊዮን ብር፣ የኮንቴርነርና የትራክ ዲሜሬጅ ሰባት ሚሊዮን ብር ያልተከፈለ ገንዘብ መኖሩን ኮሚቴው በጥያቄ አቅርቧል፡፡

በተመሳሳይ ከጂቡቲ ወደብ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት አገልግሎት ካገኙ 97 ደንበኞች ያልተሰበሰበ 22.6 ሚሊዮን ብርና 7.9 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ተጠቅሷል፡፡

የኦዲት ሪፖርቱ የጉምሩክ ኮሚሽን በወደብ ተርሚናሎች የቆይታ ጊዜያቸው ያለፈባቸውንና የወረሳቸውን ንብረቶች በጨረታ ሲያስወግድ ለድርጅቱ ገቢ መደረግ የነበረበት 130 ሚሊዮን ብር አለመክፈሉ ቋሚ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ውስብስብ ችግር ውስጥ ሆኖ ትልቁ ተሰብሳቢ ሒሳብ ያለበት ተቋም መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ተቋሙ ክፍያውን እንዲፈጽም ንግግር ቢደረግም ዕዳውን መክፈል እንደማይችል አስታውቋል ብለዋል፡፡ ይህንን ችግር ለገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት ተደርጎ ምላሽ እየተጠበቀ ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የአደጋ ሥጋት ኮሚሽን ለተሰጠው አገልግሎት መክፈል የነበረበትን ክፍያ እንዲፈጽም ተጠይቆ ለመክፈል እንደሚችል ቢገለጽም፣ ጉዳዩ ብዙ ጊዜ በመውሰዱ ለገንዘብ ሚኒስቴር ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን አክለዋል፡፡

‹‹የስኳር ኮርፖሬሽን ያለበትን የአገልግሎት ክፍያ ዕዳ አምኖ ባለመቀበሉ ምክንያት ለመተማመን ተቸግረናል፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ያሉበትን የተሰብሳቢ ሒሳብ ሰነዶች በማቅረብ ለመተማመን ተሞክሮ ያመነውን ቢከፍልም አሁንም ቀረ  ክፍያ አለበት ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በሰጡት ማብራሪያ የኦዲት ድርጅቱን ኦዲት ለማድረግ አራት የትኩረት አቅጣጫዎችና 23 መመዘኛ መሥፈርቶች መቀመጣቸውን ገልጸው፣ ድርጅቱ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ወጪ ቆጣቢና ቀልጣፋ መሆናቸውን ገምግመናል ብለዋል፡፡

በዚህ መሠረት የኦዲት ክትትሉ ካመላከታቸው ክፍተቶች መካከል ዕቃዎች ተጭነው ወደ የሚፈለጉባቸው አካባቢዎች በሚሄዱበት ወቅት የሚያጋጥሙ ቅሸባዎች፣ ከዓላማው ውጪ የሆኑ ጭነቶችን መጫን፣ የጭነቶች ከወደብ በተያዘላቸው ጊዜ አለመነሳት፣ ደንበኞች ላልተፈለገ የዴሜሬጅ ክፍያ እየተዳረጉ መሆናቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ እንደ ዋና ኦዲተሯ ገለጻ ከተቋማት መሰብሰብ የነበረበትና ያልተሰበሰበ በአጠቃላይ ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ አለ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር)፣ ‹‹ለሰጣችሁት አገልግሎት በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የኦዲት ሥራ በናሙና ታይቶ ያልተሰበሰበው ገንዘብ አስደንጋጭ ነው፣ በመሆኑም ያልተሰበሰበው ገንዘብ መሰብሰብ አለበት፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ድህነትን በጋራ የማጥፋት ውጥን

ገበሬውን ተጠቃሚ ለማድረግና ድህነትን ለመቅረፍ ከተፈለገ፣ ገበሬው አምርቶና ፕሮሰስ...

ለፍልስጤም ዕውቅና መስጠት እስከ ምን?

በጋዛ እየተካሄደ ባለው ጦርነት የሕዝቡ ስቃይ ቀጥሏል፡፡ በዌስት ባንክ...

በዋጋ ንረት የተማረሩት አሶሳዎች

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ከተማ በፍጆታ ዕቃዎች እየታየ ባለው...