Tuesday, May 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በራያ አካባቢ አስተዳደራዊ መዋቅሮች ሙሉ በሙሉ መፍረሳቸው ተነገረ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሰሞኑ በአማራና በትግራይ አዋሳኝ የራያ አካባቢዎች እንደገና በተቀሰቀሰው ግጭት፣ የወረዳና የቀበሌ አስተዳደራዊ መዋቅሮች ሙሉ በሙሉ መፍረሳቸው ተገለጸ፡፡

ኮረም፣ ዛታ፣ ኦፍላ የተባሉ ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ በትግራይ ታጣቂዎች በመያዛቸው አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ በርካታ ነዋሪዎች ወደ ቆቦ፣ ሰቆጣና ወልዲያ መፈናቀላቸውን የኦፍላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍሰሐ ሞላ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አርሚ 24 እና አርሚ 26 የተባሉ የትግራይ ታጣቂዎች በአካባቢው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ የገለጹት አቶ ፍሰሐ፣ ታጣቂዎቹ ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ የኅብረተሰቡን ከብቶችና ንብረቶች በመቀማት ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

የትግል ክልል ታጣቂዎችና የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች ወደ አካባቢው በመግባት የፌዴራል ፖሊስ አስተዳደራዊ መዋቅሩን እንዳስረከባቸው እየጠየቁ ነበር ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፣ የፌዴራል ፖሊስ ግን ምንም ዓይነት ቢሮ አላስረከባቸውም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹እነሱ መሬቱን የእኛ ነው፣ እኛ ደግሞ ሕዝቡን ነው የምንፈልገው፤›› ያሉት አቶ ፍሰሐ፣ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫና ኅብረተሰቡ በመረጠው መንገድ አካባቢው እየተዳደረ ነበር ብለዋል፡፡ የትግራይ ክልል ሰዎች ግን በሰላማዊ መንገድ በምርጫ እንደማያሸንፉ ስለሚያውቁ በኃይል ለመውረር እየሞከሩ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ማስፈጸሚያ ደግሞ፣ ‹‹በመንግሥትና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሚዘወር ቡድን አቋቁመው ችግሮች እንዲባባሱ እየተደረገ ነው፤›› ሲሉ አቶ ፍሰሐ አክለዋል፡፡

ቀደም ሲል በሕወሓትና በፌዴራል መንግሥት መካከል በተካሄደው ጦርነት ተፈናቅለው ከነበሩት ሰዎች 95 በመቶ የሚሆኑት እንዲመለሱ መደረጋቸውን የተናገሩት አቶ ፍሰሐ፣ አሁንም ቢሆን ተፈናቅሎ በሌላ አካባቢ የሚኖር ሰው ካለ መመለስ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት እየገባ ታጣቂዎችን ሲመልስና ለማስማማት ሲሞክር እንደነበር የጠቀሱት አቶ ፍሰሐ፣ ችግሩ ሊፈታ ባለመቻሉ የአካባቢው ሚሊሻዎች የትግራይ ታጣቂዎችን ለመመከት ሲሉ ወደ ግጭት እንዳመሩ ጠቁመዋል፡፡

የትግራይ ታጣቂዎች ዲሽቃና ሞርታር የተባሉ መሣሪያዎችን ሲተኩሱ እንደነበር ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡

‹‹በአንዳንድ አካባቢዎች ለቀው የመውጣት ሁኔታ እያሳዩ ነው፣ ነገር ግን ይህ የሕወሓት ተለምዶአዊ ባህሪ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአላማጣ ከተማ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች የነበሩት የትግራይ ታጣቂዎች ከአካባቢው ለቀው በመውጣት ላይ መሆናቸውን ግን አስረድተዋል፡፡

‹‹የፕሪቶሪያው ስምምነት ተጥሶ ለአራተኛ ጊዜ ወደ ጦርነት እንድንገባ ፍላጎት ያላቸው አንዳንድ የሕወሓት ኃይሎች፣ ድርጊቱን እየፈጸሙት እንዳሉ ሊታወቅ ይገባል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ክልል በኩል ያለውን ምላሽ ለማካተት የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች