Tuesday, May 28, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

እንደገና ያገረሸው ግጭት መፍትሔ ይፈለግለት!

ሰሞኑን በራያና አካባቢው እንደገና ያገረሸው ግጭት አስቸኳይ መፍትሔ ካልተሰጠው፣ አድማሱ ሰፍቶ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚደርስ አያጠራጥርም፡፡ በራያ በኩል የተጀመረው ትንኮሳ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተዛምቶ ተጨማሪ ጥፋት ከመድረሱ በፊት መፍትሔ ይፈለግ፡፡ የአማራና የትግራይ ክልሎች የሚወዛገቡባቸው የወልቃይትና የራያ አካባቢዎች፣ ከዚህ በፊት ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን አውዳሚ ጦርነት የሚያስንቅ ጥፋት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መፍትሔዎች በአማራጭነት ቀርበው ንግግርና ድርድር ማድረግ ካልተቻለ ደም መፋሰሱ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ከሰሞኑ በራያ በኩል በተከሰተ ግጭት ምክንያት በአላማጣ ከተማና በአካባቢው ሰዎች መገደላቸው፣ ነዋሪዎችም ሕይወታቸውን ለማትረፍ በብዛት መሸሻቸው ተሰምቷል፡፡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ከተካሄደው ጦርነት ያላገገመው ይህ አካባቢ፣ እንደገና ሌላ ዙር ግጭት አገርሽቶ ዜጎች ሲገደሉና ከመኖሪያቸው በገፍ ሲፈናቀሉ ያስደነግጣል፡፡

በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደተሞከረው በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጦርነት አንገፍግፏቸዋል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚዘጋጁ የውይይት መድረኮችም ሆነ የመገናኛ ዘዴዎች፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም ያለህ እያለ እየጮኸ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በተደጋጋሚ ግጭቶች በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖች ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እየተማፀኑ ነው፡፡ በአማራ፣ በትግራይና በአፋር ክልሎች የተካሄደው አውዳሚው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት መቅጠፉ በተደጋጋሚ ሲነገር ተሰምቷል፡፡ ሕይወታቸው ከዚያ መአት ውስጥ የተረፈ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት ከመዳረጋቸው በተጨማሪ፣ የሚቀምሱት አጥተው የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ እየተለመነላቸው ነው፡፡ ዕርዳታው በበቂ መጠን ባለመገኘቱም ብዙዎቹ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው ያሉት፡፡ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው በየመጠለያው የወደቁ ቁጥራቸው በርካታ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች እንደገና አዲስ ጦርነት ሲጀመርባቸው ያሳቅቃል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች ይገባኛል የሚል ጥያቄ የሚነሳባቸው ግዛቶች በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ ማግኘት ሲገባቸው፣ አመቺ ጊዜ እየተመረጠ ወረራ ሲፈጸም ወይም በቁጥጥር ሥር ማዋል ሲጀመር ለአገረ መንግሥቱ ይዞት የሚመጣው ጦስ ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በየምክንያቱ መረጋጋት እያጣች ሰላም ሲቃወስ አቅሟ እየተዳከመ፣ እንደ ዘመነ መሣፍንት በየቦታው ራሳቸውን የቻሉ ጉልበተኞች መነሳታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ጉልበተኞቹ ራሳቸውን እያጠናከሩ ማዕከላዊ መንግሥትን መገዳደር ሲጀምሩ፣ አጋጣሚውን አድፍጠው የሚጠባበቁ ታሪካዊ ጠላቶች ክብሪትና ነዳጅ ይዘው ከየአቅጣጫው ብቅ ይላሉ፡፡ አንዱ ጦርነት ወይም ግጭት አብቅቶ እንደገና ሌላው ሲተካ የአገር አቅም ይዳከማል፡፡ ኢኮኖሚው በየቦታው የሚለኮሰውን ግጭት ማስተናገድ ስለሚሳነው ቀውሱ ይባባሳል፡፡ ለአገር ልማትና ዕድገት ሊውል የሚገባው የሰው ኃይልና ሀብት ለውድመት ይዳረጋል፡፡

በኢትዮጵያ ምድር ግጭት በፍጥነት ካልቆመ በመረረ ድህነት ውስጥ ሆነው ከዛሬ ነገ ያልፍልን ይሆናል እያሉ ተስፋ የሚሰንቁ ወጣቶች፣ ስደትን አማራጭ በማድረግ በአገኙት መንገድ አገራቸውን ጥለው ይኮበልላሉ፡፡ ተምረው አገራቸውን በሙያቸው ለማገልገል የሚጣጣሩትም ተስፋ እየቆረጡ ስደትን ያልማሉ፡፡ በሰከነ መንገድ ተቀምጦ በመነጋገር ለሁሉም የሚበጅ መፍትሔ ማፍለቅ የማይቻልበት አገር ውስጥ መኖር እንደ ገሃነመ እሳት እየተቆጠረ፣ ሁሉም በአገኘው አቅጣጫ ራሱን ለማዳን የሚገደድበት ሁኔታ በፍጥነት ገጽታው መቀየር አለበት፡፡ የፌዴራል መንግሥትም ሆነ ተወዛጋቢዎቹ ክልሎች በስክነት ያለውን ችግር ሥልጡን በሆነ መንገድ ለመፍታት ጥረት ያድርጉ፡፡ የጦረኝነት አባዜ አገር እያጠፋ ስለሆነ በቅጡ ያስቡበት፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም እየተካሄደ ያለውን አጥፊ ጎዳና በአንክሮ እየታዘበ እንደሆነ ግንዛቤ ይያዝ፡፡ ማንም አሸናፊ የማይሆንበት ውጊያ ትርፉ ዕልቂት ነው፡፡

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በዓለም ላይ እጅግ የከፋ ድህነት ካለባቸው አገሮች መካከል ግንባር ቀደሟ ናት፡፡ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስንዴና ዘይትን ጨምሮ፣ ሌሎች ምግቦችና ምግብ ነክ ቁሳቁሶች ድጋፍ እንዲያደርግ ያልተለመነበት ጊዜ የለም፡፡ አሁንም ከሃያ ሚሊዮን በላይ ዜጎች የዕለት ደራሽ ዕርዳታ እየተለመነላቸው ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በስዊዘርላንድ ዋና ከተማ ጄኔቭ በተደረገ ስብሰባ ለኢትዮጵያ ዕርጥባን ሲለመን ነበር፡፡ ለጋሾች የኢትዮጵያ መንግሥት በየቦታው ያሉ ግጭቶችን እንዲያስቆም ሲያሳስቡ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ መንግሥትም ማሳሰቢያውን በቅጡ ማዳመጡን በወኪሉ በኩል ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ዓለም እነዚህ ሰዎች የዕርዳታ እህል እየተቀበሉ እስከ መቼ ነው ከውጊያ ውስጥ የማይወጡት ብሎ ማዕቀብ ቢጥል፣ የዕርምጃው ተጎጂዎች ያለ ኃጢያታቸው የጦርነት ሰለባ የሆኑ ምስኪን ወገኖች እንደሚሆኑ አያጠራጥርም፡፡

አሁንም ደግመን ደጋግመን ጦርነትም ይሁን ግጭት በፍጥነት ይቁም እንላለን፡፡ ለሕግና ለሥርዓት ተገዥ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም አግኝቶ ዕፎይ ይበል፡፡ በግዛት ይገባኛል ጥያቄም ሆነ በሌላ ምክንያት ጉዳይ ያላችሁ ወገኖች እባካችሁ ጉልበትን አማራጭ አታድርጉ፡፡ ከጉልበት በመለስ ያሉ ሕጋዊና ሰላማዊ መንገዶችን ተመልከቱ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ፣ መሥራት፣ ጥሪት ማፍራትና በደስታ መኖር ካቃተው ዓመታት እየተቆጠሩ ነው፡፡ ጦርነት የንፁኃንን ሕይወት ከመቅጠፍ፣ ንብረታቸውን ከማውደም፣ ከቀዬአቸው ከማፈናቀልና ለአካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ከመዳረግ በተጨማሪ አገር እያሳጣቸው ነው፡፡ የሚያጠቡ እናቶችን፣ ነፍሰ ጡሮችን፣ ሕፃናትን፣ አዛውንቶችንና አቅመ ደካሞችን ለከፍተኛ ጉዳት አጋልጧል፡፡ ከጦርነት አዙሪት ውስጥ በፍጥነት መውጣት አለመቻል የሚያስከትለው መዘዝ ከባድ ነው፡፡ የሚመለከታችሁ በሙሉ በአስቸኳይ እንደገና ላገረሸው ግጭት መላ ፈልጉ!

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ያቀረቡት መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰማ

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞው የውኃ ሀብት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለዘመኑ በማይመጥን ዕሳቤ አገር ማተራመስ ይብቃ!

ዘመኑ እጅግ ድንቅ የሚባሉ የሥልጣኔ ትሩፋቶችን በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች እያቋደሰ ነው፡፡ ለልማትና ለዕድገት የሚማስኑ የኑሮን ጫና ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በስፋት ሲጠቀሙ፣ ያላደላቸው ደግሞ እርስ...

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...