Wednesday, May 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ከመንግሥት ድጋፍ ባለማግኘታችን ከገበያ እየወጣን ነው አሉ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተመስገን ተጋፋው

መንግሥት ለአገር ውስጥ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራች ኢዱስትሪዎች በቂ ድጋፍ ባለማድረጉና ጥሬ ዕቃዎች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመወደዱ፣ የአገር ውስጥ   አምራቾች ከገበያ ለመውጣት መገደዳቸውን ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ አልባሳት አምራቾች ይህንን የተናገሩት፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሐሙስ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች ከአካባቢ ጋር ተስማሚ በሆነ መንገድ ዘላቂና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያግዝ ፕሮጀክት ይፋ ሲያደርግ ነው፡፡

መንግሥት ለውጭ ኢንቨስተሮች ልዩ ትኩረት መስጠቱ ተገቢ አይደለም ያሉት የአገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመኖሩና በጥሬ ዕቃ ዋጋ መወደድ ምክንያት ከውጭ አምራቾች ጋር ተወዳዳሪ መሆን አለመቻላቸውን በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡

በርካታ የአገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ወደ ተለያዩ አገሮች የመላክ አቅም እንዳላቸው፣ ነገር ግን ዘርፉ በተለያዩ ችግሮች በመተብተቡና መንግሥትም መፍታት እንዳልቻለ አክለው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የውጭ ጨርቃ ጨርቅ አምራቾች በአገሮቻቸው መንግሥታት በቂ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው የተናገሩት የአገር ውስጥ አምራቾች፣  መንግሥት የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ቢጀምርም መሬት ተወርዶ ባለመሠራቱ  ችግሩ የበለጠ እንዲጎላ አድርጎታል ብለዋል፡፡

መንግሥት ለአገር ውስጥ ጨርቃ ጨርቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች ትኩረት እንዲሰጥ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ ልከው በሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ የፈለጉትን ዓይነት ምርት ማስገባት እንዲችሉ መፈቀዱ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ለሪፖርተር የተናገሩት የአንድ ኢንዱስትሪ ኃላፊ ናቸው፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ፣ ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት ለአምስት ዓመታት ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸው፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የሚደረጉ የምርት እንቅስቃሴዎች አካባቢን በማይጎዳ ሁኔታ እንዲከናወኑ ይረዳል ብለዋል፡፡

መንግሥት ከልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ፕሮጀክቱን ተግባራዊ የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ አምራቶች በዘላቂነት በአገር ውስጥና በውጭ ተወዳዳሪ ሆነው ምርታቸውን እንዲያቀርቡ የሚያበረታታ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል አምራቾች የአመራረት ዘይቤያቸው በአካባቢ ላይ ተፅዕኖ እንዳያደርስ፣ የተረፈ ምርት አጠቃቀምና የኬሚካል አስተዳደር አያያዝ ላይ ያላቸውን አቅም ለማሳደግ ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት ያግዛል ብለዋል፡፡

በተለይ በጨርቃ ጨርቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለምርት ጥቅም ላይ የሚውሉ ኬሚካሎችና ፍሳሾችን በማራጣት መልሰው ጥቅም ላይ የሚውሉበትን ‹‹ሰርኩላር ኢኮኖሚ›› የተባለ አሠራር፣ በፕሮጀክቱ ውስጥ መካተቱን አክለው ገልጸዋል፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ኢንዱስትሪዎች በንግድ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እየተጫወቱ ነው ብለዋል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪዎች ፍሳሾችን በቀጥታ ወንዝ ውስጥ ከመልቀቅ ይልቅ፣ እንደገና በማጣራት ወደ ግብዓትነት መቀየር የሚችሉበት አሠራር እንደሚኖር አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች