Thursday, June 13, 2024

በአማራና በትግራይ ክልሎች ያገረሸው የሰላም ዕጦት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ያለፈው ሳምንት የተጀመረው በአወዛጋቢዎቹ የወልቃይትና የራያ አካባቢዎች ግጭት ስለመጀመሩ በሚጠቁሙ ወሬዎች ነበር፡፡ ሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. አማራና ትግራይ ክልሎች እንደገና ግጭት ውስጥ ስለመግባታቸው አንዳንድ መረጃዎች መነገር ጀመሩ፡፡ በማግሥቱ ማክሰኞ ዕለት ደግሞ የትግራይ ታጣቂዎች የአላማጣ ከተማን መቆጣጠራቸው ጭምር ይነገር ጀመር፡፡

ሁኔታውን አስመልክቶ ከመንግሥት ወገን እስከ ረቡዕ በነበሩት ቀናት የተሰጡ ይሉዊ መግለጫዎች አልነበሩም፡፡ የትግራይ ኃይሎች በወረፋ የተያዘ መሬታችን ነው የሚሉትን አካባቢ ዳግም በከፈቱት ዘመቻ መልሰው በእጃቸው ስለማስገባታቸው በሰፊው መነገር ቀጠለ፡፡ ወልቃይትንም ሆነ ራያን በአጠቃላይ የትግራይን መሬት ማስመለሳቸው መነገር ቀጠለ፡፡

ይህ ሁሉ በማኅበራዊ የትሰስር ገጾች ሲዘዋወር የከረመ ወሬ በብዙኃኑ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሥጋት የሚያጭር ነበር፡፡ አገሪቱ ወደ ለየለት ጦርነት እንደገና ልትገባ ትችላለች በሚል ሥጋት የገባቸው ወገኖች ቁጥር ቀላል አልነበረም፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሥልጣናት ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. የሰጡት መግለጫም አወዛጋቢዎቹ የወልቃይትና የራያ አካባቢዎች ጉዳይ፣ ጦር ሊያማዝዝ ይሆን ወይ የሚል ጥያቄን ያጫሩ ነበሩ፡፡ ሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በሰጠው መግለጫ ካለፈው ጥፋቱ የማይማረው ሕወሓት ለአራተኛ ጊዜ በአማራ ክልል ላይ እንደገና ወረራ አካሄደ ማለቱ ደግሞ ግጭት ሊቀሰቅስ ይችላል የሚለውን ሥጋት የሚያጠናክር ነበር፡፡ ረቡዕ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. የወጣው የአማራ ክልል መንግሥት መግለጫ፣ በአወዛጋቢዎቹ የወልቃይትና የራያ መሬቶች የተነሳ ሁለቱ ክልሎች ወደ ዳግም ግጭት ሊገቡ ይችላሉ የሚለውን ሐሳብ የበለጠ አጠናክሮት ነው የሰነበተው፡፡

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት፣ እንዲሁም የፀጥታና የሰላም ምክር ቤት ኃላፊ ሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደ በማክሰኞው መግለጫቸው የትግራይና የአማራ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው አካባቢ የተቋቋሙ የአማራ ክልል አስተዳደር መዋቅሮች እንዲፈርሱ፣ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡ በምዕራብ ትግራይ፣ በፀለምትና በደቡብ ትግራይ የተቋቋሙ የአማራ ክልል አስተዳደር መዋቅሮች እንዲፈርሱ፣ በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ የታጠቁ ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱና ከአካባቢዎቹ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች እንዲመለሱ የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር ከስምምነት ስለመደረሱም ተናግረው ነበር፡፡

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከአማራ ክልል መንግሥትም ሆነ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር የፈጠረው አንዳችም ውዝግብ ወይም አለመግባባት አለመኖሩን በኤክስ (በቀድሞው ትዊተር) ገጻቸው ይፋ አድርገው ነበር፡፡ በአካባቢው ማለትም የትግራይና የአማራ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው የወሰን መሬቶች አካባቢ የተፈጠረው ሰሞነኛ ግጭት መነሻው ግን፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲተገበር የማይፈልጉ ኃይሎች ናቸው ብለዋል፡፡

ሕወሓት ወረራ ሊፈጽም ይችላል የሚል ሥጋት አስቀድሞም በአካባቢያቸው እንደነበር ለሪፖርተር የተናገሩት የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ፣ የትግራይ ኃይሎች ወደ አካባቢው ተኩስ በመክፈት ጭምር መዝለቃቸው ነዋሪዎች እንዲፈናቀሉ አድርጓል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በአማራና በትግራይ ክልሎች አወዛጋቢ አዋሳኝ መሬቶች አካባቢ ግጭት ተፈጠረ መባሉን በማስመልከት አብን ባወጣው መግለጫ፣ ጉዳዩን አራተኛ ዙር ወረራ ሲል ነበር የገለጸው፡፡ ሕወሓትንም ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘለዓለማዊ ጠላት›› በማለት የኮነነው አብን፣ በአማራ ሕዝብ ላይ ማታለልና ክህደት ተፈጽሟል እስከ ማለት ይሄዳል፡፡ የአማራ ሕዝብ ሥርዓትን አምኖ ችግሮች ሁሉ በሕግ ይፈታሉ የሚል ቀናነቱ ማታለያ ሆኗል ይላል፡፡

ከአማራ ክልል መንግሥት ተሰጠ የተባለው መግለጫም ቢሆን መረርና ከረር ያለ ነበር፡፡ የፕሪቶሪያውን ስምምነት በማክበር ሕወሓት በወረራ ከያዛቸው የአማራ ክልል መሬቶች በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ መግለጫው ይጠይቃል፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት በተደጋጋሚ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በፌዴራል መንግሥት አማካይነት ውይይት ሲያደርግ መቆየቱን መግለጫው ያወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ሕወሓት ይህን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው የማንነት ጥያቄ ያለባቸውን ራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረምና ዛታ አካባቢዎች ላይ ወረራ መፈጸሙን የአማራ ክልል መንግሥት መግለጫ ያትታል፡፡

የአማራና የትግራይ ክልሎች ሰሞነኛ ክስተት ከመግለጫና ከሚዲያ ቃላት ልውውጥ ባለፈ፣ መሬት ላይ የሚታይ ችግር መከሰቱን የተለያዩ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በርካታ የአላማጣና አካባቢው ነዋሪዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ወደ ራያ ቆቦ መሸሻቸውን የአካባቢው መረጃ ምንጮች አመልክተዋል፡፡

በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ሰሞነኛ ውዝግብ በአንዴ የሰላምም የጦርነትም ወሬ ሲስተጋባበት ይታያል፡፡ ከሁለቱም ወገን የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት ይከበር የሚል ጥያቄ ይስተጋባል፡፡ በሌላ በኩል አንዱ ሌላውን ወረረኝ እያለ ሲከስ ይደመጣል፡፡ የትግራይና የአማራ ክልሎች ከአሰቃቂው የሰሜኑ ጦርነት ወዲህ ወደ ተሻለ የሰላም ሁኔታ ስለመመለሳቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡ በቅርቡ የትግራይና የአማራ ኃይሎች ጥምረት ስለመፍጠር ጭምር በርካቶች የተለያዩ ቢሆኖች (ሴናሪዮዎችን) ሲሠሩ ጭምር ሲደመጥ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ሲባል ቆይቶ ከሰሞኑ በአወዛጋቢ የወሰን አካባቢዎች ተፈጠረ የተባለው የፖለቲካ መጎሻሸም፣ በአንዴ ስለአራተኛ ዙር ጦርነት ወሬውን ሁሉ የቀየረው ይመስላል፡፡

ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? የአማራና የትግራይ ክልሎች ወደ ለየለት ጦርነት እየገቡ ይሆን? ከሰሞኑ በአወዛጋቢ የወሰን አካባቢዎች የተፈጠረው ችግር በተጨባጭ ምን ነበር? የሚሉ ጉዳዮች በርካታ ጥያቄዎችን እያስነሱ ነው፡፡ በአማራና በትግራይ ክልሎች ወደ ጦርነት መግባት የሚጠቀመው ማነው ከሚለው ተጠየቅ ጀምሮ፣ የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ የሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ሚና ምንድነው የሚለው ጉዳይ በሰፊው እየተነሳ ነው፡፡ የአማራና የትግራይ ክልሎች ውዝግብ ወደ ጦርነት ከተሸጋገረና ተባብሶ ከቀጠለ፣ ከኢትዮጵያ አልፎ በቀጣናው ሊፈጥር ስለሚችለው ቀውስ ከወዲሁ አሳሳቢ ሥጋቶች እየተነሱ ነው፡፡

በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለሪፖርተር ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህርና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር)፣ ለሰሞኑ ችግር መፈጠር ሕወሓትን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡

‹‹የሰሞኑ ሁኔታ ወዴት እያመራ ነው የሚለውን ለመናገር ያስቸግራል፤›› የሚሉት ሲሳይ (ዶ/ር)፣ ነገር ግን በተጨባጭ በራያ አካባቢ እየሆነ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እንደሚከታተሉት ተናግረዋል፡፡ የሰሞኑን ግጭት የትግራይ ኃይሎች እንደጀመሩት ከአካባቢው ሚሊሻዎች ጭምር መረጃ እንዳገኙ ይገልጻሉ፡፡ በሞርታር፣ በዲሽቃ፣ በመትረየስ ተኩስ ታጅበው ተፈናቃዮችን ይዘው ወደ አላማጣ መጡ፡፡ ረቡዕ ዕለት አላማጣ ከተማን ቢከቡም ተፈናቃዮቹ እንጂ ታጣቂዎቹ ወደ ከተማው አልገቡም ይላሉ፡፡ ራያ ባላ የተባለውን ወረዳ ሙሉ ለሙሉ እንደያዙ ይገልጻሉ፡፡ ኮረም ከተማም ቢሆን ተፈናቃዮቹ እንጂ ታጣቂዎቹ አልገቡም፡፡ በከተሞች አቅራቢያ ያሉ ኬላዎችና ዋና ዋና መንገዶችን ይዘዋል ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

‹‹በተለይ በገጠር አካባቢዎች በይበልጥ  የማንነት ጥያቄ አንስተዋል የሚሏቸውን ሰዎች እየለዩ ሲያስሩና ሲያንገላቱ ነበር፡፡ የራያ አላማጣ አስተዳዳሪም ተገድለዋል፡፡ በያዟቸው አካባቢዎች ዘረፋና የንብረት መውሰድ ነበር፡፡ በአካባቢው በነበረው ውጊያ የሞቱ ሰዎችም አሉ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ግስጋሴያቸውን የቀነሱ ሲሆን ተመልሰው መውጣታቸውንም ሰምቻለሁ፤›› ብለዋል፡፡

በራያ አካባቢ የአማራ ክልል መሥርቶት የነበረው አስተዳደር አካላት ለቀው መውጣታቸውን አስተያየት ሰጪው ጨምረው ይናገራሉ፡፡ የራያ ኦፍላና ዛታ አስተዳደር ወደ ዋግና ሰቆጣ አቅጣጫ መሄዳቸውን፣ የራያ አላማጣና የራያ ባላ አካባቢ አስተዳደር ሰዎች ደግሞ ወደ ራያ ቆቦ አካባቢዎች ተፈናቅለዋል በማለት ይገልጻሉ፡፡

የትግራይ ኃይሎች ዳግም ወረሯቸው በተባሉ አካባቢዎች የራሳቸውን አስተዳደር ገና እንዳልተከሉ ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው በመጠቆም፣ አካባቢው በትግራይ ክልል ሥር በነበረ ወቅት የነበሩና የሸሹ የአስተዳደር ሰዎችን አጅበው እንደመጡ ይገልጻሉ፡፡

መንግሥት የትግራይና የአማራ ክልሎችን እያወዛገቡ ያሉ አካባቢዎችን ጥያቄ አፈታት በተመለከተ በቅርቡ አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ እንደተናገሩት፣ በሕዝበ ውሳኔ የእነዚህ አካባቢዎች ዕጣ ፈንታ እስኪወሰን በፌዴራል መንግሥቱ ሥር እንዲቀመጡ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ‹‹የተፈናቀሉ ሰዎች መጀመሪያ እንዲመለሱ ወስነናል፡፡ በራሱ በሕዝቡ ምርጫ አካባቢያዊ አስተዳደር እንዲመሠረት ወስነናል፡፡ ፌዴራል ፖሊስና መከላከያ ፀጥታውን እንዲጠብቁ፣ ለአካባቢው በጀት እንዲለቀቅለት፣ እንዲሁም በመጨረሻ በሕዝበ ውሳኔ የአካባቢው ዕጣ ፈንታ እንዲወሰን መፍትሔ አስቀምጠናል፤›› በማለት የፌዴራል መንግሥቱ የሚከተላቸውን መንገዶች ተናግረው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ፌዴራል መንግሥት ካስቀመጠው ከዚህ የመፍትሔ አቅጣጫ በተቃራኒ የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ለእኛ ተወሰነ፣ እንዲሁም ለእነ እከሌ ተሰጠ የሚል ከፍተኛ ውዝግብ በተከታታይ ሲከሰት ይስተዋላል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ወልቃይትና ራያ ለትግራይ ተመለሱ ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ለአማራ ተሰጥቷል እያሉ ከባድ ውዝግብ ይነሳል፡፡ ከሰሞኑ በራያ አካባቢ የተፈጠረው መጠነኛ መጎሻሸም ደግሞ ይህን ውዝግብ አጡዞታል፡፡

በወልቃይት ጉዳይ የአማራ ማንነት ተሟጋች የሆነው አስፋው አብረሃ በቅርበት በሚከታተለው የወልቃይት አካባቢ ጉዳይ ላይ አስተያየቱን ሲሰጥ፣ በአካባቢው ችግር አለመከሰቱን ይናገራል፡፡ ‹‹በራያ አካባቢ እንጂ በዚህ እኛ ግድም ትንኮሳም ችግርም የለም፤›› ይላል፡፡ በራያ ተፈጥሮ የነበረውም ሁኔታ መብረዱን የተናገረው አስፋው፣ ‹‹ከአካባቢው ወጥተው የነበሩ አስተዳዳሪዎች እየተመለሱ ነው፡፡ የራያ አካባቢ ወደ ቀደመው ሁኔታ እየተመለሰ መሆኑን ሰምቻለሁ፤›› በማለት ነው ሐሙስ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሪፖርተር የተናገረው፡፡

ሲሳይ (ዶ/ር) በበኩላቸው በራያ አካባቢ ከሰሞኑ የተፈጠረውን ችግር የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሰዎች ዕውቅና እንዳልሰጡት ማስተባበላቸውን እንደሚጠራጠሩት ይናገራሉ፡፡ ‹‹በአርሚ 24 የተደራጀ ኃይል ወደ አላማጣ ሲሄድ፣ በኦሮሚያ 44 የተደራጀ ኃይል ደግሞ ራያ ባላ አቅጣጫ ሲገባ፣ እንዲሁም በራያ ኦፍላ በኩል ሦስተኛ አርሚ ሲሄድ ይህን ሁሉ ከሦስት እስከ አራት ክፍለ ጦሮች ሠራዊት ያለው ኃይል ወደ አማራ ክልል ሲዘምት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አያውቅም ማለት አያሳምንም፤›› ብለዋል፡፡

ከሰሞኑ ወደ አማራ ክልል በራያ በኩል የገባው የትግራይ ኃይል ተራ ሽፍታ ወይም ትንሽ የታጠቀ ቡድን ሳይሆን፣ በደንብ የተደራጀ ሠራዊት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በትግራይ ባለሥልጣናት በኩል አካባቢውን ያዙ ተብለናል የሚል ትዕዛዝ መሰጠቱንም ቢሆን እንደ ተራ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ለማየት እንደሚቸገሩ ይናገራሉ፡

የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ‹‹በወረራ የተያዘ መሬታችንን ለማስመለስ›› እስከ ጦርነት ያሉ አማራጮ እንዳሏቸው ሲናገሩ መደመጣቸውንም ይገልጻሉ፡፡

‹‹አማራ ክልል በለየለት ጦርነት ውስጥ ነው፣ የተዳከመ ነው፡፡ የራያንና የወልቃይት አካባቢዎችን ብንይዝ የሚያቆመን የለም የሚል ግምት በትግራይ ኃይሎች ዘንድ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ ግን የፕሪቶሪያውን ሰላም ስምምነት የሚያፈርስ ብቻ ሳይሆን አካባቢውን ወደ ተወሳሰበ ቀውስ የሚከት ነው፡፡ በርካታ ወጣቶችና ሚሊሻዎች ወረራ ተፈጸመብን ብለው ወደ ፋኖ እየተቀላቀሉ ነው፡፡ አዲሱ ግጭት የአማራ ክልል ቀውስን ከእስካሁኑ ወደ ባሰ የቀውስ ምዕራፍ ይወስደዋል፡፡ ይህ እንዲሆን ካልተፈለገና ከበስተጀርባው የሚሠራ ወይም የሚጠረጠር የፖለቲካ ሴራ ከሌለ፣ የትግራይ ኃይሎችን በአስቸኳይ አስቁሞ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ ችግሩን በሕግ መፍታት ያስፈልጋል፤›› በማለት ነው ሲሳይ (ዶ/ር) ሐሳባቸውን ያሳረጉት፡፡

የሰሞኑን የራያ አካባቢ ውዝግብ ተከትሎ በጉዳዩ ላይ ያገባኛል የሚሉ ወገኖች ሥጋታቸውንና ማሳሰቢያቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የአማራ ሕዝብ ማንነትንና ህልውናህን ለመታደግ ተነስ›› ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) በተመሳሳይ ቀን ባወጣው መግለጫ የሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ ተደርጎ ሳለ፣ ሕወሓት ግን ይህንን ሁሉ ሠራዊት ትጥቅ ሳያስፈታ እንዲቆይ ለምን ተፈቀደ? የሚል ጥያቄ አንስቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -