Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየአዲስ አበባ የኮሪደር ልማትና የሕዝባዊ ተሳትፎ ጉዳይ

የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማትና የሕዝባዊ ተሳትፎ ጉዳይ

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

መዲናችን ዋና ዋና አደባባዮቿ፣ ነባርና አሮጌ ሠፈሮቿና የጎዳና ዳርቻዎች በከፊልና ሙሉ በሙሉ ፈርሰው እየተገነቡ ነው፡፡ ለነገሩ ባለፉት ስድስት ዓመታት ባልተረጋጋ አገረ መንግሥት ውስጥም ቢሆን የአዲስ አበባ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን፣ የፌዴራል መንግሥቱም በርካታ መንገዶችና ማሳለጫዎችን ገንብቷል፣ ቀይሯል፡፡ ፓርኮችና መናፈሻዎችን፣ ሙዚየሞችና የምርምር ማዕከላትን፣ አልፎ ተርፎ የልዩ ልዩ ቢሮዎች ሕንፃዎች፣ የገበያ፣ የክህሎት ማበልፀጊያና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ባለቤት ሆናለች መዲናዋ፡፡

እውነት ለመናገር በቆሻሻ ክምርና በማይመቹ ሠፈርነት የሚጠቀሱት እነ አትክልት ተራ፣ የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም የተገነባበት ሥፍራ፣ ወዘተ በርካታ መጠራጠርና ወቀሳ ቢወርድባቸውም በተሻለ የአገር ገጽታና አመቺነት የሚጠቀሱ ልማት ሆነዋል፡፡ ከተማዋም ለነዋሪዎቿ ውብ፣ ገጽታዋ ያሸበረቀ፣ ለጤና ተስማሚና ደረጃውን በጠበቀ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ በአዲስ መልክ እየታነፀች ለመምጣቷ በርካታ ባለሀብቶችና ነዋሪዎች፣ በአንድም በሌላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፣ እያደረጉም ነው።

አሁን በመተግበር ላይ ያለው በመቶ ቢሊዮኖች የሚገመት ብር የተመደበለት በጀትም የልማቱ ተነሽዎች ወደ ተሻለ ሕይወትና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ የሚቀየሩበት መንገድ እየተሳለጠ፣ ሰዎች ከኑሯቸውና ከሥራቸው ሳይፈናቀሉ ከዳር እንዲደርስ በትኩረት ከቀጠለ በታሪክ አንድ የሽግግር ምዕራፍ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ አገር ሰላምና መረጋጋትን እያገኘች ስትሄድም ውጤቱ ይበልጥ እየፈካ መሄዱ አይቀርም፡፡ ግን ሕዝብ ሊደመጥና በጎ ተሳትፎው ሊጠናከር ግድና ግድ ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በተለይ የመልሶ ማልማት ሥራን በተመለከተ ለአረንጓዴ ልማትና መሠረተ ልማት ዝርጋታ ብቻ ሳይሆን፣ ለከተማ አስተዳደሮች ከፍተኛ የገቢ ምንጭ የሚሆን የሊዝ መሬት የሚያስገኝ ነው፡፡ መሀል ከተማ ላይ የሚገኝ መሬት ደግሞ እጅግ ተፈላጊና ውድ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ እናም መንግሥት ከተማና አገር ለመቀየር የሚያስችል ሰፊ ሀብት ሊያገኝ ስለሚችል፣ በዲሲፕሊን ገንዘቡን መጠቀምና በካሳና ምትክ ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎችን በተቻለ መጠን ሳያስከፋ ማስተናገድ ልማቱን የላቀ እንዲሆን ይረዳዋል፡፡

በእርግጥ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለመገናኛ ብዝኃን ሲያስረዱ፣ ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ የሚነሱ አሉባልታዎች መሠረተ ቢስ መሆናቸውን ጠቁመው በዚህ ወቅት በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

በልማት ሒደቱ ከአካባቢያቸው ተነሺ የሆኑ ዜጎችን ከተማ አስተዳደሩ ካሳና ምትክ ቦታ በመስጠት በተገቢው እያስተናገደ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ፣ ሒደቱ የፍትሐዊነት ችግር እንዳይኖረው ጥንቃቄ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ልማቱ ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጀምሮ ጥናት የተደረገበት መሆኑንና የከተማ አስተዳደሩም በልማቱ ዙሪያ የአካባቢውን ኅብረተሰብ ማወያየቱን በመልካም ገጹ አንስተዋል።

እንደ ከንቲባዋ ከተማ አስተዳደሩ በልማት ተነሺዎች የሚነሱ ቅሬታዎች ካሉ  ለማስተናገድ የቅሬታ ጽሕፈት ቤት አቋቁሟል፣ የፒያሳን አካባቢ በሚሸፍነው የኮሪደር ልማት ጋር ተስማምተው እንዲሠሩ የተለዩ ስድስት ቅርሶች ተለይተዋል፣ በአጠቃላይ ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ተነሳሽነት ያለ መሆኑን፣ እንደገና እየተሠሩ ያሉ የመንገድ መሠረተ ልማቶችም ከወዲሁ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው።

ለአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ኅብረተሰቡ እያደረገ ላለው ትብብር ምሥጋናቸውን ያቀረቡት ከንቲባዋ ትብብሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የሕዝቡን ሙሉ ድጋፍና ተሳትፎ ዕውን ለማድረግ ግን ብልሹ አሠራሮችን ማረም፣ የበላይ አመራሩ ብቻ ሳይሆን የበታቹ ሹም ሳይቀር በቅንነትና በትጋት እንዲሠራ ማድረግ፣ እንዲሁም አፍራሽና አዋኪ አስተሳሰቦችን በትዕግሥት እያጠሩ መጓዝ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ያለሕዝብ ተሳትፎ የትኛውም ልማት ሊከናወን ቢችልም በቀጣይነት ለትውልድ ሊተላለፍ ስላማይችል ነው፡፡

ለአብነት አንዳንድ የሕዝብ ተሳትፎ ጉድለቶች ያለውን የልማት እንቅፋትነት እናንሳ፡፡ ነገሩ ደርግ የወደቀ ሰሞን በመንግሥት እርሻዎች ላይ የነበረውን ሁኔታ እንጥቀስ፡፡ ያኔ የመንግሥት እርሻዎች የአካባቢውን ሕዝብ የማያሳትፉ፣ አንድ ከብት ወደ እርሻው ወይም ወደ ሳሩ የተጠጋ እንደሆነ ይዘው በማሰር ‹ገንዘብ ካላመጣህ አይለቀቁም› እያሉ ሕዝብ የሚያስጨንቁ በመሆናቸው ትንሽ ግርግር ሲነሳ፣ ሕዝቡ እርሻው ላይ እሳት በመልቀቅና በማውደም ድምጥማጡን ያጠፋበት እንደ ነበር በርካታ ዘገባዎችን ማስታወስ ይቻላል፡፡

ለምን? የእሱ አልነበሩማ? አላማከሩት፣ አላሳተፉት፣ የጥቅም ተካፋይ የሚሆንበት ዘዴ አልቀየሱለት፡፡ ለምንና ለማን ብሎ ነው የሚጠብቃቸው? ‹‹የአገር ሀብት ነው…›› እያሉ ደረቅ ፕሮፓጋንዳ መንዛት ብቻውን ሕዝባዊ ተሳትፎን እንደማያረጋግጥ አንዱ ማሳያ ይኼ ነው፡፡

ማንኛውም ሰው ከአገሪቱ ሀብት ጥቂት እንኳን ሳያቀምሱት በወሬ ብቻ ‹‹ጠብቅ›› ቢሉት እሺ ሊል አይችልም፡፡ ስለሕዝባዊ ተሳትፎ እየተነጋገርን መሆኑን ልብ በሉ፡፡ ሕዝባዊ ተሳትፎ የሚለው ቃል ትርጓሜው ከዘመን ዘመን እየተለወጠ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ የሕዝባዊ ተሳትፎ ትርጉም በአብዛኛው ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነበር፡፡

የሕዝባዊ ተሳትፎ አንድምታ ከምርጫ ሥርዓት ጋር፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች አባልነት ጋር ከፈቃደኛነት ሥራዎችና ድርጊቶች ጋር ብቻ እንዲያያዝ የተደረገበት ዘመን ነበር፡፡ ከ1970/80ዎቹ ‹‹ሕዝባዊ ተሳትፎ›› የሚለው ቃል ትርጉም እንደገና እየታሸና እየተሻሻለ መጥቶ በልማት/በዕድገት ዓውድ (Development Context) አንፃር እንዲብራራ ተደረገ፡፡ አሁን የቃሉ ትርጉም ሰዎች ሕይወታቸውን በቀጥታ በሚነኩ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸው አስተዳደራዊ የተግባር ዕርምጃን የሚገልጽ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማለት የታችኛው ኅብረተሰብ በዙሪያው በሚካሄዱ ፕሮግራሞች፣ ፕሮጀክቶችና በጥቅም ተካፋይነት ላይ ከዕቅድ ማውጣት ጀምሮ በውሳኔና በአፈጻጸም ሒደቶች ውስጥ ሁሉ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግበትን አሠራር መተግበር ነው፡፡

አሁን አሁን እንደሚታየው ግን ሕዝብን በጥልቀት አማክሮና አሳምኖ መሄድ ላይ ክፍተት ያለ ይመስለኛል፡፡ ግብታዊነትና ትናንት እንደ ዋዛ በርካታ የአገር ሀብት የፈሰሰበትን ግንባታ ብድግ ብሎ ማፈራረስም ተደጋግሞ ይታያል፡፡ በመንግሥታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ በማተኮር ሕዝቡን ‹‹ውጡ፣ አምጡ፣ አዋጡ…›› ማለትና በዓመታዊ የሥራ አፈጻጸምና የቀጣይ ዓመት ዕቅድ ላይ ለግማሽ ቀን ሰብስቦ ማንጫጫት ሕዝባዊ ተሳትፎ ተብሎ ሊጠቀስ አይችልም፡፡

በቅርቡ በየክፍለ ከተማው ስብሰባ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት የታዘብኩትን ላንሳ፡፡ የጥሪ ወረቀቱ ይዘት በአጭሩ ‹‹በአካባቢው ልማት፣ በመልካም አስተዳደር፣ በፀጥታ፣ በካርታ አሰጣጥ፣ በመሬትና በመሬት ነክ ጉዳዮች ዙሪያ በሚደረገው ውይይት ላይ እንዲገኙ›› የሚል መልዕክት ያለው ነበር፡፡ እኔ የማውቃቸው የቀበሌያችን ነዋሪዎች አብዛኞቹ አልሄዱም፡፡ አንዳንዶቹ  ለምን አልሄዳችሁም ሲባሉ ትርፉ ድካም ነው፣ በዚህ በጠራራ ፀሐይ በሙቀት ለመቀቀል ካልሆነ በቀር ጠብ የሚል ነገር የላቸውም በማለት በምሬት ሲናገሩ ነበር፡፡

የሕዝባዊ ተሳትፎ ዋነኛ ዓላማ እያደገ የሚሄደውን ድህነት ለመቅረፍና ሕዝቡን በነቃና በተደራጀ ተሳትፎ የልማት ሥራዎች ውስጥ እንዲገባ ማስቻል ነው፡፡ አብዛኛው የከተማችን ነዋሪ ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች የሚኖርና የኑሮ ውድነት የሚፈትነው  ነው፡፡ በእርግጥ መንግሥት ገበያ ከማረጋጋትና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ከማድረግ ባለፈ ከዚህ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በአጭር ጊዜ ሊያወጣው አይችልም፡፡ ራሱን ከድህነት የሚያላቅቀው ሕዝቡ ራሱ ነው፡፡ አገራችን ካላት 120 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ ግማሽ ያህሉን ብቻ እንኳ በነቃና በተደራጀ መንገድ ሕዝባዊ ተሳትፎውን ማረጋገጥ ከተቻለ ድህነት ሊወገድ ይችላል፡፡ በተለይ ከተሜው ደግሞ በግልጽነትና በተጠያቂነት መንገድ ተሳትፎው ከተጠናከረ ፈጥኖ ለውጡን ሊቀላቀል ይችላል፡፡

ለምሳሌ በየጊዜው እያደገ የሚሄደው የሕዝብ ቁጥር ተጨማሪ ድህነትን እንዳያስከትሉ ለማድረግ የቤተሰብ ምጣኔ ያስፈልጋል፡፡ በአነስተኝ ቁጥር ልጆችን ማፍራት አስፈላጊነቱን በሕዝባዊ ተሳትፎ ብቻ ነው ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው፡፡ መጥኖ እንዲወልድና ኃላፊነቱን እንዲገነዘብ ለማድረግ በሁሉም እንቅስቃሴዎች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖረው ማድረግ ይገባል፡፡

ተቀዳሚው የተሳትፎ ዓይነት በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የሚኖረው ተሳትፎ ነው፡፡ ይህም ከዕቅድ ጀምሮ በዓላማው ላይና በፕሮጀክቱ ዓይነት ላይ ሕዝቡ ራሱ ችግሮቹን እያነሳ ለየትኛው ችግር ቅድሚያ እንደሚሰጥ እያረጋገጠ ውሳኔ የሚያሳልፍበት ዕድል እንዲኖረው የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የተሳተፈ ሕዝብ ደግሞ ከፍተኛ በራስ መተማመን ይኖረዋል፣ በመንግሥትም ላይ የባለቤትነት ስሜት ይፈጥራል፡፡ በዕቅድና በውሳኔ አሰጣጥ ላይ አሻራውን ያኖረ ሕዝብ ለዕቅዱ ተግባራዊነት ከልቡ ይሠራል፣ ውጤታማ ፍሬም ያገኛል፡፡

ምክንያቱም ‹‹ለራስህ የሚያስፈልግህን የምታውቀው አንተው ራስህ ነህ፣ ማነው ለማን የሚያውቅ›› ተብሎ ፍላጎቱን ለይቶ፣ ግቡን አውቆ፣ አማራጮችን መርምሮ እንዲወሰን ዕድል ስለተሰጠው በማንነቱ ይኮራል፡፡ ለዚህም ነው የከተማ ሹሞች ወደ ሕዝቡ ወርደው ከሕዝቡ መማር አለባቸው የሚባለው፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት ሕዝብ ከፍተኛ የልማት ኃይል ነውና ሳይታክቱ ማሳተፍ ይገባል፡፡

በትንሹ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ እንደታየው ሕዝቡ (ደሃ ሀብታም ሳይባል) መቀነቱን እየፈታ ጊዜና ጉልበቱን እያበረከተ፣ እየተባበረና እያስተባበረ በመስጠት የመንግሥትን የሥራ ጫና ያቃልላል፡፡ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆንም ማድረግና በየመስኩ ባለቤትነት እንዲሰማው ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ በከተማ ልማቶችም ቢሆን በጊዜያዊ ቋሚ ሥራ ብቻ ሳይሆን፣ ደሃው ነዋሪ ያለምንም መድልኦ በምግብ ለሥራም ቢሆን ጥቂት ነገር ሊያገኝ ይገባዋል፡፡

በራሱ ጉልበትና ገንዘብ ለራሱ አካባቢ የሚሆን ትምህርት ቤት፣ የጤና ጣቢያና የውኃ ቧንቧ ሊዘረጋለት ይገባል፡፡ በእርግጥ ኤሌክትሪክና ውኃ የሚያገኘውም ልማት በመኖሩ ነው፡፡ የተሳትፎው ውጤት ለሌላ አካባቢ ሳይሆን፣ ለዚያው አካባቢ ልማትና ተጠቃሚነት መሆን ማስገንዘብና ማንቃት አንድ የመንግሥት ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡

የሕዝብን ተሳትፎ ለማረጋገጥ የሚቀርቡ ፕሮጀክቶች በቀላሉ ሊተገብሩ የሚችሉና የጠለቀ ዕውቀትና ክህሎት የማይጠይቁ መሆን አለባቸው፡፡ የውኃ መንገድ መቀየስ፣ አነስተኛ ግድቦች፣ ባዮጋዝ፣ የተደራጀ አነስተኛ የሥራ ፈጠራ፣ ለምሳሌ አንድ ሺሕ ሴቶችን በእንጀራ ጋገራ ለማሳተፍ ከመነሳት በሃያና በሰላሳ ቁጥር ለአስተዳደር በሚያመች መንገድ ማደራጀት ተብሎ ላይመረጥ የሚችለውም፣ ብዝኃኑን ተጠቃሚ ለማድረግ ነው፡፡ ከፍተኛ በሆኑና ውስብስብነት ባላቸው ፕሮጀክቶች ሰዎች ለመነጋገር የሚያስችል ግንዛቤ ላይኖራቸው ይችላልና ተሳትፎአቸው እንዳይስተጓጎል መጠንቀቅ የሚጠቅመውም ለዚሁ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ሰዎች ስለራሳቸው ያላቸውን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ መለስተኛ ሥልጠና መስጠት ይገባል፡፡ ሰዎችን በአነስተኛ ቁጥር ማሰባሰብና ሥልጠና ሰጪው ከእነሱ ጋር እየተነጋገረ መሠረታዊ ችግራችሁ ምንድነው? እያለ የችግራቸውን ምንጭ እየመረመረ ለመፍትሔው ስትራቴጂ እየነደፈ፣ ይህንኑም ለሕዝቡ ለራሱ መልሶ እያቀረበና ይሁንታን እያገኘ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ የሕዝቡን የተሳትፎ ውጤት መጠበቅና ተግባራዊ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡

በሌላ አብነት ሰላምና ደኅንነትም ካለ ሕዝብ ተሳትፎ ዕውን እንደማይሆን መታመን አለበት፡፡ ያለ እናንተ ተሳትፎ የአካባቢው ሰላም አይጠበቅምና ‹ተሳትፎአችሁ ያስፈልገናል› የሚሉ ሹሞች ሕዝቡ ፀረ ሰላም ኃይሎችን (ወንጀለኞችን) ሲጠቁማቸው፣ ውሎ ሳያድር እየለቀቁ ለጠቋሚው ጠላት ከሚያፈሩለት ሹሞች ጋር ሕዝቡ መተባበር እንደማይፈልግ ማጤን ግድ ይላል፡፡ አንዱ የከተማ ሹም ሕዝቡን አስተባብሮ ያስጀመረውን ፕሮጀክት፣ ሌላኛው ሹም መጥቶ የሚያስቆመው ከሆነ የሕዝቡን ተሳትፎ በቀጣይነት ማግኘት አይቻልም፡፡

ቀደም ሲል እንዳነሳሁት ያለ ሕዝብ ተሳትፎ የተሠሩ ሥራዎችን ሕዝቡ የመንከባከብ ግዴታውን አይወጣም፡፡ አሁን አሁን መሻሻል ቢኖርም፣ በየመንገዱ ዳር ከሚሊኒየም ወቅት አንስቶ የተተከሉ ችግኞች ብዝዎቹ ሳይፀድቁ ወድቀው ቀርተዋል፡፡ ለምን? ሕዝቡ አያውቃቸውም፡፡ እንዲያውም መልካም አስተዳደር ሲጓደል አንዳንድ ባለሥልጣኖች ለራሳቸው ጥቅም ለማግኘት የፈጠሩት እንቅስቃሴ አድርጎ ስለሚገምት ችግኞቹን ዞር ብሎም አያያቸውም፡፡

እውነት ለመናገር ሕዝባዊ ተሳትፎን ከሚያጨናግፉ ዋንኛ ምክንያቶች አንዱ መልካም አስተዳደር ሲጓደል፣ ኢፍትሐዊነት ሲታይና የከተማው ሹሞች በሙስና ተዘፍቀው ሲገኙ ነው፡፡ ሕዝቡ ትልልቅ ሥራዎች ሳይቀሩ አሉታዊ አስተሳሰብን ስለሚይዝባቸው ተሳትፎውን ለማደራጀት አያስችሉም፣ በጥርጣሬ ያያቸዋል፣ አይተባበሯቸውም፡፡ የከተማ ሹሞች በራሳቸው ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩና ለግል ጥቅማቸው ብቻ የሚሯሯጡ መሆናቸውን የጠረጠረን ሕዝብ ለተሳትፎ ማንቀሳቀስ ይከብዳል፡፡ ስለዚህ ሥራው ጥብቅ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ በእርግጥ ከተሞች እጅግ በርካታ ሥራዎች እንዳሉባቸው እንረዳለን፡፡ የአቅማቸውን ያህል ሠርተዋል፣ እየሠሩም ናቸው፡፡ ግን ሕዝብን ከጎናቸው አሠልፈው እንዲሠሩ መጎትጎት ያስፈልጋል፡፡

እውነት ለመናገር የአሁኗ የከተማችን ከንቲባ ብዙ ችግሮችን ለማቃለል ሌት ተቀን ደክመዋል፣ አንዳንድ የካቢኒ አባሎቻቸውና ባለድርሻ የፌዴራል አካላትም በትጋት እንደሚሠሩ መመስከር ይቻላል፡፡ ሕዝባዊ ተሳትፎን በማረጋገጥ ረገድ ግን  ሁሉም ተጨማሪ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሕዝብን ተጠቃሚነትና ተሳትፎን ማንቀሳቀስ ደግሞ ችግር ሲመጣ ብቻ አይደለም፡፡ ለፕሮፓጋንዳ ያህልም አይደለም ሥራው መከናወን ያለበት፡፡ አወያይተናል፣ አሳትፈናል የሚል የበታች አመራሮች ሪፖርት መፈተሸ ያለበትም ለዚህ ነው፡፡

በመጨረሻም አዲስ አበባን ይበልጥ ለኑሮ ተስማሚና ውብ ለማድረግ የኮሪደር ልማት በተባለ ፕሮጀክት ከፍተኛ አፍርሶ የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ መጀመሩን መቃወም፣ በማይመች ሁኔታና በድህነት እንኑር ብሎ እንደ መሠለፍ ይቆጠራል፡፡ ተግባሩ የልማት ተነሺዎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እያከበረ፣ በተጀመረው መንገድ የሕዝቡን ተሳትፎ እያረጋገጠ፣ በተቻለ መጠን የሀብት ብክነትና ውንብድናን እየገታ፣ ብሎም አፍራሹን ፖለቲካ በተግባር መመከት ከቻለ መልካም ተግባር ነው፣ ተጠናክሮ መቀጠልም አለበት፡፡

በመሠረቱ ስለአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ስለየትኞቹም የአገራችን ከተሞች ስንነጋገር ስለተገነቡት መሠረተ ልማቶች፣ ፓርኮችና መናፈሻዎች፣ ፎቆችና የጋራ መኖሪያ ኮንዶሚኒየሞች ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ሕዝባዊ ተሳትፎን በነቃና በተደራጀ ሁኔታ አንቀሳቅሶ የነዋሪዎችና የሰዎች ሁሉ የኑሮ ሁኔታ ለመለወጥ የሚችሉበትን መንገድ ውጤታማ ለማድረግ መንግሥት አሠራሩን ግልጽ፣ ተጠያቂነት የተላበሰና ፍትሐዊ ማድረግ አለበት፡፡ እናም አካሄዶችን በሙሉ ደግሞ ደጋግሞ መመርመር ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] በሚለው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለቀድሞ የሕግ ታራሚዎች የቆመው ሰው ለሰው

የደርግ መንግሥት ደጋፊዎችና የሥልጣን ተጋሪዎች፣ ከከፍተኛ የቀድሞ መንግሥት ባለሥልጣናት...

ባይደን ከምርጫ ራሳቸውን ካገለሉ በኋላ የዴሞክራቱን መድረክ የተቆጣጠሩት ካማላ ሃሪስ

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ኮቪድ መያዛቸው በተነገረ ሳምንት ነበር...

‹‹በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ የተቋማችን ውድቀት ማሳያ ነው››

የአሜሪካ ደኅንነት አገልግሎት (Secret Service) ዳይሬክተር ኪምበርሊ ቺትል ለኮንግረስ...

አደራውን ለመጠበቅ ዕድል ያላገኘው ቅርስ ባለአደራ

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ከተመሠረተ ሦስት አሥርት አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ...