Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ወይ ነዶ!

እነሆ ጉዞ ከላምበረት ወደ ሜክሲኮ፡፡ ገና ከመንጋቱ ጨረሯን መለገስ የጀመረችው ፀሐይ ረፋዱ ላይ ምድሩን እንደ ምድጃ እያጋለችው ነው፡፡ ታክሲ ጥበቃ ወረፋ የያዙ ምስኪኖች ከላይ ሙቀት ከታች ግለት እያነደዳቸው በትዕግሥት ተሠልፈዋል፡፡ ‹‹ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም…›› ብላ አንዷ ከመሀል መናገር ስትጀምር፣ ‹‹እንታገላለን ብንልስ በየትኛው አንጀታችን…›› ብሎ አንዱ መልስ ይሰጣል፡፡ ‹‹ፍጥረት በሆዱ የሚያብሰለስለውን እርስ በርሱ እየተቀባበለ ባያወራርደው ኖሮ፣ በዘንድሮ ኑሮ መድረሻችን የት እንደሚሆን ሲታሰብ ግርም ይላል…›› የሚል ድምፅ ከወደኋላ ይሰማል፡፡ ብዙኃኑ የታክሲ ወረፋ ጠባቂዎች እየተሰማ ካለው ወግ እየተቋደሱ፣ ወጪና ወራጁን እያማተሩና ከራሳቸው ጋርም እየተነጋገሩ ታክሲ ጥበቃውን ተያይዘውታል፡፡ ‹‹ጠዋት በቁር፣ ቀን በንዳድ፣ ምሽት በውርጭ እየተጠበስን ትራንስፖርት ጥበቃ የምናጠፋው ጊዜ ለምን መንግሥትን እንደማያሳስበው ሳስበው ትክት ይለኛል…›› የምትለው መጀመሪያ መናገር የጀመረችው ቀጭን ጠይም ሴት ስትሆን፣ ‹‹መንግሥት ከቤተ መንግሥት ግንባታ እስከ ከተማ ማሳመር ሰፋፊ ፕሮጀክት ዘርግቶ የእኛ እንግልት ትዝም አይለው…›› ብሎ አንዱ ጣልቃ ሲገባ አንዲት የደከመች ሚኒባስ ደርሳ ቆመች፡፡ ግልግል!

ወያላው በየተራ ቆጥሮ ካስገባን በኋላ ቦታ ቦታችንን ይዘን ተቀመጥን፡፡ ‹‹ሳበው!›› በማለት ወያላው ለሾፌሩ ማሳሰቢያ ሲሰጥ ጎልማሳው ሾፌር በኋላ መመልከቻ መስታወቱ አጨንቁሮ አይቶ ሞተሩን ቀስቅሶ ጉዞ ተጀመረ፡፡ እንደ ጉዞ ፍታት የሚቆጠረው የጠዋት መንገድ በበርካታ ተሽከርካሪዎች ተጨናንቆ ስለነበር፣ ለአፍታም ቢሆን የብዙዎቹ ተሳፋሪዎች ቀልብ ውጭ ወዳለው ትዕይንት ተስቦ የታክሲ ውስጥ ወግ ለመጀመር ጊዜ ፈጀበት፡፡ ዕድሜ ጠገቧ ታክሲያችን የሠራ አካላቷ እየተንቋቋ በተጨናነቀው ጎዳና ውስጥ ስታዘግም፣ ‹‹አሄሄ… ይኼ ዕድሜ የሚሉት ነገር በሰው ብቻ ሳይሆን በቁሱም ላይ ነው ለካ ፍጥጥ ብሎ የሚታየው…›› ብለው አንድ ዕድሜ የጠገቡ ሸበቶ አዛውንት ሲስቁ፣ ‹‹አይ አባታችን ይህች አሁን ያረጀች መኪና እኮ ከሃያ ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ የተዜመላት ነበረች…›› እያለ ጎልማሳው ሾፌር ምላሽ ሲሰጣቸው የሁላችንም ቀልብ ወደ ውስጥ ተሰበሰበ፡፡ ይሻላል!

‹‹እንዲያው ይኼ የዕድሜ ነገር ሲነሳ የሁላችንም ስሜት መቅበጥበጥ ነው ግርም የሚለኝ…›› ብላ ያቺ ቀጭን ጠይም ነገር ወጋ ስታደርግ፣ ‹‹የዕድሜ ነገር ካላቅበጠበጠን ምን ሊያቅበጠብጠን ኖሯል…›› ታዲያ ሲል አንዱ ከኋላ መቀመጫ፣ ‹‹ኑሮን የሚያህል እንደ መርግ የሚከብድ ነገር ትከሻችን ላይ እያናጠረ የምን ዕድሜ ነው የምታወሩት…›› ብላ አንዲት ወይዘሮ ሐሳብ ማዋጣቱን ተቀላቀለች፡፡ አዛውንቱ ሁላችንንም በየተራ ቃኘት ሲያደርጉ ቆይተው፣ ‹‹እናንተ በሙሉ ሊባል በሚያስችል ደረጃ የዕድሜ ነገር የሚያሳስባችሁ አይመስለኝም፡፡ ገና ምኑን ነክታችሁት ነው በዕድሜ ነገር የምትታወኩት፡፡ በዚህ በአፍላ ዘመን ከባዱን የኑሮ ትግል አሸንፋችሁ ለመጣል በርቱ እንጂ፣ ማንም መጥቶ የኑሮን ቀንበር እንደማያቃልላችሁ ለመገንዘብ እኮ ማስተርስ ዲግሪ አያስፈልጋችሁም…›› አሉ፡፡ መሀል መቀመጫ የተሰየመ ነጭ መነጽር ዓይኖቹ ላይ የሰካ ምሁር መሳይ፣ ‹‹አባቴ ያሉት ትክክል ነው፡፡ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላው ጥበቃ ከያዝን ቀልጠን እንቀራለን፡፡ ዋናው ጉዳይ መሆን ያለበት ኑሮን አሸንፎ የተሻለ ሕይወት ለመምራት ራስን ማዘጋጀት ነው…›› እያለ አብራራልን፡፡ መልካም ነው!

ጉዞአችን ቀጥሏል፡፡ ወያላው ሒሳብ እየተቀበለ መልስ ለሚያስፈልገው እየሰጠ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር አንድ ከሲታ ጎልማሳ፣ ‹‹ድሮ በአንድ ብር የምንሄድበትን መንገድ እንዴት ሆኖ ነው ዛሬ ሃያ አምስት ብር የምንጠየቀው…›› እያለ ሲናገር፣ ‹‹እባክህ በድሮ በሬ ያረሰ የለም ሲባል አልሰማህም እንዴ…›› የሚለው ወያላው ነው፡፡ በዚህ መነሻ ድሮና ዛሬ ላይ የተመሠረቱ ወጎች ሲሰለቁ፣ ‹‹ይልቅስ አንድ ወግ ልንገራችሁ…›› ብለው አዛውንቱ ሾፌሩ ትኩረታችንን ለመሳብ ንግግራቸውን ገታ አደረጉ፡፡ ሁላችንም ምን ሊነግሩን ይሆን ብለን ፊታችንን ወደ እሳቸው ስናዞር፣ ‹‹…አንድ ጊዜ ከአምባሳደር ወደ አራት ኪሎ ላዳ ተሳፍረን እንመጣለን፡፡ ያኔ ከአምባሳደር አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል አጠገብ ድረስ በሃምሳ ሳንቲም ነበር የምንሳፈረው፡፡ እናም አራት ኪሎ ደርሰን ሒሳባችንን ከፍለን እየወረድን ሳለ አንደኛው ተሳፋሪ መቶ ብር አውጥቶ ለላዳው ሾፌር ሰጠው፡፡ ሾፌሩ እንዴት ለሃምሳ ሳንቲም ሒሳብ መቶ ብር ትሰጠኛለህ ብሎ ተናደደ…›› ብለው እየሳቁ ሳል አጣደፋቸው፡፡ እኛም አብረናቸው መሳል ነበር የቀረን!

አዛውንቱ ሳላቸው ተግ ብሎ ትንሽ ዕፎይታ ከወሰዱ በኋላ፣ ‹‹…የሾፌሩ ንዴት ምንም ያልመሰለው ተሳፋሪ እባክህ መልሴን አምጣ ብሎ መደንፋት ሲጀምር፣ ሾፌሩ እንግዲያውስ ንግድ ባንክ ዘርዝሬ ልምጣ ብሎት ላዳዋን ጥግ አስይዞ ወረደ፡፡ እኔም ጎልማሳ ስለነበርኩ ይህንን ጉድ አያለሁ ብዬ ቆምኩ፡፡ ባንክ ገብቶ ሲመለስ በካኪ ወረቀት የተሞላ ነገር ይዞ ብቅ አለ፡፡ ተሸክሞ ይዞት የመጣውን ካኪ ወረቀት ለሰውዬው እያቀበለው ይኸው መልስህ አለው፡፡ ሰውዬው በንዴት ምንድነው ብሎ ሲያፈጥበት፣ ለወደፊቱ ታክሲ እንዳትቸገር ብዬ የአንድ መቶ ብር ባለሃምሳ ሳንቲም ነው ያመጣሁልህ፡፡ በጣም እንዳይከብድህ ደግሞ የራሴን ሃምሳ ሳንቲም ወስጃለሁ ብሎ እየሳቀበት በቆመበት ጥሎት ሲሄድ የነበረው ሁኔታ ዛሬም እንደ ያኔው ያስቀኛል…›› ብለው በሳል የታጀበውን ሳቃቸውን ሲቀጥሉ አብረናቸው ሳቅን፡፡ ‹‹የዚህ ወግ መልዕክት ምን እንደሆነ አንድ ላይ ቢነግሩን ጥሩ ነበር…›› ብሎ ከጥግ በኩል አንድ ጎረምሳ ጥያቄ ሲያቀርብላቸው፣ ‹‹ልጄ ተመራምረህ ድረስበት እንጂ እስከ መቼ በማንኪያ አጉርሱኝ ትላለህ…›› ብለው አሳቁበት፡፡ ወይ አለመብሰል!

በቀርፋፋው የማለዳ ጉዞ እንደምንም ብላ መስቀል አደባባይ የደረሰችው ታክሲያችን መብራት አስቁሟት ሳለ፣ ‹‹ይኼ አደባባይ እንዴት አማረበት እባካችሁ…›› የምትለው ያቺ ቀጭን ሴት፣ ‹‹አሁንማ ከተማው በሙሉ የፈረንጅ አገር እንዲመስል ተብሎ እየተቆፈረ ነው፡፡ አገር ሲያምር የሰው ልጅም አብሮ ካላማረበት ምን ዋጋ አለው…›› ብላ ነገር ቆሰቆሰች፡፡ ‹‹ልማቱም ሆነ ይገኛል ተብሎ የሚታሰበው ዕድገት ሰው ሰው እንዲሸት እኮ ነው የብልፅግና መንግሥታችን እንቅልፍ አጥቶ እየሠራ  ያለው…›› በማለት አንዲት ቀላ ያለች ወጣት ከጋቢና ስትናገር፣ ‹‹ልጄ እንደ አፍሽ ያድርግልን፣ ከላይ ያሉትም በዚያ መንፈስ እንደሚሠሩ ደጋግመው እንደሚናገሩ ሰምተናል፡፡ ነገር ግን የማገር ዓይጦቹ ያንን የሌብነት አባዜያቸውን ይዘው ገብተው ፍጥረትን እያስለቀሱት ነው…›› ብለው አዛውንቱ ሲናገሩ ሁላችንም ተከዝን፡፡ ወያላው፣ ‹‹መንግሥት እጅና እግሩ ተጠፍሮ የተያዘው በሌቦች እንደሆነ እኮ ገና ያኔ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነግረውን ነበር…›› እያለ ሲስቅ በትውስታው እየተጀነነ ነበር፡፡ ያኔም ሌባ አሁንም ሌባ መግነናቸው ያስደንቃል!

‹‹አንተ ደግሞ ከቲክቶክና ከዩቲዩብ የምትለቃቅመው ነገር እኮ ነው እንዲህ ጅንን እያደረገ የሚያስወራህ…›› የሚለው ጎልማሳው ሾፌር ሲሆን፣ ወያላው ግን ከማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚገኝ ዕውቀት አይናቅም በሚል መታበይ፣ ‹‹ሾርት ሜሞሪ በበዛበት አገር ውስጥ የትናንቱን ለማስታወስ መቻል አቅም ይጠይቃል…›› ብሎ ያሾፍበታል፡፡ መሀል መቀመጫ ያለው ባለነጭ መነጽር፣ ‹‹ቀን እየሠራህ ማታ መማር ሲገባህ ማንም ጥራዝ ነጠቅ የሚጨፍርበትን አጉል ዕውቀት አትመፃደቅበት…›› ብሎ ሲወርፈው ሾፌሩ መሪውን በቡጢ እየነረተ ነበር የሳቀው፡፡ ወያላው ከደረሰበት የነገር የሚሳይል ጥቃት ለመሸሽ ነው መሰል አንገቱን ወደ ውጭ ሲመዝ፣ ‹‹አቤቱ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› የሚል ጥቅስ ከጭንቅላቱ በላይ ያለው የታክሲው ግድግዳ ላይ ተሰቅሎ ነበር፡፡ ‹‹አንዳንዴ ነገር ሲገጥም እንዲህ ነው ያሰኛል…›› ብላ ያች ቀጭን ጠይም ስትናገር፣ ‹‹እንደ ብልፅግና ልማታችን ነዋ…›› ብላ ቀይዋ ዘው ስትል እርስ በርስ ተያየን፡፡ ጉድ እኮ ነው!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል፡፡ ከላምበረት የተጀመረው ጉዞ እያዘገመም ቢሆን ወደ ሜክሲኮ ሲቃረብ፣ ‹‹ለእያንዳንዱ ጅማሬ ፍፃሜ አለው…›› ሲል ጎልማሳው፣ ‹‹እያንዳንዱ ፍፃሜም ጅማሬ ነበረው…›› የሚለው ባለመነጽሩ ነው፡፡ ‹‹አይ እናንተ፣ ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ ሆነሳ ነገራችሁ፡፡ ነገር እንደ ፀጉር እየሰነጠቁ መቀባበል ነው የሚሻለው ወይስ በጎደለው እየሞሉ ችግሮችን ማቃለል ነው የሚጠቅመው፡፡ እኔ በበኩሌ ነፍስ ካወቅኩበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን እንዲሁ በነገር ስንቋሰል፣ ቃላትና ሐረጎችን እየመነዘርን ስንዘላለፍ፣ ከጽንሰ ሐሳብ ይልቅ ለአጉል ወሬ ስንሟሟትና እንዲያው በአጠቃላይ ለአገር ምንም በማይጠቅሙ ነገሮች ላይ ስንራኮት ይኸው አለን፡፡ ትውልድ ይመጣል፣ ትውልድ ይሄዳል እኛ ግን ያው ነን…›› እያሉ አዛውንቱ ሲመረሩ፣ ‹‹አባታችን ምን ይደረግ ብለው ነው፣ ብንታደል ኖሮ እኮ በሚያኮሩ ታሪኮቻችን ተግባብተን፣ የማይጠቅሙትን ደግሞ ዶሴያቸው ውስጥ ዘግተን እንደ አያት ቅድመ አያቶቻችን ሰው መሆንን ማሳየት እንችል ነበር፡፡ ግና ምን ያደርጋል ከንቱ ሆነን አገራችንንም ከንቱ አደረግናት፡፡ ወይ ነዶ…›› የምትለዋ ወይዘሮዋ ነበረች፡፡ ሜክሲኮ ደርሰን ወያላው ‹‹መጨረሻ…›› ብሎ ሲያሰናብተን የወይዘሮዋን ወይ ነዶ የተዋስን ይመስል እየተብሰለሰልን ተለያየን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት