Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናመንግሥት የሪል ስቴት ንብረት ታክስና የተሽከርካሪ ዝውውር ታክስ ለመጣል አቀደ

መንግሥት የሪል ስቴት ንብረት ታክስና የተሽከርካሪ ዝውውር ታክስ ለመጣል አቀደ

ቀን:

መንግሥት የአገሪቱን የታክስ ገቢ ለማሳደግ የሪል ስቴት ንብረት ታክስና የሞተር ተሽከርካሪ ዝውውር ታክስ ለመጣል ማቀዱ ታወቀ።

መንግሥት ሁለቱንም አዲስ ዓይነት ታክሶች ከዘንድሮ ጀምሮ እስከሚቀጥለው ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ለመጣል ያቀደ ሲሆን፣ ይህንን ዕቅዱንም በሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ሰነድ ውስጥ እንደተካተተ ሪፖርተር ከሰነዱ ለመረዳት ችሏል።

የታቀደው የሞተር ተሽከርካሪ ዝውውር ታክስ በአገሪቱ ውስጥ ባሉ ሁሉም ተሽከርካሪዎች ላይ የሚተገበር እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

- Advertisement -

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ጎረቤት አገር ኬንያም የሞተር ተሽከርካሪ ዝውውር ታክስ ለመጣል ያቀደች ሲሆን፣ ይህንን ዕቅዷንም በቅርቡ ኬንያን ለጎበኙ የዓለም የገንዘብ ድርጅት ተወካዮች ማስረዳቷ ተሰምቷል።

ኬንያ ያቀደችው የተሽከርካሪ ዝውውር ታክስ እ.ኤ.አ. በ2024 የሚጣል እንደሆነ፣ የታክስ አጣጣሉም በሁለት መንገድ እንደሚሰላ ለማወቅ ተችሏል። የመጀመሪያ በሁሉም ተሽከርካሪዎች ላይ ወጥና አንድ ዓይነት የታክስ ተመን ማውጣት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ወጥ በሆነው የታክስ ተመን ላይ በእያንዳንዱ ተሽከርካሪ የሞተር አቅም ታስቦ የሚጣል ክፍያ እንደሆነ የአገሪቱ ብሔራዊ ግምጃ ቤት ከጥቂት ወራት በፊት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

ታክሱ በዓመት የሚከፈል ሲሆን፣ የተሽከርካሪ ባለቤቶች ለተሽከርካሪዎቻቸው የገዙትን ኢንሹራን በሚያሳድሱበት ወቅት አብሮ እንደሚሰበሰብ የአገሪቱ መንግሥት አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የታቀደው የሞተር ተሽከርካሪ ዝውውር ታክስ ተመንና ሥሌት በግልጽ ባይታወቅም፣ መንግሥት ይህንን ታክስ የመጣል ሥልጣን የሚያቋቁም ሕግ እ.ኤ.አ. በ2024 ውስጥ እንደሚያወጣ ሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ሰነድ የድርጊት መርሐ ግብር ላይ ተጠቁሟል።

የፌዴራል መንግሥት የተሽከርካሪ ዝውውር ታክስ የመጣል ሥልጣንን በሕግ በማቋቋም የታክስ ገቢውን የመሰብሰብና የመጠቀም ኃላፊነቶችን ግን፣ ለክልሎችና ለሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ሊሰጥ እንደሚችል ምንጮች ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪዎች እንዳሉ ሲገመት፣ ከእነዚህም ውስጥ ከ62 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተመዘገቡ መሆናቸውን፣ ከአዲስ አበባ በመቀጠል ደግሞ የኦሮሚያ ክልል በተሽከርካሪዎች ብዛት ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የቅርብ ጊዜ የመንግሥት መረጃዎች ያመለክታሉ።

በ2008 ዓ.ም. የአገሪቱ የተሸርካሪዎች ቁጥር 708,410 የነበረ ሲሆን፣ በሰኔ ወር 2009 ዓ.ም. 831,265  መድረሱን፣ በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. ደግሞ 1.2 ሚሊዮን እንዳደገ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

በአጠቃላይ በአገሪቱ የተሽከርካሪዎች ቁጥር በየዓመቱ በፍጥነት እየጨመረ ከመሆኑ አንፃር፣ መንግሥት ለመጣል ካቀደው የተሽከርካሪ ዝውውር ታክስ የሚያገኘው ገቢም እንዲሁ እያደገ እንደሚሄድ ይታመናል።

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች በሙሉ እንደየ ሞተር አቅማቸው የመንገድ ፈንድ ክፍያ በየዓመቱ የሚከፍሉ ሲሆን፣ አሁን የታቀደው የተሽከርካሪ ዝውውር ታክስ ከመንገድ ፈንድ ክፍያ በተጨማሪነት የሚጣል ነው።

የመንግሥት ሌላኛው ዕቅድ የሪል ስቴት ንብረት ታክስ መጣል ነው፡፡ ይህንንም እ.ኤ.አ. በ2025 ተግባራዊ እንደሚደረግ በሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ሰነድ ላይ የተቀመጠው ዝርዝር የድርጊት መርሐ ግብር ያመለክታል። መንግሥት ያቀደው አዲስ የሪል ስቴት ታክስ የሚጣለው፣ በአልሚዎች ላይ ይሁን በሪል ስቴት አልሚዎች፣ ወይም የተገነቡ ቤቶችን በሚገዙ ነዋሪዎች ላይ ይሁን፣ ሰነዱ በግልጽ አያመለክትም። ነገር ግን የታቀደው የሪል ስቴት ታክስ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች እንዲሰበሰብ ታቅዶ በመረቀቅ ላይ ከሚገኘው የንብረት ታክስ በተጨማሪ፣ የታቀደ አዲስ የታክስ ዓይነት መሆኑን ከሰነዱ ለመረዳት ተችሏል። 

መንግሥት ዘንድሮ ተግባራዊ ማድረግ በጀመረውና ለሦስት ዓመታት በሚቆየው ሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ ዘመን ውስጥ ሌሎች የታክስ ማሻሻያዎችንም ለማድረግ አቅዷል። 

ከእነዚህም መካከል የግል ገቢ ግብር (የደመወዝ ግብር) የተመን መዋቅርን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ማሻሻል፣ የዊዝሆልዲንግ ታክስ ምጣኔዎችን (ዲቪደንድ ታክስና የሮያሊቲ ክፍያ ተመኖችን) ማሻሻል፣ በገቢ ዕቃዎች ላይ የተጣለውን ሱር ታክስ በሒደት ሙሉ በሙሉ ማንሳት፣ በሥራ ላይ የሚገኘውን የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ማሻሻል፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ መብቶችን ማሻሻል ይገኙበታል።

እነዚህ የታክስ ማሻሻያ ዕቅዶች በሒደት ላይ ያሉትን፣ ማለትም የተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያና የተሸከርካሪ ታክስ ነፃ መብት ማሻሻያና የኤክሳይስ ታክስ ቴምብር ቀረጥን ለመጣል የተጀመሩ ሥራዎችን እንደማይጨምሩም ታውቋል።

በተጨማሪም በዚሁ የኢኮኖሚ ሪፎርም የትግበራ ዘመን ውስጥ በግብርና ዘርፍ ላይ ግብር ለመጣል የሚያስችል ጥናት በማካሄድ ለማጠናቀቅ ታቅዷል።

ሰነዱ እንደሚያስረዳው፣ የውጭ ሀብት ወይም የውጭ ልማት ፋይናንስ ተደራሽነት ላይ እርግጠኛ የመሆን አዝማሚያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመምጣቱ፣ የአገር ውስጥ የታክስ ገቢ አሰባሰብን ማሻሻል ለሁለተኛ አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ በመሠረታዊነት አስፈላጊ አድርጎታል።

በመሆኑም ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙ ገበሬዎችን ታሳቢ ያደረገ የግብርና ገቢ ግብር መጣልና በፊስካል ፖሊሲ ያልተሸፈኑ አዳዲስ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ወደ ግብር ሥርዓት በማምጣት የግብር መሠረቱን ለማስፋትና ከግብር የሚገኘውን የገቢ አቅም ለማጠናከር ታልሟል። ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥት ወጪዎችን ለመቀነስ ታልሟል፡፡ በዚህም ለክልሎች የሚተላለፍ የበጀት ድጎማ እንዳይጨምር እንደሚደረግ፣ የአፈር ማዳበሪያ ድጎማና ሌሎች የመንግሥት ድጎማዎች ለታለመላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ብቻ እንዲውሉ ለማድረግ ታቅዷል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...