Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ማበረታቻ ጎን ለጎን ዋጋቸውና ጥራታቸውም ይታሰብበት!

መንግሥት በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች እንዳይገቡ በተለያዩ መንገዶች ክልከላ እያደረገ ነው፡፡ በአንጻሩ በነዳጅ ከሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ይልቅ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ ማበረታቻዎችን እየሰጠ ነው፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በተለይ ሙሉ በሙሉ ተበትነው የሚመጡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በአገር ውስጥ ሲገጣጠሙ የማኅበራዊ ዋስትና ከሚባለው የሦስት በመቶ ታክስ ውጪ ከታክስ ነፃ ናቸው፡፡

በቀጥታ የሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በነዳጅ ከሚሠሩ ተሽከርካሪዎቹ ያነሰ ታክስ እንዲከፈልባቸው ተደርጎ የሚገቡም ናቸው፡፡ በተወሰነ ደረጃ ዕቃዎቻቸው መጥተው እዚህ የሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚከፍሉት ደግሞ አምስት በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ብቻ ነው፡፡

በቀጥታ የሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው ታክስም በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ከሚጣለው ታክስ በእጅጉ እንዲቀንስ ተደርጓል፡፡ አሁን በተሰጠው ማበረታቻ በቀጥታ የሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሌሎች ታክሶች ሳይታሰብባቸው የሚጠበቅባቸው 15 በመቶ ቀረጥ ብቻ ነው፡፡

ማበረታቻው ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በኤሌክትሪክ ለሚሠሩ ተሽከርካሪዎች የውጭ ምንዛሪ ከባንኮች ማግኘት ይቻላል፡፡ ይህም ማበረታቻ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ለማስመጣት ሌላ የተሻለ ዕድል መስጠቱን ያስገነዝበናል፡፡

እንዲህ ያለው ማበረታቻ በእርግጥም በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች በገፍ እንዲገቡ ያስችላል ተብሎ ይታመናል፡፡ ከቤት አውቶሞቢሎች ባሻገር የከተማ አውቶቡሶችን በኤሌክትሪክ በሚሠሩ አውቶቡሶች የመተካት ዕቅድ ያለ መሆኑም፣ መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማብዛት የነዳጅ ወጪውን ለመቀነስ ቁርጠኛ መሆኑን ያመለክታል፡፡

መንግሥት በዚህ ዘርፍ ያለውን ጠንከር ያለ አቋሙን የምናይበት ሌላው መገለጫ ደግሞ፣ በቅርቡ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ሚኒባሶችን ለሙከራ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሥራ እንዲጀምሩ ማድረጉ ነው፡፡

የመንግሥት ውሳኔ በዚህ ብቻ የሚያበቃ አልሆነም፡፡ በነዳጅ የሚሠሩ ሞተር ሳይክሎች የማይበረታቱ መሆኑንም አሳውቋል፡፡ እንዲህ ያሉ ዕርምጃዎች መንግሥት በነዳጅ ከሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ይልቅ በኤሌክትሪክ ለሚሠሩት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ያሳያል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተጨባጭ እያየን ያለነውም በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች መንገዱን እየያዙ መሆኑን ነው፡፡ ጥቂት የማይባሉ የመኪና መሸጫዎች በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን አብዝተው መያዝ መጀመራቸው በራሱ መጪው ጊዜ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ብልጫ እንደሚይዙ ጠቋሚ ነው፡፡

ሆኖም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አስፈላጊነት ታምኖበትና ጠቀሜታውም ተሰልቶ ማበረታቻ እየተሰጠ እንዲገቡ መፈቀዱ ብቻ፣ የሚፈለገውን ውጤት ያስገኛል ማለት እንዳልሆነም ሊታወቅ ይገባል፡፡

ተሽከርካሪዎቹን እንዲገቡ ከመፍቀድ ጎን ለጎን ዘላቂ ጠቀሜታ እንዲሰጡ፣ አብረው ሊተገበሩ የሚገባቸው ወሳኝ ጉዳዮች የተዘነጉ ስለሚመስል እነዚህን ወሳኝ የሚባሉ ዕርምጃዎች በቶሎ መተግበር ይገባል፡፡

ከእነዚህ ተሽከርካሪዎች ጋር በተያያዘ በአፋጣኝ መተግበር አለባቸው ተብለው ከሚጠቀሱ ዕርምጃዎች መካከል፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በትክክል የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው የተፈበረኩ ወይም የተገጣጠሙ መሆናቸውን በሚገባ ማረጋገጥ አንዱ ነው፡፡ እንደ ተገልጋይ ወይም እንደ ሸማች ይህ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ በዚህን ያህል ደረጃ ማበረታቻ የተሰጣቸው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አስመጪዎችና መገጣጠሚያዎች፣ የመሸጫ ማበረታቻውን ባገናዘበ መልኩ ዋጋቸው የተመጣጠነ ሆኖ ለተጠቃሚው ማስተላለፍ አለባቸው፡፡

ማበረታቻ የሚሰጠው አስመጪውን ወይም መገጣጠሚያውን ለመጥቀም ብቻ እንዳልሆነም መታወቅ አለበት፡፡ መንግሥት ሊያገኝ የሚገባውን ግብር የሚተመነው ዜጎች ከተሰጠው ማረታቻ በዋጋ ደረጃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማሰብ ጭምር መሆኑ ሊሳት አይገባም፡፡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ የሚሰጠው ማበረታቻ ግቡን እንዲመታ እንዲሁም ዜጎች ፈልገው እንዲገለገሉበት ለማድረግ በተመጠነ የትርፍ ህዳግ ግብይቱ ሲፈጸምና ይህም ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ሦስተኛውና ጊዜ ሊሰጠው የማይገባው ጉዳይ ደግሞ፣ የእነዚህ ተሽከርካሪዎች የጥገና አገልግሎትና አገልግሎቱ በሠለጠነ የሰው ኃይል እንዲካሄድ ማስቻል ነው፡፡ ሌላው ጥያቄ ደግሞ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ በቀላሉ ኤሌክትሪክ ሊሞሉበት የሚችሉበት የኤሌክትሪክ ማደያ ስቴሽኖች ግንባታ ነው፡፡

እነዚህ ወሳኝ የመሠረተ ልማት ግንባታና አገልግሎቶች መተግበር ያለባቸው ወይም ሊጀመሩ የሚገባቸው ተሽከርካሪዎቹ መንገድ ከሞሉ በኋላ ሳይሆን ከዲሁ ነው፡፡ በተለይ የባትሪ መሙያዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ማመቻቸት ግድ ይላል፡፡

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም ሌላው እንደ ሥጋት እየታየ ያለው ባትሪያቸው ካለቀ ወይም ከተበላሸ መልሶ ለመተካት ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል መባሉ ነው፡፡

ይህ ሥጋት ትክክል ከሆነ እንዲህ ያሉ ዛሬ ሳይሆን ወደፊት የሚያጋጥሙ ችግሮትን ለማቃለል ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያም ኅብረተሰቡ በቂ መረጃ እንዲኖረው ማድረግና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን በአግባቡ መተንተን ሁሉ ይጠይቃል፡፡

ሥጋቱን ለመቀነስም እንደ ኢንሹራንስ ያሉ ተቋማት የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ፣ እነርሱም የበኩላቸውን በማድረግ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለሚጠቀሙ ተገልጋዮች የተለየ የኢንሹራንስ ሽፋን በማዘጋጀት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል ሊያመቻቹ ይገባል፡፡

በአጠቃላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካዎች አገራችን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ጠቀሜታ የሚኖራቸው ቢሆንም፣ በአግባቡ እንዲያገለግሉ ምቹ ሁኔታዎች ሊፈጠሩላቸው ይገባል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት