Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሐሳብ ኮሪደር!

ሰላም! ሰላም! ውድ ወገኖቼ ሳምንት አልፎ ሳምንት እየተተካ ስንገናኝ ደስታዬ ወደር የለውም፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ለአገሬና ለወገኖቼ ብቻ ሳይሆን፣ በመላው ዓለም የሚኖሩ ሰብዓዊ ፍጡራን ጭምር ሰላም እንዲሆኑ እመኛለሁ፡፡ እናንተም እንደ እኔ ይህ ምኞት እንደሚኖራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ‹‹ሰላም… ሰላም… በዓለም ዙሪያ ሁሉ ለሰው ልጅ በሙሉ…›› እንዳለው የወርቃማው ዘመን ድምፃዊ መሐሙድ አህመድ፣ እኛም ለሰላም አበክረን ብንተባበር መልካም ነው እላለሁ፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹እኛ የሰው ልጆች ከፈጣሪ በተሰጠን ፀጋ መጠቀም ብንችል እኮ እንኳንስ እርስ በርሳችን፣ በጣም አስፈሪ የሚባሉ የዱር አውሬዎችን አላምደን በሰላምና በፍቅር መኖር እንደሚቻል የናሽናል ጆግራፊን ዶክመንትሪ ማየት በቂ ነው…›› የሚለው ሲታሰበኝ አዛውንቱ አባቱ የነገሩኝ ታሪክ አይረሳኝም፡፡ አዛውንቱ ባሻዬ ከረጅሙ ዕድሜያቸውና ከሰፊው ልምዳቸው በመነሳት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የሚነግሩኝ ታሪኮች፣ ምሳሌዎች፣ አባባሎች፣ ተረቶችና ወጎች ለእኔ እንደ ዩኒቨርሲቲ ዕውቀት ጠቅመውኛል ብላችሁ ያጋነንኩ እንዳይመስላችሁ፡፡ በእሳቸውና በልጃቸው ድጋፍ ባይሆን ኖሮ እኔ አንድ ተራ ደላላ ከእናንተ ጋር በየሳምንቱ ሐሳብ ለመለዋወጥ አልገናኝም ነበር፡፡ በጭራሽ አይሞከርም!

አዛውንቱ ባሻዬ የሰው ልጅ እንኳንስ እርስ በርሱ ጥቅጥቅ ያለ ደን ውስጥ ከሚኖሩ አስፈሪ አውሬዎች ጋር መላመድ እንዴት እንደሚችል፣ በአንድ ወቅት የነገሩኝን ላካፍላችሁ እስቲ፡፡ ‹‹ልጅ አንበርብር አሁን የምነግርህ ነገር አዲስ አይደለም፣ ምናልባት በአለፍ ገደም ሰምተኸው ሊሆን ይችላል፡፡ በአንድ ወቅት አንዲት ሴት ከባሏ ጋር የነበራት የደራ ፍቅር ቀዝቅዞባት ትበሳጫለች፡፡ መፍትሔ ፍለጋ ዘመድ፣ ወዳጅና ጎረቤት ስታማክር ጠብ የሚል ነገር አጣች፡፡ አንድ ችግሯ ያሳሰባቸው እናት እስቲ እዚያ ማዶ ያሉ አዋቂ መፍትሔ አያጡምና አማክሪያቸው ብለው ይነግሯታል…›› ብለው ባሻዬ ንግግራቸውን ገታ አድርገው በሐሳብ ጭልጥ አሉ፡፡ እኔ ደግሞ ወጋቸው በመቌረጡ ደስተኛ ስላልነበርኩ፣ ‹‹ባሻዬ ይቀጥሉ እንጂ ምን ነካዎት…›› ስላቸው፣ ‹‹አይ ልጅ አንበርብር በዚህ ዘመን እኛም እኮ እስኪ መፍትሔ እንዲሆናችሁ እንዲህ አድርጉ የሚል መካሪ ብናገኝ ኖሮ፣ አገራችን እንዲህ መላ ቅጧ ይጠፋ ነበር ወይ…›› ብለው ሲመልሱልኝ እኔም ክፍት አለኝ፡፡ እውነት ነው ጎበዝ እንዲህ የመሰለ ሐሳብ የለም እኮ፡፡ ሕመሙ በዛብን!

ባሻዬ ከሰጠሙበት ትካዜ ውስጥ ወጥተው፣ ‹‹…ያቺ የከፋት ምስኪን ሴት ከመንደሯ ማዶ ያለው አካባቢ ያሉ አዋቂ ዘንድ ደርሳ የደረሰባትን ችግር ተናገረች፡፡ በጣም የሚወዳት ባሏ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አመሉ እየተለወጠ መሆኑን፣ በፍፁም የማታወቀው እስኪመስላት ድረስ መቸገሯን ነገረቻቸው፡፡ አዋቂው በይ እንግዲህ መፍትሔ የምትፈልጊ ከሆነ ዱር ሄደሽ ከአንበሳ ጋማ ላይ ሦስት የፀጉር ዘለላዎችን ይዘዥ ነይ ሲሏት፣ ሴትየዋ ደንግጣ እንዴት አድርጌ ስትላቸው፣ መፍትሔ ለመፈለግ ማድረግ የሚቻለው ይኸው ብቻ ነው ብለው አሰናበቷት…›› ብለው ሲስቁ እኔ ግን እንደ ሴትየዋ ደነገጥኩ፡፡ ከአንበሳ ጋማ ላይ ሦስት ዘለላ ፀጉሮች ምን ዓይነት ጀግና ነው በመቀስ መቁረጥ የሚችለው ብዬም ተጨነቅኩ፡፡ ‹‹አንበርብር የቸገረው መላ አያጣም እንደሚባለው፣ ሴትየዋ አውጥታና አውርዳ ካሰበችበት በኋላ ወስና ለወሳኙ ተግባር ራሷን አዘጋጀች…›› ሲሉ በፍርኃት ልቤ ፍስስ አለችብኝ፡፡ እንዴት ነው አንዲት ግራ የገባት ምስኪን ሴት የደኑ ንጉሥ ዘንድ ሄዳ ከጋማው ላይ የፀጉር ዘለላዎች የምትወስደው የሚለው ግራ አጋባኝ፡፡ ጎበዝ በተፈጥሮዬ ደፋርና ጀግና የምወድ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ብሆንም፣ አጉል ጀብደኝነት ለእኔ ሐሳብ አይመችም፡፡ ወድጄ አይደለም!

አዛውንቱ ባሻዬ ግን ወጋቸውን ቀጥለዋል፡፡ ‹‹ቆራጧ ሴት ያሰበችውን ዓላማ ለማሳካት አዋቂው በነገሯት መሠረት መሰናዶዋን ጀመረች፡፡ ይህች ብልህ ሴት ከአንበሳ ጋማ ላይ ዘለላ ፀጉር አምጪ ተባለች እንጂ፣ ዘዴው እንዴት እንደሆነ ስላልተነገራት በራሷ መንገድ ዝግጅት ማድረጓ አስደናቂ ነበር፡፡ በመጀመሪያ አያ አንበሳ የሚገኝበትን የደን ክፍል አውቃ ከዚያ ከእንቅልፉ የሚነቃበትን ጊዜ አረጋገጠች፡፡ ከእንቅልፉ ሲነሳ ለቁርሱ የሚሆነውን በቀጥታ ገበያ ሄዳ አንድ ሙክት በግ ገዛች፡፡ በጉን አሳርዳ በብልት በብልት ከመደበች በኋላ በመጀመሪያ ቀን አንድ የፊት እግር ይዛ ወደ ደኑ ንጉሥ ገሰገሰች፡፡ ከእንቅልፉ ሊነቃ ሲገላበጥ ራቅ ብላ የበጉን እግር ወርውራለት ሄደች፡፡ በነጋታው ስትመጣ አንበሳ እየተገላበጠ ሳለ ትንሽ ጠጋ ብላ ሁለተኛውን የፊት እግር አስቀመጠችለት፡፡ በሚቀጥለው ቀን እስኪነቃ ጠብቃ ሲነሳ አንዱን የኋላ እግር በጣም ጠጋ ብላ ልትሰጠው ስትቃረብ ጭራውን እየቆላ ጠበቃት፡፡ እሷም በጣም ተጠግታው የሚበላውን ስትሰጠው፣ እየተሻሻት መብላት ሲጀምር ደስታዋ ወደር አልነበረውም…›› ብለው ሲስቁ እኔም በሐሳቤ አጀብኳቸው፡፡ ውይ ደስ ሲል!

እሳቸው በተመስጦ ውስጥ ሆነው፣ ‹‹በአራተኛው ቀን የቀረውን እግር ይዛለት ስትሄድ፣ አንበሳው ቀድሞ ነቅቶ በደስታ መሬት ላይ እየተንከባለለ ሲጠብቃት ከትናንቱ የባሰ ቀረበችው፡፡ እሱም እናቱ ከገበያ የመጣችለት ሕፃን ልጅ ይመስል እየቦረቀ እግሯ ሥር ሲንከባለል ያስደንቅ ነበር፡፡ ከዚያም የመጨረሻውን የበግ እግር ሰጥታው በደስታ መመገብ ሲጀምር ከጋማው ላይ የተወሰኑ ዘለላዎችን ቆርጣ ተሰናብታው ሄደች፡፡ በመሃረቧ ጥቅልል አድርጋ የያዘቻቸውን የአንበሳ ጋማ የፀጉር ዘለላዎች ይዛ ወደ አዋቂው ቤት በደስታ እየከነፈች ደረሰች…›› ብለው አሁንም ወጋቸውን ቆም ሲያደርጉ እኔም አዋቂው ምን መፍትሔ ይሰጧት ይሆን ብዬ፣ ‹‹ከዚያስ ባሻዬ…›› ከማለቴ፣ ‹‹አዋቂው ለመሆኑ እንዴት ነው አንበሳው ዘንድ የደረሽውና ከጋማው ላይ የፀጉር ዘለላዎችን የቆረጥሽው ብለው ሲጠይቌት፣ አጠቃላይ ዝግጅቷንና ክንውኗን ዘርዝራ ስታስረዳቸው መፍትሔ ለማግኘት ያደረገችውን ደፋር ጥረት በእጅጉ አመሠገኑ፡፡ ከዚያም መፍትሔ ለማግኘት በዚህ ደረጃ ማንም ሊያስብ የማይችለውን አድርገሽ፣ ከአስፈሪው የደኑ ንጉሥ አንበሳ ጋማ ላይ በጥበብ ዘለላ ፀጉሮች ማምጣት ከቻልሽ፣ ለዓመታት አብረሽ የኖርሽውን ባልሽን በቀላሉ የአንቺ ማድረግ አያቅትሽምና መልሱ እጅሽ ላይ ነው ብለው አሰናበቷት…›› ሲሉኝ የአዋቂው ድንቅ ሐሳብ በእጅጉ አስገረመኝ፡፡ ግሩም ድንቅ ነው!

ወገኖቼ ያው እንደምታውቁት ይህንን ወግ አስታውሼ ያመጣሁት ወግ ለመጠረቅ አይደለም፡፡ በኩዳዴ ፆም ሱባዔ ላይ ያሉት አዛውንቱ ባሻዬ ያኔ ይህንን ከላይ የነገርኳችሁን ወግ ያኔ ሲነግሩኝ፣ ‹‹ልጅ አንበርብር እየለገምን እንጂ ሰላማችንም ሆነ ተስፋችን ያለው እጃችን ላይ ነው፡፡ ፈጣሪ በሚወደው መንገድ ተከባብረን፣ ተፈቃቅረንና ተረዳድተን ለአገራችን በአንድነት መቆም ብንችል እንኳንስ ደም ልንፋሰስ ለኩርፊያ የሚበቃ ቅራኔ የለንም…›› ብለውኝ ነበር፡፡ ምሁሩ ልጃቸው ደግሞ፣ ‹‹አንበርብር መላ አገራችንን ዞረህ ብታካልል እኮ በሕዝባችን መካከል አንዳችም የሚያጣላ ነገር የለም፡፡ ይልቁንም ሕዝባችን ገበያ በለው ወይም ሌላ ሥፍራ ሲገናኝ እኮ ስለዝናብ መኖርና አለመኖር፣ ስለማኅበራዊ ክንውኖችና ሌሎች መልካም ነገሮች በፍቅር ከመጠያየቅ ውጪ አንዳችም ፀብ የለውም፡፡ ግና ምና ያደርጋል እኛ ተምረናል የምንባለው በማይረባ ከንቱ ፖለቲካችን ለአገር ልማት፣ ለሕዝብ ኑሮ ዕድገት ሳይሆን ለሥልጣንና ለጥቅም ስንል አገራችንን የደም ምድር አደረግናት፡፡ በሕዝብ ስም እየማልንና እየቆመርን አገሪቱን ሲኦል አድርገን ሕዝባችንን መከራ እናበላለን፡፡ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ግጭት መጠንሰስና መጥመቅ የዕለት ተዕለት ሥራችን ከሆነ ዓመታት እየነጎዱ ነው…›› ሲለኝ ሐሳቤ ዝብርቅርቅ እያለ እናደዳለሁ፡፡ ያበግናል!

ምንም እንኳ የድለላ ሥራ ተቀዛቅዞ ቢከርምም በአለፍ ገደም ስልኬ ስትጮህ በከፍተኛ ጉጉት ውስጥ ሆኜ ማንሳቴ አልቀረም፡፡ ብዙዎቹ ጥያቄዎች የባንክ ብድር መቼ ተለቆ የመሬትና የይዞታ ሽያጭ ቢዝነስ የሚጦፈው የሚል ነው፡፡ እንዴት ነው ነገሩ ጎበዝ፣ እኔ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሹም አይደለሁም፡፡ እንዲያውም እኮ ከባንኮች አጠቃላይ ብድር ከ23 በመቶ ወይም ከ440 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር የወሰዱ አሥር ግለሰቦች ብቻ ናቸው ከተባለ ወዲህ፣ ጭቁኑ ሕዝባችን ሀብታም የሚባል ስም አትጥሩብን ብሎ ሰላማዊ ሠልፍ እንዳይወጣ ሥጋት ይዞኛል፡፡ የባንኮቻችን ጉዳይ ተከድኖ ይብሰል ተብሎ ካልተተወ በስተቀር ብሔራዊ ባንክ በውስጥ ገመናቸው መደንገጡን እየነገረን፣ ለዘረፋ የመጋለጥ ደረጃቸው በጣም እያሳሰበው እንደሆነ በቀጥታ እያሳሰበን የብድር ጣሪያ መለቀቅና አለመለቀቅ ጉዳይ ሲነሳ ክፍት እያለኝ ነው፡፡ በቀደም አንድ የከተማው የዘመኑ ባለሀብት የሚባል ለአንድ ሥራ ፈልጎኝ ስንነጋገር፣ በንግግሩ መሀል ከአፉ አልጠፋ ያለው ይኸው የባንክ ብድር ጉዳይ ነው፡፡ እርግጥ ነው ለሚሠራ ሰው ገንዘብ ያስፈልገዋል፡፡ ገንዘቡ ግን ሥራ ላይ ሳይውል ቀርቶ ባንኮችንም ሆነ አገርን ዕዳ ውስጥ እንዳይከት ቁጥጥር የማስፈለጉ ሐሳብ ውልብ አለብኝ፡፡ የግድ ነው!

የኑሮአችን ጉዳይ ሲነሳ ደግሞ መንግሥት ሰሞኑን የደረሰበት ውሳኔ ግን አንጀቴን አርሶታል፡፡ የውጭ ባለሀብቶች በወጪና በገቢ ንግድ፣ እንዲሁም በጅምላና በችርቻሮ ሥራ እንዳይሳተፉ ተጥሎ የነበረው ገደብ መነሳቱ በበኩሌ ትልቅ ዕርምጃ ነው እላለሁ፡፡ የአገራችን አስመጪና ጅምላ ነጋዴም በሉት ቸርቻሪ በጣም ክፉ ከመሆኑ የተነሳ አዘኔታ እንደሌለው እኔ ዋናው ምስክር ነኝ፡፡ አንድ ጊዜ አንዱ ከውጭ በገፍ የምግብ ዘይት እያስገባ መክበሩን አውቃለሁ፡፡ ሰውዬው በጣም ጨካኝ ከመሆኑ የተነሳ በእኛ በምስኪኖች ላይ በአንድ ጊዜ ከውጭ ባስገባው ዘይት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፉን ሰምቻለሁ፡፡ እኛ ላይ ስንጥቅ ቢያተርፍ እንኳ መቶ ሚሊዮን ብር ማትረፍ ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን የትርፍ ህዳግ ሕግ ስለሌለ ከአሥር እጥፍ በላይ እያተረፈ፣ ዛሬ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሰባት ያህል ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች አሉት፡፡ የአገራችን ባለሀብቶች በአግባቡ አትርፈው ቢበለፅጉ ደስ ይላል እንጂ አያስከፋም፡፡ ነገር ግን አልጠግብ ባይ ስለሆኑ አሁን ቢበቃቸው እኔ ደስተኛ ነኝ፡፡ እኛ በእነሱ መበልፀግ ሳይከፋን እነሱ ግን ሲጨክኑብን ደስ አይልም፡፡ የኑሮ ውድነቱ የሚባባሰው በእነሱ የማይጠረቃ ፍላጎት ስለሆነ የውጮቹ ገብተው ተንፈስ ሲያደርጉን ማየት ስለምፈልግ፣ መንግሥትን በዚህ ውሳኔው አመሠግነዋለሁ፡፡ መልካም ሐሳብ ይደገፋል!

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ በተለያዩ አገሮች ሲዞር የገጠመውን ሲነግረኝ፣ ‹‹ሌላው ቀርቶ ከኬንያ ጀምሬ እስከ ደቡብ አፍሪካ በነበረኝ ጉዞ በርካታ የውጭ የጅምላና የችርቻሮ ገበያዎችን አይቻለሁ፡፡ እንደ ሾፕራይት፣ ፒክ ኤንድ ፔይ፣ ስፓር፣ ማስ ማርት፣ ውል ዎርዝስና የመሳሰሉት ትልልቅ ሱፐር ማርኬቶች በምርቶች አቅርቦትና ዋጋ ተመራጭ ናቸው፡፡ በተለይ እንደ ቅቤ፣ ወተት፣ ሥጋ፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች ዋጋ ከአገራችን ጋር በአቅርቦት ብዛትና ጥራት፣ እንዲሁም በዋጋ ሲነፃፀሩ በጣም ያስገርማል፡፡ እኛ እኮ የኋላቀር ግብይት ሥርዓትና የስግብግብ ነጋዴዎች ሰለባና መጫወቻ ነን…›› የሚለኝ አይረሳኝም፡፡ ሰሞኑን ከመንግሥት ውሳኔ በኋላ ይህንን ጉዳይ ሳነሳለት፣ ‹‹አንበርብር የአገራችን ባለሀብቶች ባይንገበገቡ ኖሮ የውጮቹ ገብተው ሥራቸውን እንዲቀሟቸው አንፈልግም ነበር፡፡ እንግዲህ እነሱ በአድማ ገበያውን ተቆጣጥረውት ከብዝበዛ አንላቀቅም ካሉ፣ እኛም ነፃ አውጭ ብንፈልግ ሊፈረድብን አይገባም፡፡ ምነው ቢባል ገበያው በሥርዓት ተመርቶ እኛም እንደ ሰው መኖር ስላለብን ነው…›› ሲለኝ፣ እሱ ውስጥ ያለው እውነት ከእኔ ጋር እየተጣጠመ ነበር፡፡ የጋራ ጉዳዮቻችን እንዲህ ቢጣጣሙ እኮ የማይረቡ ሐሳቦች መጫወቻ አንሆንም ነበር፡፡ እውነቴን ነው!

በሉ እስኪ እንሰነባበት፡፡ ቀኑ አልቆ ምሽቱ ሲቃረብ ለሐሳቤም ሆነ ለውሎዬ ማሳረጊያ ወደ ሆነችው ግሮሰሪ ማምራት የግድ ነበር፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እዚያ እየጠበቀኝ ስለሆነ ግሮሰሪያችን ደረስኩ፡፡ የግሮሰሪያችን ነባር ደንበኞችን ሰላምታ እየሰጠሁ ምሁሩ ወዳጄ ወደ ተቀመጠበት አመራሁ፡፡ የቀረበልንን ያላበው ቢራ እየተጎነጨን የባጥ የቆጡን ስንቀበጣጥር ሳለ፣ ‹‹እኔ እኮ የማይገባኝ ዘንድሮ እዚህ አገር የሚታመን ሰው ጠፋ በቃ…›› የሚል ድምፅ ከወደ ባንኮኒ አካባቢ ተሰማን፡፡ ባንኮኒው ላይ ከቆሙ አራት ሰዎች ወግ የተረዳነው፣ በቅርቡ የአፍሪካ ኅብረት ግቢ ውስጥ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ሊያዘዋውሩ ሲሉ ስለተያዙት ካህን ጉዳይ ነበር ወሬው፡፡ ከእነሱ ትይዩ ያለውን ጠረጴዛ ከበው ከተቀመጡ አንዱ፣ ‹‹ጣታችንን ሌሎች ላይ ስንቀስር የራሳችንንም እንከኖች ማስተዋልም ተገቢ ነው…›› እያለ ሲናገር ሰማነው፡፡ ምሁሩን የባሻዬ ልጅ በዓይኔ ጠቀስ ሳደርገው ጥያቄ መሆኑ ገብቶት፣ ‹‹ችግር እንደ ተራራ የተቆለለባት አገር ውስጥ በየቀኑ አዳዲስ አጀንዳ መፈልፈል አለመቆሙ ይደንቃል…›› እያለ ሲመልስልኝ እኔ በሐሳብ ጭልጥ እያልኩ ነበር፡፡ ቁሳዊው የልማት ኮሪደር ብቻ ሳይሆን ለችግሮቻችንም የሐሳብ ኮሪደር ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት