Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየሚያዝያው ድልና መታሰቢያው

የሚያዝያው ድልና መታሰቢያው

ቀን:

የታሪክ ሥፍራዎችና ሜዳዎች፣ የነፃነት ቀኖችና ወሮች ከነዘመናቸው የማይረሱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ዓድዋና የካቲት ሐያ ሦስት ቀን በመቼውም ዘመን በማናቸውም ወርና ቀን ቢሆን ሲታወሱ ትዝ የሚለው፣ በ1888 ዓ.ም. ከጣሊያኖች ጋር ተደርጎ በነበረው ጦርነት የተገኘው ድልና በዚህ ምክንያት በዓለም ላይ ጮራውን የፈነጠቀው የኢትዮጵያ የመታወቅ ዝና ነው፡፡ ድሉም ሲታሰብ አብረው ከሚታሰቡት ከንጉሠ ነገሥቱ ከአፄ ምኒልክ ጀምሮ ከሠራዊት እስከ መኳንንት የነበሩት የጦር ጀግኖች ናቸው የሚለው ‹‹ትንሣኤና ሕይወት ሚያዝያ ፳፯ት›› የተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡

የሚያዝያው ድልና መታሰቢያው | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ድል የተመታው ፋሺስቱ ቤኒቶ ሙሶሎኒ

‹‹ለአፄ ምኒልክና ለአፄ ኃይለ ሥላሴ ካሉዋቸው የድል ቀኖች ዋናዎቹ የካቲት 23 ቀን (1888) እና ሚያዝያ 27 ቀን (1933) ናቸው፡፡ ከዚህም አስቀድሞ ለነበሩት ለአፄ ዮሐንስ የድል ቀኖችና ሜዳዎች ነበሯቸው፡፡ እነ ጉንደት፣ እነጉራዕ፣ እነ ሰሐጢና እነ ዶግዓሊ የየራሳቸው የድል ቀኖች አሏቸው ሲልም ያክላል ታሪካዊው ድርሳን፡፡

የጣሊያን ጭንቅ በሰባቱ ዕለታት አምሳል

- Advertisement -

‹‹ሰኞ ገጠመው ምክንያቱን እንጃ፣

አነባባሪ ባዲስ ጠበንጃ፡፡

በአዲስ ጠበንጃ በምንሽር፣

አገዳደሉ ሆድ የሚያሽር፡፡

ገዳይ ማክሰኞ ማልዳ

ጣሊያን ተጨንቆ ሲል ወለል ቀዳ፡፡

ገዳይ ረቡዕ፣

ትምባሆ ሲያጡ ጣሊያን ሲራቡ፡፡

ገዳይ ሐሙስ፣

ያንን አህያ ያንን ብስብስ፡፡

ገዳይ ዓርብ ዕለት፣

ጣሊያን ውሃ አጥቶ የተጠማለት፡፡

ገዳይ ቅዳሜ፣

የፈሪው እናት ስትለምን ዕድሜ፡፡

ገዳይ እሑድ፣

         ያንን አህያ ያንን አይሁድ

መትረየስ ጮኸ አልቢን ፈነዳ፣

ገዳይ ሐሙስ ማለዳ

ሮብ አንስቶ ደግሞም ሐሙስ፣

ካሚዎን ሞልቶ ደሙ እስኪፈስ፡፡

ሮብ ተጠምዶ ሐሙስ ተፈታ፣

ገዳይ ሰኞ ቸቸላ፣

አያል ሰላቶ ምሳ ሲበላ፡፡

ገዳይ ማክሰኞ ጉራንባ

አያሌ ጠላት እንዲያ ሲባባ፡፡

ገዳይ ረቡዕ ጎራጎራ፣

እንደሽምብራ ጥይት ሲዘራ፡፡

ገዳይ ሐሙስ፣

የሰሌ ሬሳ ሲልከሰከስ፡፡››

ይህ የጣሊያንን ጭንቅ በሰባቱ ዕለታት አምሳል የሚያሳየው ተራኪ ግጥም፣ አቶ መስፍን ኃይሉ ‹‹አደራ!›› ብለው በ2002 ዓ.ም. ካሳተሙት መጽሐፋቸው ውስጥ የተገኘ ነው፡፡

የሚያዝያው ድልና መታሰቢያው | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

 

‹‹የማትናድ ሕንፃና የማትፈርስ ግንብ››

ኢትዮጵያ በወራሪው የፋሺስት ጣሊያን ሠራዊት ላይ ድል የተቀዳጀችበት 83ኛ ዓመት እሑድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አራት ኪሎ በሚገኘው የሚያዝያ 27 ቀን አደባባይና የድል ሐውልት ሥር እንደሚከበር ይጠበቃል፡፡

ስለ ድል ቀኑ አከባበር -ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ጊዜ ድረስ- ዝርዝር መግለጫ ከሚመለከታቸው አካላት ባይወጣም፣ እንደወትሮው የመንግሥት ከፍተኛ ሹማምንት፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላት፣ የተለያዩ አገሮች ኤምባሲዎች ሚሊቴሪ አታሼዎችና የከተማው ነዋሪ ኅብረተሰቡ በበዓሉ እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡

ከሰማንያ ሦስት ዓመት በፊት የተገኘው የሚያዝያ 27ቱ ድል ለመላው ለአፍሪካ አህጉር ነፃ አወጣጥ መንገድ ጠራጊ መሆኑንም ‹‹ትንሣኤና ሕይወት ሚያዝያ ፳፯ት›› እንዲህ ያመሠጥራል፡፡ ለኢትዮጵያ ድጋፍ በሰጠችው የእንግሊዝ ጦር ሠራዊት ውስጥ ከቅኝ ግዛቶቿ የአፍሪካ አገሮች የተካተቱት አፍሪካውያን ወታደሮች ኅሊና ውስጥ ‹‹እኛም ነፃ መውጣት አለብን!›› የሚለው መነሳሳት የታየው በሚያዝያው የኢትዮጵያ ድልና  ስኬት መሆኑም ያወሳል፡፡

እንደ ታሪካዊው ድርሳን አዘጋገብ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ከ1928 ዓ.ም. ከሚያዝያ 27 ቀን (አዲስ አበባ በፋሺስት ኢጣሊያ የተያዘችበት) እስከ 1933 ሚያዝያ 27 ቀን (አዲስ አበባ በድል የተያዘችበት) ድረስ የጠላት ኰቴ በመስኮቿ ላይ ቢዘዋወርም ገዢነቱን አላወቀችለትም፡፡ ጫካው ሁሉ የጃርት ወስፌ ስለሆነበትና ሜዳውም ቢሆን አቃቅማ ብቻ ሆኖ ስላስቸገረው ምን ያህል ጭንቀት እንዳደረበት አምስት ዓመት ያልሞላው የሥቃዩ ዘመን ምስክር ነው፡፡››

ፋሺስት ኢጣሊያ በመስከረም 1928 ዓ.ም. በወልወል በኩል የጀመረችው ወረራ አጠናክራ ለአምስት ዓመታት አገሪቱ በወረራ ከያዘችበት በኢትዮጵያውያን ተጋድሎና እርመኛ አርበኝነት በድል የተጠናቀቀበት መሆኑ ነበር፡፡

የወቅቱ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (1923-1967)  በስደትና በዲፕሎማሲያዊ ትግል ከቆዩበት የእንግሊዟ ባዝ ከተማ በሱዳን በኩል በምዕራብ ኢትዮጵያ ኦሜድላ ላይ ጥር 12 ቀን 1933 ዓ.ም. የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ያውለበለቡበት፣ ከወራት ቆይታ በኋላም ከአርበኞች ጋር የዘለቁበትና በዕለተ ቀኑ ሚያዝያ 27 አዲስ አበባ የደረሱበት ነበር፡፡

የፋሺስቶች ወረራና ለጊዜውም ቢሆን ኢትዮጵያን መያዛቸው፣ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጀመረው በአውሮፓ ውስጥ ነው ከሚለው አተያይ በተቃራኒው፣ በአፍሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ መስከረም 22 ቀን 1928 ዓ.ም. በተፈጸመው ወረራ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመሩን የሚሞግቱ ምሁራን (ፕሮፌሰሮቹ ንጉሤ አየለ፣ ዓለሜ እሸቴ፣  ሪቻርድ ፓንክረስት) አሉ፡፡ እንዲያውም የአፍሪካ ቀንድ ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም. የዘለቀ የጦርነት ጎራ ሆኖ መዝለቁም ታውቆለታል፡፡

ከድል ሐውልት ማዕቀፍ ውስጥ በተናጠል ኪነ ቅርፆች ላይ ከተጻፉት መታሰቢያዎች መካከል ቀዳሚው፣ ለአገራቸው ነፃነት አምስት ዓመት ሙሉ በዱር በገደል እየተንከራተቱ ደማቸውን ላፈሰሱና አጽማቸውን ለከሰከሱ ለስመ ጥሩ አርበኞች የቆመ የዘላለም መታሰቢያ ነው፡፡

ሌሎቹ አምስት ዓመት ሙሉ በጠላት የጭቆና ቀንበር ውስጥ ተቀምጠው የሞት ጥላ በራሳቸው ላይ እያንዣበበ ሐሳባቸውን ከአርበኞችና ከስደተኞች ሳይለቁ አገራቸውን በስውር ላገለገሉ የውስጥ አርበኞች የቆመ መታሰቢያ፡፡ ያለ አገር ክብርና ነፃነት አለመኖሩን ተረድተውት የጠላት መሣርያ ከመሆን መከራና ስደትን መርጠው አምስት ዓመት ሙሉ ተስፋ ባለመቁረጥ ሲንገላቱና ሲንከራተቱ ለኖሩ ስደተኞች የቆመ መታሰቢያ የሚሉ ናቸው፡፡

አፍሪካዊ አውሮፓዊን ድል ለማድረግ የቻለበት ከዓድዋው ድል ቀጥሎ ሁለተኛው የድል ቀን ሚያዝያ 27 መሆኑ በአፍሪካውያንም ሆነ በሌላው ዓለም እንደሚታወቅ ይወሳል፡፡

ከስድስት አሠርታት በፊት፣ በታተመ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የታሪክ ድርሳን ላይ እንደተመለከተው፣ በነገሥታቱ መሪነት ኢትዮጵያን የድል አክሊል እንደተቀዳጀች እንድትኖር ያደረጓት ሕይወታቸውን ስለሠዉላትና የማትናድ ሕንፃና የማትፈርስ ግንብ አድርገው ስለገነቧት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ምርምር በማድረግ ብዙ ድርሳናት የጻፉት የቴልአቪቭ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የታሪክ ምሁሩ ሀጋይ ኤርሊህ (ፕሮፌሰር) እንደጻፉት፣ የአርበኞች ድል በዘመኑ የነበሩ የዓለም ኃያላን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ተቀብለው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች አባል እንድትሆን አድርጓል፡፡

በጦርነቱ መባቻ በፋሺስት መሪ ሙሶሎኒ ትዕዛዝ ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም. የጣሊያን ጦር በወረራ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን፣ ከአምስት ዓመታት በኋላ በአርበኞች ትግል በተገኘው ድል በዚሁ ቀን ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ተመልሰው አዲስ አበባ በመግባታቸው በዓሉ ለኢትዮጵያ ሁለተኛ የድል በዓል ሆኗል።

የጣሊያን ጦር ዓድዋ ላይ በኢትዮጵያ ጀግኖች ከተሸነፈ ከአርባ ዓመታት በኋላ እንደገና ለበቀል ሲመጣ በተደራጀ የጦር መሣሪያ በአየር ኃይል መርዛማ ኬሚካል በመጠቀም ንፁኃን ዜጎችን ቢፈጅም፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ለወራሪው ኃይል ሳይበገሩ ለአምስት ዓመታት ታግለው ማሸነፋቸው ይወሳል።

እንደ ሀጋይ ኤርሊህ ማብራሪያ፣ በወረራው መጀመሪያ ንጉሠ ነገሥቱ ከጣሊያን ጋር ውጊያ መግጠማቸው፣ ፍልሚያው እየተጠናከረ ሲሄድ ጣሊያን በናፓል የመርዝ ጋዝ ሕዝቡን ፈጅቷል፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ መንግሥታቱ ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) መሄዳቸውን፣ አርበኞቹ ውስጥ ለውስጥ እየተገናኙ በዱር በገደሉ የሽምቅ ጦርነት ከፍተው የትጥቅ ትግላቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን፣ ከአምስት ዓመታት ፍልሚያ በኋላ ለድል መብቃታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...