Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ልበ ድፍን!

ከጣፎ ወደ መገናኛ የሚያመራው ታክሲ ውስጥ ተጭነናል፡፡ በበዓል ዋዜማ ሁሉንም ነገር ለፈጣሪ ሰጥተንና ሕግ ለማክበር እየተጣጣርን፣ ለማይቀረው የኑሮ ትግል ጎዳና ወጥተናል፡፡ ‹‹ኑሮና ታክሲ ሞልቶ አያውቅም፣ ግቡ… ግቡ…›› እያለ ወያላው በዞረ ድምር ውስጥ ሆኖ ያገኘውን ሰው ሁሉ ለማስገባት ይጣራል፡፡ ‹‹አብዛኛው ሰው ኑሮው ጎድሎበት እንጂ ሞልቶለት አያውቅም…›› እያለም ስለሰው ችግር ያወራል፡፡ ወያላው ነገር ዓለሙን ረስቶ ታክሲውን ለመጠቅጠቅ የቆረጠ ይመስላል፡፡ አንዳንዶች ‹ኧረ ሕግ ተላልፈሃል ብሎ የትራፊክ ፖሊስ ይይዝሃል› ሲሉት፣ ‹‹የትራፊክ ፖሊስ አጎቴ ነው፣ እንዲያውም ከታክሲዋ ገቢ የተወሰነ ድርሻ አለው፡፡ ስለዚህ ትርፍ ካልጫንኩ ሊከሰኝ ይችላል…›› ብሎ አረፈው፡፡ አንድ ሙሉ ልብስ የለበሰ ሰው ታክሲዋን አስቁሞ፣ ‹‹ቦታ አለህ?›› ሲለው ወያላው ለሾፌሩ፣ ‹‹እለፍ… እለፍ…›› እያለ ለሰውዬው ደግሞ በመስኮት በኩል፣ ‹‹ቦታ እንኳን አዲስ አበባ ለገጣፎም የለም…›› እያለ አላገጠ፡፡ ታክሲውን መጠቅጠቅ ተከልክሎ በብስጭት ከተማው ውስጥ ቦታ ጠፍቷል፣ ለገጣፎም አይገኝም ሲል ከቀልቡ ያለ አይመስልም፡፡ እንዲያው ለነገሩ በዚህ ዘመን ብዙዎች ከቀልባቸው ጋር መሆናቸው ያጠራጥራል!

ሁለት ሴቶች የቡና ዋጋ ከመጠን በላይ መወደዱ እያንገፈገፋቸው ያወራሉ፡፡ አንደኛዋ፣ ‹‹አሁንማ አረንጓዴ አልማዝ መባል ነው የቀረው…›› አለች፡፡ ቡና በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ዘንድ ያለው ጠቀሜታ ላቅ ያለ ነው የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ምንም እንኳን በመላው ዓለም ቡና ቢጠጣም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለው ፍቅር ልዩ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን አብረው ተሰብስበው ቡና እየጠጡ ችግራቸውን፣ ደስታቸውንና ሐዘናቸውንም የሚወያዩበት ከፍተኛ ማኅበራዊ ጠቀሜታ ያለው ባህላዊ እሴታችን ነው ያሉም አልጠፉም፡፡ እንደ ዘመኑ ፌስቡክና ቲክቶክ የማኅበራዊ ግንኙነት ዋነኛ መገለጫ ነው፡፡ አንደኛዋ ሴት በቡና ላኪ ነጋዴዎች እየተበሳጨች፣ ‹‹ለአገር ውስጥ ገበያ አንድ ፍሬ እንኳን ሳያስቀሩ ሁሉንም ለቃቅመው መላካቸው ምን የሚሉት ራስ ወዳድነት ነው?›› አለች፡፡ ሌላኛዋ ሴት ደግሞ፣ ‹‹ዶላር ነዋ… ዶላርዬ… ለዶላር ሲባል እንኳንስ ከገበያ ከማሳው ላይ ያለውንም በሙሉ ገዝተውታል…›› አለች፡፡ አንደኛዋ፣ ‹‹መንግሥት ቡናን እንደ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃ አለመቁጠሩ የሚያሳዝን ነው፡፡ ለእኛ ከምግብ እኩል የሚያስፈልገን ቡና ነው፡፡ ቡና እየጠጣን ስናወጋ የኑሮን ጫና ያረግብልናል…›› አለች፡፡ የዋጋው ከመጠን በላይ መናር አለመገኘቱ አናዷታል፡፡ በስንቱ ተናዳ ትችለው ይሆን?

አንደኛው ተሳፋሪ በሴቶቹ ወሬ ጣልቃ ገብቶ አስተያየቱን ሰነዘረ፣ ‹‹እንኳንስ አዲስ አበባ ይቅርና የቡናው አገር ጅማ እንኳን አንድ ኪሎ ግራም ቡና በብዙ ብሮች እየተሸጠ ነው…›› አለ፡፡ አንዲት እናት፣ ‹‹ቱ… ቱ… ቱ…፣ አበስኩ ገበርኩ ታዲያ አዲስ አበባ ውስጥ ስንት ሊሆን ነው?›› አሉ፡፡ አንደኛዋ ሴት፣ ‹‹ባይሆን ውጭ አገር ያሉ ዘመዶቻችን ሲመጡ ቡና ይዘው እንዲመጡ እንማፀናቸዋለን እንጂ፣ እዚህማ ዋጋውም አቅርቦቱም የሚቀመስ አይሆንም…›› አለች፡፡ ወያላው፣ ‹‹የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና… ቡና…›› እያለ ማንጎራጎር ጀመረ፡፡ ሾፌሩ የወያላውን መዝሙር ሰምቶ፣ ‹‹አይ ድምፅ፣ ይህንን ሻካራ ድምፅህን ለምን አታስሞርደውም?›› አለው፡፡ ወያላውም፣ ‹‹የት?›› አለው፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹ሰሞኑን ሥጋ ቤቶች ስለሚከፈቱ እዚያ ሂድ…›› ብሎ በፌዝ አሳሳቅ ቀለደበት፡፡ የሾፌሩ ድምፁ ከመጎርነኑ የተነሳ ጆሮ ይጠልዛል፡፡ ጆሮ የማይችለው የለ አትሉም ታዲያ!

ወያላው መልሶ፣ ‹‹መጀመርያ እኮ የቡናን ቅጠል ስትቅም የተገኘችው ፍየል ናት…›› አለ፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹ምን ቡናን ብቻ ጫትንም ሆነ ሻይ ቅጠልን ከፍየል ውጪ ማንም ሊያገኘው አይችልም…›› አለ፡፡ ‹‹አክቲቪስቶቻችንም ቡና ካልጠጡ በሥራ ላይ እኛን ማነቃቃት አይችሉም፡፡ ማነቃቃታቸው በቡና ካልታገዘ እነሱም እንደኛ ነው የሚፈዙት፡፡ ለነገሩ የቡና ዋነኛው ጠቀሜታ ይኼው ነው፡፡ ማነቃቃት፣ ማነቃቃት፣ ማነቃቃት…›› ወያላው የቡናንና የአክቲቪስቶችን ታሪካዊ ግንኙነት ለሾፌሩ ተረከለት፡፡ ቆይተው ግን ወደ ሌላ ርዕስ አመሩ፡፡ ወያላው እያሾፈ፣ ‹‹አንዳንድ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች ቡና በኪሎ መሸጣቸውን ትተው በፍሬ እየቆጠሩ መሸጥ ጀምረዋል…›› አለ፡፡ በመቀጠልም፣ ‹‹ልጆች ሲላኩ፣ ማነሽ እስቲ አሥራ አምስት ፍሬ ቡና ገዝተሽ ነይ…›› ይባላሉ እያሉ ተሰምቶ የማይታወቅ ወሬ ጀመረ፡፡ አንዲት ተሳፋሪ የወያላው ንግግር አልተዋጠላቸውም፡፡ ‹‹እባክህን እስቲ አታሟርትብን፣ ቡናችን መለማመኛችን ነው…›› አሉት፡፡ ወያላው ማንን ይሆን የሚለማመኑበት ብሎ ዙሪያ ገባውን ሲያይ፣ እሳቸውም አፍጠው እያዩት መልስ ቢጠብቁ ዝም አለ፡፡ ‹ዝም አይነቅዝም› ነው መሰል ነገሩ!

ዝምታውን በመስበር፣ ‹‹ኋላ አፍ እከፍታለሁ ብለህ ለአባብዬ ነግሬው ዘጠኝ መርፌ ነው ግንባርህ ላይ የሚተክልልህ…›› አሉ እየተውረገረጉ፡፡ ሌሎች ደግሞ፣ ‹አባብዬዎች አሁንም አሉ እንዴ?› በሚል ስሜት ሲያጉተመትሙ፣ ‹‹ማዘር እንደሚመለከቱት ግንባሬ በጣም ጠባብ ናት፣ እንኳን ለዘጠኝ መርፌ ቀርቶ ለሁለት መርፌም አትበቃም…›› እያለ ማዘርን ወያላው አበሳጫቸው፡፡ ማዘር ቆጣ እያሉ፣ ‹‹ልብ አድርግ ዘጠኝ መርፌ… ዘጠኝ መርፌ… ዘጠኝ መርፌ… ብያለሁ…›› አሉ፡፡ ወያላው እንኳን ሊደነግጥ፣ ‹‹ለመሆኑ አባብዬ ማናቸው? ባህላዊ መርፌ ወጊ ናቸው? ታዲያ ከመቼ ጀምሮ ነው መርፌ ግንባር ላይ የሚወጋው? ትንሽ ብርድ ቢጤ እያስቸገረኝ ስለሆነ ጭኔ ላይ ይሁንልኝ…›› አላቸው፡፡ ወያላው ነገሩ ቢገባውም እያላገጠ ነው፡፡ አንዳንዶች ወያላው ዝም እንዲል ለመኑት፡፡ ወያላው ግን ቢያንስ የመናገር መብቴን ልጠቀም ያለ ይመስላል፡፡ በመጨረሻም፣ ‹‹በዚህ ዕድሜዎ አባብዬ ከሚሉ በቴሌቪዥን በሚተላለፍ የአምልኮ ፕሮግራም ቢፀልዩ አይሻልዎትም?›› አላቸው፡፡ በንዴት ተንተከተኩ፣ ‹‹ታየዋለህ በቅርብ ቀን፣ በቅርብ ቀን ጠብቅ…›› አሉ፡፡ ወያላው፣ ‹‹ምን? የሚመረቅ ፊልም ነው?›› እያለ አፍ አፋቸውን ብሎ ዝም አሰኛቸው፡፡ ጉደኛው ወያላ ጠብቅ እየተባለ ማስፈራሪያ ሲሰጠው፣ አዲስ የሚመረቅ ፊልም ይጠብቃል፡፡ ለነገሩ ነቢያት ነን ብለው ስንቶች በስንቶች ሕይወት እየቀለዱ አይደል!

አንዲት ሴት ታክሲውን ስታስቆም ወያላው፣ ‹‹ላግባት?›› አለ፡፡ ተሳስቶ ሊሆን ይችላል ቢባልም፣ ‹‹ላግባት?›› ማለቱ ላስገባት በማለት ፋንታ ሆን ብሎ እንደሆነ ተገለጠልን፡፡ የወያላው ንግግር የገረማቸው አንድ በዕድሜ ጠና ያሉ ሰው፣ ‹‹ወይ ልጄ ማግባት መቼ እንዲህ ቀላል ሆነ? ትዳር ማለት እኮ…›› ብለው የጀመሩትን ሳይጨርሱ በሐሳብ ጭልጥ ብለው ሄዱ፡፡ ወያላው እዚህ ላይ ሌላ ነገር አመጣ፣ ‹‹ይቅርታ አባት ዘንድሮ ለማግባት የሚያስፈልገው ገንዘብ ሳይሆን ምላስ ብቻ በቂ ነው…›› ሲል ሁላችንም ፀጥ አልን፡፡ ይኼ ወያላ በቃ መልስ አያጣም ማለት ነው? ወያላው ለምንም ነገር ግድ ያለው አይመስልም፡፡ ሾፌሩ በዕድሜ ላቅ ያለ ቢሆንም፣ እሱም ግዴለሽ ነገር ነው፡፡ ሴትየዋ በወያላው አነጋገር ስለተበሳጩ አሁንም አሁንም፣ ‹‹የለህማ…›› እያሉ ብቻቸውን ያወራሉ፡፡ ከፊታቸው የተቀመጠች ወጣት፣ ‹‹ማዘር ማንን ነው የለህማ የሚሉት?›› ስትላቸው፣ ‹‹ምን አገባሽ?›› ብለው መለሱላት፡፡ ወያላው በሁለቱ ንግግር ለመዝናናት እየፈለገ፣ ‹‹ፋሲካን ተደብራችሁ ማሳለፍ ፈልጋችኋል መሰል…›› እያለ ሲናገር፣ ‹‹እንኳን እኔ አንተም አልተባልክ ጫታም…›› ስትለው ወጣቷ ሴትየዋ ደግሞ፣ ‹‹ዕድሜ ለጀበናዬ ቅብርር ብዬ ነው የማሳልፈው፣ አንተ አለህ እንጂ ገጣባ ፊትህን አመድ ያስመሰልከው…›› ሲሉት የታፈኑ ሳቆች ተሰሙ፡፡ በዚህ ጊዜማ እንዴት ተደርጎ ይሳቃል!

ይኼን ጊዜ ሾፌሩ ወያላውን መተንኮስ ጀመረ፡፡ ‹‹አየህ ይህንን ታንክ የሄደበት የመሰለ ፊትህን ይዘህ አፍ መካፈት የሚያመጣውን? በመጀመሪያ ደረጃ እሳቸው እንዳሉህ የፊትህን ገጣባ ቀንስ፡፡ ሁለተኛ ከጫት ቀጥሎ በአደገኛ ሁኔታ የተፀናወተህን ነገር ፍለጋ አስተካክል፡፡ ሦስተኛ ብዙ ከማውራት ብዙ ለማዳመጥ ረስህን አዘጋጅ…›› በማለት ጨዋ ቢጤ ምክር ቢጤ ጣል አደረገለት፡፡ ወያላው የሚበገር አልሆነም፡፡ ‹‹ፈሪ ስለሆንክ እኔን ለመተቸትም ሆነ ለመምከር የሞራል ብቃት የለህም፡፡ ዝም ብለህ በአዘዝኩህ አቅጣጫ ንዳ…›› በማለት ምላሽ ሰጠ፡፡ የታከተው ሾፌር የታክሲውን ሬዲዮ ሲከፍት በታክሲ እጥረት ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡ አንደኛው አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹የትራንስፖርት ሥምሪት ሲስተም አስፈላጊ ቢሆንም በርካታ ታክሲዎች ሊጨመሩ ይገባል፡፡ ዝም ብሎ ታሪፍ መጨመር ፌር አይደለም…›› እያለ ይናገራል፡፡ ወያላው እያሽሟጠጠ፣ ‹‹እንኳን አዳዲስ ታክሲዎች ሊጨመሩ አሁን ያሉትም በየት በኩል በወጣን እያሉ ነው፡፡ የግብር፣ የመለዋወጫ፣ የነዳጅ፣ የቅባት፣ የጋራዥ ወጪ እንዲህ በናረበት ጊዜ ተጨማሪ ታክሲ ከየት ሊገኝ ነው?›› አለ፡፡ ሁሉም ብሶቱን ካወራ እኮ ለመስማትም ይከብዳል!

የታሪፍ ጭማሪ ያሳሰባቸው የሚመስሉ አዛውንት፣ ‹‹አሁን ልክ ተናገርክ ልጄ! ገበያው እንደ እሳት እየተጋረፈ ነው፡፡ የምግብና የሌሎች ቁሳቁሶች ዋጋ በአልጠግብ ባይ ነጋዴዎች ምክንያት አልቀመስ ብሏል፡፡ ሁሉም ነገር ከመደበኛ ዋጋው የትርፍ ትርፍ እየተገኘበት ይሸጣል፡፡ የዋጋ ቅናሽ ተደረገባቸው የተባሉ ምርቶችን ማግኘት አልተቻለም፡፡ በጡረታ ገቢ ኑሮ ከብዶ አልተቻለም፡፡ መንግሥት የውጭ ጅምላና ችርቻሮ ነጋዴዎችን ለማስገባት መወሰኑ ትክክለኛ ዕርምጃ ነው፡፡ የእኛዎቹ አልጠግብ ባዮች ከገበያ ውስጥ ተጠራረርገው ካልወጡ ሰላም አይኖርም…›› እያሉ እርር ትክን አሉ፡፡ ‹‹ፋዘር  ልክ ነዎት የውጭ ነጋዴዎች ገብተው የምግቡን ብቻ ሳይሆን፣ የበርጫ ዋጋም ቢያረጋጉልን አሪፍ ነበር…›› ሲላቸው፣ ‹‹በል ዝም በል ሰማሁህ፣ ካልጠፋ ነገር እሱም ተወደደ ብለህ ታማርራለህ?›› አሉት፡፡ ‹‹አይ ፋዘር አንዳንዴ እኮ እሱን ቅመን ነው ያለ እራት የምናድረው…›› ሲላቸው፣ ‹‹እውነትህን ነው፣ ስትመረቅን የጠገብክ ስለሚመስልህ ለአንተ ሁሉም ነገር ቀላል ነው…›› ብለውት፣ ‹‹ልጄ…›› ሲሉት፣ ‹‹አቤት አባቴ?›› አላቸው፡፡ ‹‹ግን ምርቃና ከዚህ ሌላ እንዴት ያደርጋል?›› ሲሉት፣ ‹‹አንዳንዴ አገር የሚያስተዳድሩ እስኪመስልዎት ድረስ ልብ ይደፍናል…›› እያላቸው ወያላው ‹‹መጨረሻ!›› ሲለን ሰውዬው እያማተቡ ሲለዩን፣ እኛም እየሳቅን ተለያየን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት