Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሳንፎርድ ትምህርት ቤት የጠየቀው ከፍተኛ የክፍያ ጭማሪ ቅሬታና ተቃውሞ አስነሳ

ሳንፎርድ ትምህርት ቤት የጠየቀው ከፍተኛ የክፍያ ጭማሪ ቅሬታና ተቃውሞ አስነሳ

ቀን:

  • በተመሳሳይ ጾታ አስተምህሮት ላይ ለቀረበው ቅሬታ ትምህርት ቤቱ ይቅርታ ጠይቋል
  • የትምህርት ሚኒስቴርና የብሔራዊ ባንክ መመሪያዎች ተጥሰው ክፍያ በዶላር መጠየቁ ተገልጿል
  • በትምህርት ሚኒስቴር ተፅዕኖ ከሕግ አግባብ ውጭ ቦርድ መመረጡም ተጠቁሟል
  • ለትምህርት ቤት ግንባታ ከውል ውጭ 28 ሚሊዮን ብር ተከፍሏል ተብሏል

በታምሩ ጽጌ

የሳንፎርድ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ቦርድ እ.ኤ.አ. ለ2025 የትምህርት ዘመን በነባር፣ በመካከለኛና በአዲስ ገቢ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ላይ ከ25 እስከ 60 በመቶ የክፍያ ጭማሪ እንደሚያደርግ አሳውቆ፣ ወላጆች ክፍያውን እንዲፈጽሙ አስገዳጅ ሁኔታዎችን ማቅረቡን የተቃወሙ ወላጆች፣ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ቅሬታዎቻቸውንና አቤቱታቸውን እያቀረቡ ነው፡፡

ሳንፎርድ ትምህርት ቤት የጠየቀው ከፍተኛ የክፍያ ጭማሪ ቅሬታና ተቃውሞ አስነሳ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ትምህርት ቤቱ የአገሪቱን ሕግ፣ ባህልና ሃይማኖታዊ አስተምህሮት የሚቃረን የተመሳሳይ ጾታ አስተምህሮት የያዙ መጽሐፍት ማቅረቡና ለማስተማር ያደረገው ሙከራም ወላጆች ወዲያውኑ ተቃውሞአቸውን በማሰማታቸው፣ ትምህርት ቤቱ ወላጆችን ይቅርታ ጠይቋል፡፡

በሳንፎርድ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ወላጆች፣ ትምህርት ቤቱ ለትርፍ ያልተቋቋመ የዘለቄታ በጎ አድራጎት ማኅበር ከመሆኑ አንፃር፣ እንዲሁም በብርና በዶላር ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ክምችት እያለው፣ ሕግንና መመርያዎችን በጣሰ ሁኔታ ከ25 እስከ 60 በመቶ ጭማሪ ክፍያ መጠየቁ አግባብ አለመሆኑን ለትምህርት ሚኒስቴር፣ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣንና ሌሎች ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም የትምህርት ቤቱ ተቀማጭ ገንዘብ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ በሚዘዋወርበት ወቅት ሌሎችን ባንኮች ባላሳተፈ ሁኔታ ከአንድ ባንክ ጋር ብቻ ስምምነት በመፈጸም ወደ ግል ባንክ እንዲዘዋወር መደረጉንም ተቃውመዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ ‹‹የትምህርት ቤት ክፍያን ማስማማት ‹‹(Harmonization)›› በሚል፣ ለኢትዮጵያውያን ወላጆች በተጻፈላቸው ደብዳቤ ከ25 እስከ 60 በመቶ የክፍያ ጭማሪን በሚመለከት፣ እ.ኤ.አ. እስከ ሜይ 13 ቀን 2024 ድረስ መስማማት አለመስማማታቸውን እንዲያሳውቁት፣ ያ ካልሆነ ግን ከትምህርት ቤቱ ጋር ያላቸው ግንኙነት ተቋርጦ፣ ሌሎች ተማሪዎችን እንደሚቀበል እንዳሳወቃቸው፣ ወላጆች ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ያቀረቡት ሰነድ ያሳያል፡፡ ትምህርት ቤቱ፣ ትምህርት ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ሊተገብሩት ይገባል በማለት ያወጣውን መመሪያ ማለትም ‹‹ኢትዮጵያውያን ወላጆች ክፍያ የሚፈጽሙት “በብር ነው”›› የሚለውን ጥሶ፣ ክፍያውን የሚቀበለው በዶላር መሆኑን ማሳወቁንም በአቤቱታቸው አሳውቀዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችንና የውጭ አገር ዜግነት ያላቸውን ተማሪዎች ተቀብሎ የሚያስተምር ሲሆን፣ ክፍያውንም በሚመለከት ለኢትዮጵያውያን ቀድመው ትምህርት የጀመሩ (C2)፣ መሀል ላይ የጀመሩ (C1) እና በቅርብ የጀመሩ  (C4) በሚል በሦስት የአከፋፈል ደረጃ የሚያስከፍል ሲሆን፣ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸውን ተማሪዎች (C3) በሚል የአከፋፈል ሥልት እንደሚያስከፍል ከሰነዶች መረዳት ይቻላል፡፡

ወላጆች ለትምህርት ሚኒስቴር ባቀረቡት አቤቱታና ለትምህርት ቤቱ ባቀረቡት የሕግ ማስጠንቀቂያ እንደገለጹት፣ እጅግ የተጋነነውን የጭማሪ ክፍያ ውሳኔ ያስተላለፈው የሳንፎርድ ትምህርት ቤት በጎ አድራጎት ማኅበር ቦርድ ቢሆንም፣ በሕገወጥ ሁኔታ የተመረጠ በመሆኑ የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች በሕግም ሆነ በወላጆች ተቀባይነት የለውም፡፡ ቦርዱ ከመመረጡ ከኅዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም. በፊት የነበረው ቦርድ ኦዲት ተደርጎና የትምህርት ቤቱ አጠቃላይ ሁኔታ ሳይታወቅ፣ ‹‹የትምህርት ሚኒስትሩ አዘዋል›› በሚል ማስፈራሪያ፣ በሕጉ መሠረት 51 በመቶ የሚሆኑት የአገር ውስጥ ወላጆች መሳተፋቸው ወይም ኮረም መሟላቱ ሳይረጋገጥ፣ እንዲሁም በትምህርት ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ቅድሚያ ዕጩዎችን የመለየት ሥራ ‹‹ከምርጫ ቀን በፊት ይከናወን›› የሚለው መመርያ ተጥሶ፣ በዕለቱ የተገኙ ወላጆች ሳይዘጋጁ እዚያው ጥቆማ ተደርጎ ምርጫ መካሄዱ ሕገወጥ መሆኑን ወላጆች አስገንዝበዋል፡፡ ይህንንም ወላጆች ቀድመው ‹‹ሕግ ይከበር›› ብለው በጽሑፍ ያስገቡትን አቤቱታ ትምህርት ሚኒስቴርና የሲቪል ማኅበረሰብ ባለሥልጣን ምርጫውን ማካሄዳቸው የተወሰኑ ሰዎች ላይ ተጠያቂነት እንዳይመጣ የተደረገ አካሄድ መሆኑን ወላጆች ተናግረዋል፡፡  

ቦርዱ ትምህርት ቤቱ ለምን ጭማሪ ማድረግ እንዳስፈለገው በተሻሻለው የትምህርት ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ጥልቅ ጥናት ሳያካሂድ በተመረጠ በአንድ ወር ውስጥ ውሳኔ መወሰኑ፣ እንዲሁም ትምህርት ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች ፈቃድ አሰጣጥና ዕድሳት መመሪያ አንቀጽ 21(3) ድንጋጌ መሠረት 51 በመቶ ከሚሆኑ ወላጆች ጋር ስምምነት ላይ ሳይደረስ፣ ቦርዱ ያሳለፈው ውሳኔ ሕግን የጣሰና ተገቢነት የሌለው መሆኑን ወላጆች ደጋግመው አንስተዋል፡፡

ወላጆች የቦርዱን ውሳኔ ከመቀበል ውጭ ሌላ አመራጭ እንደሌላቸው ትምህርት ቤቱ በኢሜል ማሳወቁን የገለጹት ወላጆች፣ የሚያሳዝነው ነገር የቦርዱ አመራር የሆኑ የሕግ ምሁራን ኢትዮጵያውያን ወላጆች፣ የትምህርት ቤቱ ድርጊት ‹‹ሁሉም ነገር ከሕግ በታች ነው›› የሚለውን መርሕ የሚጣረስ መሆኑን እያወቁ፣ እነሱም ተባብረው የሕግ ጥሰቱን ማጀባቸው ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ እንደማይችል ሊያውቁት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር ታዋቂ ሰዎች በሚል የመንግሥትን ድርሻ ይዘው በቦርዱ ውስጥ እንዲካተቱ ያደረጋቸው ግለሰቦች፣ የራሳቸው ትምህርት ቤት ያላቸውና ከሳንፎርድ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ጋር ቀጥተኛ የሆነ የጥቅም ግጭት የሚፈጥር መሆኑን የጠቆሙት ወላጆች፣ በትምህርት ቤቱ ውስጥ የተጀመረው ሕግን ያልተከተለ አካሄድ፣ ሆን ተብሎ በትምህርት ቤቱ ላይ ግጭት (ረብሻ) በማስነሳት፣ ትምህርት ቤቱን ማስተዳደር እንዳልተቻለ በማስመሰል፣ ትምህርት ቤቱን በአክሲዮን እንዲተዳደር ድርሻ እንዲሸጥና ባለድርሻ ለመሆን (ለመግዛት) በማሰብ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት እንደይዙ እንዳደረጋቸው ያስረዳሉ፡፡

ሳንፎርድ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤትን በቦርድ የሚመራ ተመራጭ፣ ከሁለት ጊዜ በላይ መመረጥ የሌለበት ቢሆንም ከ14 ዓመታት በላይ የግል ርስት አድርገውት የቆዩ የቦርድ አባላት እንደነበሩ የጠቆሙት ወላጆች፣ ትምህርት ቤቱ በተለያዩ ጉዳዮች እንዲጠመድና ሰላም እንዳያገኝ እያደረጉ ያሉት እነሱ ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡ ይኸንንም የሚያደርጉት ሕንፃ ለማስገንባት ከተቋራጭ ጋር ውል ከታሰረ በኋላ፣ ተቋራጩ ካሸነፈበት ዋጋ ውጭ ያለምንም ምክንያት 28,077,624 ብር መከፈሉን የትምህርት ቤቱ ኦዲት ስለሚያሳይ ቢቆይም አንድ ቀን የሕግ ተጠያቂነት ይመጣል የሚል ሥጋት ስለገባቸውና ሰላም ስለነሳቸው ሊሆን እንደሚችል መገመታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ የሳንፎርድ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት በጎ አድራጎት ማኅበር ቦርድ ከወላጆች አቅም በላይ ስለመሆኑ፣ ውይይት ሳይደረግበት፣ ከትምህርት ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ ውጭና፣ ከትምህርት ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ፈቃድ አሰጣጥና ዕድሳት መመሪያ አንቀጽ 21 (3) ድንጋጌ ውጭና ከአገሪቱ ሕግ ውጭ በሆነ ሁኔታ በማን አለብኝነት የተጨመረው ከፍተኛ የክፍያ መጠን፣ በሌሎች ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች መሠረት እንዲደረግ፣ የክፍያው መጠን የብሔራዊ ባንክ በሚደነግገው መሠረት  እንዲወሰንና ትምህርት ሚኒስቴርም ግንቦት 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሁሉም ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ያስተላለፈው ክፍያን የተመለከተ ሰርኩላር እንዲከበር እንዲያደርግ ለትምህርት ሚኒስቴር አቤቱታውን አቅርበዋል፡፡

የቦርዱ ውሳኔ የሕፃናት ደኅንነትን (The Best Interest of the Child) ቀዳሚ ማድረግ የሚገባውንና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 36(2) ሥር የተደነገገውን በግልጽ የሚጥስና ሕፃናት ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው በግድ የሚለይ መሆኑን ልብ ሊል እንደሚገባም ወላጆች አሳስበዋል፡፡

በሳንፎርድ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ልጆቻቸው የሚማሩ ኢትዮጵያውያን ወላጆች ያነሱትንና የተጋነነ ነው ያሉት የክፍያ ጭማሪን በሚመለከት ባነሱት ተቃውሞ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ፣ ሪፖርተር በኢሜል አድራሻቸው ጥያቄ ያቀረበላቸው የሳንፎርድ ትምህርት ቤት ኃላፊ ሚስተር አንቶኒ ሀሚልተን ምላሻቸውን በኢሜል ሰጥተዋል፡፡

ሚስተር ሀሚልተን በምላሻቸው እንደገለጹት፣ ሳንፎርድ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ቀደም ብሎ የነበሩበትን አድሎአዊ አሠራሮች፣ ሙስና፣ የትምህር ጥትራትና ሌሎች ተግዳሮቶችን ለማስወገድና የአሠራር ለውጥ ለማምጣት እየሠራ ይገኛል፡፡ አዲስ የተመረጠው ቦርድና ማኔጅመንትም በትምህርት ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ከትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎች ተቋማት ጋር ተቀራርቦ በመሥራትና ስትራቴጂካዊ የሆነ ውሳኔ በመስጠት ላይ ነው፡፡ ነፃ የትምህርት ዕድል የሚያገኙ ተማሪዎችን ቁጥር ለመጨመርም በመተዳደሪያ ደንቡ (Bylaw) አንቀጽ 5(3) ድንጋጌ መሠረት፣ ከመጪው ክረምት (August) ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ትምህርት ቤት ባለበት እንዲቀጥል ከማድረግ ይልቅ ማሻሻልና አስፈላጊ ነገሮችን እያሟሉ መቀጠል ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው አካሄድ መሆኑን ጠቁመው፣ የትምህርት ቤቱ ቦርድና ማኔጅመንት አስፈላጊውን ውሳኔ በመስጠት፣ ሳንፎርድ አጉል ባህሪ ያላቸውን፣ የማይወክሉትን፣ አሳሳች መረጃ የሚሰጡትንና ከለውጥ ጎዳና ሊያስወጡት በሚንቀሳቀሱት ላይ ዕርምጃ እየወሰደ መሥራቱን እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡

ሌላው ወላጆች ትኩረት የሰጡትና ቁጣን የቀሰቀሰው ጉዳይ ሳንፎርድ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት የአገሪቱን ሕግ የጣሰ፣ ባህልና ሃይማኖዊ አስተምህሮትን የሚቃረን የተመሳሳይ ጾታ አስተምህሮት በትምህርት ቤቱ አዲስ ካሪኩለም ውስጥ ለጀማሪ ሕፃናት እንዲካተት ማድረጉና ድርጊቱን የሚደግፉ መጽሐፍት በትምህርት ቤቱ መጽሐፍት ቤት መገኘታቸው ነው፡፡

የሳንፎርድ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ወላጆች ሳያውቁና በሚስጥር ትምህርት ቤቱ የተመሳሳይ ጾታ ማስተማሪያ መጽሐፍ አዘጋጅቶ ማስተማር መጀመሩን በማወቃቸው፣ ትምህርት ቤቱ ድረስ በመሄድ ባቀረቡት ተቃውሞና ቁጣ፣ የትምህርት ቤቱ ኃላፊ ይቅርታ በመጠየቅ የማስተማር ሒደቱ እንደሚቋረጥ ማሳወቃቸውን ተናግረዋል፡፡

የሳንፎርድ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ኃላፊ ሚስተር አንቶኒ ሀሚልተን ለወላጆች በጻፉት የይቅርታ ደብዳቤ፣ ምንጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያን ሕግ  ማክበር ግዴታ መሆኑንና ወላጆችም የተቃወሙት የተመሳሳይ ጾታ አስተምህሮ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ተቀባይነት እንደሌለው፣ ሁሉም የትምህርት ቤቱ አስተማሪዎችና ረዳቶቻቸው፣ የኢትዮጵያን የባህልና የሃይማኖት እሴቶችንና የሕግ የበላይነትን ማክበር እንዳለባቸው፣ እንዲሁም በትምህርት ቤቱ ውስጥ ምንም ዓይነት ነገር ቢፈጠር ለወላጆች ማሳወቅ እንዳለባቸው እንደሚያስገነዝቡ በመግለጽ፣ ይቅርታ መጠየቃቸውን ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ የተመሳሳይ ጾታ አስተምህሮ መጽሐፍት እንዴት ወደ ትምህርት ቤቱ ሊገባ እንደቻለ አጣርተው ለወላጆች እንደሚያሳውቁና ወላጆች ትምህርት ቤቱን ለመርዳት ያደረጉን ጥረት እንደሚያደንቁ በመግለጽ የማስተማር ጅማሮው መቆሙን አስረድተዋል፡፡

ሪፖርተርም ስለተመሳሳይ ጾታ አስተምህሮትና መጽሐፍት ወላጆች ያነሱትን ጥያቄ በሚመለከት ለትምህርት ቤቱ ኃላፊ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የትምህርት ቤቱ ኃላፊ ሚስተር ሀሚልተን፣ የተመሳሳይ ጾታ አስተምህሮትን በሚመለከት በርካታ ስም የማጥፋት ሒደቶች ወይም ውንጀላዎች መከናወናቸውን አስታውሰው፣ ትምህርት ቤቱ ባደረገው ማጣራት ምንም ዓይነት ማረጋገጫ እንዳላገኘ ተናግረዋል፡፡ አንድም የትምህርት ቤቱ መምህራን የአገሪቱን ሕግ የሚጥስ ተግባር እንዳልፈጸሙ ማረጋገጣቸውንም ለላወጆች እንዳሳወቁ ገልጸዋል፡፡

በሳንፎርድ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት በሚማሩ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ላይ ተፈጻሚ የሚሆን ከፍተኛ የክፍያ ጭማሪ እንዲደረግ፣ የትምህርት ቤቱ ቦርድ ስላሳለፈው ውሳኔ፣ ትምህርት ቤቱ ለምን ኦዲት እንዳልተደረገና ከውል ውጭ ተከፍሏል ለተባለው ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ፣ ቦርዱ በትምህርት ሚኒስቴር ትዕዛዝ ከሕግ ውጭ በጥቂት ወላጆች ተሳትፎ ስለመመረጡ፣ የጥቅም ግጭት መኖሩ እየታወቀ የቦርድ አባል እንዲሆኑ ስለተመረጡ ትምህርት ቤት ስላላቸው ታዋቂ ስለተባሉት ግለሰቦች፣ በትምህርት ሚኒስትሩ ትዕዛዝ በግዳጅ ነፃ የትምህርት ዕድል እንዲጥ ለትምህርት ቤቱ ስለተላለፈው ትዕዛዝና ከአገሪቱ ሕግ፣ ባህልና ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ያፈነገጠ የተመሳሳይ ጾታ አስተምህሮ ጅማሮ ማብራሪያ እንዲሰጠው ሪፖርተር ለሳንፎርድ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ቦርድ፣ ለትምህርት ሚኒስቴር፣ ለበጎ አድራጎትና ማኅበራት ድርጅት ባለሥልጣን ቢያቀርብም ምላሽ ለማግኘት አልተቻለም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...