Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኢትዮጵያ ብዙ ፈተና እየገጠማት ቢሆንም ከፈተናው ውስጥ ቀስ እያልን እንወጣለን ብዬ አስባለሁ›› ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር

ከጥቂት መታት በፊት በኢትዮጵያ የመንግት ለውጥ መካሄዱን ተከትሎ  በቀደሙት ጊዜያት ከተቋማዊ ስሙ ባለ በሚያከናውናቸው ተግባራት፣ ተቋሙን ይመሩት በነበሩ ኮሚሽሮች እንዲሁም በአጠቃላይ ተቋማዊ ባህው ከአስፈጻሚው የመንግት አካል ጋር በነበየተጋመደ ትስስር ሳቢያ በከፍተኛ ደረጃ የገለልተነትና የቅቡልነት ጥያቄ ይነሳበት የነበረበውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እንዲመሩ የተሾሙት ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (/)፣ ኮሚሽ በከፍተኛ ደረጃ እንዲለወጥና ገለልተኝነቱ እንዲረጋገጥ፣ ሥልጣንና ኃላፊነቱ እንዲሰፋ ለተጫወቱት ቁልፍ ሚና የጀርመን አፍሪካ ፋውንዴሽን (ዲኤኤስ) ... በ2021 ሽልማት ማበርከቱ ይታወሳል፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ ይህንን ኃላፊነት ከያዙ አምስት ዓመታት ሞልተው የመጀመያው የልጣን ዘመናቸው ሊጠናቀቅ ወራት ቀርተዋል፡፡ ሲሳይ ሳህሉ ከዋና ኮሚሽነር ዳንኤል ጋር በተቋሙና በአጠቃላይ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝና ምልከታ ላይ ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ዋና ኮሚሽነር ሆነው ከተሾሙ ወዲህ እንደገና የተሻሻለው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ላይ ምን ዓይነት ለውጥ አመጣ? አሁን አገሪቱ ላለችበት ሁኔታስ ምን አስተዋጽኦ አደረገ?

ዶ/ር ዳንኤል፡- በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ የተደረገው የሕግ ማሻሻያ ለኮሚሽኑ አጠቃላይ አሠራርና ነፃነት በጣም አስፈላጊ የነበረ ነው፡፡ ይህም ማሻሻያ የተቋምና የአሠራር ነፃነት ለማረጋገጥ የሚያስፈልግ ነበር፡፡ በተለይም የተቋሙን ተጠሪነት ከሥራ አስፈጻሚው ወስዶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰጠ ነው፡፡ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች የሚመረጡበትን ሒደትና አሠራር ግልጽና አሳታፊ የሚያደርግ፣ እንዲሁም ኮሚሽነሮች የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን እንደሌለባቸው የሚደነግግ ነበር። ይህ የተቋሙን ነፃነት ከማረጋገጥ አንፃር አስፈላጊ ማሻሻያ ነበር፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የተቋሙን የአሠራር ነፃነት ማረጋገጥ ሲባል፣ በተለይ ከሰው ሀብትና ከበጀት አስተዳደር ጋር የተገናኙ ነፃነቶችን የሚያረጋግጥ ነበር፡፡ ኮሚሽኑ ከሕጋዊ ምንጮች ሀብት ለማሰባሰብም ሆነ ከመንግሥት የተቀበለውን በጀት ተገቢ ነው ብሎ ባሰበው መንገድ ሥራ ላይ እንዲያውል ነፃነት የሚሰጥ ማሻሻያም ነበር፡፡ ኮሚሽኑ በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፅዕኖ ሥር እንዳይወድቅ ኮሚሽነሮች የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይሆኑም የሚለው ድንጋጌ አስፈላጊ ነበር፡፡ የኮሚሽኑን አሠራር ለማሳለጥ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ የሚገኙ ቦታዎች በሙሉ ያለ ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሥልጣን ያለው መሆኑን፣ እንዲሁም ኮሚሽኑ በመደበኛው ሁኔታ ብቻ ሳይሆን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥም ቢሆንም እንኳ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታን የመከታተል ሥልጣን ያለው መሆኑን፣ የኮሚሽኑን ሥልጣን ተግባርና ኃላፊነት የሚዘረዝሩ በርካታ ድንጋጌዎች ነበሩ በማሻሻያው ውስጥ የተካተቱት፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ማሻሻያዎች ሲታዩ የአሠራርና የተቋም ነፃነትን የሚያረጋግጡ ስለሆነ በጣም አስፈላጊ ማሻሻያ ተድርጎ ይወሰዳል፡፡

ሪፖርተር፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንድ አዋጅ ካፀደቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ እንደገና እንዲሻሻል የሚጠይቁ ተቋማት እንዳሉ ይነገራል፡፡ በማሻሻያ ሒደት ይጨመር ወይም ይቀንስ በማለት እናንተ እንዲስተካከል የጠየቃችሁት ድንጋጌ ነበር?

ዶ/ር ዳንኤል፡- በአብዛኛው የኮሚሽኑን ተቋማዊና የአሠራር ነፃነት ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ማሻሻያዎች ተደርገዋል ብለን እናስባለን፡፡ ምናልባት ወደፊት ማሻሻያ ቢደረግ አንድ ማሻሻያ ያስፈልገው ይሆናል ተብሎ የሚታሰበው ጉዳይ የኮሚሽኑን ምክረ ሐሳቦች ተፈጻሚነት የሚመለከተው ነው፡፡ ምክንያቱም ኮሚሽኑ በሚያከናውነው ሥራ የሚደርስባቸው ግንኙነቶችና ምክረ ሐሳቦች ተፈጻሚነታቸው ካልተረጋገጠ የሚፈለገውን  ውጤት ማምጣት አይቻልም፡፡ ምናልባት ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታና ከልምዳችን ተነስተን ተፈጻሚነቱን ለማረጋገጥ ምን ዓይነት ማሻሻያዎች ያስፈልጉ ይሆናል ብሎ በማሰብ፣ ይህ እንደ አንድ የማሻሻያ ሐሳብ ተደርጎ ሊወሰድ ይችል ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- የኮሚሽኑን የምርመራ ውጤቶችና ምክረ ሐሳቦች ተቀብሎ ከማስፈጸም አኳያ፣ ከመንግሥት አካላት በተለይ ከአስፈጻሚውና ሕግ አውጪ አካል በኩል የቀረቡ ምክረ ሐሳቦችን የመቀበልና የመፈጸም ችግር እንዳለ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ኮሚሽኑ ይህንን እንዴት ይመለከተዋል?

ዶ/ር ዳንኤል፡- የምክረ ሐሳቦቻችን ተፈጻሚነት ላይ ያለው መልክ ቅይጥ ነው፡፡  በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ምክረ ሐሳቦቻችን በሰጠነው አስተያየት መሠረት ተፈጻሚ ሲሆኑ የተመለከትንባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ይህንን በተለያዩ ዘርፎች ልትመለከተው ትችላለህ፡፡ አንዱ የሰብዓዊ መብቶችን ሁኔታ ክትትል ስናደርግ በተለይ ሰዎች ታስረው በሚገኙባቸው ማረሚያ ቤቶች የሰብዓዊ መብቶችን ደረጃ መሠረት አድርገን የምናደርገው ክትትል አለ፡፡ ለምሳሌ በማረሚያ ቤት ያሉ ሰዎች መብት አጠባበቅና አያያዝን ስለማሻሻል፣ ወይም በአንድ ተቋም ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የመብት ጥበቃ ስለማሻሻል፣ በማሳደጊያ ውስጥ ያሉ ሕፃናትን በሚመለከት፣ አረጋውያንን በሚመለከት፣ በመጠለያ ጣቢያዎችና በመሳሰሉ አካባቢዎች የምናደርጋቸው የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ሥራዎች አሉን፡፡ በእነዚህ የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ሥራዎች በምንደርስበት ግኝትና በምንሰጠው ምክሐረ ሐሳብ መሠረት በተለየ ጉዳይ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቀጥታ ስለምንሠራ፣ ያንን ምክረ ሐሳብ የሰጠናቸው ተቋማት በብዛት ተግባራዊ ሲያደርጉ ተመልክተናል፡፡ ይህንንም ሄደን ተከታትለን ዓይተናል፣ አረጋግጠናል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ሥራ የሚዲያ ትኩረት ስለማይስብ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ላይታወቅ ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ ሚዲያ ጥፋቶችና አደጋዎች ላይ ስለሚያተኩር ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ከክትትል ሪፖርት አንፃር ተግባራዊ የተደረጉ ምክረ ሐሳቦች በርካታ ናቸው፡፡ ሁለተኛው ብዙ ጊዜ በሕግና በፖሊሲ ማውጣት ሒደት ውስጥ የምንሰጠው ምክረ ሐሳብ፣ በተለይም አንድ ፖሊሲ በሚዘጋጅበት ጊዜ በሰብዓዊ መብቶች ይዘት ወይም በሰብዓዊ መብቶች ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ዓይነት ሲሆን ጉዳዩ ከሚመለከተው ተቋም፣ እንዲሁም ከፍትሕ ሚኒስቴርና ከፓርላማ ጋር በቅርበት ክትትል እናደርጋለን፡፡ በዚህም ሕጉ ወይም ፖሊሲው እንዴት መሻሻል እንዳለበት የራሳችን ምክረ ሐሳብ እንሰጣለን፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ሁልጊዜም ባይሆን በበርካታ አጋጣሚዎች በሰጠነው ምክረ ሐሳብ መሠረት ረቂቅ ሕጉ ወይም ፖሊሲው ላይ መሻሻል እናያለን፡፡ ስለዚህ ይህ ምክረ ሐሳባችን ተግባራዊ የሚደረግበት ሌላው ጉዳይ ነው፡፡

ሦስተኛው በመንግሥት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ወይም አሠራር እንዲሻሻል የግድ ሪፖርት በማውጣት ብቻ ሳይሆን ውትወታ በማድረግና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ወይም ኃላፊዎች ጋር በአካል በመነጋገር  የምንሠራቸው ሥራዎች አሉ፡፡ በዚህም ረገድ የምንሰጣቸው ምክረ ሐሳቦችና አስተያየቶች ብዙ ተግባራዊ ሲደረጉ ዓይተናል፡፡ የሰጠነው ምክረ ሐሳብ ግምት ውስጥ ሲገባና ተግባራዊ ሲደረግ ተመልክተናል፡፡ አራተኛው ተፈጽሟል ከተባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ የምናደርገው የምርመራ ውጤትና የምንሰጣቸውን ምክረ ሐሳቦችን ይመለከታል፡፡ ብዙ ጊዜ ከግለሰቦች የሚመጡ አቤቱታዎች አሉ፡፡ እነዚህን አቤቱታዎች መርምረን የምንሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያለአግባብ ታስረናል ወይም ደግሞ በእስር ወቅት ተፈጽሞብናል የሚሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲኖር፣ በሁሉም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቻችን ብዙ ጊዜ አቤቱታዎች ይቀርቡልናል፡፡ በዚህ ረገድም የምንሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች ብዙ ጊዜ ተግባራዊ ሲደረጉ እንመለከታለን፡፡ ምናልባት ትንሽ በሚፈለገው መጠን ተግባራዊ አልተደረገም የምንለው በጣም ሰፋ ያለ የመብት ጥሰት የተፈጸመባቸው፣ በተለይ በግጭት ዓውድ ውስጥ የተፈጸመ ወይም የመንግሥት የፀጥታ አካላት ተሳትፈውበታል የተባለ ከሕይወት መጥፋትና ከአካል መጉደል ጋር የተያያዙ ሁኔታዎችን በተመለከተ የተደረጉ ምርመራዎችና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን በተመለከተ፣ የተወሰኑት ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ቢሆንም ተግባራዊነታቸው የሚቀር ምክረ ሐሳቦች አሉ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘም ቢሆን የተወሰኑ የተፈጸሙ ምሳሌዎች አሉ፡፡

ለአብነት ያህል በጋምቤላ ክልል ያደረግነው ምርመራ በተለይ በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ተፈጽሟል በተባለ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ በሰጠነው ምክረ ሐሳብ መሠረት ዕርምጃ ተወስዶ፣ እንዲያም የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነርንና ምክትል ኮሚሽነርን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት ባወጣነው ሪፖርት መሠረት ክስ ቀርቦባቸው ጉዳዩ በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ነው ያለው፡፡ በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል የከረዩ አባገዳ አባላትን በሚመለከት በሰጠነው ምክረ ሐሳብ መሠረት በጉዳዩ የሚጠረጠሩ ሰዎች ላይ ምርመራ የሚጀመር መሆኑን፣ በተወሰኑት ላይ ምርመራ መጀመሩን ተረድተናል፡፡ ነገር ግን በምንፈልገው መጠን እየሄደ አይደለም፡፡ በሶማሌ ከልል እንዲሁ ባደረግናቸው ምርመራዎች የተጎዱ ሰዎች እንዲካሱ ባቀረብነው ምክረ ሐሳብ መሠረት ካሳ ተፈጽሟል፡፡ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ የተደረጉበት ሁኔታ አ፡፡ በተተመሳይ የምክረ ሐሳባችን ተፈጻሚነት በምሳሌነት ለመጥቀስ የምወደው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ጽንሰ ሐሳብን ሲሆን፣ ይህንን ጽንሰ ሐሳብ ያመነጩት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥት ደርጅት ጋር በመሆን ነው፡፡ ለመንግሥት ምክረ ሐሳብ አቅርበን መንግሥትም ተቀብሎ በምክረ ሐሳቡ መሠረት ተግባራዊ የማድረግ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ቆይተው አሁን በመጨረሻ ፖሊሲው ፀድቋል፡፡ ቀጣዩ ሥራ ተግባራዊነቱን መከታተል ይሆናል ማለት ነው፡፡ የሰጠናቸው ምክረ ሐሳቦች መፈጸማቸውን የሚያመላክቱ ብዙ ምሳሌዎች አሉ፡፡  ነገር ግን ሁሉም ምክረ ሐሳቦች ተቀባይነት አግኝተው ተግባራዊ ሆነዋል ማለት አይደለም፡፡  

ሪፖርተር፡- በዋና ኮሚሽነርነት ከተሾሙ ወዲህ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?

ዶ/ር ዳንኤል፡- የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተለይ ከግጭት ዓውድ ጋር ተያይዞ በሰዎች ላይ የሚደርስ የሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የመፈናቀልና የንብረት መውደም የመሳሰሉት ጉዳዮች እየተከሰቱ ነው፡፡ ይህም ባለፉት ዓመታት ውስጥ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ አሳሳቢ ሆኖ እየቀጠለ ነው፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ከተነሳው ግጭት አንስቶ በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው የትጥቅ ግጭት፣ እንዲሁም በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ያሉት ሁኔታዎች አሳሳቢ ናቸው፡፡ በእውነት ኢትዮጵያ ውስጥ በግጭት ያልተጠቃ አካባቢ አለ ማለት አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም አካባቢዎች  በግጭት ዓውድ ውስጥ መጠነ ሰፊ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው የሚታየው፡፡ በአጠቃላይ ይህም አሳሳቢ የሆነ ጉዳይ ነው፣ ከፍተኛ ሥቃይ ነው ያለው፡፡ ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሁሉ የበለጠ ከፍተኛ የሚያደርገው በሕይወት ላይ የሚደርስ ጉዳት በመሆኑ ነው፡፡ ከሞትና ከአካል ጉዳቶች በተጨማሪ መፈናቀሉ በከፍተኛ ቁጥር ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ፆታዊ ጥቃትን ይጨምራል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት አሳሳቢና መጠነ ሰፊ የሆነ የሰብዓዊ መብት ሥጋትና አደጋ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደቀጠለ ነው ያለው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከሰብዓዊ መርሆችና ደረጃዎች አንፃር ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን ለመለማመድና ሐሳብን በነፃነት ለማራመድ፣ የሚዲያ ነፃነትን ለማረጋገጥ ብዙ መሰናክሎች ቢኖሩም አዎንታዊ ዕርምጃዎች አሉ፡፡ በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ዘርፍ ጉዳዮች ላይ በሴቶች መብት፣ በሴቶች ተሳትፎ፣ የአካል ጉዳቶችን መብትና አካታችነት በማረጋገጥ አበረታች ዕርምጃዎች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በዚህ መልኩ እንዲቋቋምና ሥራውን እንዲያከናውን ምቹ ሁኔታ ተጀምሯል፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለአንድ አገር የሰብዓዊ መብቶች መስፋፋትና ጥበቃ ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ነገር ግን መልሶ ሊያጠለሸው የሚችለው ከባዱ ፈተና በግጭት ዓውድ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉና በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ ወንጀሎች መበርከት፣ መታገት፣ መታፈንና ሕይወት መጥፋት የመሳሰሉት በጣም አሳሳቢ የሰብዓዊ መብት ቀውስ ሆነው ቀጥለዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኮሚሽኑ በሚያከናውናቸው የምርመራ ሪፖርቶች መሠረት በሚሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች፣ እንዲሁም በሚወጡ ሕጎችና ፖሊሲዎች ላይ መስተካከል አለባቸው በማለት የሚያቀርባቸው ጉዳዮች ተፈጻሚ የማይሆኑ ከሆነ የሚሄድበት ርቀት ምን ድረስ ነው?

ዶ/ር ዳንኤል፡- ሁሉም ምክረ ሐሳብ አይፈጸምም ማለት አይቻልም፣ የሚፈጸሙ አሉ፣ የማይፈጸሙም አሉ፡፡ ነገር ግን ይህንን ነገር የምንመለከተው እንደ ሒደት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ የበላይነት፣ የዴሞክራሲ አሠራር፣ የሰብዓዊ መብቶች መከበርና የሰብዓዊ መብቶች ባህል ማደግ በሒደት የሚመጣ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ የሚፈለገው ግብ ማለትም የሕግ የበላይነት የተከበረበት፣ ሰብዓዊ መብቶች የተከበሩበትና ሰላም የሰፈነበት ማኅበረሰብ እንዲኖረን በምናደርገው ሒደት ላይ የኮሚሸኑ ሥራ ጥሩ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ፈተናው በዝቷል፣ ፈተና አለ፣ ብዙ እንቅፋቶች አሉ፡፡ ቢሆንም ኢትዮጵያ ወደፊት ለመሄድ በተለያዩ ተቋማት አማካይነት ጥረት እያደረገች ነው፡፡  እኛ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የምንሠራ ሰዎች ለዚህ እጥረት ዕገዛ እያደረግን ነው፡፡ ያ ሒደት ደግሞ ጉዞው ሙሉ በሙሉ የተሟላ ነው ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ነገር ግን ቢያንስ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ ጥረት የበለጠ እየሠራን ከሄድን ያው ቤት ተሠርቶ ለማለቅ ጊዜ እንደሚወስደው፣ ማለትም መሠረት ከተጣለ በኋላ ብሎኬት እየተደረደረ ሸክላ እየተጣለ ነው የሚሄደውና ያንን ለማስቀጠል የበለጠ ብሎኬትና ሸክላ እየደረደሩ የመገንባት ሥራ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ወደፊት አንዳንድ ጊዜ ወደ ኋላ እያለ ሊያስቸግር እንደሚችል ግምት ውስጥ እያስገባን፣ ነገር ግን ተስፋ ባለመቁረጥና ትልቁን ጉዞና ትልቁን ሥዕል በመመልከት መሥራት አለብን ብለን ነው የምናስበው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የዴሞክራሲ ተቋማት ለአንድ አገር መሠረት ስለሆኑ የመንግሥትንም ሆነ የሌሎች ተቋማትን ድክመትና ስህተት በሚመለከት መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ላይ ሐሳቦች ይሰጣሉ፡፡ በዚህ መሠረት አስፈጻሚው አካል የሚሰጡትን አስተያየቶች ከመቀበል ይልቅ በእነዚህ ተቋማት ጫና እንደሚያሳድር ይነገራል፡፡ በአስፈጻሚው አካል የደረሰባችሁ ጫና አለ? ሊገለጽ የሚችል አጋጣሚም ካለ ቢነግሩን?

ዶ/ር ዳንኤል፡- የመንግሥት አስፈጻሚ አካል በሥራችን ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ በመግባት ወይም ጫና በማሳደር የደረሰብን ተፅዕኖ የለም፡፡ መንግሥትም በሥራችን ውስጥ ጣልቃ ገብነት ለማድረግ ቢሞክርም አንደኛ እኛም አንቀበልም፣ በሌላ በኩል ግን የመንግሥት የፖለቲካ ፈቃደኝነትና ቁርጠኝነት ከታየባቸው ሁኔታዎች አንዱ  ይህንን ዓይነት ኮሚሽን እንዲቋቋም ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ ለሥራው የሚያስፈልጉትን ኮሚሽነሮች፣ ባለሙያዎችና ሠራተኞች እንዲሰባሰቡ፣ እንዲደራጁና ይህንን ዓይነት ሥራ እንዲያካሂዱ ዕገዛና ድጋፍ አድርጓል፡፡ በሥራችን ውስጥ ጣልቃ አለመግባቱን አሳይቷል፡፡ ጣልቃ አልገባም፣ ግን ደግሞ ልግባ ቢልም እኛም አንቀበልም፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የለም፡፡ ይህ ሲባል ለሥራችን ሁሉ ከመንግሥት የሚፈለገውን ትብብር ሁልጊዜ እናገኛለን ማለት አይደለም፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ከተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንቅፋት ያጋጥመናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ መድረስ የምንፈልግበት ቦታ ላይ እንዳንደርስ መሰናክል ሊያጋጥመን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሚያስፈልገንን መረጃ አለማግኘትና ለሥራችን የሚያስፈልገንን በጀት ስለማናገኝ ገንዘብ ያጥረናል፡፡ በእርግጥ የበጀት ጉዳይ የእኛ ተቋም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተቋማትን የሚመለከት ነው። ምክንያቱም የመንግሥት ሀብትና አቅም ውስን በመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ይህም አንድ እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በክልል ደረጃና አልፎ አልፎ በፌዴራል ደረጃ የኮሚሽናችን የምርመራ ግኝቶችና ምክረ ሐሳቦች ላይ የሚሰጡት ምላሽ ተገቢ አለመሆንም ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት መሰናክሎች አልፎ አልፎ ያጋጥሙናል። እኛም በመሰናክሎቹ ተስፋ ሳንቆርጥ ዓላማችንን ይዘን መሥራታችንን ቀጥለናል፡፡ ተስፋ የሚሰጠንና የሚያበረታታን ግን ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤት በዚህ መልኩ ምላሽ ይሰጣል ማለት አይደለም፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ በርካታ ኃላፊዎችም ቢሮዎችም ለሥራችን ተገቢውን ድጋፍና ትብብር የሚያደርጉ ስላሉ፣ አልፎ አልፎ ትብብር የማያደርጉ ቢያጋጥሙንም እንደሚለወጥ በማመን ሥራችንን እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡ ሲለወጥ ደግሞ ተመልክተነዋል፡፡ ለምሳሌ በአንዳንድ ክልሎች ላይ ባወጣነው ሪፖርት የክልሉ መንግሥት የመጀመሪያ ምላሽ ነገሩን የመካድ፣ የመቃወምና እኛንም የማውገዝ ዓይነት ይሆንና ውሎ አድሮ ግን ሁኔታውን ተረድተው ያንን ምላሻቸውን ይቀይራሉ፡፡ እንዲያውም ምክረ ሐሳባችንን ተቀብለውና እኛንም ተቀብለው አነጋግረው ተግባራዊ አድርገው የሚያሳዩን አሉ፡፡ ስለዚህ መሰል እንቅፋቶች ቢያጋጥመንም እንዲቀየሩ እያደረግን ለመሥራት የሚያስችለን ሁኔታ በመኖሩ በዚህ መንፈስ እንሠራለን፡፡  

ሪፖርተር፡- ሕዝብ በሚከፍለው ግብር የሚተዳደሩ የመንግሥት ወይም የሕዝብ የሚባሉ ሚዲያዎች ኮሚሽኑ የሚያወጣቸውን የምርመራ ውጤቶችና ምክረ ሐሳቦች ከግል ሚዲያዎች አንፃር ሲታዩ እየመረጡ ነው የሚዘግቡት የሚል አስተያየት በተለያየ መንገድ ሲነሳ ይደመጣል፡፡ ኮሚሽኑ ይህን እንዴት ይረዳዋል?

ዶ/ር ዳንኤል፡- እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚታወቀው በግልና በመንግሥት ቁጥጥር የሚተዳደሩ ሚዲያዎች አሉ፡፡ በመንግሥት ቁጥጥር የሚተዳደሩ ሚዲያዎች በመሠረቱ በኢትዮጵያ ታሪክ በአብዛኛው በመንግሥት ሥርና ቁጥጥር ይተዳደራሉ እንጂ፣ የሚታሰበውና ሊሆን የሚገባው የመንግሥት ሚዲያ ሳይሆን የሕዝብ ሚዲያ ነው መሆን የነበረባቸው፡፡ ‹‹Public Media Broadcaster›› በሚለው ጽንሰ ሐሳብ መሠረት ሊሆኑ የሚገባቸው እንዲያ ነበር፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በታሪካችን ያው እነዚህ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉትና የሚተዳደሩት ሚዲያዎች በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥትና አስተዳደር የመደገፍ ወይም የማገዝ ፀባይ አላቸው፡፡ በኢትዮጵያ የሕዝብ ሚዲያ የመፍጠር ሒደት ውስጥ ገና ብዙ ዕርምጃና ብዙ መንገድ እንደሚቀረን የሚያመለክት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሚያከናውናቸው ሥራዎች፣ የሚደርስባቸው ግኝቶችና የሚያቀርባቸውን ምክረ ሐሳቦች በብዛት ሲሸፈን ነው የምንመለከተው በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ከሚተዳደሩት ሚዲያዎች በተሻለ በግሎቹ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለው ሚዲያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ሥራ ምንም ሽፋን አይሰጥም ለማለት ሳይሆን፣ በአብዛኛው ግን እየተሸፈነ ያለው በግል ሚዲያ ተቋማት ነው፡፡ ይህ ቀስ በቀስ እየተሻሻለ ይመጣል ብለን እናስባለን፡፡ ምክንያቱም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉት ሚዲያዎች ዓላማቸው የሕዝብ ሚዲያ መሆን ስለሆነ፣ ነፃና ገለልተኛ ተቋማት ለሚያከናውኑት ሥራ ተገቢውን ሽፋን የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡ በእርግጥ ሚዲያ የራሱ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ አለው፡፡ የራሱ መርህና የአሠራር ነፃነት ስላለው በራሳቸው ኤዲቶሪያል መርህና አሠራር መሠረት መብትና ነፃነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በተለይ ግን በሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ የበለጠ ሚና ሲኖራቸው ለማየት እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም የሕግ የበላይነት ጉዳይ የሰብዓዊ መብቶች ትልቅ አጀንዳና ለሕዝብ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ለሕዝብ አሳሳቢ የሆነ ጉዳይ በሚገባው መጠን ለዓላማውም ጭምር ትኩረት በመስጠት፣ በተለይ ደግሞ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በአደባባይ ማጋለጥ፣ እንዲታወቁና እንዲነገሩ፣ የተጎዱ ሰዎች እንዲካሱና እንዲጠገኑ፣ ያጠፉ ሰዎች ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ድጋሚ እንዳይከሰቱ፣ ሊደረጉ የሚገባቸው የፖሊሲ፣ የሕግና የአሠራር፣ የተቋም ለውጥ በሚመለከት የውይይት መድረኮች በማመቻቸትና በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በዚህ ረገድ የበለጠ ሥራ የሚጠበቅባችው ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ የሚከናወኑኮሚሽኑም ሆነ ሌሎች የውጭና የአገር ውስጥ የመብት ተቋማት የሪፖርት ጥራት እንዴት ይመለከቱታል? አንዳንድ ተቋማት በስልክ ብቻ ሪፖርት አጠናቅረው ይፋ ያደርጋሉ ይባላሉና ይህ ትክክለኛውንና የሚጠበቀውን ውጤትን ሊያመጣ ይችላል?

ዶ/ር ዳንኤል፡- እንግዲህ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ ምርመራ ለማድረግና ለማጣራት፣ ለክትትልና ለመሳሰሉት ሥራዎች የሚመረጠው ቦታው ላይ በአካል በመገኘት ሲሠራ ነው፡፡ መርሁም እንደዚያ ነው፡፡ በአካል መገኘት ይጠይቃል፡፡ የዓይን ምስክሮችን፣ እማኞችን፣ የሕክምና ባለሙያዎችን፣ የመንግሥት አካላትን፣ የሃይማኖትና የኅብረተሰብ ተወካዮችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችንና የመሳሰሉትን ሁሉ ቃለ መጠይቅ ማድረግ፣ መረጃ መሰብሰብ፣ በአካል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል፣ የተባሉትን ቦታዎች ተገኝቶ ምልከታ ማድረግ፣ የሰነድ ማስረጃዎችን ማሰባሰብ፣ አንዳንድ ጊዜ እንደ አስፈላጊነቱ ሳይንሳዊ የማረጋገጫ ቴክኒኮችን በመጠቀም በአካል በመገኘት መሠራት አለበት፡፡ ትክክለኛው አሠራር ይህ ስለሆነ እኛም አሠራራችን በዚያ መንገድ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ምርመራና ክትትል ጨምሮ፣ ሁሉም ቦታ በአንድ ጊዜ በአካል መድረስ ያዳግታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የፀጥታ ሁኔታው ላይፈቅድ ይችላል፡፡ መንግሥታትም የሰብዓዊ መብት ምርመራና ክትትል የሚያደርጉ አካላት በቦታው ተገኝተው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ላይፈቅዱ ይችላል፡፡ ይህ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ምርመራ የሚከናወንበት ሥልት አለ። ከርቀት ሆኖ ምርመራ ከሚካሄድባቸው ሥልቶች አንፃር በስልክ ወይም በሌላ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ሰዎችን በማነጋገር፣ ወይም ማነጋገር የምትፈልጋቸውን ሰዎች በማግኘት ወደ የምትፈለግበት ቦታ እንዲመጡ ማድረግንና ማነጋገርን ይጨምራል፡፡ ስለዚህ የተለያዩ ዓይነት ቴክኒኮችን በመጠቀም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ ማድረግ ይቻላል፡፡ የሚመረጠው በአካል ተገኝቶ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ግን በሁለተኛው አማራጭ ከርቀት ምርመራ ማድረግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን በጣም ጥንቃቄ የተሞላበት ነው፡፡ የማስረጃ አሰባሰብና የማስረጃ ምዘና፣ እንዲሁም የትንተና ሥልቶችን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኩል ምርመራ ለማድረግ የምንጠቀምበት የማስረጃና የመረጃ ማሰባሰብ፣ እንዲሁም መተንተንና መመዘኛ ሥልቶች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሚጠቀምባቸው ሥልቶች ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለዚህም ነው ከእኛ ኮሚሽን ጋር በጣምራ ለመሥራት ፈቃደኛ የሆነው፡፡ ምክንያቱም እኛ የምንጠቀመው እነሱ ከሚጠቀሙት ሥልት ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ማለት ነው፡፡ የተመድ ሥልት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ የእኛን ባለሙያዎች በዚህ ሥልት መሠረት አሠልጥነን ሥራችን በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንሠራለን፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባለው የምርመራ ሥልት ላይ ተመሥርተን ነው የምንሠራው፡፡ ለዚህም ነው ሥራችን በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኘው፡፡ ኮሚሽናችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት አግኝቶ የአንደኛ ደረጃ ዕውቅና ተሰጥቶት፣ በተመድ የሰብዓዊ መብቶች መድረክ ላይ የመሳተፍ መብቱ የተረጋገጠው በዚህ የተነሳ ነው፡፡ ሥራችንን ተመልክተው ነው፡፡ ምክንያቱም በተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ተቋም ጋር ምንም ልዩነት የሌለው የምርመራ ሥራ ነው የምናከናውነው፡፡ ይህንን አሠራራችንን መጥተው ዓይተው ይህን ሥራ ለማከናወን ብቃት ያለው ተቋም መሆኑን ስላረጋገጡ፣ ተመድ ከዚህ በፊት አድርጎት በማያውቀው መንገድ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር መሥራት እፈልጋለሁ አለ፡፡ የጣምራ ምርመራ አከናውነን የመጨረሻው ሪፖርትም እስከ ተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ደረጃ ቀርቦ፣ ምክር ቤቱም ደረጃውን የጠበቁ ሪፖርትና ለሌሎች አገሮችም ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው ብሎ አመሥግኖ የተቀበለው በዚህ የተነሳ ነው፡፡ እኛ ይህንን ዓይነት ሥራ መሥራት የሚችል ተቋም ገንብተናል ማለት ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በበጀት እጥረት ወይም በፀጥታ ሥጋትና ሌሎች ምክንያቶች መድረስ ያልቻላችሁባቸው ቦታዎች አሉ?

ዶ/ር ዳንኤል፡- አዎ፣ በርካታ ናቸው፡፡ የሰው ኃይል አቅማችንም የፋይናንስ አቅማችንም በጣም ውስን ነው፡፡ በዚህ የተነሳ አገራችን በቆዳ ስፋትም ሆነ በሰው ብዛት ትልቅ ናት፡፡ የእኛ ተቋም ደግሞ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ከሌሎች ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ጋር ብታነፃፅረው ለምሳሌ ጋናን ብትወስድ በሕዝብ ብዛት ከኢትዮጵያ አንድ ሦስተኛ አካባቢ ብትሆን ነው፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማቸው ያለውን የሰው ኃይል ብዛትና የሀብት መጠን ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተቋም ጋር ሲወዳደር ከእኛ በሦስት እጥፍ ይልቃል፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማችን አቅሙ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ እናም የዚህ ዓይነት የሰብዓዊ መብቶች ተቋም በዓለም ላይ በሁሉም አገሮች ሊባል በሚችል ደረጃ አለ፡፡ እነዚህ ተቋማት በብዛት ትልልቅ ናቸው፡፡ ብዛት ያለው የሰው ዓይል አላቸው፣ በቂ ሀብትም በመንግሥት እየተመደበላቸው ይሠራሉ፡፡ የእኛ ተቋም የሰው ኃይሉም ሆነ የሚመደብለት በጀት በጣም አነስተኛ በመሆኑ የምንሠራው በውስን አቅም ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የምንፈልጋቸው ቦታዎች በሙሉ ለመድረስ አንችልም፡፡ በተለይ ደግሞ የሰብዓዊ መብቶች ትምህርትና ግንዛቤ ለማስፋፋትና መሰል ተግባራትን ለማከናወን፣ ለሌሎች ለምንፈልጋቸው ሥራዎች ባለብን ውስንነት የተነሳ መሥራት አንችልም፡፡

ሪፖርተር፡-  ለኮሚሽኑ ፓርላማው ከሚያፀድቅለት በጀት በጨማሪ ሌላ የገንዘብ ምንጭ አለው?

ዶ/ር ዳንኤል፡- አለን፣ በእርግጥ በመንግሥት የሚመደብልን በጀት ብቻውን ሥራችንን ለመሥራት ላያስችለን ይችል ነበር፡፡ ሥራችንን የሚደግፉ ዓለም አቀፍ አጋሮች ለሥራችን ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ በኮሚሽናችን ማቋቋሚያ አዋጅ ኮሚሽኑ እነዚህን ከመሰሉ ሕጋዊ ምንጮች ለሥራው የሚያስፈልገውን ሀብት የማሰባሰብ ሥልጣን ያለው መሆኑ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ሥራችንን የሚያምኑበት ዓላማችንንም የሚደግፉ ዓለም አቀፍ አጋሮች ለሥራችን የተወሰነ የፋይናንስ ድጋፍ ያደርጉልናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለፖለቲካና ለሲቪል መብቶች የምታደርጉትን ክትትል ያህል ለማኅበራዊና ለኢኮኖሚያዊ መብቶች የምትሰጡት ትኩረት እኩል ነው ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ዳንኤል፡- በእርግጥ በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በጣም ብዙ ጊዜ ትኩረት የሚሰጠው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች አከባበር ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ለማኅበራዊና ለኢኮኖሚያዊ መብቶችም እኩል ትኩረት እንሰጣለን፡፡ ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነው አንዱ ኮሚሽኑ ውስጥ ከዚህ ቀደም ያልነበረ ራሱን የቻለ የማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ መብቶች ክፍል እንዲቋም አድርገናል፡፡ ይህም ደግሞ ራሱን በቻለ የማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ መብቶች ዘርፍ ኮሚሽነር የሚመራ ነው፡፡ በኮሚሽኑ ውስጥ ከዚህ በፊት ያልነበሩ የሥራ ክፍሎች እንዲቋቋሙ ማድረጋችን ይጠቀሳል፡፡ ለምሳሌ የአካል ጉዳትን በሚመለከት የአካል ጉዳተኛና የአረጋውያን መብትን በሚመለከት ራሱን የቻለ የሥራ ክፍል ተቋቁሟል፡፡ ስደተኞችን፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችንና ፍልሰተኞችን በሚመለከትም ራሱን የቻለ የሥራ ክፍፍል እንዲቋቋም አድርገናል፡፡ እነዚህ ሁሉ የሥራ ዘርፎች በየራሳቸው የዘርፍ ኮሚሽነር የሚመሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ቢያንስ በእኛ ተቋም ደረጃ ለዚህ ጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ምናልባት የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ እንጂ፣ ያነሰ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ አይደለም ብለን ስለምናምን ሰፊ ትኩረት የምንሰጠው የሥራ ዘርፍ ነው፡፡ በዚህ ረገድም ብዙ ሥራዎች መሥራት ጀምረናል፡፡ በዚህ መሠረትም እንቀጥላለን፡፡ ነገር ግን  የማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ብዙ ትኩረት የማያገኙት ለአፈጻጸማቸው የአገርን ሀብትና አቅም የሚጠይቁ በመሆናቸው፣ በሰብዓዊ መብቶች ጽንሰ ሐሳቡም የአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደ መጠን ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ መብቶች ናቸው ስለተባለ፣ ብዙ ጊዜ የአቅም መጠን እነዚህን መብቶች ተግባራዊ ማድረግ ላይ እንቅፋት ይሆናል፡፡ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶችን በተመለከተ የአንዳንዱ መብት ጥበቃና ተግባራዊ አፈጻጸም ላይ ከሀብት ጋር አይያያዝም፡፡ ለምሳሌ የአንድ ሰው በማረሚያ ቤት ወይም ተይዞ በሚገኝበት ቦታ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እንዳይደረግበት፣ ወይም የማሰቃየት ተግባር እንዳይፈጸምበት የመጠበቅ መብቱ ከሀብት ጋር አይያያዝም፡፡ አንድን ሰው ላለማሰቃየት ሀብት አይጠይቅም፣ የሚያስፈልገው እንዳይሰቃይ ለማድረግ መጠበቅ ነው የሚጠይቀው፡፡ ስለዚህ አንዳንዶቹ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ለአፈጻጸማቸውና ለተግባራዊነታቸው የመንግሥትን የኢኮኖሚ አቅም የማይጠይቁ ስለሆነ፣ ያለምንም ቅድም ሁኔታ ተግባራዊ ሊሆኑ ወይም ሊደረጉ ይገባል፡፡ መከበራቸው ሊረጋገጥ ይገባል ተብለው የሚታሰቡ ሰዎችን የሰብዓዊ መብቶች ድርጀቶች የቅድሚያ ትኩረት አድርገው ሲሠሩባቸው ትመለከታለህ፡፡ በአጠቃላይ እንግዲህ በእኛ ኮሚሽን በኩል ይህኛውም ዘርፍ ከሌላው ጋር እኩል ትኩረት የምንሰጠው የሥራ አካል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካ አስተሳሰብና በአጠቃላይ በማኅበረሰቡ ዕሳቤ ለሰብዓዊ መብቶች መጠበቅ ያለውን ዕይታ እንዴት ይገልጹታል?

ዶ/ር ዳንኤል፡- ቅይጥ መልክ ያለው ይመስላል፡፡ ሰብዓዊ መብቶች ባህል የሆኑበት አገር እንዲፈጠር የሚል ራዕይ ይዘን ነው እንደ ኮሚሽን እየሠራን ያለው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የገባንበት የፖለቲካ ውጥንቅጥ ስትመለከተው ቢያንስ የተወሰኑ ኢትዮጵያውያን እህቶችና ወንድሞች የሐሳብና የአስተሳሰብ ልዩነት የሰዎች መብት መሆኑን መቀበል ያቅታቸዋል፡፡ የሐሳብ ልዩነትን አክብሮና ተቻችሎ መኖርን ገና በትክክል ለመረዳትና ለመቀበል የፖለቲካ ፈቃደኝነት፣ የሥነ ልቦና ዝግጁነት፣ የአስተሳሰብ ዝግጁነት ያለመኖር ያለ ይመስላል፡፡ እናም በዚህ የተነሳ ይመስለኛል የአስተሳሰብና የፖለቲካ ልዩነቶቻችን የበዙት፡፡ ለዚህም ይመስለኛል የማያባራ ግጭት ውስጥ ስንገባ የሚታየው፡፡  በአሁኑ ወቅት የማያባራ ይመስላል፡፡ ግን ማባራት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህም ከፖለቲካና ከሰብዓዊ መብቶች ባህል ማዳበር ጋር አብሮ የሚመጣ ነው፡፡ ነገር ግን እንዳለመታደል ሆኖ እስካሁን የመጣንበት የፖለቲካ ባህላችንና ልምዳችን የሰብዓዊ መብቶችን ለማክበር ገና ብዙ ዕርምጃ እንደሚቀረን ያሳያል፡፡ ከመሠረታዊ ባህሎች አንዱ የሐሳብ ልዩነትን መቀበል ነው፡፡ ነገር ግን ምናልባትም ከሌላ ወገን የሚመጣን ሐሳብ የማትቀበለው፣ የምትፀየፈውና የሚያስቆጣህ አስተሳሰብ እንኳ ቢሆን ያንን የሐሳብ ልዩነት መቀበል ከሁሉም ወገኖች የሚጠበቅ ነው፡፡ መንግሥት ኃይሉን ተጠቅሞ የሐሳብ ልዩነት ያላቸውን ሰዎች አለማጥቃት፣ ተቃዋሚ ቡድኖችም ቢሆኑ ከእነሱ የተለየ ቡድን ብለው የሚያስቡትን መንግሥትም ሆነ ሌሎች አካላትን በሐሳብ ልዩነት የተነሳ ማጥቃታቸው መቆም አለበት፡፡ እነዚህ ነገሮችን አክብሮ መኖር የሰብዓዊ መብቶች ባህል ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ዕርምጃ ይቀረናል፡፡ በሌላ በኩል መረሳት የሌለበት ግን እንዲህ ዓይነት ያለመቻቻል ባህል ሲገለጥ የሚስተዋለው በሚያሳዝን ሁኔታ በአብዛኛው ሰላማዊ በሆኑና ያልተማሩ በሚባሉ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ሳይሆን፣ በተማረው የኢትዮጵያ ማኅብረሰብ ውስጥ ነው፡፡ በተማረው የኅብረተሰብ ክፍል በጣም መሪር የሆነ ፅንፍ የያዘ፣ ጫፍና ጫፍ የረገጠ አቋምና ወደ ጥላቻ የሚያዘነብል ስሜት ታያለህ፣ ይህ ያስደነግጣል፡፡ ምክንያቱም በመደበኛው ምናልባት ያልተማረ ተብሎ በሚወሰደው የማኅበረሰብ ክፍል ዘንድ አብሮ መኖርና መቻቻል እያለ፣ ተማረ ሠለጠነ እየተባለ በሚጠራው የማኅበረሰብ ክፍል ያንን ያህል የመካረርና የጥላቻ ስሜት ሲታይ በጣም ያስደነግጣል፡፡ ለምንድነው መቻቻል መፍጠር ያልቻልነው ሲባል የሰብዓዊ መብት ባህል አለመኖር፣ የፖለቲካ ባህል ያለማደግ፣ የዴሞክራሲ ልምምዳችን ገና በሚፈለገው ልክ ባለመሆኑ ነው፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ ሒደት ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡     

ሪፖርተር፡- ባለፉት ዓመታት በተለይ የመንግሥት ለውጥ ከተደረገ ወዲህ ማሻሻያ የተደረገባቸውን የዴሞክራሲ ተቋማትና ሌሎች ገለልተኛ ሚባሉ ተቋማትዝብ ዘንድ ጥሩ ስምና ዝና ላቸው ግለቦች ለጥቂት መታትም ቢሆን ሲመሩ ታይቷል፡፡ ነገር እዚህን ተቋማት ይመሩ የነበሩ ግለሰቦች ከነበሩበት ልጣን በአንድም በሌላ ምክንያት ለቀዋል፡፡ ከእነዚህ ተቋማት አንዱና በሚያከናውናቸው ተግባራትም በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን እየመሩ ይገኛሉ፡፡ አልፎ አልፎ የለውጡ ማሳያ የነበሩ ግለሶቦች ሲለቁ ዶ/ር ዳኤል ግን ቀረ የሚ አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡ በዚህ ረድ የተሰማዎ ጋት ነበር?

ዶ/ር ዳንኤል፡- ሥጋትና ፍርኃት አድሮብኝ አያውቅም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደምታስታውሰው አዲስ የተፈጠረ የፖለቲካ ምዕራፍ ነበር፡፡ በዚያ የፖለቲካ ምዕራፍ ውስጥ ማሻሻያ እንዲደረግባቸውና ለውጥ እንዲኖራቸው ከታሰቡት ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ነበር፡፡ እኔም በመንግሥትና በሕዝብ ጥያቄ ወደ እዚህ ኃላፊነት መጣሁ፡፡ የኢትዮጵያ ችግር ውስብስብ ስለሆነ ይህ ሥራ ቀላል ሊሆን እንደማይችል፣ ኢትዮጵያ ውስጥም የተጀመረው አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ሙከራ ቀላል እንደማይሆን ከመጀመሪያውም እገነዘብ ነበር፡፡ በእርግጥ በጠቅላላ የተጀመረው አዲስ የፖለቲካ ሥራ በወቅቱ ብዙ የሕዝብ መነሳሳትና ፍላጎትን ያሳየ የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ግን በጣም ውስብስብና ሥር የሰደደ በመሆኑ ጉዞው ቀላል ሊሆን እንደማይችል እረዳ ነበር፡፡ ነገር ግን እኔም በዚህ ሥራና ሒደት ውስጥ አስተዋጽኦ እንዳደርግ ዕድል ሳገኝና በመንግሥትም በሕዝብም ጥያቄ ሲቀርብልኝ፣ በከበሬታም በኃላፊነትም ስሜት ነው የተቀበልኩት፡፡ ሥራው ቀላል እንደማይሆን ከመጀመሪያው ግምት ነበረኝ፡፡ በዚያ መንፈስ ነው አሁንም እየሠራሁ ያለሁት፡፡ ባለፉት ዓመታት ሁሉም እንደሚመለከተውና እንደሚረዳው ጉዞው ቀላል አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ በጣም ከፍተኛ በሆነ ነውጥ ውስጥ ነው ያለፈችው፡፡ ከፍተኛ ዋጋ ነው የተከፈለው ግን በዚህ ሒደት ውስጥ አንድ ተዓማኒ የሆነ የሰብዓዊ መብቶች ድምፅ ሊሆን የሚችል፣ ለሰብዓዊ መብቶች አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል፣ ስለሰብዓዊ መብቶች ሊያስተምር፣ ክትትል ሊያደርግ፣ ምርመራ ሊያካሂድ የሚችል ተቋም እንዲኖረን ተደርጎ መሥራት መቻሉ ደግሞ ጥሩ ዕርምጃ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ አንፃርም ጥሩ ልምድና ሙከራ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተቋም የመመሥረት ልምድም ለሌሎች ተቋማት እንደ ምሳሌ እያገለገለ ነው፡፡ ባለፉት ጊዜያት አንዳንድ ተቋማት ለውጥ ሲያካሂዱና ተቋማቸውን ማደራጀት ሲፈልጉ ብዙ ጊዜ የእኛን ልምድ ለመጋራት ብለው ይመጣሉ፣ እኛም በደስታ እንካፍላለን፡፡ ይህ ጥሩ ሙከራና ልምምድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ፈተና እየገጠማት ቢሆንም ከፈተናው ውስጥ ቀስ እያልን እንወጣለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ አሁንም መጀመሪያ ቀን በነበረኝ እምነትና ተስፋ መጠን ያህል ነው ሥራዬን የምሠራው፡፡

ሪፖርተር፡- ከተሾሙ አምስት ዓመታት ሊሆን ጥቂት ወራት ይቀራሉ፡፡ የሥራ ዘመንዎም ከሦስት ወራት በኋላ ይጠናቀቃል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ በኮሚሽነርነት ለመቀጠል ፍላጎትዎ እንዴት ነው?

ዶ/ር ዳንኤል፡- እሱን እንግዲህ ወቅቱ ሲደርስ ብናገር ይሻላል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...

‹‹ዘላቂ ጥቅም ያመጣል ብዬ ያሰብኩትን ሥራ ለመተግበር እንደ መሪ መጀመሪያ ቃሌን ማመን አለብኝ›› እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመቀላቀል የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘ 25ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ጉዞው በውጤታማነት ሲራመድ የነበረ ባንክ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት...