Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ሰብሰብ ብለው ካፒታላቸውን በማደራጀት ለውድድር ይዘጋጁ!

በኢትዮጵያ የውጭ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ቢዝነሶች ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ አሁን ላይ እጅግ ጥቂት ከሚባሉ የቢዝነስ ዘርፎች ውጪ በሁሉም ቢዝነሶች ውስጥ ገብተው ከውጭ ተመሳሳይ ኩባንያዎች ጋር የሚፎካከሩበት ሜዳ እየሰፋ ነው፡፡

የውጭ ኩባንያዎች ይሳተፉባቸው የነበሩ በርካታ ዘርፎች እየተከፈቱ መምጣት በቴሌኮም ዘርፍ ለመጀመርያ ጊዜ የውጭ ኩባንያ ገበያውን አስችሏል፡፡ በቀጣይ ሊቀላቀል የሚችል የቴሌኮም ኩባንያም እንደሚኖር ይታመናል፡፡ ለረዥም ጊዜ ከዛሬ ነገ ይፈቀዳል እየተባለ ለዓመታት ሲጠበቅ የነበረው የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የሚፈቅደው ሕግ ወጥቷል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት የውጭ ባንኮች የኢትዮጵያን ገበያ ሲቀላቀሉ ያለውጭ ተፎካካሪ በከለላ የቆዩት የአገራችን ባንኮች ለየት ያለ ውድድር የሚጠብቃቸው ይሆናል፡፡ 

እንደ ባንኩ ሁሉ የኢንሹራንስ ዘርፉም ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት መሆኑ እንደሚሆን የሚጠበቅ በመሆኑ የአገራችን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውድድራቸው እንደቀደመው እርስ በርስ መሆኑን የሚያስቀር ነው፡፡ እየተከፈቱ በመምጣት አሁን ደግሞ የጅምላና ችርቻሮው የወጪና ገቢ ንግዱ ሁሉ የውጭ ተወዳዳሪዎች እንዲገቡበት መፈቀዱ በአገሪቱ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ብዙ ለውጦች ያመጣል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ዕርምጃዎቹ በውድድር የተሻለ አገልግሎት ለማግኘት ያስችላል ተብሎም ይታመናል፡፡ በአብዛኛው የቢዝነስ ዘርፎች የውጭ ኩባንያዎች መግባት ሊሰጥ የሚችለው ጥቅም የጎላ ነው ቢባልም ተፅዕኖ የለውም ተብሎ ግን አይታሰብም፡፡ ሁኔታው የምርጫ ዕጦት ወይም አይቀሬ በመሆኑ የተወሰነ ዕርምጃ ነው፡፡ የአገር በቀል ኩባንያዎች የሚጠብቃቸውን ውድድር ታሳቢ አድርገው ከተዘጋጁ ጥሩ ተፎካካሪ በመሆን ወደፊት ይራመዳሉ፡፡ በቅርቡ እንኳን ኢትዮ ቴሌኮም ተወዳዳሪ ቢመጣበትም አጠቃላይ አሠራሩን አስተባብሎ አገልግሎቱን በማስፋቱ ጠንካራ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚችል በተግባር እያሳየ መሆኑ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ 

በአንፃሩ ለምሳሌ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ያለውን ሁኔታ ስናይ ጠንካራ ተፎካካሪ ያለመሆን ሊያሳጣ የሚችለው ነገር ቀላል ያለመሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ብዙ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ከውጭ ኮንትራክተሮች ጋር ተፎካክረው ገበያውን በበላይነት ለመቆጣጠር የሚያስችላቸው ዕድል ጠቦባቸዋል፡፡ 

በተለይ ትልልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶችና የፋይናንስ ተቋማት የሚያስገነባቸው ረዣዥም ሕንፃዎች ግንባታዎች ላይ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ጠንካራ ተወዳዳሪዎች መሆን አልቻሉም፡፡ በዚህ ምክንያት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ግንባታዎች ለውጭ ኩባንያዎች እየወሰዱ ብዙ ሀብት ወደ ውጭ እንዲወጣ ምክንያት ሆኗል፡፡ እንዲህ የለው ሁኔታ የውጭ ኩባንያዎች መግባት ሊፈጥር የሚችለው አንድ ተፅዕኖ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ስለዚህ ጠንካራ ተወዳዳሪ ካለመሆን ጋር ተያይዞ በሌሎች ዘርፎችም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይከሰት ምን ያህል እየታሰበበትና ዝግጅት እየተደረገበት እንደሆነ በእጅጉ ያሳስባል፡፡ በኮንስትራክሽንም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ሊኖር የሚችል ውድድርን ለመቋቋም ብቻ ሳይሆን አሸንፎ በገበያው የበላይነትን ለማግኘት አገር በቀል ኩባንያዎች ከተለመደው አሠራር በመላቀቅ ጠንካራ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችላቸውን አቅም መፍጠር የሞት ሽረት ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡

ከንግድና የአገልግሎት አሰጣጥ ጋር አብሮን የቆየውን ኋላቀር አሠራር ማስወገድ፣ የተላበሰ የቢዝነስ አመራር ካልተቻለ በቀላሉ የውጭ ኩባንያዎችን በመወዳደር ቀላል አይሆንም፡፡ 

ስለዚህ ብቁ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ በሁሉም ረገድ ራስን ማዘጋጀት እንደተጠበቀ ሆኖ ሰብሰብ ብሎ ጠንካራ ካፒታል አሰባስቦ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን የውጪ ተወዳዳሪ መሆን የሚችልበት ዕድል ሊፈጠር እንደሚችል በማሰብ ጭምር ካልተሠራ ወደፊት እየሰፋ የሚሄድበት ውድድር አሸንፎ ለመውጣት ቀላል አይሆንም፡፡ 

ሌላውን ትተን በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ የገነባቸውን የፋይናንስ ተቋማት ሕንፃዎች የገነቡና እየገነቡ ያሉ የውጭ ኮንትራክተሮች ሥራውን ሊሠሩ የቻሉት ልምድ ስላላቸው ብቻ ሳይሆን የተደራጀ አሠራርና የፋይናንስ አቅም ስላላቸው ጭምር ነው፡፡ 

ኢትዮጵያውያን ኮንትራክተሮችም እነዚህን ሕንፃዎች በዲዛይኑ መሠረት መሥራት የሚችሉበት ዕድል ሰፊ እንደነበር ደፍሮ መናገር የሚቻለው ለየብቻ ከመሥራት በጥምረት ተወዳዳሪ መሆን የሚችልበት ሰፊ ዕድል በመኖሩ ነው፡፡ ሥራው የተለየ የሚጠይቅ ነገር የለውም ሊገኝ የማይችል ባለሙያ ቢኖር እንኳን ከውጭ በመቅጠር ጭምር ተወዳዳሪነታቸውን ከፍ በማድረግ በቢሊዮን የሚገዙበት ብር እዚሁ ማስቀረት ይችላሉ፡፡

ነገር ግን ሁሉም በየግሉ ለመሥራት የሚሻ መሆኑ በትብብር አትራፊ መሆን የሚችልበትን ዕድል ለመጠቀም ያለመቻል ተጎጂ አድርጓናል፡፡ ከዚህም በኋላ ቢሆን የኮንስትራክሽን ዘርፉም ሆነ አሁን ለውጭ ኩባንያዎች የተከፈቱ ቢዝነሶች ላይ ያሉ በየግላቸው ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ባሻገር ሰብሰብ ብሎ ጠንካራ ኩባንያ መሠረት ከቻሉ የውጭ ከባንያዎች ሥጋት ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ በተናጠል ተወዳዳሪ ለመሆን ሲታሰብ ቢያንስ ኢትዮ ቴሌኮም ተወዳዳሪ እየመጣ ነው ብሎ እንደወስደው ዓይነት ሥር ነቀል ለውጥ ማድረግ አንዱ ነው፡፡ 

ካልሆነ በየቢዝነስ ዘርፉ ያሉ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ሰብሰብ ብለው ካፒታላቸውን አደራጅተው ጠንካራ ኩባንያ መፍጠር ግድ ይላቸዋል፡፡ 

ይህ ዓይነቱ መንገድ ከውድድር ውጪ ከመሆን ከማዳኑ በላይ ኢትዮጵያ የምትጠቀስበት ትልልቅ ኩባንያዎችን ወደ መፍጠር ሊወሰድ ሁሉ ይችላል፡፡ 

እስካሁን በዓለም ገበያ ከቡና ውጪ ስማችንን የሚያስነሳ ይኼ ነው የሚባል ተቋም ካለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ነው፡፡ 

በሌሎች የቢዝነስ ዘርፎችንም የኢትዮጵያን ስም የሚያስጠሩ ከአገር አለፈው በውጭ ተወዳዳሪ የሚሆኑ ኩባንያዎችን መፍጠር ከተፈለገ በጋራ ትልቅ ራዕይ ያለው ሥራ ይሠራ፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት