Friday, May 17, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ቅንጦት አይደለም!

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባዔ በወሰነው መሠረት በየዓመቱ እ.ኤ.አ. ሜይ 3 የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት ቀን የሚዘከርበት ምክንያትም የፕሬስ ነፃነትን አስፈላጊነት ግንዛቤ ለማዳበር ከመሆኑም በላይ፣ መንግሥታት እ.ኤ.አ. በ1948 የፀደቀውን ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ መሠረት በማድረግ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ ለማስገንዘብ ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት የሰብዓዊ መብቶች አካል ከሆነው ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ መብት ጋር ከፍተኛ ዝምድና አለው፡፡ ለዚህም ነው በአምባገነኖች መዳፍ ሥር ከሚገኙ እጅግ በጣም ጥቂት አገሮች በስተቀር በበርካታ አገሮች በከፍተኛ ስሜት የሚዘከረው፡፡ እኛ የፕሬስ ነፃነት ቀንን ለምን እንዘክራለን? ስለፕሬስ ነፃነት እንዴት ነው በግልጽነት የምንነጋገረው? በየአዳራሹ ለታይታ በሚደረጉ ዲስኩሮች? ወይስ ከልብ ታምኖበት? የፕሬስ ነፃነት ቀንን ለመዘከር ስብሰባ ለመቀመጥ ስንዘጋጅ ዓላማውን ከልብ መቀበላችን ግልጽ መደረግ አለበት፡፡

የፕሬስ ነፃነት ቀን ሲታሰብ በአገር ደረጃ ምን አገኘን? ምን አጣን? የተሟላው የቱ ነው? የተጓደለውስ? እያልን በግልጽ መነጋገር ካልቻልን ችግሩ በከፋ ሁኔታ ይቀጥላል፡፡ በሐሳብ መለያየት ብርቅ ባልሆነበት ዓለም ውስጥ በልዩነቶቻችን ምክንያት የተከሰቱ ችግሮችን ከሥር መሠረታቸው ዘርዝረን ማየት ካቃተን፣ የፕሬስ ነፃነት ቀን ተዘከረ ወይም ታሰበ ማለት አይቻልም፡፡ የሚዲያ ሰዎች እርስ በርሳቸው፣ ከመንግሥትና ከሕዝቡ ጋር በፕሬስ ነፃነት ዙሪያ በሚታዩ ሥር የሰደዱ ችግሮች ላይ በግልጽ መነጋገር ካልቻሉ ስለፕሬስ ነፃነት ማውሳት ፋይዳ የለውም፡፡ ለፕሬስ ነፃነት ቀን እንኳን አደረሰን ተብሎ መልካም ምኞት ለመለዋወጥም አይመችም፡፡ ሒሳብ የምናወራርድበት የፕሬስ ቀን ምን ማለት ነው? ጋዜጠኞችና ኤዲተሮች ስለሚጽፉት ወይም ስለሚዘግቡት ጉዳይ መነጋገር ብቻ ሳይሆን፣ ከፕሬስ ውጤቶች ሕዝቡ የሚያገኘው ምንድነው? መረጃዎች ትክክለኛና ሚዛናዊ ሆነው ይደርሱታል? ወይስ ሸፍጥና ሴራ ብቻ ነው የበዛው?

ሚዲያው የራሱን ችግር መነጋገሩ እንዳለ ሆኖ፣ መረጃ ያለ ምንም እንከን ወደ ሕዝቡ ይፈሳል ወይ? ጋዜጠኞች ራሳቸውን በራሳቸው ሳንሱር እያደረጉ ነው ወይ ለሕዝቡ የሚያቀርቡት? የሚተላለፈው መረጃ በሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የሚፈጥረው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ምን ይመስላል? የሚሉት ተጠቃሽ መሆን አለባቸው፡፡ በአገሪቱ አንድ የምርጫ ክልል (Constituency) ውስጥ 100 ሺሕ ሕዝብ ይኖራል፡፡ በአገራችን የሚገኙ ጋዜጦች ምን ያህል ናቸው? የጋዜጦቻችን የአንድ ወር ኅትመት በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ የሚኖር ሕዝብን ማዳረስ ካልተቻለው፣ የፕሬስ ነፃነት ቀንን እንዴት ነው የምንዘክረው? በመላ አገሪቱ ሃምሳ ያህል የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች አሉ፡፡ የአገራችን ጋዜጦች የአንድ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብን መድረስ ይችላሉ ወይ? በአማርኛ ቋንቋ የሚታተሙት በጣት የሚቆጠሩ ጋዜጦች የአገሪቱን የተማረ የሚባል የኅብረተሰብ ክፍል መድረስ ለምን አዳገታቸው?

የተለየ ሐሳብን ማክበር የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ወደ ጎን እየተገፋ ትችቶችን ያለ መስማት ፈተና ተጋርጧል፡፡ ከመንግሥት ጀምሮ በየደረጃው የራሳቸውን ከባቢ የፈጠሩ ጭምር ትችትን አይታገሱም፣ ልዩነትን አይታገሱም፣ የሐሳብ ልዩነትን አይቀበሉም፡፡ ትችትንና ልዩነትን፣ እንዲሁም በሐሳብ መለያየትን መታገስ የሚፈልጉ አለመኖራቸው ለንግግር ነፃነት ጭምር ፈተና እየሆነ ነው፡፡ በሐሳብ መለያየት ሞት ይመስል ከየአቅጣጫው ቁጣዎች ይሰማሉ፡፡ የሐሳብ ነፃነትን በመጋፋት ፀጥና እረጭ ያለ ድባብ እንዲሰፍን ይፈለጋል፡፡ ይህ ችግር የመንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የባለሀብቶችና ለሐሳብ ነፃነት ቀናዒ የሆነ መንፈስ የሌላቸው ግለሰቦች ጭምር ነው፡፡ ለሐሳብ ነፃነት ፈተና ከሆኑ ችግሮች መካከል አንዱ ሚስጥራዊነት በመሆን ተጠያቂነትን ማዳፈን ነው፡፡ አትዩኝ፣ አትናገሩኝ፣ አትጠይቁኝ፣ ወዘተ የሚሉ እየበዙ በመሆናቸው የሐሳብ ነፃነት ፈተና ውስጥ ነው ያለው፡፡ ይህ ችግር ከመንግሥት ጀምሮ እስከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድረስ በጉልህ የሚታይ ነው፡፡

መንግሥት እያንዳንዱን ፖሊሲ ሲቀርፅ የንግግር ነፃነትን ለማክበርና ለማስፋፋት ጥረት ያደርጋል ወይ? ካላደረገስ መፍትሔው ምን ሊሆን ነው? በሕገ መንግሥቱ የሠፈረው አንቀጽ 29 ለፕሬስ ነፃነት ዋስትና ሰጥቷል፡፡ መንግሥት ደግሞ ይህንን ነፃነት የማስከበር ተነሳሽነት በተግባር ሲታይ፣ ለፕሬስ ነፃነት መከበር ያበረከተው አስተዋጽኦ ከሚፈለገው ጋር ይመጣጠናል? ከጋዜጠኞች ጋር ለዓመታት የዘለቀው አተካሮ አሁን ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የምናስበው በሐዘን ነው፡፡ ይህም የፕሬስ ነፃነት ቀን ሲዘከር በሐሳብ መለያየት ሞት አይደለም ነበር ብለን እንድናስብ ያደርገናል፡፡ የንግግር ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ጋዜጠኞችንም ሆነ ሐሳባቸውን በነፃነት መግለጽ የሚሹ ወገኖችን ያሸማቅቃሉ፡፡ የፕሬስ ነፃነት ላይ ጥሰት ሲፈጸም ኧረ ነውር ነው የሚሉ የመንግሥት ሹማምንት፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ አባላትና ሌሎችም ይመለከተናል የሚሉ ከሌሉ፣ ስለፕሬስ ነፃነት ወይም ስለንግግር ነፃነት እንዴት ነው መነጋገር የሚቻለው?

በፕሬስ ነፃነት ጉዳይ በተለይ የልሂቃን ሚና ግልጽ ሆኖ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ልሂቃኑ የንግግር ነፃነትን አምነውበት መቀበል ወይም መፈለግ አለባቸው፡፡ ለምን ቢባል የንግግር ነፃነት ይኑር ሲባልና ይህንን ነፃነት ከጥቃት መከላከል እንዳለበት መተማመን ሲኖር፣ ልሂቃኑ የሚስማማቸውን ብቻ አይደለም መስማት ያለባቸው፡፡ እንዲያውም የማይደግፉት ሐሳብ ጭምር እንዲደመጥ ማበረታታት ይኖርባቸዋል፡፡ የማንፈልገውን ጭምር ካልሰማን የንግግር ነፃነት ውበት የለውም፡፡ የምንጠላውን ወይም የማንስማማበትን ጭምር መስማት የንግግር ነፃነትን መደገፍ ነው፡፡ ለማይስማማን ንግግር ጭምር ጥብቅና መቆም ካቃተን የራሳችን ንግግር ሳይቀር አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅ መገንዘብ ይገባል፡፡ እየመረረንም ቢሆን ለሐሳብ ልዩነት ክብር መስጠት ያስከብራል እንጂ አያስነቅፍም፡፡ የሐሳብ ልዩነት በነፃነት ካልተስተናገደ ስለፕሬስ ነፃነት የሚደረገው ዲስኩር ትርጉም ያጣል፡፡ በሐሳብ መለያየት ሞት ስላልሆነ ለሚስማማን ብቻ ሳይሆን ለሚጎረብጠን ጭምር ዕውቅና እንስጥ፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ቅንጦት እንዳልሆነ እንገንዘብ!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለፖለቲካዊም ይሁን ኢኮኖሚያዊ ትግል መቀዛቀዝ ምክንያቱ የጠራ ርዕዮተ ዓለም አለመኖር ወይስ የምሁራን መዳከም?

መሬት ላራሹ ብለው በተነሱ ተማሪዎችና ምሁራን ድምፅ የተቀጣጠለው የመጀመሪያው...

በአዲስ አበባ ለሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሰጡ ድጋፎችንና መሥፈርቶችን ያካተተ አዲስ መመሪያ ወጣ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው ወስጥ ለሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች...

የዘንድሮ የወጭ ንግድ ገቢ ከዕቅዱም ሆነ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑ ተገለጸ

የኢትዮጵያ የወጭ ንግድ ገቢ በተያዘው የበጀት ዓመትም የታቀደውን ያህል...

ሕይወትም እንዲህ ናት!

ከዊንጌት ወደ አየር ጤና ነው የዛሬው የጉዞ መስመራችን፡፡ አንዳንዴ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...

የሰላምና የኑሮ ውድነት ጥያቄው ምላሽ ይሻል!

የዘንድሮ የዓለም ሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲከበር፣ የአየር ንብረት ለውጥ በሥራ ከባቢ ደኅንነትና ጤና ላይ እያደረሰ ያለው ተፅዕኖ ትኩረት እንዲሰጠው ማሳሰቢያ...