Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የተፈጠረውን ክስተት ሲቪል አቪዬሽን በጥልቀት ሊመረምር ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ በመብረር ላይ ሳለ የደኅንነት ችግር ሊያስከትል የሚችል ክስተት በገጠመው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በረራ ቁጥር ET 154 ላይ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የደኅንነት ምርመራ እንደሚያደርግ ምንጮች ገለጹ።

ማክሰኞ ሚያዚያ 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የውስጥ ክፍል ላይ ከፍተኛ ጭስ መከሰቱን፣ ነገር ግን በመንገደኞች ላይም ሆነ በአውሮፕላኑ ላይ ምን ዓይነት እክል ሳይፈጠር በአዲስ አበባ አየር ማረፊያ በሰላም ማረፉን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በአውሮፕላኑ ውስጥ ጭስ የታየ ቢሆንም አውሮፕላኑ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ማረፊያ በተመደበለት የመንገደኞች ማስተናገጃ በር ያለ ምንም እክል ሳያጋጥመው በማረፉና መንገደኞች ከአውሮፕላኑ ላይ ደኅንነታቸው እንደተጠበቀ መውረዳቸው ተመላክቷል፡፡

የክስተቱ መንስዔ በመጣራት ላይ መሆኑን የገለጸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ለተፈጠረው ክስተትም ደንበኞቹን በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ በመብረር ላይ በነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን ውስጥ ለጊዜው በምን ምክንያት እንደተነሳ ያልታወቀ ጭስ ተከስቶ እንደነበርና መንገደኞችም በተፈጠረው ክስተት ከፍተኛ ድንጋጤና ፍርኃት ውስጥ ገብተው ነበር።

የአውሮፕላኑ ዋና አብራሪ ባስተላለፉት የደኅንነት ጥንቃቄ ዕርምጃ መሠረትም ሁሉም ተሳፋሪዎች በአውሮፕላኑ ላይ የተገጠመውን የአየር መሳቢያ የፊት ጭምብል (oxygen mask) እስከማድረግ ደርሰው እንደነበር ምንጮቻችን ገልጸዋል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የበረራ ደኅንነት ክፍል እክል የገጠመው አውሮፕላን ቀጣይ በረራ እንዳያደርግ በማገድ፣ በበረራ ወቅት ያጋጠመውን የደኅንነት ክስተት እንደሚያጣራ ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አየር መንገዱ በሚሰጠው የአገር ውስጥ የበረራ አገልግሎት ላይ የደኅንነት አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ክስተቶች ደጋግመው መከሰታቸውን ያስታወሱት ምንጮቹ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን አጠቃላይ የደኅንነት ፍተሻ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

ባለፈው ጥር ወር 2016 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ሲበር የነበረ አንድ የመንገደኞች አውሮፕላን በመቀሌ አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ ለማረፍ በሚሞክርበት ወቅት፣ ከማረፊያው አስፋልት ውጪ የመውጣት እክል ገጥሞት እንደነበር ይታወሳል።

ይህ አውሮፕላን ለማረፍ በሚሞክርበት ወቅት ጎማው ባጋጠመ እክል የደኅንነት ችግር ሊያስከትል የሚችል ክስትት እንዳጋጠመው ምንጮች ገልጸዋል።

ሌላው የመንገደኞች አውሮፕላንም በተመሳሳይ በአርባ ምንጭ አየር ማረፊያ ከማረፊያ መስመሩ (ራንዌይ) የመውጣት እክል ገጥሞት እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ አራት የደኅንነት እክሎች የተመዘገቡ መሆኑን የጠቀሱት ምንጮቹ፣ ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ ሲበር የነበረውን ጨምሮ እክል ያጋጠማቸው አውሮፕላኖች Q400 በመባል የሚታወቁት አየር መንገዱ በአገር ውስጥና ወደ ጎረቤት አገሮች ለሚደረጉ በረራዎች የሚገለገልባቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካሉት 178 አውሮፕላኖች መካከል 33 የሚሆኑት Q400 በመባል የሚታወቁት ለመካከለኛ ርቀት የሚጠቀምባቸው አውሮፕላኖች ናቸው።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች