Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከፒያሳ በሳር ቤት እስከ ወሎ ሠፈር ለኮሪደር ልማት ፕሮጀክት 3,250 አባወራዎች ይነሳሉ

ከፒያሳ በሳር ቤት እስከ ወሎ ሠፈር ለኮሪደር ልማት ፕሮጀክት 3,250 አባወራዎች ይነሳሉ

ቀን:

ከፒያሳ በመነሳት በሳር ቤት በኩል እስከ ወሎ ሠፈር ድረስ የሚገነባው አዲሱ የኮሪደር ልማት፣ 3,250 አባወራዎችን ወይም ከ14 ሺሕ በላይ ሰዎችን እንደሚያስነሳ ተመላከተ፡፡ ተነሺዎችን ለማስፈር 21 ሔክታር መሬትና ስድስት ቢሊዮን ብር  የካሳ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ታውቋል፡፡

ከአሥር ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቱ ከፒያሳ በመነሳት እስከ ብሔራዊ፣ ከብሔራዊ እስከ ሜክሲኮ አደባባይ፣ ከሜክሲኮ አደባባይ እስከ ሳር ቤትና ከሳር ቤት እስከ ወሎ ሠፈር ተብሎ በአምስት ንዑስ ፕሮጀክቶች ተከፋፍሎ ዲዛይን እንደወጣለት ሪፖርተር የተመለከታቸው የዲዛይን ዶክመንቶች ያሳያሉ፡፡ አጠቃላይ ፕሮጀክቱ አምስት ክፍላተ ከተሞችን የሚነካ ሲሆን እነዚህም አራዳ፣ ልደታ፣ ቂርቆስ፣ ንፋስ ስልክና ቦሌ ናቸው፡፡

ጠቅላላ ፕሮጀክቱ 460 ሔክታር መሬት ይዞታ የሚነካ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 114 ሔክታር ለመልሶ ማልማት ነፃ እንደሚደረግ ዶክመንቱ ያሳያል፡፡

- Advertisement -

ፕሮጀክቱን ለማስፈጸም 40 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ለአብነት ያህል ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ለፈጣን የአውቶቡስ መስመር ግንባታ ይውላል፡፡ ስድስት ቢሊዮን ብር ለማኅበራዊ ቤቶች ግንባታ፣ ስድስት ቢሊዮን ለተነሺዎች ካሳ ክፍያ፣ አራት ቢሊዮን ብር ለመንገድ ግንባታ፣ ሦስት ቢሊዮን ለፓርክ (Green Park) ተመድቧል፡፡ በተጨማሪም የፓርኪንግ ቦታዎች፣ ሰባት ያህል ድልድዮች፣ የመሠረተ ልማትና የሕዝብ መገልገያ ቦታዎች ይገነባሉ፡፡

ወጪ የሚደረገውን 40 ቢሊዮን ብር በአምስት ዓመታት ውስጥ በእጥፍ ለማስመለስ መታቀዱንም ሰነዱ ያመለክታል፡፡ በኮሪደር መስመሩ ላይ መንግሥት 114 ሔክታር መሬት ነፃ ለማድረግ ያቀደ ሲሆን፣ ይኼንን መሬት 70 ሺሕ ብር በካሬ ለአልሚዎች በማከራየት በአምስት ዓመት ውስጥ 99 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ዶክመንቱ ያሳያል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በዚህ መስመር ላይ መንግሥት ሊያከራያቸው ካቀዳቸው የመኖሪያ፣ የንግድና የቢሮ ሕንፃና ቤት ከ5.8 ቢሊዮን ብር በላይ በየዓመቱ ገቢ ለማስገኘት መታቀዱ ታውቋል፡፡ ከፒያሳ እስከ ሜክሲኮ አደባባይ አብዛኛው ቦታ ለአረንጓዴ ልማት ማለትም ለሕዝብ መዝናኛ ቦታዎችና ፓርኮች ታቅዷል፡፡ አምባሳደር አካባቢ ያለው የመከላከያ ሚኒስቴር ግቢ ሙዚየም፣ ካፌና መዝናኛ የሚኖረው የባህል ማዕከል እንደሚቀየር ዲዛይኑ ያሳያል፡፡

የሰይጣን ቤት ተብሎ የሚታወቀው ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ ያለው ቦታ ወደ ባህል ማዕከልና መዝናኛ ቦታ በመጠነኛ ለውጥ ያደርጋል፡፡ ከአፍሪካ ኅብረት ፊት ለፊት ያለው 1.2 ሚሊዮን ካሬ ሜትር ቦታ ‹‹የአፍሪካ ማዕከል›› ለመገንባት ይውላል፡፡ ማዕከሉ ሙዚየም፣ ላይብረሪ፣ የባህልና መዝናኛዎች ሲኖሩት አጠቃላይ አካባቢው ከፍተኛ ጥበቃ ያለው የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አገልግሎት ይቀየራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከሜክሲኮ ሳር ቤት ባለው ንዑስ ፕሮጀክት ከታሰቡት ብዙ ዕቅዶች ውስጥ ሆስፒታልና አዲሱ ቱሞሮ (Adisu Tomorrow) ልዩ የኢኮኖሚ ዞንም ይገኝበታል፡፡ በዚህ አካባቢ ከአራት ወለል ሕንፃ (G+4) በታች የሆኑ ሕንፃዎች ሁሉም ይፈርሳሉ፡፡ የኮሪደር ልማቱን ለማስፈጸም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሜጋ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት ቤት፣ የከተማ አስተዳደሩ፣ የአዲስ አበባ ዕቅድና ልማት ኮሚሽንን ጨምሮ ሃያ ተቋማት ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...