Thursday, June 13, 2024

‹‹አራተኛ መንግሥት›› የሚባለው ሚዲያ ቁመና ማሽቆልቆልና መጪው ጊዜ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በአንድ አገር ውስጥ ሕግ አውጪ፣ አስፈጻሚና ተርጓሚ የሚባሉ ሦስት የመንግሥት ምሰሶዎች ወይም አካላት እንዳሉ ቢታወቅም ሚዲያ በሦስቱ የመንግሥት አካላት ላይ ባለው የኃይል ሚዛንን የመፈተሽና የመቆጣጠር ሚና (Watchdog Role) አራተኛው መንግሥት እየተባለ ይጠራል፡፡ ሚዲያው በዚህ ሚናው አማካይነት ሦስቱ የመንግሥት አካላት ሹማምንት ሕዝቡን ሲበድሉ፣ ሕዝቡ በደሉን አስመልክቶ ድምፁን የሚያሰማበትና በዳዮችን የሚያጋልጥበት መድረክ ነው፡፡ በበለፀጉት አገሮች የሚዲያው አራተኛ ሚና በአመዛኙ የሚታይ ቢሆንም፣ ዴሞክራሲ ባልዳበረባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ይህ ዓይነቱ ዕሳቤና ዕርምጃ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ ከዓመታት በፊት የመንግሥት ለውጥ መካሄዱን ተከትሎ በፖለቲካ አስተሳሰባቸው የታሰሩ ጋዜጠኞችን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችንና ፖለቲከኞችን ከእስር መፍታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተወደሰ መልካም ተግባር ከመባልም አልፎ፣ ኢትዮጵያ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን እንድታስተናግድ መደረጓ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

በተጨማሪም በ2013 ዓ.ም. ፀድቆ ወደ ሥራ የገባው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ለዘርፉ አንድ መልካም ዕርምጃ ተድርጎ ተወስዶም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በሚዲያ ኢንዱስትሪው ታይቶ የነበረው መልካም ጅማሮና የለውጥ ምኅዳር እያደር መደብዘዙና በተግዳሮቶች ውስጥ ማለፉ ግድ የሆነ ይመስላል፡፡

በዚህ ረገድ ለማሳያነት ከሚቀርቡ ሐሳቦች ውስጥ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ወደ ሥራ የገባውን የሚዲያ አዋጅ በመጣስ በሚዲያ አማካይነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ተጠርጣሪ የሆኑ ጋዜጠኞች በፖሊስ እየታፈኑ ሲያዙ ብቻ ሳይሆን፣ ፍርድ ቤት ሲቀርቡም በአዋጁ መሠረት እየተከናወነ አለመሆኑና ባለሙያዎች ሥራቸውን በነፃነት እንዳይሠሩ፣ እንዲሸማቀቁና የፕሬስ ምኅዳሩ የበለጠ እንዲጠብ እያደረገው መምጣቱን የዘርፉ ተቆርቋሪዎች በተለያየ መንገድ ሲያነሱት መስማት የተለመደ ጉዳይ መሆኑ ነው፡፡

በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 1238 አንቀጽ 86 በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል (ጋዜጠኛ) በወንጀል ሥነ ሥርዓት የሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ፣ ክሱ በቀጥታ በዓቃቤ ሕግ አማካይነት ለፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት ተደንግጓል።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤትና በርካታ የዘርፉ ተዋናዮች የአገሪቱ ከፍተኛ የሕግ አውጪ አካል የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣው ይህ አዋጅ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ይበልጥ ለማስፋትና ሙያተኞች በኃላፊነት ስሜት እንዲሠሩ ለማበረታታት  ያለመ ቢሆንም፣  ከሕጉ መንፈስ ተቃራኒ በሆነ መንገድ የዜጎች መብት በፍትሕ አካላት በተደጋጋሚ እየተጣሰ ነው የሚል ክስ ሲያሰሙ ሰነባብተዋል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎቸና የመብት ተሟጋቾችን ተገቢውን የሕግ ሥነ ሥርዓት ባልተከተለ መንገድ በቁጥጥር ሥር ማዋል፣ ዕገታ፣ ባልታወቀ ሁኔታና መንገድ ተያዙ መባል፣ እንዲሁም ባልተጠበቀ ሁኔታና ቦታ ተለቀቁ መባል የተደጋገመ ተግባር መሆኑን በመጥቀስ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾችና የሙያ ተቆርቋሪ አካላት ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን ሲያነሱ መስማት የተለመደ ተግባር ሆኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት አካላት ጦማሪነት፣ አክቲቪስትነት፣ ጋዜጠኝነትና ፖለቲከኝነት በኢትዮጵያ መደበላለቁንና መስመር መጥፋቱን በመጥቅስ መንግሥት የሚዲያ ነፃነትን የሚጋፋ ተግባር አለመፈጸሙን፣ ይልቁንም የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚደረግ ተግባር መሆኑን ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ በኢትዮጵያ ጦማሪነት፣ አክቲቪስትነትና ከጋዜጠኝነት ጋር ተዛማጅ የሆኑ ሙያዎችን ለመበየን የወጣ ግልጽ ሕግ በሌለበት፣ የመንግሥት አካላት ሁሉንም በአንድ ጨፍልቀው በመውሰድ ፍርደ ገምድል ውሳኔ እየሰጡ ነው የሚሉም ይደመጣሉ፡፡

በሚዲያው ኢንዱስትሪ ለበርካታ ዓመታት የሠሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ባለሙያ፣ ‹‹ለዓመታት ለኖርኩበት ሙያ ከምንም በላይ ትልቅ ክብር አለኝ፣ ነገር ግን እንደ አገር ከጊዜ ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ መልክ እየያዘ ነው፤›› ይላሉ፡፡

ባለሙያው ወደ ሥራ ሲገቡ አለቃቸው የተናገራቸውን ንግግር በማስታወስ፣  ‹‹እንኳን ወደ አራተኛው የመንግሥት ተቋም መጣህ ነበር ያለኝ፤›› ብለው፣ ነገር ግን  የሚዲያ ኢንዱስትሪው የመንግሥትነት ሚናው ቀርቶበት እንደ አንድ ማንኛውም ተቋም ተከብሮ ባለበት መሥራት መቻሉም ትልቅ ተስፋ ነበር በማለት ስለችግሩ ያስረዳሉ፡፡

ከተቋቋመ ጥቂት ዓመታትን ያስቆጠረውና የኢትዮጵያ ሚዲያ ኢንዱስትሪ ለአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርግ፣ ጥራቱ የተጠበቀ፣ ተደራሽ፣ በኃላፊነት ስሜት የሚንቀሳቀስና ነፃነቱ የተረጋገጠ አስተማማኝ የመገናኛ ብዙኃን እንዲስፋፋ የማድረግና መሰል ዓላማዎችን ይዞ እንደተነሳ የሚነገርለት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ባለፉት ዓመታት ካወጣቸው ቁጥራቸው የበዛ መግለጫዎች ውስጥ፣ በርካታዎቹ በኢትዮጵያ ያለው የሚዲያ ምኅዳር መጥበቡን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡

ለአብነት ያህል ምክር ቤቱ እ.ኤ.አ. በታኅሳስ 2023 በሰጠው መግለጫ መገናኛ ብዙኃን ነፃነታቸውን ለድርድር ሳያቀርቡ በሥነ ምግባር እንዲመሩና ሥራቸውን በነፃነት እንዲሠሩ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ በተመሳሳይ እ.ኤ.አ. በሐምሌ 2023 አንድ የአገር ውስጥ  ሚዲያ ተቋም የቢሮና የሚዲያ ቁሳቁሶች በመዘረፋቸው ምክንያት በሰጠው መግለጫ ደግሞ በመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ላይ የሚፈጸም ዘረፋና የወንጀል ድርጊት መደጋገም ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና መረጃን ለሕዝብ ተደራሽ የማድረግ መብት ላይ ሥጋት መደቀኑን አስታውቆ ነበር፡፡

የተመድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እ.ኤ.አ. በግንቦት 2023 ለሁለት ቀናት በነበራቸው ጉብኝት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት፣ የሲቪክና የሚዲያ ምኅዳር ውስጥ እየተፈጠሩ ያሉ ክስተቶች አሳሳቢ እየሆኑ መምጣታቸውን መግለጻቸው ሌላው ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት እ.ኤ.አ. በሚያዝያ 2023 በሰጠው ተመሳሳይ መግለጫ ባለፉት አራት ዓመታት የፍትሕ ሥርዓቱ የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረገበት ቢሆንም፣ ጋዜጠኞችን በተመለከተ ከሕጉ አግባብ ውጪ የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ለማስቀረት አለመቻሉ በእጅጉ እንዳሳሰበው ገልጾ ነበር፡፡

ምክር ቤቱ አሳሰቡኝ በማለት ካወጣቸው በርካታ መግለጫዎች መካከል ሌላኛው ጉዳይ እ.ኤ.አ. በመጋቢት 2023 ያውጣውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት በአንዳንድ የኢንተርኔት የግንኙነት መተግበሪያዎች ላይ የጣለው ገደብ፣ መገናኛ ብዙኃን በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን መረጃ የማሰባሰብ፣ የማደራጀትና ለሕዝብ ተደራሽ የማድረግ መብት ላይ ተግዳሮት መፍጠሩን መገንዘቡን ገልጾ ገደቡ እንዲነሳ ያሳሰበበትን ከብዙዎቹ እንደ ማሳያ ይወሰዳሉ፡፡  

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ባለሙያዎች ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችና ጥቃት በተመለከተ፣ መቀመጫቸውን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገሮች ያደረጉ የመብት ተሟጋች ተቋማትና ግለሰቦች አቤቱታና ቅሬታ መስማት እየተለመደ መጥቷል፡፡

መቀመጫውን በፈረንሣይ ያደረገውና ከ180 አገሮች በላይ እንደሚሠራ የሚነገርለት ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (Reporters Without Borders) የተሰኘው ተቋም እ.ኤ.አ. 1948 የወጣውን የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ መሠረት በማድረግ፣ የጋዜጠኝነት ሙያና የጋዜጠኞች ደኅነት በአጠቃላይ የሰው ልጆች ነፃና ተዓማኒነት ያለው መረጃ የማግኘት መብታቸው መረጋገጡን በመዳሰስ በየዓመቱ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ወቅታዊ ቁመና፣ የአገሮችን ደረጃና የሚዲያ ምኅዳር የግምገማ ጥናት ይፋ ያደርጋል፡፡

ይህ ተቋም በሚያወጣው ሪፖርት መሠረት ኢትዮጵያ የዓለም የሚዲያ ነፃነትን ቀን ለ26ኛ ጊዜ ባከበረችበትና የሚዲያ ምኅዳሩ በተሻለ ሁኔታ በተከፈተበት ወቅት እ.ኤ.አ. በ2019 በመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ደረጃ 110ኛ፣ እ.ኤ.አ. በ2020 99ኛ፣ እ.ኤ.አ. 2021  ደግሞ 101ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ ነበር፡፡

ዓመታት እየተቆጠሩና ዘርፉ በጫና ውሰጥ እያለፈ፣ ጋዜጠኞች በሕግ ከተቀመጠው አሠራር ውጪ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው እየበዛ ሲሄድና የመንግሥት እጅ ፈርጣማ መሆኑ ሲቀጥል፣ አገሪቱ በሚዲያ ነፃነት ረገድ አሳይታ የነበረውን እመርታ እንዲያሽቆለቁል ማድረጉ አመላካች ውጤቶች አሁንም እየታዩ ነው፡፡

በተመድ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አማካይነት በየዓመቱ ሚያዝያ 25 ቀን በሚከበረው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ይፋ የሚደረገው የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት አመላካች መለኪዎች መሠረት፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2022 በ114ኛ፣ እ.ኤ.አ. በ2023 በ114ኛ፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ2024 በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሎ በ141ኛ ደረጃ ተቀምጣለች፡፡

ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች በዓመታዊ ሪፖርቱ በእርስ በርስና በብሔር ተኮር ግጭቶች በኢትዮጵያ ታይቶ የነበረው የሚዲያ ነፃነት ወደ ከፋ ሁኔታ መቀየሩን፣ ጋዜጠኞች የበቀል ዕርምጃን በመፍራት እንደሚሠሩና በአሁኑ ወቅት 15 ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮችን ጨምሮ  በአዲስ አበባ የሚገኙ 18 ኤምባሲዎች የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንን አስመልክቶ በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ የንግግርና የሚዲያ ነፃነት መሠረታዊ የሰዎች መብት በመሆኑ ሊከበር እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

 ጋዜጠኞች ሥራቸውን ሲሠሩ ዛቻ እንደሚደርስባቸውና ያለ በቂ ምክንያት በቁጥጥር ሥር እንደሚውሉ ያወሳው የኤምባሲዎች መግለጫ፣ የፕሬስ ነፃነት ቀን ያለመታከት እውነትን ለመዘገብ የሚሠሩ ጋዜጠኞች የሚታሰቡበት ቀን ነው ብሏል፡፡ በመሆኑም ጋዜጠኞች ያለ ምንም ሥጋትና ፍርኃት የሚሠሩበት ምኅዳር እንፍጠር ሲሉ ኤምባሲዎቹ በመግለጫቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኤምባሲዎቹ መግለጫ ያልተዋጠለት የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለኤምባሲዎቹ በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሬስ ነፃነት እንዲከበር ፅኑ አቋም አለው፡፡ ነገር ግን ይህ መብት ሊተገበርና ሊጠበቅ የሚገባው በሕግ የበላይነት ማዕቀፍ ውስጥ ነው፤›› ሲል አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአጋሮቿና ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚመጣ ገንቢ ግንኙነትን የምትቀበል መሆኑን ቢገልጽም፣ በተደጋጋሚ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በመሰባሰብ ‹‹በደቦ›› የሚወጡ መግለጫዎች ለሁለትዮሽ ግንኙነት የማይጠቅሙ፣ እንዲሁም ከተለመደውና ቅቡልነት ካለው በሁለትዮሽ የዲፕሎማሲያዊ ስምምነት ከተመሠረተው ግንኙነት፣ ደንቦችና አሠራሮች ጋር የሚጣረሱ ናቸው ሲል መግለጫውን አጣጥሎታል፡፡

ጋዜጠኛ ሰሎሞን ሙጨ በኢትዮጵያ የጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ዘጋቢና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር መሥራችና ናቸው፡፡ ስለአገራዊ የሚዲያ ቁመና ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመንግሥት ለውጥ ከመደረጉ ከስድስት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ በርካታ መሰናክሎችና እንቅፋቶች ውስጥ ያልፉ ከነበሩ ዘርፎች መካከል ሚዲያው በትልቁ የሚነሳ ዘርፍ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ ዘርፉ የነበረበት ችግር በተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ አማካይነት ተቀርፎና ወደ ተሻለ ምዕራፍ በመግባቱ፣ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በኢትዮጵያ መከበሩ አንድ ትልቅ አገራዊ ትዝታ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡

በዚህም ምክንያት የመንግሥት ለውጥ መካሄዱን ተከትሎ የታየው የነበረው አዝማሚያ በተለይም የኅትመት ሚዲያ ውጤቶች ወደ ጠንካራ አቋም በመመለስ፣ ደፋር በሚባል ዕይታ መንግሥት አካሄዱን እንዲያርምና እንዲስተካከል ሰፋ ያለ ጠንካራ ትንታኔ የሚሰጡና ለማንበብ የሚያጓጉ እንደነበሩ ጋዜጠኛው ያስታውሳሉ፡፡ በእነዚህ ጥቂት የጅማሮ ዓመታትም አንዳንዶች መንግሥትን በማሞገስ፣ ግን ደግሞ የመንግሥትን የተሳሳተ አካሄድ በመንቀፍና በመተቸት የየራሳቸውን ዕይታ በነፃነት ሲያንፀባርቁ ማየት የቅርብ ጊዜ ትዝታ መሆኑ ግን አሳዛኝ ነው ይላሉ፡፡

በጋዜጠኞች ላይ ተደጋጋሚ የዘፈቀደ እስር፣ በሚዲያ ተቋማት ላይ የሚደርስ ዝርፊያና ስርቆት፣ በጋዜጠኞች ላይ የሚደረግ የማሳደድና የማስፈራራት ተግባር፣ በመኖሪያቸውና በተገኙበት ቦታ ሁሉ ታፍነው የተወሰዱ ጋዜጠኞች የት እንዳሉ የማይታወቅበት ሁኔታ መኖርና ከብዙ ጩኸት በኋላ ያሉበት ቦታ መታወቅ ወይም መለቀቅ የተለመደ ተግባር እንደሆነ ጋዜጠኛ ሰሎሞን ይናገራሉ፡፡

በተጨማሪም ጋዜጠኞች በሚሰጡት ጠንካራ ትንታኔ ምክንያት እውነቱንና ሀቁን በመናገራቸውና የሚዲያ ሥራቸውን በነፃነት ስለሠሩ ብቻ በሚደርስባቸው ዛቻና ሥጋት አገር ጥለው የተሰደዱ፣ አፋቸውን ዘግተው የተቀመጡና በእስር ላይ ሚገኙት በርካቶች ስለመሆናቸው አክለው ተናግረዋል፡፡

በቀጣዮቹ ዓመታት ምናልባት አገራዊ ምርጫን የመሳሰሉ ትልልቅ ሁነቶች ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዓይኑን የሚጥልባቸው ክስተቶች ላይ የሚዲያ ነፃነቱ ለቀቅ ሊል እንደሚችል የሚናገሩት ጋዜጠኛ ሰሎሞን፣ ከዚያ ውጪ ባለው ትንበያ ግን የኢትዮጵያ ሚዲያ የዓለም የሚዲያ ተቋማት የተጎናፀፉትን የሚዲያ ነፃነት በአጭር ጊዜ ይደርስበታል ብሎ መናገር ቅንጦት ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -