Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ 12 ሰዎችና ስድስት ዝሆኖች መገደላቸው ተገለጸ

በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ 12 ሰዎችና ስድስት ዝሆኖች መገደላቸው ተገለጸ

ቀን:

በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 12 ሰዎችና ስድስት ዝሆኖች መገደላቸው ተገለጸ፡፡

በብሔራዊ ፓርኮች አካባቢ በሚኖሩ ነዋሪዎችና በእንስሳቱ መካከል በቀጠለ ግጭት፣ በተለይ ሰዎች ወደ እንስሳት መጠለያው በሕገወጥ መንገድ እየገቡ እየተስፋፉ በመሆናቸው፣ የጉዳትና የሞት አደጋው እየጨመረ መጥቷል ሲሉ፣ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን መኮንን ተናግረዋል፡፡

ምክትል ዳይሬክተሩ ይህን የተናገሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የቱሪዝም ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማትን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት ነው፡፡ በሰውና በዱር እንስሳት መካከል ግጭትና የሚደርስ ጉዳት በባቢሌ ዝሆኖች መጠለያና በጩበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርኮች  በከፍተኛ ሁኔታ የሚስተዋልና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የመጣ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

ቋሚ ኮሚቴው ሕገወጥ ሠፈራ፣ ወረራ፣ እንዲሁም በሁለት ክልሎች መካከል በሚገኙ ፓርኮች ያለው ችግር በአፋጣኝ ታይቶ የአጭር ጊዜ መፍትሔ ሊበጅለት የሚገባ ቢሆንም፣ ባለሥልጣኑ እስካሁን መፍትሔ ሊሰጠው አለመቻሉን አስታውቋል፡፡

በሁሉም ፓርኮች በሚባል ደረጃ ሕገወጦች መሬቱን እየተቆጣጠሩ በመሆናቸው፣   የሚመለከታቸው አካላት በፓርኮች አካባቢ የሚገኙ ዜጎች እንዲወጡና መጠለያው እንዲከበር ርብርብ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ አስቻለው አላምሬ በሰጡት አስተያየት፣ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ የሚያሳየው ብርቅዬ እንስሳት እየጠፉ፣ እየተገደሉና  እየተሰደዱ ፓርኮች በሕገወጥ መንገድ እየተወረሩ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ለዚህ ሥራ የተቋቋመው ባለሥልጣንና ባለሥልጣኑን የሚከታተለው የቱሪዝም ሚኒስቴር ይህንን አሥጊ ደረጃ የደረሰ ጉዳይ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ አክለውም በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እንስሳት እየተገደሉ፣ ከአገር እየተሰደዱና እየጠፉ ተቋሙ ይህንን የማይከላከል ከሆነ በማቋቋሚያ አዋጁ መሠረት የታለመለትን ሥራ እየሠራ አለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን በአገሪቱ በሚገኙ በሁሉም ፓርኮች በሚባል ደረጃ በዱር እንስሳት ላይ የሚፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶችን ለመቀነስና ግንዛቤ ለማስጨበጥ፣ ከፖለቲካና ከፀጥታ አመራሮች ጋር በመሆን የሕግ የበላይነት ሥራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም አሁንም ትልቅ ሥራ የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡

በስንቅሌ የሚገኙት ቆርኪ የሚባሉት የዱር እንስሳት፣ እንዲሁም በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙት የዋሊያ ዝያርዎች ቁጥራቸው እየቀነሰ መሆኑን የገለጹት አቶ ሰሎሞን፣ በሰሜን ተራሮች ውስጥ በሚገኙ ዋሊያዎች ላይ ቆጠራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ በኦሮሚያ ክልል መሬቱን ለኢንቨስትመንት የመስጠት ተግባር መኖሩን፣ የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በልቅ ግጦሽ ጉዳት እንደደረሰበትና በተመሳሳይ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በሕገወጥ እንቅስቃሴ ምክንያት ቁመናው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ‹‹እየተባባሰ መጥቷል›› ያሉት በሁለት ክልሎች መካከል ያሉ የዱር እንስሳት መጠለያ ቦታዎች ላይ የሚደረግ መቀራመት መኖሩን ጠቅሰው፣ ምክር ቤቱና የቱሪዝም ሚኒስቴር ዕገዛ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ በኦሮሚያና በጋሞ ዞኖች መካከል እንደሚገኝ በሁለቱም ወገኖች ችግር እየደረሰበት እንደሆነ፣ በአፋር ክልል የሚገኘው አሌዲጊ አሰቦት ዕጩ ብሔራዊ ፓርክ በከፍተኛ ሁኔታ መጠለያው እየተጎዳና በክልሉ ለጥበቃ የማይመቹ አስተሳሰቦች እየተስተዋሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ ሰሎሞን በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ የዝሆኖች መራቢያና መዋለጃ ቦታ በሁለቱም ክልሎች በሕገወጦች መያዙን ጠቅሰው፣ ይህን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው የኦሮሚያና የሐረሪ ክልል ፕሬዚዳንቶች በተገኙበት በጉዳዩ ላይ ምክክር በማድረግ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትሯ ናሲሴ ጫሊ (አምባሳደር) በሰጡት ማብራሪያ፣ የዱር እንስሳት ጥበቃን በተመለከተ እንደ አገር መጠነ ሰፊ ችግሮች አሉብን ብለዋል፡፡ ሕገወጥ ሠፈራዎች፣ ሕገወጥ አደኖች፣ ሕገወጥ ኢንቨስትመንቶች፣ ሕገወጥ የግጦሽ ሥምሪት፣ ሕገወጥ የእርሻ ሥራ የወሰንና የእንስሳት ግጭትን የሚያስፋፉ ጉዳዮች እየሆኑ ስለመምጣታቸው ገልጸዋል፡፡

በአጎራባች ክልሎች መካከል ፉክክር በሚመስል ሁኔታ በአንደኛው ክልል የሆነ ክስተት ሲፈጠር፣ በዚያኛውም ክልል ተመሳሳይ ድርጊቶች እየተፈጠረ ፓርኮችን የህልውና ጥያቄ ውስጥ እያስገቡ ነው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...