Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እናቶች በደም እጥረት እየሞቱ መሆናቸው ተገለጸ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እናቶች በደም እጥረት እየሞቱ መሆናቸው ተገለጸ

ቀን:

  • በበጀት ዓመቱ በሁሉም ክልሎች የ5,716 ጨቅላ ሕፃናት ሞት መመዝገቡ ተመላክቷል

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ ሆስፒታሎች በሚያጋጥም የደም እጥረት ምክንያት እናቶች ለሞት እየተዳረጉ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

ይህ የተነገረው የጤና ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሐሙስ ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲያቀርብ ነው።

የቋሚ ኮሚቴው አባል ማኅተመ ኃይሌ (ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ የጤና ተቋማት ከፍተኛ የሆነ የደም እጥረት መኖሩን ገልጸው፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው እናቶች ለሞት እየተዳረጉ ነው ብለዋል። ‹‹በሪፈር የተላከ ታካሚ ደም እንደሌለው ታይቶ አንቀበልም እስከማለት የደረሱ ሆስፒታሎች ተመልክተናል፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

አዳዲስ የተቋቋሙ ክልሎችን ማጠናከር ይገባል ያሉት ማኅተመ (ዶ/ር)፣ በእነዚህ ክልሎች የሚገኙ የጤና ተቋማት ከአቅማቸው በላይ የሆነ ችግር እየተጋፈጡ እንደሚገኙ አብራርተዋል። በተለይም ሚዛን አማን ሆስፒታልና ቴፒ አጠቃላይ ሆስፒታል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እየሠሩ እንደሆነ ገልጸዋል።

የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በ2016 ዓ.ም. በመላ አገሪቱ 549 እናቶች ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለሞት መዳረጋቸውን፣ 5,716 ጨቅላ ሕፃናት ለሞት መዳረጋቸውን፣ ለዚህ የሞት መጠን መንስዔ የሆኑ ችግሮችን በመለየት መፍትሔ መስጠት ለምን አልተቻለም ሲል ጥያቄ አቅርቧል፡፡  

በተጨማሪም በአሥር ክልልና በአንድ ከተማ አስተዳደር በተከሰተ የኮሌራ ወረርሽኝ 366 ሰዎች መሞታቸውን፣ በተለይም በትግራይ፣ ቤንሻንጉልና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ከፍተኛ ሞት መመዝገቡ፣ በኩፍኝ ወረርሽኝ በሁሉም ክልሎች 321 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውንና በተመሳሳይ በወባ ወረርሽኝ 349 ሞት መመዝግቡ ተመላክቷል። በዚህም ወረርሽኞቹን ለመግታት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠይቋል።

የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሳይ ኃይሉ (ዶ/ር) ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፣ የጤና ተቋማት ሩቅ በመሆናቸው እናቶች ለወሊድ በጊዜ ወደ ተቋማቱ አለመምጣት ዋናው ምክትያት መሆኑን ገልጸዋል። ከወረርሽኞች ሥርጭት አንፃርም ከፍተኛ የሞት ምጣኔ የተመዘገበባቸው ክልሎች የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የመፀዳጃ ቤት አጠቃቀምና ሽፋን ዝቅተኛ እንደሆነ አመላክተዋል። ‹‹ወረርሽኞቹ እንዳይስፋፉ ከክልል እስከ ወረዳ በቅንጅት ለመሥራት ተሞክሯል። ለመከላከል ባይሞከር ኖሮ ከዚህ የከፋ ሊሆን ይችል ነበር፤›› ብለዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሲዝ የመጀመሪያ ደረጃ፣ ቴፒ ጄኔራል ሆስፒታልና ኩክ ጤና ኬላ የጤና መሠረተ ልማት ስላልተሟላላቸው ከፍተኛ የውኃ አቅርቦት ችግር እንዳለባቸው፣ ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ ተጀምረው የቆዩ የጤና ተቋማትን ለማጠናቀቀ ምን እየተሠራ ነው? ተብሎ ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሳ ጥያቄ የጤና ሚኒስትር ደኤታው አየለ ተሾመ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፣ 67 በመቶ የሚሆኑ የጤና ተቋማት የውኃ፣  76 በመቶ ያህሉ ደግሞ የኃይል አቅርቦት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመት 150 ጤና ጣቢያዎች የውኃ አቅርቦት እንዲኖራቸው እየተሠራ መሆኑን፣ በጨረታ ሒደቱ ላይ ባጋጠመ ችግር ግን ሃያ አምስቱን ብቻ ማጠናቀቅ እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡

የሕይወት አድንና የመሠረታዊ መድኃኒቶች አቅርቦት 73.5 በመቶ እንደሆነና የፍላጎትና የአቅርቦት ልዩነቱን ለመፍታት እየሠራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ፣ የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አብዱልቃድር ገልገሎ (ዶ/ር) ናቸው። ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት ከውጭ ተባዝተው ለሚመጡ መድኃኒቶች በዓመት 183 ሚሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ቢሆንም፣ ከመስከረም እስከ ጥር ባሉት ወራት የተገኘው ግን 15 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው ብለዋል። በተጨማሪም የተቋማት መድኃኒትን በብድር መግዛት ለተቋሙ ማነቆ እንደሆነበት ጠቁመዋል። በእነዚህ ምክንያቶችም የአቅርቦቱንና የፍላጎቱን መራራቅ ለማጥበብ አዳጋች እንዳደረገው ገልጸዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ከማኅበረሰብ ጤና መድን አባላት የተሰበሰበ ገንዘብ በጊዜ  ወደ ባንክ ከማስገባት አንፃር ክፍተቶች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ኦዲት በተደረጉ የጤና ተቋማት በኩል በኦዲት ግኝቱ መሠረት የተመለሰ ገንዘብ አፈጻጸም ከ50 በመቶ በታች መሆኑ ጥያቄ አስነስቷል።

ይህንን አስመልክቶም የጤና መድን አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ያምሮት አንዷለም በሰጡት ምላሽ፣ አገልግሎቱ ያለበት ኃላፊነት የአባልነት መዋጮ እንዲሰበሰብ እንጂ፣ ገንዘቡን በዋናነት የሚሰበስቡት የክልል መንግሥታት ናቸው ብለዋል። ‹‹ገንዘቡን ሰብስቦ ባንክ እንዲገባ የማድረግ ኃላፊነት የክልል መንግሥታት ነው። እኛ የምንረከበው ተሰብስቦ ባንክ ከገባ በኋላ ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሮ ወርቀሰሙ ማሞ፣ ሚኒስቴሩ ከተጠሪ ተቋማት ጋር በጋራ መሥራቱ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል። ሆስፒታሎች አክሞ የማዳን አቅማቸው ሊጎለብት እንደሚገባ፣ በእናቶችና በጨቅላ ሕፃናት ሞት ላይ ከአምናው አንፃር የታየው ጭማሪ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል በማለት አሳስበዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...