Friday, May 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ካልቀየረ መንግሥት ተመጣጣኝ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ካልቀየረ መንግሥት ተመጣጣኝ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

ቀን:

የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ከሳምንት በፊት ለኢትዮጵያውያን የሚደረገውን የቪዛ አሰጣጥ ሒደት ለማጥበቅ ያሳለፈውን ውሳኔ ካልቀየረ፣ መንግሥት ተመጣጣኝ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ አስታወቀ፡፡

የአውሮፓ ኅብረት በቪዛ ጉዳይ በቅርቡ ያሳለፈውን ውሳኔ እንዲሽር ኢትዮጵያ እንደምትፈልግ ጠቅሰው፣ ይህ ካልሆነ ግን ከውሳኔው ጋር የሚጣጣም የራሷን ተመጣጣኝ ዕርምጃ ትወስዳለች ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ ናቸው፡፡

ቃል አቀባዩ በሳምንታዊ መግለጫቸው የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈው የቪዛ ውሳኔ ትክክል እንዳልሆነ በመግለጽ፣ ኢትዮጵያ ለኅብረቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን በጠበቀ መንገድ ማሳወቋን አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

ኅብረቱ ወደ አውሮፓ የገቡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው በመመለሱ ረገድ ለኢትዮጵያ መንግሥት ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ቢያቀርብም፣ ባለሥልጣናት ተገቢውን ምላሽ ባለመስጠታቸው በኢትዮጵያውያን ላይ የቪዛ አሰጣጥ አሠራሩን ማጥበቁን በማስታወቅ ነበር ውሳኔውን ያስተላለፈው፡፡

በአውሮፓ ኅብረት በተለይም ‹‹ሸንገን ቪዛ›› ውስጥ በሚገኙ አገሮች ጥገኝነት የጠየቁ ኢትዮጵያውያን ጉዳያቸው የመኖሪያ ፈቃድ የማያሰጥ ሆኖ ሲገኝ፣ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ታይቶ ወደ አገራቸው መመለስ አለባቸው የሚባሉትን ኢትዮጵያ እንድትወስድ በመጠየቁ ምክንያት ውሳኔው መተላለፉን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ከኅብረቱ ጋር እየሠራ የቆየ መሆኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ ውሳኔው በበርካታ ሚዲያዎች እንደተዘገበው የቪዛ ክልከላ አይደለም ብለዋል፡፡

በመሆኑም ማንኛውንም መሥፈርት የሚያሟላ ግለሰብ ቪዛ ማመልከትና ማግኘት እንደሚችል፣ ነገር ግን ከዚህ ቀደም ለቪዛ ማመልከቻ ይሰጥ የነበረው 15 ቀናት ወደ 45 ቀናት፣ እንዲሁም ወደ ኅብረቱ አባል አገሮች በተደጋጋሚ እንዲገቡ ይፈቅድ የነበረውን የቪዛ አሰጣጥ ለአንድ ጊዜ ብቻ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ በኅብረቱ በኩል ከቪዛ ጋር በተገናኘ የተወሰዱ ዕርምጃዎች ተገቢ እንዳልሆኑ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ኅብረቱ አባል አገሮች የገቡ ዜጎቿን በተለይ በገቡበት አገር መኖር እንደማይችሉ በፍርድ ቤት ተወስኖ ሒደቱ ካለቀ በኋላ፣ መመለስ ያለባቸው ዜጎች ክብራቸውንና ደኅንነታቸውን በጠበቀ መንገድና ዓለም አቀፍ ተሞክሮን ብቻ ተመርኩዞ መከናወን አለበት የሚል አቋም እንዳላትም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያውያንን ከአውሮፓ አገሮች የማስመለስ ሥራ እንዲያከናውን የተቋቋመ ብሔራዊ ኮሚቴ መሥራት ስለሚቻልበት ከኅብረቱ ጋር ሲመክር መቆየቱን፣ ዜጎችን በማስመለሱ ሒደት በሁለት ዙር ከአውሮፓ ኅብረት አመራሮችና አባላት ጋር ውይይት አድርጎ መመለሱን ተናግረዋል፡፡

 ከውይይቱ በኋላ የግለሰቦችን ዜግነት በተመለከተ አስፈላጊው ማጣራት የሚያደርገው ብሔራዊ ኮሚቴ በኖርዌይ፣ በስዊድን፣ በፊላንድ፣ በስዊዘርላንድና በኔዘርላንድስ የማጣራት ተግባራት አከናውኖ መመለሱም ተገልጿል፡፡

ኮሚቴው ከጥገኝነት ጠያቂዎች ውስጥ ኢትዮጵያዊ ናቸው ተብለው በኅብረቱ ከተለዩ ተመላሽ ግለሰቦች መካከል ማጣራት ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም፣ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በሕገወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ የሚገቡ ሰዎች ተመሳሳይ የሆነ ባህል፣ ቋንቋና ሃይማኖት ጭምር የሚጋሩ በመሆናቸው፣ ዜግነታቸውን ለማጣራት ጊዜ የሚወስድና ጥንቃቄ የሚጠይቅ መሆኑን አቶ ነብዩ ተናግረዋል፡፡

በአውሮፓ ኅብረት በኩል ኢትዮጵያውያን ናቸው ተብለው የተለዩና ወደ አገራቸው ይመለሱ ተብለው የቀረቡ 89 ሰዎች ቢኖሩም፣ ከእነሱ ውስጥ ኢትዮጵያውያኑ 26 ብቻ  መሆናቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ እነዚህም መካካል አምስት ከስዊድን፣ አምስት ከኖርዌይ፣ ስምንት ከስዊዘርላንድ፣ ስድስት ከኔዘርላንድስና ሁለት ከፊላንድ ይገኙበታል ሲሉም አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን የመሆናቸውን ጉዳይ የማጣራት ሥራ አዳጋች በመሆኑ፣ ማጣራት ከተደረገ ወዲህ እስካሁን ከአውሮፓ 15 ዜጎች ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ መደረጉም ተነግሯል፡፡

ሥራው በዚህ መልኩ እየተከናወነ ባለበት ወቅት ኅብረቱ የወሰደው ዕርምጃ፣ በተለይም የኢትዮጵያ መንግሥት ፈጣን ትብብር አላሳየም በሚል ምክንያት የተደረሰበት ውሳኔ ግን ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኅብረቱ እንደሚለው በኢትዮጵያ በኩል መታየት ያለባቸው ክፍተቶችና ጉዳዮች ካሉ በትክክለኛው የመግባቢያ መንገድ እንደሚታይ ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ካላቸው ጠንካራ አጋርነት አኳያ ይህ ዓይነት አካሄድ ጊዜውን ይመጥናል ተብሎ አይታሰብም ብለዋል፡፡

በሕገወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ የተሻገሩና በአገሪቱ መኖር ያልቻሉ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለመመለስ፣ ኢትዮጵያ ኃላፊነት በተሞላበትና ዓለም አቀፍ አሠራሩን ተከትላ እንደምትሠራ አስረድተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ