Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለውጭ ተቋማት ክፍት የተደረገው የፋይናንስ ዘርፍና የኢትዮጵያ ባንኮች ሥጋት

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ኩባንያዎች እንዲከፈት መንግሥት ውሳኔ ያሳለፈና ለተግባራዊነቱም እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም አሁንም የውጭ ኩባንያዎች በዚህ ዘርፍ መግባታቸው ቢዘገይ መልካም ነው የሚሉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ ላይ ይኸው ሐሳብ የተንፀባረቀ ሲሆን፣ መንግሥት ግን ውሳኔውን እንዳፀና መሆኑ ታውቋል፡፡ በውጭ ባንኮች መግባት ዙሪያ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፈቀዱ ላይ ተቃውሞ ባይኖራቸውም፣ የሚገቡበት ጊዜ ቢራዘም የተሻለ ይሆናል በማለት ሐሳባቸውን በዚሁ ጉባዔ ላይ ሲያንፀባረቁ ተሰምቷል፡፡

በሰባተኛው ዓመታዊ የምሥራቅ አፍሪካ ፋይናንስ ጉባዔ ላይ ለመወያየት በአጀንዳ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል አንደኛው ይኸው የውጭ ባንኮች ወደ ገበያው መቀላቀል፣ ‹‹በኢትዮጵያ ባንካች ላይ የሚኖረው መልካም አጋጣሚ ወይስ ተግዳሮት›› በሚል ርዕስ በተደረገ ውይይት ላይ ያልተጠበቁ አስተያየቶች የተሰነዘሩበት ሆኗል፡፡ አብዛኛው የመድረኩ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ በሯን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ማድረጓ ተገቢ መሆኑን የሚያምኑ ቢሆንም፣ አሁን ባለው ሁኔታ እንዲገቡ የሚፈቀድ ከሆነ ሊያስከትል የሚችለውንም ጫና በተለያዩ መንገዶች በመድረኩ ሲገለጽ ተሰምቷል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ የውጭ ባንኮች መግባት ላይ ቢስማሙም፣ የአገር ውስጥ ባንኮች የዝግጅት ጊዜ ያስፈልጋቸዋል የሚለውን አቋም አንፀባርቀዋል፡፡

የአገሪቱ ባንኮች ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች አንፃር ሲታይ በተለይ በካፒታል አቅማቸው ዝቅተኛ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አቤ፣ የእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ባንኮች ካፒታል በዶላር ሲመነዘር የሚኖራቸው የካፒታል መጠን ዝቅተኛ እንደሆነ በቀላሉ መረዳት እንደሚቻልም ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ምናልባት የምንዛሪ ለውጥ ቢደረግ ደግሞ የእነዚህ ባንኮች ካፒታል ከዶላር አንፃር ካፒታላቸው ይመዘን ቢባል የበለጠ የካፒታል አቅማቸው የሚያዘቀዝቅ በመሆኑ፣ ባንኮች ካፒታላቸውን ለማሳደግም ቢሆን ጊዜ ያስፈልጋቸዋል የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡

የውጭ ባንኮች መግባት አይቀሬ መሆኑ ቢታወቅም ከገቡ በኋላ ሊኖር ስለሚችለው ተፅዕኖ በተመለከተ በመድረኩ ከዋና ሥራ አሰፈጻሚ ዕይታ አንፃር አስተያየታቸውን የሰጡ የወጋገን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አክሊሉ ውበት (ዶ/ር)፣ የውጭ ባንኮች መግባት ጠቃሚ ቢሆንም ተፅዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉበት ዕድል እንዳለ አመልክተዋል፡፡ የውጭ ባንኮች አሁን ባለው ሁኔታ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ደንበኞችን ብሎም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና መሰል ተቋማትን ትኩረት ሊያደርጉባቸው እንደሚችሉም ጠቅሰዋል፡፡ ይህንኑም ተከትሎ አሁን በአገር ውስጥ ባንኮች አገልግሎት እያገኙ እያገኙ ያሉት ደንበኞች ወደ እነዚህ የውጭ ባንኮች ቢሄዱ የአገር ውስጥ ባንኮች ችግር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ የሚለውን ሥጋታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን ሊመጡ የሚችሉትን ባንኮች ታሳቢ በማድረግ ስትራቴጂክ በሆነ መልክ ማሰብና በተለይም ሰፊውን ያልተሳካ ገበያ በመካከለኛና አነስተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ያሉትን የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠራ ዕድል ሊሰጥ እንደሚችል አክሊሉ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

በእነዚህ ርዕስ ላይ ተጨማሪ ሐሳብ የሰነዘሩት አቶ አቤ፣ አሁን ያለውን የባንካች ዝግጅት፣ የሕግ ማዕቀፉን በግልጽ ከባንኮች የሚጠበቀውን ሁኔታ ከማስቀመጥ አንፃር የሚቀር ነገር እንዳለ አመልክተዋል፡፡ ተቆጣጣሪው አካል ወደፊት የሚኖረውን አቅጣጫ በግልጽ ቢያመለክት የተሻለ ስለመሆኑም የገለጹት አቶ አቤ፣ ተወዳዳሪ የሆነ የፋይናነስ ተቋማት እንዲኖሩ ግን አሁንም ሊሠሩ የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉም ያምናሉ፡፡

ከሰው ኃይል ጋር በተያያዘም አቶ አቤ እና አክሊሉ (ዶ/ር) ተመሳሳይ ሥጋት ያንፀባረቁ ሲሆን፣ የውጭ ባንኮች ወደ ገበያው ሲገቡ አሁን ያሉ ብቁ የሚባሉ ሠራተኞች ወደ እነዚህ ባንኮች ሊፈልሱ እንደሚችሉ በመጥቀስ፣ ይህንም ጉዳይ የሚያሳስብ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡  

የውጭ ባንኮች በተፈቀዱ የባንክ የሥራ ዘርፎች በሰው ኃይል ብቃት ረገድ ያለው ክፍተት ጠንካራ የአገር ውስጥ ባንኮች አስቀድመው መኖራቸው አስፈላጊ መሆንን የገለጹት አቶ አቤ፣ ለዚህ ደግሞ Merger & Acquisition ሊኖር እንደሚገባ ጠንከር ባለመንገድ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ጉዳዩ አሁንም በርካታ የባንክ ባለሙያዎችን እያወያየን ሲሆን፣ ጠንካራና ተወዳዳሪ የሚሆን የፋይናንስ ተቋማት እንዲኖሩ ለማድረግ ብዙዎችን እየገዛ ያለው ሐሳብ በሁሉም የፋይናንስ ዘርፍ ያሉ ተቋማት በውህደት ጠንካራ ተቋም መፍጠር አለባቸው የሚለው ነው፡፡

በዚህ ውይይት መደምደሚያ ላይ መቋጫ ባይሰጥም ጉዳዩ እንደገና አነጋጋሪ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

በፋይናንስ ዘርፉ አማካሪ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ሲሳይ በበኩላቸው በዕለቱ በሰጡት አስተያየት፣ የውጭ ባንኮች መግባት አይቀሬ መሆኑን በመጠቆም፣ የአገር ውስጥ ባንኮች ራሳቸውን መገምገምና መገመት እንደሚገባቸው፣ ብሎም የውህደትን (Merger & Acquisition) ስትራቴጂ ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ በመጥቀስ አብሮ ስለመሥራት ማሰብ እንደሚኖርባቸው በመግለጽ የአቶ አቤን ሐሳብ አጠናክረዋል፡፡

የአይ አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር) ደግሞ፣ የአገራችን የፋይናንስ ተቋማት አብዛኛዎቹ ከአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማት አንፃር ሲታዩ ገና ብዙ የሚቀራቸው መሆኑን አልሸሸጉም በኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራና ተወዳዳሪ የፋይናንስ ተቋም እንዲኖር ከተፈለገ እንዱና ቀዳሚው አማራጭ ውህደት በመሆኑ ተቋማቱ በዚህ ዙሪያ ብዙ ሥራ ሊሠሩ የሚገባ ስለመሆኑ በመጥቀስ የአቶ አቤን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ ይሁን እንጂ የውጭ ባንኮች ሳይገቡ እንዲቆዩና ጊዜ ይሰጥ በሚል የተሰነዘሩ ሐሳቦችን እንደማይጋሩ አመልክተዋል፡፡ እየመጣ ላለው ውድድር አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ከሚያስፈልጉ ወሳኝ ጉዳዮች መካከል ካፒታላቸውን ማሳደግ፣ የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ማዘመን፣ የደንብኞቻቸውን ቁጥር ማሳደግና የመሳሰሉት በመሆኑን የገለጹት ገመቹ (ዶ/ር) እነዚህን ወሳኝ ጉዳዮች አሟልተው ለመገኘት በውህደት ቀዳሚ አማራጭ ስለመሆኑ ለሪፖርተር  ከሰጡት ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ አቶ አቤ በውህደት ዙሪያ በሰጡ ተጨማሪ ማብራሪያ አሁን ያሉት ትናንሽ ካፒታል ያላቸው በርካታ ባንኮችን ይዞ መወዳደር የማይቻል ከመሆኑም በላይ ጠንካራ የፋይናነስ ተቋም ለመፍጠር በውህደት አራትና አምስት ባንኮች መፍጠር ቢቻል የበለጠ ጠቃሚ ስለመሆኑም ጠቆም አድርገዋል፡፡ ትናንሽ ተቋማትን ይዘን የትም አንደርስም ያሉት ገመቹ (ዶ/ር) ጉዳዩ ሊታሰብበት ይገባልም ይላሉ፡፡

የውጭ ባንኮች መግባትና አለመግባት ላይ መከራከሩ ብዥታ የፈጠረባቸው አንድ አስተያየት ሰጪ ደግሞ አሁን ያለው አማራጭ ተባብሮ መሥራት ነው፡፡ ይዘግዩ ትንሽ ይቆዩ የሚለው ጉዳይ የሚሠራ የማይመስላቸው መሆኑን ገልጸው፣ አሁን ላይ አንዳንድ የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሮ እየከፈቱ መሆኑ በራሱ እየገቡ ስለመሆኑ ያመለክታል ይላሉ፡፡ በሌላ በኩልም የባንክ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ሳፋሪኮም ኤምፒሳ ገብቶ ሥራ የጀመረ በመሆኑ፣ የውጭ ፋይናንስ አልገቡም ማለት አይቻልም በማለት  የራሳቸውን ምልከታ አንፀባርቀዋል፡፡

በዚህ የምሥራቅ አፍሪካን የፋይናንስ ጉባዔን በይፋ የከፈቱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ ግን፣ መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት ተግባራዊ ከሚያደርጋቸው ስትራቴጂዎች መካከል አንዱ የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ማድረግ የሚለውን አፅዕኖት ሰጥተዋል፡፡ በቅርቡም ተግባራዊ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

ዘርፉን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ማድረግ የሚሰጠውን ጠቀሜታ በተመለከተ እንዳብራሩትም የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት መደረጉ ፈጠራንና ውድድርን በማፋጠን መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ጭምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለማሳደግ መንግሥት የወሰደው የፖሊሲ ለውጥ የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ገበያው ገብተው እንዲሠሩ በማድረግ ተጨማሪና አዲስ ካፒታል ለማምጣት ጭምር የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርጥ የሚባሉ ተሞክሮዎችን ለማምጣት የሚያግዝ ስለመሆኑም በዚሁ ንግግራቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ የውጭ የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ እንዲገቡ በሯን ከመክፈቷ ባሻገር የካፒታል ገበያ በማቋቋም ላይ መሆኗንም የጠቀሱት አቶ ማሞ፣ ይህ ገበያ በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ወደ ሥራ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

ይህም የኢንቨስትመንት ባንክ፣ የአማካሪ ድርጅቶችን በማካተት በአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ እንዲከፈትና የፋይናንስ ዘርፍ ተደራሽነት እንዲሰፋ የሚያደርግ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለውጭ የፋይናንስ ተቋማት በሯን ለመክፈት ከወሰደችው የፖሊሲ ዕርምጃ ሌላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ዘርፉን ለማሳደግ እየወሰዳቸው ያሉትን የሪፎርም ሥራዎች አመላክተዋል፡፡

በተለይ የተረጋጋ የፋይናንስ ዘርፍ እንዲኖር እየተሠሩ ነው ያሏቸውን ሥራዎች በዝርዝር ያቀረቡት አቶ ማሞ፣ በተለይ በዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎትና አካታች የፋይናንስ ሥርዓትን ለመፍጠር እየተሄደበት ነው ያሉትን ሥራዎችም ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ያሉበትን ደረጃ በተመለከተም በፋይናንስ ተደራሽነት፣ በሀብት በተቀማጭ ገንዘብና በመሳሰሉት አፈጻጸሞች ዕድገት እየተመዘገበ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ይህንንም በአኃዛዊ መረጃ ደግፈው ያቀረቡ ሲሆን፣ እስከ ጥር 2016 ዓ.ም. መጀመርያ ድረስ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፋይናንስ ተቋማት ቁጥር 121 ደርሷል፡፡

እነዚህ የፋይናንስ ተቋመት አጠቃላይ የሀብት መጠናቸው 3.4 ትሪሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብም 2.4 ትሪሊዮን ብር መድረሱን የገለጹት አቶ ማሞ፣ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጡት ብድር ክምችት 2.3 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

  ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ በተለይ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱ የተለያዩ መነሻ የውይይት ጽሑፎች በተለያዩ ባለሙያዎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ስለመሆኑ ታውቋል፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ በተለይ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱ የተለያዩ መነሻ የውይይት ጽሑፎች በተለያዩ ባለሙያዎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ስለመሆኑ ታውቋል፡፡

የዘንድሮው ጉባዔ በዋናነት አጀንዳ ሆኖ እንዲመከርበት የተፈለገው ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፋይናንስ ዘርፍ ትልልቅ ለውጦች እየታዩ በመሆኑ ይህ ለውጥ ይዞ የሚመጣውን ዕድልና ተግዳሮት ላይ መምከር ነው፡፡ በተለይ ከዚህ ለውጥ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ከዚህ ለውጥና ገፊ ጉዳዮ መካከል ያለውን መልካም ዕድል እንዴት እንጠቀም የሚለው ላይ ያተኮረ እንደነበረም ገመቹ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች