Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ከወረቀት ሥራ ተላቆ ዲጂታላይዝድ የሚሆነው መቼ ነው?

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የአገልግሎት ክፍተት ካለባቸው ዘርፎች መካከል የሎጂስቲክና የትራንስፖርት ዘርፍ  ተጠቃሽ ነው፡፡ ደካማ የሎጂስቲክና የትራንስፖርት አገልግሎት አለባቸው ከሚባሉ አገሮች መካከል አገራችን አንዷ ተጠቃሽ ናት፡፡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ውጭ በአብዛኛው የሎጂስቲክና የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ሊባል የሚችል ችግር ስላለ እምብዛም መሻሻል አይታይበትም፡፡ በዘርፉ ላይ ለሚታየው ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ ቢጠቀስም በተለይ አገልግሎቱን ከማዘመን አንፃር ያለው ክፍተት በቀዳሚነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስን የተመለከቱ በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ በግልጽ የሚታየው የአገልግሎት አሰጣጥ ኋላ ቀርነትና ከብቃት ጋር የተያያዙ ችግሮችም ዘርፉን እንዳያድግ አድርጎታል ማለት ይቻላል፡፡

በአንድ አገር ኢኮኖሚ ውስጥ ወሳኝ የሆነ ሚና አለው የሚባለው ይህ ዘርፍ ጥርት ያለ ፖሊሲ የሌለው መሆንና የአገልግሎት አሰጣጡም ቢሆን ለሌብነት በር የሚከፍት ሆኖ መገኘቱ ተገልጋዮችን በአግባቡ እንዳይስተናገዱ ከማድረጉ በላይ የአገር ኢኮኖሚ ላይ ሁሉ ተፅዕኖ እያሳረፈ ነው፡፡

የወጪና ገቢ ንግድ በአግባቡ እንዳይቀላጠፍ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክ ወጪዎች ዋጋቸው የተመጣጠነና ፍትሐዊ እንዳይሆን አንዳንድ ምክንያት ሲጠቀስ የሚሰማው በዘርፉ ዙሪያ የሚሰጡ አገልግሎቶች ደካማ ሆኖ መገኘት ጭምር ነው፡፡

የወጪና ገቢ ንግድን የሚያጓጉዙ አሽከርካሪዎች ከወደብ ዕቃ ለመጫንና ጭነው ለመመለስ ያለባቸው አበሳ እንደ ዋዛ ይታለፋል እንጂ ችሮታቸው ሥር እየሰደደ እንዲሄድ ይኸው ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ያለው ችግር አንዱ ነው፡፡ 

ጉዳዩን እጅግ አነስተኛ በሆነ ምሳሌ እንግለጽ ከተባለም አንድ ወደ ጂቡቲ የገቢ ዕቃ በመጫን ፈቃድ ያገኘ ተሽከርካሪ ወደ ጂቡቲ ለመግባት አሽከርካሪው የግድ መያዝ ያለበትን ፈቃድ ለማግኘት የሚያጠፋውን ጊዜ ነው፡፡ ይህ በየአራት ወሩ መታደስ ያለበት የአሽከርካሪዎች የጂቡቲ መግቢያ ፈቃድ ለማግኘት ወይም ለማደስ ቀኑን ሙሉ ሊጠበቅ ይችላል፡፡ ቀናት ሊወስድ የሚችልበት አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ይህ ማለት ወደ ጂቡቲ መግቢያ አንድ ተራ ወረቀት ለመስጠት የሚወስደው ጊዜ ወደ ወደብ መጫን ያለበት ዕቃ ወይም ከወደብ ወደ መሀል አገር መጓጓዝ ያለበት ምርት ለቀናት እንዲዘገይ አደረገ ማለት ነው፡፡ በዚህ ላይ የፈቃዱ ዕድሳት በየአራት ወሩ መሆን በራሱ አሰልቺ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም እንዲህ ያለው አገልግሎት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ያልታገዘና ወረቀትን መሠረት አድርጎ የሚሠራ መሆኑ የአገልግሎት አሰጣጡን የበለጠ አማራሪ እያደረገው ነው፡፡ ዲጂታላይዜሽን በተስፈፋበት በዚህ ወቅት በወረቀት ላይ የተመሠረቱ ሥራዎች የሚበዙበት ዘርፍም እንደሆነ ተገልጋዮች በምሬት ሲናገሩ ይሰማል፡፡

ከመነሻው ገቢ ንግድ ምርቶችን ለማጓጓዝ ተሽከርካሪን ለማንቀሳቀስ ቢሮክራሲ በበዛበት የአገልግሎት አሰጣጥ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ችግር ሳይፈታ ሌላውን የዘርፉን ችግር ማስተካከል አይችልም፡፡

ስለዚህ የአገራችን የትራንስፖርትና የሎጂስቲክ አገልግሎትን እጅግ ውድ ከሚያደርጉ ጉዳዮች አንዱ ዘርፉን በተመለከተ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ተቋማት ውስጥ ያሉ ቀልጣፋና በዘመናዊ መንገድ አገልግሎት እንዲሰጡ ያለመደራጀታቸው ነው ማለት ይቻላል፡፡

ጊዜ ገንዘብ በሆነበት በዚህ ወቅት ምርትን በቶሎ ወደብ ማድረስና በቶሎ ከወደብ ዕቃን ለማንሳት የማይቻለውም የችግሩን ምንጭ ዓይቶ መፍትሔ ሊወሰድ ባለመቻሉ ጭምር ነው፡፡

በየጊዜው በወደብ ወይም በደረቅ ወደብ ያሉ ምርቶች በወቅቱ ከማይነሳባቸው ምክንያቶች አንዱ ከትራንስፖርት የሎጂስቲክ አገልግሎቶች ጋር የተያያዙ አሠራሮችን መስተካከል አለመቻሉ ነው፡፡

ዘርፉን የሚመሩ ተቋማት የወጪና ገቢ ንግድ እንዲቀላጠፍ የሚያስችል አሠራር ያለመዘርጋታቸው ደግሞ ሄዶ ሄዶ የወጪ ንግድ ምርት ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ይረዳል፡፡ በተመሳሳይም በወቅቱ ከወደብ ተነስተው ወደ መሀል አገር መግባት ያለባቸው ምርቶች እንዳይነሱ የሚፈጠሩ መሰነካከሎች እንዲሁም በወደብ ላይ ያለአግባብ ለሚቆዩ ዕቃዎች የሚከፈለው ወደብ አከራይና ሌሎች ወጪዎች ተደማምረው ሸክሙ እንዲያርፍ የሚደረገው ሸማቹ ላይ ነው፡፡ የአገልግሎት አሰጣጥ አለመቀላጠፍና አለመዘመን ጉዳቱ አገልግሎት የሚሰጡ የትራንስፖርት ድርጅቶች ላይ ብቻ የሚቀር ሳይሆን አገራዊ ኢኮኖሚ ላይም ተፅዕኖ እያሳረፈ ነው፡፡

በተለይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በቶሎ አጓጉዞ ወደ መሀል አገር ባለማድረስ ብቻ የሚፈጠር መዘግየት የሚያስከፍለው ተጨማሪ ዋጋ ሸማቹ ላይ እየተቆለለ እንዳይቀጥል ከተፈለገ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉ ራሱን ሊፈትሽ ይገባል፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት የምትሰቃይ አገር በፍጥነት አገልግሎት የሚሰጥበትን አሠራር ባለመዘርጋቷ ብቻ ያለአግባብ በቶሎ ላልተነሱ ዕቃዎች በውጭ ምንዛሪ ያልተገባ ኪራይ ስትከፍል መመልከትም ተገቢ አይሆንም፡፡ ወጪ እንዲሸከም የሚደረገው ሸማቹ ነው፡፡ ጉዳዩን ጠለቅ ብለን ከተመለከትነው የአገራችን የሎጂስቲክና የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ እጅግ ደካማ ሆኖ መገኘቱ ለዋጋ ንረቱ መባባስ አንድ ምክንያት ነው፡፡

ስለዚህ የአገሪቱ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት እያስከፈለ ያለውን ዋጋ በመገንዘብ አጠቃላይ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል አጠቃላይ ፖሊሲው ደግሞ ሊፈተሽ ይገባል፡፡ ዘርፉን የሚመሩ መንግሥታዊ ተቋማትም ሆኑ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎች በየድርሻው የአገልግሎት አሰጣጣቸው የሚያሻሽሉበትን ብቻ ሳይሆን ተጠያቂ የሚሆኑበትም አሠራርን ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት