Wednesday, June 12, 2024

የሱዳንን ጦርነት ከጀርባ ሆነው የሚያፋፍሙ አገሮችና የጦርነቱ ድንበር ተሻጋሪ ገፅታዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሱዳን የተቀሰቀሰው ጦርነት ለአንድ ዓመት የአስከፊነት መጠኑን ሳይቀንስ በአስፈሪ ሁኔታ ተባብሶ እንደቀጠለ ነው። እ.ኤ.አ. ከኤፕሪል 2023 ጀምሮ የተከሰተው ውድመት አገሪቱን ወደ መበታተን አፋፍ አድርሷታል። በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከሚስተዋሉ የመፈናቀል ቀውሶች አንፃር ሱዳን ግንባር ቀደሟ ሆናለች። ወደ 6.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሱዳናዊያን ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፣ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉት ደግሞ ወደ ጎረቤት አገሮች፣ አብዛኞቹ ወደ ቻድ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ተሰደዋል።

በሌተና ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሀን የሚመራው የሱዳን ብሔራዊ የጦር ኃይል (SAF) እና በመሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ በመባል በሚታወቁት) የሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) መካከል የተፈጠረው የለየለት ጦርነት መነሻ በከፊል የሥልጣንና የሀብት ፉክክር እንደሆነ ይነገራል። ይሁን እንጂ ይህ ጦርነት አሁን ላይ መልኩን ቀይሮ በፍጥነት ወደ ብሔር ግጭትነት እየተሸጋገረ ነው። በጦርነቱ ምክንያትም ሱዳን ወደ ለየለት መከፋፈል ውስጥ ገብታለች።

እ.ኤ.አ. እስከ ማርች 2024 አጋማሽ ድረስ አርኤስኤፍ አብዛኛውን ዋና ከተማ ካርቱምንና የአገሪቱን ምዕራባዊ ክፍል ተቆጣጥሮ በመሃል ላይ አሻራውን አስፍቷል። SAF በበኩሉ ምሥራቃዊና ሰሜን ምሥራቅን ይቆጣጠር ነበር። በጥር ወር መገባደጃ ላይ በጀመረው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ፣ ኤስኤኤፍ አሁን የኦምዱርማንን መንትያ ከተማ ካርቱምን በከፊል በመቆጣጠር በመካከለኛው ሱዳን በተለይም በኤል ጌዚራ ክፍለ አገር የግዛቱን ዋና ከተማ ዋድ ማዳኒ ጨምሮ የRSF ግስጋሴን ለመቀልበስ እየገፋ ነው።

አሁን ባለው የሱዳን ሁኔታ የሱዳኑ ጦርነት ከሱዳን ድንበር የማይሻገር ወይም በሱዳን ብቻ ተወስኖ ከመሆን እየራቀ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ሱዳን ከምትገኝበት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ጋር ይያያዛል። ሱዳን ከአራት ዓለም አቀፍ ቀጣናዎች ጋር ማለትም፣ ከአፍሪካ ቀንድ፣ ከሰሜን አፍሪካ፣ ከሳህልና ከባህረ ሰላጤው ዓለም አቀፍ ቀጣናዎች ጋር ድንበሮችን የምትጋራ ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ የተቀመጠች ቁልፍ አገር ናት።

በዚህም ምክንያት ከሱዳን ጦርነት ጀርባ በርካታ የውጭ ኃይሎች የጦር መሳሪያ ድጋፍ በማደረግ ጦርነቱን የበለጠ እያቀጣጠሉት ይገኛሉ። ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎችም ለጦርነቱ በርካታ ሰላማዊ ሱዳናዊያንን በመመልመል የማሰባሰብ ተግባር ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እየተሳተፉ መሆናቸው ሲታከልበት ደግሞ ጦርነቱን የበለጠ አስፈሪ አድርጎታል።

ከሱዳን ጦርነት ጀርባ የተገኙ አገሮች

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወደ ሱዳንና አጎራባች አገሮች ያሰማራው ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን በሱዳን ጦርነት ውስጥ ከጀርባ ሆነው እየተሳተፉ የሚገኙ አገሮችና ቡድናችን ባለፈው ጥር ወር ባቀረበው የምርመራ ሪፖርት ይፋ አድረጓል።

የባለሙያዎች ቡድኑ መረጃ እንደሚያመለክተው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የጦር መሳሪያ አቅርቦት የሚያገኝባቸውና እስካሁን ድረስ ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙ ሦስት ዋና ዋና መንገዶች አሉ። ዋናው በምሥራቅ ቻድ በኩል መሆኑን ያመለከተው የቡድኑ የምርመራ ሪፖርት፣ የተለያዩ የአየር በረራ ክትትል ባለሙያዎች እንዳረጋገጡትም ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ ከዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትሱ አቡ ዳቢ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተነስተው ወደ ምሥራቃዊው ቻድ አም ድጃራስ አውሮፕላን ማረፊያ የሚያጓጉዙ የጭነት አውሮፕላኖች መኖራቸውን ገልጿል። እነዚህ የጭነት አውሮፕላኖች በምሥራቅ ቻድ አም ድጃራስ አየር ማረፊያ ከመድረሳቸው በፊትም እንደ ኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ባሉ አገሮች ለምን እንደሆነ ያልታወቀ መጠነኛ ቆይታ እንደሚያደርጉ ገልጿል። 

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ግን ይህንን ውንጀላ ያስተባበለች ሲሆን፣ በረራዎቹ መደረጋቸውን፣ ዓላማውም ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ እንደሆነና ጭነቱም ለሱዳናውያን ስደተኞች የመስክ ሆስፒታል ለማቋቋም የሚውሉ ቁሳቁሶች መሆናቸውን ገልጻለች።

የባለሙያዎች ቡድኑ ግን በቻድና በዳርፉር ከሚገኙ ምንጮች ያሰባሰበውን መረጃ መሠረት በማድረግ ዩናይትድ ኤምሬትስ የተነሱት የጭነት አውሮፕላኖች ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የጦር መሣሪያ የሚያጓጉዙ መሆናቸው እንዳረጋገጠ ገልጿል።

የባለሙያዎች ቡድኑ በቻድና በዳርፉር የሚገኙ በርካታ ምንጮች፣ የአካባቢው ተወላጆችና አስተዳደራዊ መሪዎችና በእነዚያ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች፣ የጦር መሣሪያዎችንና ጥይቶችን የጫኑ አውሮፕላኖች በሳምንት ብዙ ጊዜ በምሥራቃዊ ቻድ አም ድጃራስ አየር ማረፊያ እንደሚያርፉ፣ ከዚያም የመጣው የጦር መሣሪያ በጭነት ተሽከርካሪዎች ተጭኖ ከአየር ማረፊያው በምዕራብ በር በኩል ወደ ዳርፉር ድንበር እንደሚጓዝ እንደነገሩት በሪፖርቱ ዘርዝሮ አቅርቧል።

በምሥራቃዊ ቻድ ኮሪደርም መጠነ ሰፊና ቀጣይነት ያለው የጦር መሣሪያ አቅርቦት እንደሚደረግ በዚህም ቀላልና ትናንሽ የጦር መሣሪያዎችን ጨምሮ እስከ ሰው አልባ ተዋጊ የአየር ተሽከርካሪዎች (ድሮኖች)፣ ፀረ አውሮፕላን ሚሳኤሎች፣ ሞርታርና ልዩ ልዩ ጥይቶች ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እየደረሰ መሆኑን አረጋግጧል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የጦር መሣሪያ አቅርቦት የሚያገኝበት ሌላኛው ቁልፍ መስመር ደቡብ ሊቢያ ሲሆን በዚህም በኩል ከጦር መሣሪያ በተጨማሪ ከፍተኛ የነዳጅ አቅርቦት በመረከብ ወደ ዳርፉር እንደሚያጓጉዝ የባለሙያዎች ቡድኑ ማረጋገጡን አስታውቋል። 

ከነዳጅ በተጨማሪ ለፈጣን ወታደራዊ እንቅስቃሴ የሚያገለግሉ ሊንድ ክሩዘር ተሽከርካሪዎችን እንደሚያስገባ፣ ለአብነትም ባለፈው መስከረም ወር 12 ላንድ ክሩዘር ተሽከርካሪዎች በደቡብ ሊቢያ በኩል ወደ ዳርፉን መግባታቸውን የባለሙያዎች ቡድኑ በማስረጃ ማረጋገጡን አስታውቋል። ከጦር ማሣሪያ ድጋፍ በተጨማሪ በሊቢያ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር ተሰልፋው መዋጋታቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል።

ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የውጭ የጦር መሣሪያ ድጋፍ የሚቀርብበት ሌላኛው መስመር ከደቡብ ሱዳን በኩል ሲሆን፣ በዚህም ከደቡብ ሱዳን ለነዳጅ አቅርቦት መስመር አረጋግጧል። ነዳጅ የጫኑ መኪኖች በየሳምንቱ ከጁባ ወደ ዋዉ ተብሎ ወደሚታወቀው የሱዳን ክፍል እንደሚጓዝ፣ በኋላም በሲቪል ተሽከርካሪዎች ተጭኖ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወደ ሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች እንደሚያመራ ሪፖርቱ ገልጿል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በመጀመሪያው ዙር የዳርፉር ጦርነት (አኤፕሪል እስከ ጁላይ 2023) ወቅት ውስብስብ የጦር መሣሪያዎችን ይጠቀም እንዳልነበረ የገለጸው ይኸው ሪፖርት፣ ከኦገስት ወር ጀምሮ ግን ከዚህ በፊት የማይጠቀምባቸውን በርካታ ዓይነት ከባድና ውስብስብ መሣሪያዎችን መጠቀም እንደጀመረ ገልጿል።

በተለይም በኒያላ፣ ኤል ፋሸርና ኤል ጀንሲ በተባሉት አካባቢዎች በተደረገው ጦርነት ላይ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ሰው አልባ የውጊያ አውሮፕላኖችንና ድሮኖችን፣ ሃውትዘር የተባለውን መድፍ፣ ባለብዙ ሮኬት ማስወንጨፊያዎችን፣ ከሰውን ትከሻ የሚወነጨፉ ፀረ አይሮፕላን መሣሪያዎችን መጠቀሙን ሪፖርቱ አትቷል። ኒያላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተደረገ ጦርነትም የሱዳን ብሔራዊ ጦር አንድ የጦር አውሮፕላንን መትቶ መጣሉን ሪፖርቱ ጠቁሟል።

በራሺያ መንግሥት የሚደገፈው የዋግነር ቡድን በዚሁ የሱዳን ጦርነት ድጋፍ በማድረግ እየተሳተፈ መሆኑን፣ የቻይና የጦር መሣሪያም ወደ ሱዳን እየፈሰሰ ስለመሆኑ የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

የአሜሪካ መንግሥት የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ከጥቂት ወራት በፊት የተሾሙት ቶም ፔሬሎ ከአንድ ሳምንት በፊት ለአሜሪካ ኮንግረንስ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ፊት ቀርበው በሰጡት ምስክርነትም ዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስን ጨምሮ የተለያዩ የአካባቢው አገሮች ለሁለቱም የሱዳን ተፋላሚዎች የጦር መሣሪያ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ለተባበሩት መንግሥታት የባለሙያዎች ቡድን ድጋፍ እናደርጋለን ያሉት ልዩ መልዕክተኛው፣ ‹‹ስለዚህ የባለሙያዎች ቡድኑ የምርመራ ሪፖርት ላይ የተገለጹ ግኝቶች ታዓማኒና አስተማማኝ ናቸው፣ መሬት ላይ ያለው እውነታም ይህንኑ የሚያሳይ ነው፤›› ብለዋል። 

መቀመጫውን በለንደን ያደረገው ቻተም ሃውስ፣ በኢትዮጵያና ሱዳን ‘የግጭት ኢኮኖሚ’ የሆነው የሰሊጥ ምርት (The ‘conflict economy’ of sesame in Ethiopia and Sudan) በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በኤፕሪል ወር 2024 ባወጣው የጥናት ሪፖርት እንደገለጸው ደግሞ የሱዳን ጦር ኃይል (SAF) ከግብፅ፣ ኳታርና ቱርክን ጨምሮ ከውጪ መንግሥታት በቀጥታ ድጋፍ እያገኘ መሆኑን ለዚህም እንደ ወርቅ፣ ቁም እንስሳትና የግብርና ምርቶች ያሉ ስትራተጂካዊ ሸቀጦችን ለአጋሮቹ በመሸጥ የጦር አቅሙን ለመገንባት የሚያስችል ገቢ ያገኛል።

ግብፅ ከሱዳን ጦር ኃይል በኩል የሚላክላትን ወርቅ በመግዛት የገጠማትን የውጭ ምንዛሪና የከፋ የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ቀውስ ማስታመሚያ እንዳደረገችው የቻተም ሃውስ የጥናት ሪፖርት ይጠቁማል።

ሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች የውጭ ግንኙነታቸውን ከስልታዊ ግቦች ጋር ለማጣጣም እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ የውጭ ተዋናዮችም በቀጣናዊ ተፅዕኖዋቸውን ለማሳደግ ሱዱንን ጦርነት መጠቀሚያ መድረክ አድርገው እንደሚመለከቱት አስረድቷል።

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የጦር መሣሪያ ድጋፍ እንደምታደረገው ሁሉ፣ የሱዳን የጦር ኃይል (SAF) ደግሞ ከኳታር እንዲሁም በኳታር በኩል ከኢራንና ከቱርክዬ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖችን (ድሮኖችን) ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን ድጋፍ እያገኘ መሆኑን አመልክቷል።

 የጦርነቱ ማስቀጠያ የግንዘብ ምንጮች 

የሱዳን ብሔራዊ ጦር (SAF) በርካታ ጠቃሚ የኢኮኖሚ ዘርፎችንና ኩባንያዎችን ይቆጣጠር የነበረ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ መጀመር በኋላ ከእነዚህ ኩባንያዎች ያገኝ የነበረው ትርፍ ተሽርሽሮበታል። የዚህም ምክንያቱ አብዛኛዎቹ የሱዳን ብሔራዊ ጦር ቁልፍ ሀብቶች የሚገኙት በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሙሉ ቁጥጥር ሥር በወደቀችው የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በመሆኑ ነው።

በአሁኑ ጊዜ የሱዳን ብሔራዊ ጦር የሚያደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ በከፊል የሚደገፈው ከጦሩ ጋር ግንኙነት ባላቸው ሀብታም ግለሰቦችና ነጋዴዎች እንደሆነ የቡድኑ ሪፖርት ያመለክታል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ በበኩሉ ከጦሩ ጋር ግንኙነት ባላቸው እስከ 50 በሚደርሱ ኩባንያዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግለት የባለሙያዎች ቡድኑ መረጃ ያመለክታል። ከእነዚህ ኩባንያዎች ውስጥ አብዛኞቹ ከሱዳን ውጪ በተለያዩ አጎራባች አገሮች የተመሠረቱና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ መሐመድ ዳጋሎ የቤተሰብ አባላት የሚመሩ እንደሆነም መረጃው ይጠቁማል። እነዚህ ኩባንያዎችም በማዕድን፣ በፀጥታ፣ በግብርና በማኑፋክቸሪንግ፣ በሪል ስቴት፣ በኮንስትራክሽንና እንደ አማካሪና ቱሪዝም ያሉ አገልግሎቶችን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ መሆናቸውን ይገልጻል።

ለአብነትም ዋነኛ ከሚባሉት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የገንዘብ ምንጭ በመሆን ከሚጠቀሱት መካከል አል-ጁነይድ ፎር መልቲ አክቲቪቲስ የተባለና በሥሩ በርካታ እህት ድርጅቶችን ያቀፈ ኩባንያ ተጠቅሷል። ይህ ኩባንያ አብደልራሂም ዳጋሎ በተባሉት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ምክትል አዛዥና አብዱልጀባር መሐመድ አህመድ (ከዳጋሎ ቤተሰቦች ጋር ዝምድና ያላቸው) በተባሉ ግለሰብ ባለቤትነት የተያዘ መሆኑን የባለሙያዎች ቡድኑ አረጋግጧል። የአል-ጁነይድ ኩባንያ አጠቃላይ ሀብት በብዙ ሚሊዮን ዶላር እንደሚገመት የባለሙያዎች ቡድኑ ሪፖርት ጠቁሟል።

የባለሙያዎች ቡድኑ በሱዳን የወርቅ ምርትና ንግድ የጦርነቱ ተፋላሚዎችን ለመደገፍ ይውል እንደሆነ ለማረጋገጥ ሰፊው የጥናት እንቅስቃሴ ያደረገ ሲሆን በዚህም ስለሱዳን የወርቅ ንግድ ዝርዝር መረጃና የቅርብ ዕውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች ቃለ መጠይቅ በማድረግና በሚስጥር የቀረቡ ሰነዶችን ለመመልከት ችሏል።

የሱዳን ጦርነት በኤፕሪል 2023 ከመቀስቀሱ በፊት የሱዳን ፈጥኖ ደረሽ ኃይል (RSF) በስፋት በሚቆጣጠረው ዳርፉር አካባቢ የሚመረተው የወርቅ ማዕድን ለአገሪቱ አጠቃላይ የወርቅ ምርት የሚያበረክተው አነስተኛ ድርሻ ቢሆንም ፈጥኖ ደረሽ ኃይሉ ዳርፉር ውስጥ በራዶም፣ ሲንጎ አግባሽ በተባሉ አካባቢዎች እንዲሁም በደቡብ ዳርፉር ዳራባ በተባለ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ሁለት የወርቅ አምራች ኩባንያዎች እንዳሉት አረጋግጧል። በሱዳን ከሚመረተው የወርቅ ማዕድን 30 በመቶውን ድርሻ የሚይዘው ባህላዊ መንገድ የሚመሠተው ወርቅ ሲሆን በዚህም የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልና ሌሎች የአካባቢው ሚሊሻዎች በባህላዊ መንገድ ወርቅ እንደሚያመርቱ ቡድኑ አረጋገጧል።

በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ የምርት መቀነስ ቢኖርም የወርቅ ማዕድን ለሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ሁነኛ የገቢ ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል። ለምሳሌ ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር ግንኙነት ያለው በዱባይ አገር የሚገኝ አንድ ሱዳናዊ የወርቅ ነጋዴ 50 ኪሎ ግራም ወርቅ በግንቦት 2023 መቀበሉን ቡድኑ አረጋግጧል። 

ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ወደ ተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ ይላክ የነበረው ወርቅ አሁን ላይ በሱዳን ወደብ (Port Sudan) በኩል ተሻገሮ በድብቅ ለግብፅ እየቀረበ መሆኑን የባለሙያዎች ቡድኑ የምርመራ ሪፖርት አመላክቷል።

የሱዳን ጦርነትና ኢትዮጵያ 

ኢትዮጵያና ሱዳን በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለረዥም ጊዜ ተፎካካሪ ሆነው ቆይተዋል። መንግሥቶቻቸው እርስ በርስ ጣልቃ በመግባት የሌላውን አገር አገዛዝ የሚቃወሙ ታጣቂዎችን የመደገፍ ታሪክ አላቸው። እ.ኤ.አ. በ2020 መገባደጃ ላይ በትግራይ ውስጥ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ የሱዳን ብሔራዊ ጦር ኢትዮጵያና ሱዳን የሚወዛገቡበትን የአል ፋሻጋ ድንበር ግዛት ለመያዝ ተንቀሳቅሷል። ይህ ዕርምጃ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ከፍተኛ ቅራኔ እንዲፈጠር አድርጓል። በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ሱዳን ለትግራይ ተዋጊዎች የጦር መሣሪያ ድጋፍ ስታደርግ ነበር የሚል ጥርጣሬና ክስ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ሲሰነዘር ነበር። ከዚህ ውንጀላ ጀርባ ያለው እውነታ ምንም ይሁን ምን ሱዳን ለተወሰኑ ከፍተኛ የሕወሓት አባላት መሸሸጊያ ስትሆን፣ እንዲሁም ወደ ምሥራቅ ሱዳን የተሰደዱ 60,000 የትግራይ ተወላጆችንም አስጠልላለች። 

በቅርቡም የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የትግራይ ታጣቂዎች በጄኔራል አልቡርሐን ከሚመራው የሱዳን ብሔራዊ ጦር ጋር ተሠልፈው እየወጉት እንደሆነ በይፋ አስታውቋል። 

የትራይ ታጣቂዎች ከሱዳን ጦር ኃይል (SAF) ጋር ተሠልፈው እየተዋጉ ነው የሚለውን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ክስ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ‹‹መሠረተ ቢስ ውንጀላ›› ሲል ውድቅ አድርጎታል።

‹‹የሱዳን ሕዝብና መንግሥት እጅግ አሳሳቢ የሆኑ የውስጥ ተግዳሮቶች ቢኖሩበትም በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ተስፋ የቆረጡ የትግራይ ስደተኞች ተቀብሎ ዕርዳታና ጥበቃ አድርጓል። በመሆኑም የትግራይ ክልል ወይም የትግራይ ተወላጆች እንደ ሁለተኛ ቤታቸው የሚቆጥሯትን አገር ሱዳን የሚጎዳ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የሚገቡበት ምንም ምክንያት የለም፤›› ብሏል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከሰሞኑ ያቀረበውን ክስ በተመለከተ የተጠየቁት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ በሰጡት ምላሽ፣  ‹‹እንዲህ ዓይነትና መሰል ውንጀላዎች ቀደም ሲል ወደ ሱዳን ተሰደው ከነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ተያይዞ ሊነሳ ይችላል። ነገር ግን ይህንን መረጃ መሠረት በማድረግ በጦርነቱ ምክንያት ከካርቱም እንዲወጣ የተደረገው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እያጣራ ይገኛል። ዝርዝር መረጃ ሲገኝ ምላሽ የሚሰጥበት ይሆናል፤›› ብለዋል። 

የኢትዮጵያና የሱዳን ግንኙነት አሁን የበለጠ እየተቀረጸ ያለው በሱዳን የጦር ኃይልና በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል እየተደረገ ባለው ጦርነት ነው። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ውዝግብ እንዳይባባስ በመቆጠብ እንዲሁም የሱዳኑ ጦርነትን በተመለከተ እስካሁን ገለልተኛ ሆነው ለመቆየት ጥረት ማድረጋቸውን የቻተም ሃውስ ሪፖርት ይገልጻል። ከዚህ በተጫማሪም የኢጋድ መሪዎች በኩል የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎችን ለማሸማገል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዳበረኩቱም ይጠቁማል። 

ነገር ግን በኢትዮጵያ መንግሥትና በሱዳን ወታደራዊ አገዛዝ መካከል ያለውን የቅርብ ጊዜ የጠላትነት ታሪክ መነሻ በማድረግ ሊፈጠር የሚችለውን ለውጥ ለመመልከት ቢሞከር፣ ኢትዮጵያ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) የበላይነት እንዲያገኝ ልትደግፍ እንደምትችል የቻተም ሃውስ ጥናት አመልክቷል።

‹‹በተለይም የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለውን የድንበርና ሌሎች የሁለትዮሽ ውዝግቦችን ለመፍታት ከተስማማ፣ እንዲሁም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የአዲስ አበባ መንግሥትን አቋም ለመቀበል ፈቃደኛ ከሆነ ኢትዮጵያ ልትደግፈው ትችላለች፤›› ብሏል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከልም ወሳኝ የክርክር ጉዳይ መሆኑን የሚጠቁመው ይኸው ጥናት፣ ኢትዮጵያ ለሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ድጋፍ የምትሰጥ ከሆነ፣ ግብፅም ይህንኑ በማስላት ለሱዳን ጦር ኃይል (SAF) መደገፏ እንደማይቀር አስረድቷል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን ከመደገፉ በፊት ነገሮችን በጥንቃቄ መመዘን ይኖርበታል ብሏል። 

ነገር ግን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን መደገፍ በኢትዮጵያ መልካም ስም ሊመጣ የሚችለውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት ኢትዮጵያና ሱዳን ወደ ግጭት ሊገቡ የሚችሉበት ሁኔታ አለ ለማለት እንደማይቻል ያስቀምጣል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት በሱዳን ጦርነት ላይ ከያዘው ገለልተኛ አቋም ተንሸራቶ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን ወደ መደገፍ ካደላ፣ ይህ ሊሆን የሚችለው የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬትስ በምታሳድረው ተጽእኖ ሊፈጠር የሚችል እንደሆነ ገልጿል።

ይህ ሁኔታ ከተከሰተ ደግሞ የባህረ ሰላጤው አገር የሆነችው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከሞላ ጎደል ላለፉት አሥር ዓመታት በአፍሪካ ቀንድና በአኅጉሪቱ ውስጥ ያሉ ሌሎች የፖለቲካ ሁኔታዎችን በመቅረጽ ረገድ እየተጫወተች ያለችውን የላቀ ሚና የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ ይሆናል ብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ነብዩ ተድላ በበኩላቸው ከሱዳን አለመረጋጋት ተያይዞ ወደ ኢትዮጵያ ሊሻገሩ የሚችሉ አደጋዎች እንደሚኖሩ ይታመናል ብለዋል። ይህንን ከግምት በማስገባትም የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትም ያንን ለመከላከል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። አክለውም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሱዳንን ጦርነት በተመለከተ የሚያራምደው አቋም ግልጽ መሆኑን፣ ይኸውም የሱዳን ችግር በአፍሪካ ኅብረት የአደራዳሪነት ሚና በሱዳናዊያን ይፈታ የሚል እንደሆነ ተናግረዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -