Wednesday, June 12, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከስቀለው ከይሰቀል ፖለቲካ ባህል መላቀቅ ስለምን ተሳነን?

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

የዛሬ ጽሑፌን ፈር ማስያዣ ይሆነኝ ዘንድ በአንድ ገጠመኜ ለመንደርደር ወደድሁ። ከዓመታት በፊት ተማሪ በነበርንበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 6 ኪሎ ዋናው ግቢ በተለያዩ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች የሚናጥበት ቀውጢ ወቅት ነበር።

ታዲያ የዛን ቀውጢ ሰሞን የሥነ ተግባቦት /Communication Skill/ መምህራችን የነበሩት ስምዖን ገብረመድኅን (ዶ/ር) በአንድ የትምህርት ክፍለ ጊዜያችን፣ ‹‹ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!›› ተብሎ የተጀመረና እርሳቸውም በተማሪነት ዘመናቸው አባል የነበሩበት የዛን ጊዜው የለውጥ ጥያቄ የነጎደበትን የእርስ በርስ መጠፋፋትና የስቀለው ፖለቲካችን ባህልን ከወቅቱ የግቢያችን ነውጥ ጋር እያነጻጸሩ አስገራሚም፣ አሳዛኝም የሆነ አንድ ገጠመኛቸውን እንዲህ አወጉን።

‹‹መሬት ላራሹ፣ ዲሞክራሲያዊ መብት ያለ ገደብ፣ የሃይማኖት እኩልነት… ወዘተ.›› የሚሉ ጥያቄዎችን በማቀንቀን የሚታወቁት የዛን ጊዜው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በልደት አዳራሽ ተስብስበው መፈክር በሚያሰሙበትና በማርኪሲስት ርዕዮተ ዓለም ዙሪያ በሚሟገቱበት አንድ ወቅት ላይ እንዲህ ሆነ።

በ6 ኪሎው የልደት አዳራሽ እጅግ በተሟሟቀ አብዮታዊ ስሜት፤ በአገራዊ ወኔ በሚካሄድ ስብሰባ ወቅት የዚህ ስብሰባ ተሳታፊ የሆነ አንድ ተማሪ አስተያየት ለመስጠት ፈልጎ እጁን ያወጣል፤ ተማሪው ይፈቀድለትና ወደ መድረክ ይወጣና አስተያየቱንም እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-

‹‹… ወገኖቼ እያነሳናቸው ያሉት የለውጥ፣ የፍትሕ ያለ እና የዲሞክራሲ መብት ይከበር ጥያቄዎቻችን ተገቢ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ነገሥታት/መንግሥታት የሚሾሙትም ሆነ የሚወርዱት በአምላክ ፈቃድ ነውና ምናልባት ሳናውቀው ከፈጣሪ ስንጣላ እንዳንገኝ…›› የስብሰባው ተሳታፊ ተማሪዎች ንግግሩን አላስጨረሱትም በአንድ ድምፅ ሆነው፣ ‹‹ይሰቀል! ስቀለው! ስቀለው!›› በሚል መብረቃዊ ጩኸትና መፈክር አዳራሹ ተናወጠ፡፡ ያ ምስኪን ተማሪም በጓደኞቹ እየተገፈታተረ ከመድረኩ እንዲወርድ ሆነ በማለት መምህራችን ስምዖን (ዶ/ር) የዛን ጊዜ የአብዮት ዘመን ትዝታቸውን በቁጭትና በኀዘን ስሜት ውስጥ ሆነው አውግተውናል።

በዛን ዘመን የሶሻሊስት አራማጆች ዘንድ፤ ‹‹ሃይማኖት ሕዝብን የማደንዘዣ ዕፅ ነው›› (Religion is an Opium) የሚለውን ፀረ ሃይማኖት የሆነ አስተምህሮአቸውን ያስታውሷል።

ይህን የመምህራችን ስምዖንን ትዝታን እንደያዝን ዛሬም ድረስ ‘ከስቀለው፤ ከመጠፋፋት ፖለቲካ’ ባህል መላቀቅ ስለምን ተሳነን በሚለው ሐሳብ ላይ አብረን ጥቂት እንቆዝም እስቲ።

ለሺሕ ዘመናት የዘለቀ የሃይማኖት አስተምህሮ ውስጥ ያለፍን፣ ገናና ሥልጣኔ የገዘፈ ታሪክና የዳበረ ባህል አለን የምንል ማኅበረሰቦች ምን ብንሆን ነው – የሃይማኖት አባትን ያህል ሰው በገመድ አንቀን ለመገደል የደፈርነው? የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባትና መንፈሳዊ መሪ የነበሩትን የሰማዕቱን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን የጭካኔ አገዳደልን ያስታውሷል።

በተመሳሳይም የመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ፕሬዚዳንት የነበሩት ቄስ ጉዲና ቱምሳም የኦነግ አባልና ደጋፊ ነዎት በሚል ነበር በጭካኔ በጥይት ተደብደበው የተገደሉት። የአሁኑ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስም በለውጥ/በአብዮት ስም ነበር ለሰባት ዓመታት በወኅኒ በግፍ ተግዘው እንዲማቅቁ የተደረጉት። እንዲሁም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት የሆኑት ካርዲናል ብፁዕ ብርሃነ ኢየሱስም ታስረው ነበር፡፡ 

‹‹የአፍሪካ አባት›› በሚል ጥቁሩ ዓለም የሚያደንቃቸው የአዛውንቱ የግርማዊ ቀዳማዊ  ኃይለ ሥላሴና የ60ዎቹ ኢትዮጵያውያን ሚኒስትሮች፣ ሹማምንትና አርበኞች የጅምላ ጭፍጨፋንም ልብ ይሏል። ይህን ከኢትዮጵያ አልፎ መላውን ዓለም በድንጋጤ ጭው ያደረገውን በለውጥ ስም የተወሰደ አብዮታዊ ርምጃን/የጅምላ ጭፍጨፋን አስመልክቶ በወቅቱም፤ እንደ ቢቢሲ ያሉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን፤ “What Happened to the Bloodless Ethiopian Revolution?!” ሲሉ ድንጋጤ የታከለበትን ዜናን አከታትለው ነበር።

ፖለቲካችንን ክፉኛ የተጣባው ይሄ የይሰቀልና የመጠፋፋት ባህል ዛሬም አብሮን ዘልቋል። ታቦት በቆመበት፣ ምሕረትና ይቅርታ በሚታወጅበት ዓውደ ምሕረት ላይ ቆመው፤ “…እንዴት አንድ ወንድ ይጠፋል እንደ ዳዊት ግንባሩን ብሎ የሚገድለው?!” ብለው ጦርነትን/ሞትን የሚያውጁ፣ ጥላቻን የሚሰብኩ የሃይማኖት አባቶችን ለመታዘብ የበቃንበት አስጨናቂ ዘመን ላይ መድረሳችንን ልብ ይሏል። 

እነርሱ ላም ሲያርዱ፣

እኛም ጥጃ እንረድ፣

ቢሆንም ባይሆንም፣

እጃችን ደም ይልመድ።

     ደመናው ሲደምን ይወረዛል ገደል፣

     ይዘገያል እንጂ መች ይረሳል በደል።

ላዩ ጨረቃ፤ ታቹ ጨረቃ፣

‹ደምላሽ› አለችው እናቱም አውቃ።

የሚሉ ቂምን ያረገዙ፣ የጦር አውርድ ዓይነት ስያሜዎችና ሥነ ቃሎች ያሉን ኩሩ ሕዝብ ነን። በገደምዳሜውም ቢሆን ከዕርቀ ሰላም ይልቅ ለበቀልና ለእርስ በርስ እልቂት/መጠፋፋት የቀረብን/የመረጥን ማኅበረሰብ ነን የሚለውን የመከራከሪያ ሐሳብ ሊክድ የሚደፍር ካለ… እንደው ሌላው ሁሉ ቢቀር ባሳለፍናቸው ሁለት ዓመት አንድ ሚሊዮን ወገኖቻችንን ሕይወት በከንቱ የቀጠፈውን የእርስ በርስ ጦርነት/እልቂት ማስታወስ ብቻ በቂ ይሆናል።

ያለፈውን የቅርብ ታሪካችንን ዘመን ስንፈትሽም፣ ‹‹ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም›› በሚል መፈክር የተጀመረው የ1966ቱ ለውጥ/አብዮት አፍታም ሳይቆይ፤ ‹‹አብዮት የገዛ ልጆቿን እንኳን ሳይቀር ትበላለች!›› ወደሚል አስፈሪ ፅልመት ተቀይሮ- ያለ ምንም ደም በሚል የሰላምና የዕርቅን መንገድ የመረጠ የመሰለው አብዮት፤ ‹‹የማይታረቅ የመደብ ቅራኔ ውስጥ ነን፤ እናም ወይ እኛ ወይ እነርሱ ካልጠፉ በስተቀር…›› ወደሚል ጠላትነት/ባላንጣነት ነበር የተቀየረው።

በአብዮቱ ግራና ቀኝ የተሰለፉት ኃይላት ተቀራርቦ ለመነጋገርና ለዕርቀ ሰላም አማራጭ በሩን ጥርቅም አድርገው ሲዘጉ- በኢትዮጵያ ምድር የሞት መላእክት የጥፋት ሰይፋቸውን መዘው በአራቱ ማእዘን ቆሙ። ከዚህ በኋላ በምድራችን ላይ የሆነውን ዘግናኝ እልቂት ለማወቅ የሚፈልግ እንደምንም ጨክኖና ስሜቱን ተቆጣጥሮም ቢሆን በደም የጨቀየ፤ ዘግናኝ የታሪካችንን ምዕራፍ ማንበብ ነው የሚጠበቅበት።

አሊያም በመስቀል አደባባይ ያለውን የቀይ የሽብር እልቂት/የሰማዕታት ቤተ መዘክርን ቢጎበኝ የሄድንበት የጥፋት መንገድ ምን ያህል ከባድ እንደነበርና የዛን ዘመን አስፈሪ ፅልመት በጥቂቱም ቢሆን ይከስትለታል።

ኢትዮጵያ ሀገሬ ታጠቂ በገመድ፣

የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ፣

ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ።

የሚለው የኢትዮጵያውያን ምስኪን እናቶችን እንጉርጉሮ መነሻውም ይኸው ዕርቅንና ሰላምን የገፋው የይሰቀል የፖለቲካ ታሪካችን መራር ሐቅ አካል ነው…።

ግን… ግን… ደግሞ፤

በአንፃሩ በዚህ ሁሉ ውስጥ እንደ ማኅበረሰብ እንዴት አብረን ቆየን ብለን ብንጠይቅ፤ ‹‹ይቅር ለእግዚአብሔርና ዕርቅ ደም ያደርቅ!›› የሚል በተግባር የሚገለጽ ሥነ ቃል ያለን ሕዝብ መሆናችንንም መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም። ለአብነትም፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት የጋሞ አባቶች እንደ ባህላቸው ሣር በጥሰው ሄደው ጫፍ ላይ የደረሰን የእልቂት ድግስን በዕርቀ ሰላም እንዲፈታ ያደረጉበትን ክስተት ማስታወስ ይገባናል።

እንዲህ ዓይነቱ የዕርቀ ሰላም ባህል ከሰሜን ኢትዮጵያ ጫፍ እስከ ደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተንሰራፋ ነው። አሁን ላለንበት የሰላም እጦትና የይሰቀል ፖለቲካዊ ባህላችን ለፈጠረው ቀውሶቻችን መፍትሔ ለመሻት እነዚህን አገራዊ እሴቶቻችንን በቅጡ መፈተሽ ያለብን ይመስለኛል። አበቃሁ!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደቡብና በምዕራብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት በዋና ጸሐፊነት ሆነው ያገለገሉ፣ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ከፍተኛ ተመራማሪ፣ የታሪክና የቅርስ አስተዳደር ባለሙያ፣ እንዲሁም በዩኒቨርሳል ፒስ ፌዴሬሽን (Universal Peace Federation – UPF) የሰላም አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles