Wednesday, June 12, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከሦስት መቶ ዓመት በፊት የትንሣኤ መብራትን በኢየሩሳሌም የሚያወጡት ኢትዮጵያውያን አበው ነበሩ

በቀሲስ ሰሎሞን ወንድሙ መታፈሪያ

በኢየሩሳሌም እስከ አሥራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ (1694 ዓ.ም.) ድረስ ለሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የትንሣኤ መብራት የሚወጣው በኢትዮጵያውያን አባቶች ነበር፡፡

ይኽ ታሪክ እንዲህ ነበር፡፡ ብርሃን በሚወጣበት ቅዳሜ ዕለት በሚሰበሰቡበት ከኹሉ አስቀድሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተቀብሮ ወደ ነበረበት የመቃብር ቦታ ነጭ ልብስ ለብሶ የሚገባው የኢትዮጵያው መምህር ነበር፡፡ በዚህን ዕለት ጳጳሳቱና መነኮሳቱ በአንድነት ወደ መካነ መቃብሩ ሲሄዱ ከፊት ለፊት የሚሄደው ከኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የሚላከው ኢትዮጵያዊ አባት ነበር፡፡ ይኽ አባት ይኽንን የትንሣኤውን ብርሃን ለማውጣት ብቻ ከኢትዮጵያ የሚመጣ ነበር፡፡ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት መምህራን የሮም፣ የአርመን፣ የኩርጅ፣ የሶሪያና የቅብጥ አብያተ ክርስቲያናት መምህራን በተቀመጠላቸው ቅደም ተከተል መሠረት ከርሱ በኋላ ወደ መካነ መቃብሩ ይገባሉ፡፡ ብርሃን በሚወጣበት ቅዳሜ በአንድነት ጧፍ አብርተው ከመካነ መቃብሩ ይወጣሉ፡፡

የትንሣኤውን መብራት ለማብራት ይኽ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መምህር ነጭ ልብስ ለብሶ ዘይት የተሞላበት ያልተቃጠለ ፈትል ያለበት የብርጭቆ ቀንዲል ይዞ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መካነ መቃብር ይገባል፡፡ ወደ መካነ መቃብሩ ገብቶ መዝጊያውን ዘግቶ ይቆማል፡፡ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት መምህራን ደግሞ ከሕዝባቸው ጋር ጧፍ ይዘው ‹‹ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ (ትንሣኤኽን ለምናምን ለእኛ፣ ብርሃን ላክልን ወደ እኛ)›› በማለት እየዘመሩ በደጁ ላይ ይጠብቁታል፡፡ ይኽ በመቃብሩ ሥፍራ ያለው የኢትዮጵያ መምህር ብርሃን ከወጣለት በኋላ ሌሎቹ ገብተው መካነ መቃብሩን እንዲሳለሙ መዝጊያውን ያንኳኳል፡፡ ከዚኽ በኋላ ኹሉም መምህራን በኢትዮጵያዊው መምህር ከተያዘው የትንሣኤ መብራት በእጃቸው የያዙትን ጧፍ በፍጥነት በማብራት ወደ ራሳቸው አብያተ መቃድስ ሄደው ብርሃነ ትንሣኤውን ያከብራሉ፡፡

 አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በመጽሐፈ ምሥጢር ይኽንን ምስክርነት አረጋግጠዋል፡፡ አፄ ዘርአ ያዕቆብ ኢትዮጵያውያን ይኽ የትንሣኤ ብርሃን የሚወርደው ለእነሱ ብቻ መሆኑን አስበው እንዳይታበዩ የምክር ቃል ልከውላቸው ነበር፡፡ በተአምረ ማርያም ተአምር 25 ላይ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት መምህራን ኢትዮጵያውያን ከመካነ መቃብሩ አባረው በራሳቸው ብቻ የትንሣኤውን መብራት ለማብራት ባደረጉት ሙከራ የትንሣኤው መብራት ሊበራላቸው ያለመቻሉን በኋላ በምቅዋመ ማርያም ቆሞ እያለቀሰ ይፀልይ በነበረው በኢትዮጵያዊው ተሳላሚ እጅ ላይ የብርሃን ፋና ሲንቦገቦግ በማየታቸው ይቅርታ እንደጠየቁት ተጽፏል፡፡ መካነ መቃብሩ በገባ ጊዜ በርሱ እጅ ላይ የትንሣኤው መብራት እንደወረደና ኢትዮጵያውያን የትንሣኤው ብርሃን የሚወርደው በኛ እጅ ነው በማለት እንዳይታበዩ ተጽፏል፡፡

 በግሪክና በሩሲያ አብያተ ክርስቲያናት በትንሣኤ ሌሊት የሚበራውን መብራት የሚያመጣው ሕዝቡ ነው፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ‹‹ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን›› (ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ) በማለት እያወጁ ብርሃኑን ውሰድ እያሉ በሕዝቡ እጅ ያለውን ጧፍ ያበራሉ፣ ብርሃኑን ያካፍላሉ፡፡ የበዓለ ትንሣኤ መብራት የሚወጣው (የሚበራው) ከአንድ የጧፍ መብራት ነው፡፡ ይኸንን የትንሣኤውን መብራት የሚያወጡት (የሚያበሩት) ጳጳሳት ወይም የገዳሙ ወይም የደብሩ መምህር ናቸው፡፡ ይኽንን የትንሣኤ መብራት እንደ ተርታ መብራት ማንም ሰው ተነስቶ አይለኩሰውም ወይም አስቀድሞ ሲበራ ከነበረ መብራት ላይ አይለኮስም፡፡

የበዓለ ትንሣኤ መብራት ሥርዓተ ዑደት

በበዓለ ትንሣኤ ወንጌል ከመነበቡ አስቀድሞ ቀሳውስቱ ጸሎተ ዕጣን አድርሰው፣ የትንሣኤውን ሥዕል እንዲሁም መስቀል ከፍ አድርገው በመያዝ መብራት አብርተው ቤተ መቅደሱንና ቤተ ክርስቲያኑን በመዞር ሥርዓተ ዑደት እንዲፈጽሙ ታዝዟል፡፡ በዚህም መሠረት ልዑካኑ ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ‹‹ዲያቆኑ ተንሥኡ ለጸሎት›› በማለት ከሕዝቡ ጋር እየተቀባበሉ ጸሎተ አኰቴት ያደርሳሉ፡፡

ታላቁ የትንሣኤ መብራት የሚበራው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወትና ሞቱን ለማዘከር፣ ትንሣኤውን ለማሰብ ነው፡፡ በጥንት ዘመን በዕለተ ቀዳሚት ድንጋይ በመስበቅ አዲስ መብራት የማብራትና የትንሣኤውን ሻማ የመባረክ ሥርዓት ይከናወን ነበር፡፡ ካህኑ በቤተ ክርስቲያን በር ላይ ቆመው እንጨት ሰብቀው አዲስ የትንሣኤ መብራት ያበራሉ፡፡ የትንሣኤ ሻማም የሚለኮሰው ከዚህ መብራት ነው፡፡ ካህናቱና ምዕመናን ከዚህ መብራት ላይ በእጃቸው የያዙትን ጧፍ በመለኮስ ተሠልፈው እየዘመሩ ዑደት ያደርጋሉ፣ ቤተ ክርስቲያኑንም በብርሃን ይሞሉታል፡፡ መብራቱ የጽድቅ ፀሐይ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ይኽ ሰዓት ከማለዳ ጀምሮ የትንሣኤውን ብርሃን ለማየት ሲናፍቁ ለነበሩ አማንያን ታላቅ የምሥራች ጊዜ ነው፡፡ ልዑካኑ የትንሣኤውን ሥዕልና መስቀሉን ከፍ አድርገው ተሸክመው ዕጣን እየታጠነ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሦስት ጊዜ ዑደት ይደረጋል፡፡ ይኽም የመስቀሉ ክብር የሚገለጥበት፣ ልቡናችንን ወደ መስቀሉ የምናነሣበት፣ ነፍሳችንና ሥጋችን በመስቀሉ ያገኘቱን ሰላምና ፍቅር የምገልጥበት ሥርዓት ነው፡፡

ምዕመናን የካህናቱን ዝማሬ እያደመጡ የግል ጸሎታቸውን እያደረሱ ይቆያሉ፡፡ ብርሃነ ትንሣኤውን ለማወጅ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለቅጽበት መብራት ጠፍቶ የጨለማ ጊዜ ይሆናል፡፡ በዚኽን ጊዜ በምሥዋዑ ላይ ካለው መብራት በስተቀር የቤተ ክርስቲያኑ መብራት በሙሉ ጠፍቶ አዲስ የበራውን ሻማና መስቀሉን ይዘው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዑደት ያደርጋሉ፡፡ ይኽም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ከዕፀ መስቀል ወርዶ በከርሰ መቃብር መቆየቱን ለማመልከት ነው፡፡ በጣም ጥቂት ደቂቃ ቆይቶ የትንሣኤ መብራት ይበራል፡፡

የበዓለ ትንሣኤ ሥዕልና መስቀል

በበዓለ ትንሣኤ፣ ወንጌል የትንሣኤውን ሥዕል እንዲሁም መስቀል ከፍ አድርገው በመያዝ መብራት አብርተው ቤተ መቅደሱንና ቤተ ክርስቲያኑን በመዞር ሥርዓተ ዑደት እንዲፈጽሙ በታዘዘው መሠረት ዑደት ይደረጋል፡፡ በአንዳንድ ታላላቅ ገዳማትና አድባራት ደግሞ በትንሣኤው ሥዕል ፈንታ ‹‹ኲሉ ብርክ ይስግድ ከመ ለስሙ ለኢየሱስ ክርስቶስ›› ተብሎ ስመ አምላክ የተጻፈበት፣ የቅድስት ሥላሴ፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥነ ስቅለትና የቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕላት የተቀረፁበት የቅዱስ ሥጋውና የክቡር ደሙ ዙፋን የኾነውን የቃል ኪዳኑን ታቦት በነጭ መጎናፀፊያ አክብረው የመጾር መስቀሉን ከፍ አድርገው ይዘው በመውጣት ሥርዓተ ዑደት ይፈጽማሉ፡፡

የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ታላቅ መስቀል በቀይ መጎናፀፊያ ሸፍነው ይዞራሉ፡፡ ይኽንንም መስቀል ‹‹የትንሣኤ መስቀል›› (Easter Cross) ይሉታል፡፡ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መቃብር ለማሰብም ትንሽ ሳጥን ከምሥዋዑ በኋላ ያኖራሉ፡፡ የትንሣኤውን ሥዕልና መስቀሉን ከፍ አድርገው ይዘው ጌታ ከማርያም መግደላዊት ጋር እንደ ተነጋገረ እያስታወሱ ይዘምራሉ፡፡

በምሥራቃውያንና በምዕራባውያን፣ በቅብጣውያን እንዲኹም ኢየሩሳሌም በሚገኘው የዴር ሡልጣን ገዳማችን አባቶች በበዓለ ትንሣኤ ዑደት የትንሣኤ ልዩ ዓርማ ይያዛል፡፡ በአገራችን ብዙ ቦታዎች በሥርዓተ ዑደቱ መስቀሉ እንጂ ሥዕለ ትንሣኤውና የትንሣኤው ዓርማ ሲያዝ አይታይም፡፡ ለሥርዓቱ ተገቢ ትኩረት ካለመስጠት እንጂ ይኽንን ማዘጋጀቱ አስቸጋሪ አይደለም፡፡ በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የሚደረገውን ሥርዓተ ዑደት ከሚከተሉት ብርሃናዊ ሥዕለ ገጻት መመልከት ይቻላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles