Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከሕፃናት መንደር የተቀዳ ስኬት

ከሕፃናት መንደር የተቀዳ ስኬት

ቀን:

‹‹በተለያየ የሕይወት አጋጣሚ፣ በሰው ሠራሽም ሆነ በተፈጥሮ ችግሮች የኤስኦኤስ ሕፃናት መንደርን ተቀላቅለው ቤተሰባዊ ፍቅርና እንክብካቤ አግኝተው እያደጉ ያሉና የቆይታ ጊዜ ጨርሰው የወጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆች አሉ፡፡ መንደሩ መልካም የትምህርት ጊዜ አሳልፈው ራሳቸውን በማብቃት ለማኅበረሰቡና ለአገር መልካም ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ዜጎችም አፍርቷል፡፡ ለእኛ ለወጣቶች የኤስኦኤስ ቤተሰብ ትልቅ ግብዓት ነው፡፡ እኔም በኤስኦኤስ የሕፃናት መንደር አዲስ አበባ ያደግኩ ወጣት ነኝ፡፡ ለእኔና ለእኛ ስኬት ከጀርባ ኤስኦኤስ አለ››፡፡

ይህን ያለው ወጣት ኢዮብ በቀለ በኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ኢትዮጵያ አድገው፣ ድጋፍና እንክብካቤ አግኝተው ለከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ከበቁ ወጣቶች አንዱ ነው፡፡

ድርጅቱ በኢትዮጵያ ሥራ የጀመረበትን 50ኛ ዓመት አስመልክቶ ግንባት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ባዘጋጀው መድረክ የተገኘው ወጣት ኢዮብ፣ በመንደሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች አድገው መውጣታቸውን፣ ለማኅበረሰቡ በመንግሥትም ሆነ በግል ተቋማት ተቀጥረው ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሆነ፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች ተፅዕኖ እየፈጠሩ እንደሚገኙ እሱ ምስክር መሆኑን ገልጿል፡፡

እሱን ጨምሮ በድርጅቱ የሕፃናት ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ልጆች የትምህርት፣ የጤናና የተለያዩ ተጨማሪ ክህሎት ማግኘታቸውን፣ በተለይ በኢትዮጵያ በሚገኙ በሰባቱ የድርጅቱ መንደሮች ያደጉና የሚያድጉ ወጣቶች፣ ሰብዓዊነት ላይ ስለተሠራባቸው የበኩላቸውን ለመወጣት ማኅበር መመሥረታቸውንም አክሏል፡፡

መንደሩ በልጆቹ ላይ የሚሠራው የሰብዓዊነት ሥራ፣ በወጣቶች ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ በማሳደሩ ‹‹የቀድሞ የኤስኦኤስ ልጆች ማኅበር›› በማቋቋም የሰብዓዊነት ራዕዩን ለማስቀጠል እየሠሩ መሆኑንም ተናግሯል፡፡

ማኅበሩ የወጣቶችን ተሳትፎ በመደገፍና በማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች በመሳተፍ የተለያዩ ተፅዕኖ የሚፈጥሩና ለአገር ዕድገት መረጋገጥ አስተዋጽኦ የሚያበርክቱ ወጣቶችን ለማፍራት እንደሚሠራም ገልጿል፡፡

መንደሩ፣ ወጣቶች የድርጅት ቆይታቸውን ጨርሰው ከወጡ በኋላ ለሚገጥማቸው የተለያዩ ተግዳሮቶች ከጎን እንደሚቆም፣ ከሕክምናና የሥራ ዕድል ከማግኘት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚተጋም ጠቁሟል፡፡

በኤስኦኤስ ሕፃናት መንደሮች ፕሮግራም ውስጥ ያለፈው ወጣት ኢዮብ እንደሚለው፣ በመንደሩ የተለያዩ አገልግሎቶችን፣ ሥልጠናዎችን አግኝቷል፡፡ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተምሮ የመጀመርያና ሁለተኛ ዲግሪ ይዟል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ የፋይናንስ ባለሙያ ሆኖ እያገለገለም ነው፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን በርካታ አብረውት ያደጉ ወንድምና እህቶቹ በተለያዩ ደረጃዎች ይገኛሉ፡፡ ‹‹የኤስኦኤስ ትሩፋቶች በመሆናችን እንኮራለን፤›› ብሏል፡፡

ሆኖም በኤስኦኤስ የሕፃናት መንደር አድገው፣ ተምረውና የቆይታ ጊዜ ጨርሰው ወደ ማኅበረሰቡ የሚቀላቀሉ ወጣቶች ችግር እንደሚገጥማቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ከርመዋል፡፡ በኤስኦኤስና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተሠራ ጥናትም ይህንኑ አመላክቷል፡፡

በመንደሩ የሚኖሩበት ድባብ ከውጪው የተለየ መሆኑ የሚፈጥረው ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ፣ አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚገጥማቸው ውጣ ውረድ ቀላል አይደለም፡፡

ከመንደሩ ወጥቶ ራሱን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ወጣት ኃይለሚካኤል ዋሲሁን፣ የመንደሩ ሠራተኞች ፍቅርና እንክብካቤ ሰጥተው፣ ዋጋ ከፍለው ማሳደጋቸውን በማስታወስ፣ ከማሳደጊያው ሲወጡ በርካታ ፈተናዎች እንደሚገጥማቸውና መንግሥት ችግራቸውን ሊፈታ እንደሚገባ ተናግሯል፡፡

በማኅበሩ በኩልም ሆነ በሌላ አጋጣሚ፣ በመንደሩ ያደጉ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማጎልበት ሲሠሩ፣ ሼዶች ለማግኘት እንደሚቸገሩ፣ በወረዳና በተለያዩ ተቋማት መታወቂያ ከማግኘት ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት እንደሚፈተኑ አስታውቋል፡፡

ኤስኦኤስ የመንግሥትን ጫና ተካፍሎ ከልጅነት እስከ ጋብቻ እንዳደረሳቸው፣ ከመንደሩ ከወጡ በኋላ በመንግሥት ተቋማት ፈተና እንደሚገጥማቸውም በመጥስ በመድረኩ ለተገኙ የመንግሥት አካላት ‹‹ችግራችንን ለመፍታት ምን እየሠራችሁ ነው›› ሲል ጥያቄ አቅርቧል፡፡

በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕፃናት መብት ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዘቢደር ቦጋለ በማሳደጊያ ተቋማት ያሉ ሕፃናት ትምህርት አግኝተው፣ መሠረታዊ ፍላጎት ተሟልቶ አድገው፣ ወደ ወጣትነት ዕድሜ ደርሰውና ከተቋማት ወጥተው ወደ ሥራ ሲገቡና ከኅብረተሰቡ ሲቀላቀሉ መታወቂያ፣ የሥራ ዕድል ከማግኘትና ከሌላው ማኅበረሰብ እኩል ተጠቃሚ ከመሆን አንፃር ተግዳሮቶች እንዳሉባቸው የሚነሳው ጥያቄ  በአብዛኛው የሚስተዋል ችግር ነው ብለዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት ከኤስኦኤስ ሕፃናት መንደር ጋር በጋራ በመሆን ከሕፃናት መንደር የሚወጡ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ ‹‹የማሳደጊያ ተቋማት የመውጫ ሥርዓት›› ተዘጋጅቷል ያሉት ዘቢደር፣ በረቂቅ ደረጃ ያለው ሥርዓት ተግባራዊ ሲሆን፣ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት የሚተገብሩትና በመንደሩ የሚኖሩ ሕፃናት ሆኑ የቆይታ ጊዜ ጨርሰው የሚወጡ ወጣቶች የሚገጥማቸውን ችግር የሚፈታ ነው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...