Friday, May 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ215 ሺሕ ኩንታል በላይ ዩሪያ ማዳበሪያ የጫነ መርከብ ጂቡቲ ወደብ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለዘንድሮ እርሻ ከሚያስፈልገውና ግዥ እየተደረገበት ካለው 19.4 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ፣ 215,360 ኩንታል ማዳበሪያ የጫነ መርከብ በመጪው እሑድ ጂቡቲ ወደብ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡

በግዥ ላይ የሚገኘውን የ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ የጫነ መርከብ ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ጂቡቲ እንደሚደርስ፣ የኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለሪፖርተር ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ ለዘንድሮ የምርት ዘመን 19.4 ሚሊዮን ኩንታል ጠጣር የአፈር ማዳበሪያ (ኤንፒኤስ፣ ኤንፒኤስ ቦሮንና ዩሪያ) ግዥ በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ጋሻው፣ ከተገዛው ማዳበሪያ ውስጥ እስከ ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ከ12.7 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ማዳበሪያ በ29 መርከቦች ተጓጉዞ ጂቡቲ ወደብ ደርሷል ብለዋል።

ባለፈው የምርት ዘመን (2015/16) ከውጭ የተገዛው የአፈር ማዳበሪያ 13.9 ሚሊዮን ኩንታል እንደነበር ይታወሳል። ዘንድሮ የሚገዛው ማዳበሪያ ካለፈው የምርት ዘመን ማዳበሪያ ጋር ሲነፃፀር የ5.5 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ አለው።

በአጠቃላይ ዘንድሮ ለሚገዛው ማዳበሪያ ግዥ 930 ሚሊዮን ዶላር በጀት በመንግሥት መመደቡ ይታወቃል፡፡

የዘንድሮ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ የተፈጸመው በመስከረም 2016 ዓ.ም. ሲሆን፣ የመጀመሪያው መርከብ በጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም. ጂቡቲ ወደብ ሲደርስ ሥርጭቱም በጥቅምት ወር መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ወደብ ከደረሰው ማዳበሪያ ውስጥ እስከ ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ 11 ሚሊዮን 767,852 ኩንታል በከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎችና በባቡር ወደ አገር ውስጥ ተጓጉዞ፣ በመሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካይነት ለአርሶ አደሮች እየቀረበ መሆኑን አቶ ጋሻው ተናግረዋል።

ዓምና የአፈር ማዳበሪያ ግዥ የተፈጸመው በጥቅምት ወር እንደነበር፣ የመጀመሪያው መርከብ ጂቡቲ በታኅሳስ ወር 2015 ዓ.ም. ደርሶ ሥርጭቱም በዚያው ወር መጀመሩ አይዘነጋም፡፡

ዘንድሮ የሚገዛው 19.4 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ ድረስ ገብቶ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ከሰኔ አጋማሽ እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ እንደሚሆን አቶ ጋሻው አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች