Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየ12ኛ ክፍል የግል ትምህርት ቤት ተፈታኞች ላፕቶፕ እንዲያዘጋጁ መወሰኑ ጥያቄ አስነሳ

የ12ኛ ክፍል የግል ትምህርት ቤት ተፈታኞች ላፕቶፕ እንዲያዘጋጁ መወሰኑ ጥያቄ አስነሳ

ቀን:

የትምህርት ሚኒስቴር በብሔራዊ ደረጃ በወረቀትና በኦንላይን ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና፣ የግል ትምህርት ቤት ተፈታኞች የራሳቸውን ላፕቶፕ እንዲያዘጋጁ መወሰኑ ጥያቄ አስነሳ፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ዓመት በተመረጡ ከተሞች በኦንላይን ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና፣ ተማሪዎች እንዲዘጋጁ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡

የግል ትምህርት ቤቶች የትምህርት ሚኒስቴር ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት ላፕቶፕም ሆነ ሌሎች ግብዓቶችን አዘጋጅተው በፈተና ወቅት ኢንተርኔት ከተጠለፈ ወይም ከተቋረጠ እነሱም ሆኑ ሚኒስቴሩ ከባድ ችግር ውስጥ እንደሚወድቁ ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል ያሉት፣ የአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች ማኅበር ተወካይ ወ/ሮ ሐረገወይን ገረሱ ናቸው፡፡

- Advertisement -

የግል ትምህርት ቤቶች እንዲህ ዓይነት መሠረተ ልማት ያሟላሉ ወይ የሚለውን ራሱ ሚኒስቴሩ መፈተሽ እንዳለበት የተናገሩት ወ/ሮ ሐረገወይን፣ በአገር ደረጃ በትምህርት ቤቶች የኢንተርኔት አቅርቦት ተደራሽ ሆኖ ሲስተሙ በምንም ዓይነት ምክንያት ሳይቋረጥ አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረግ ተሞክሮ ስለሌለ ችግሩ የከፋ እንደሚሆን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር የያዘውን አቋም መሠረት በማድረግ በርካታ የግል ትምህርት ቤቶች ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸው፣ አንዳንድ ወላጆች ሚኒስቴሩ ያስቀመጠውን አሠራር የሚደግፉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ተማሪዎች ባለመዱት አካባቢ ሄደው ከሚፈተኑ ይህ አሠራር የተሻለ መሆኑን ተወካይዋ ገልጸው፣ እንዲህ ዓይነት የፈተና አሰጣጥን የይድረስ ይድረስ ከማድረግ ይልቅ ሰፊ ጥናት ተደርጎበት ቢሰጥ የተሻለ ነው ብለዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ይህንን አሠራር ተፈጻሚ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምሮ እንደነበር አስታውሰው፣ ዘንድሮ በብሔራዊ ደረጃ በኦንላይን ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና ሙሉ ለሙሉ ተዘጋጅቶበታል ማለት ከባድ እንደሆነ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በተለይ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ይህንን እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ መተግበር እንደሚቻል፣ ይህም አሠራር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚተገበር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር አሠራሩን ተግባራዊ የሚያደርገው አዲስ አበባን ጨምሮ በዘጠኝ የክልል ከተሞች በሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች መሆኑን ያስረዱት ተወካይዋ፣ ተማሪዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ የኮምፒዩተር ዕውቀታቸውን እንዲያዳብሩ የትምህርት ካሪኩለሙን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በየትኛውም አገር ለትምህርት የደረሱ ልጆች በቴክኖሎጂ መደገፍ እንዳለባቸው የማያጠራጥር ነው ያሉት ተወካይዋ፣ ነገር ግን መንግሥት ኮምፒዩተር ማስተማር አትችሉም ማለቱንና ይህም ከፈተና አሰጣጡ ጋር የሚጣረስ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ለትምህርት የደረሱ ልጆች በቴክኖሎጂ ታግዘው ካልተማሩ አሁን ሊሰጥ የታሰበው ፈተና ላይ ሊደናገሩ እንደሚችሉ፣ በዚህም የተነሳ በርካታ የግል ትምህርት ቤቶች ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ጠቁመዋል፡፡

መንግሥት ባወጣው የትምህርት ካሪኩለም መሠረት ብቻ ትምህርት የሚሰጥ ከሆነ በርካታ ተማሪዎች ምንም ዓይነት የቴክኖሎጂ ዕውቀት እንደማይኖራቸው ገልጸው፣ ለዚህም እንደ መነሻ ማንሳት የሚቻለው አገሪቱ በቴክኖሎጂ አለማደጓን ነው ብለዋል፡፡

የዲኮሎስት ኑር አካዴሚ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ፋጡማ አህመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ፈተናን በኦንላይን ለመስጠት ያቀደው ዕቅድ በጎ ተግባር ቢኖረውም ግልጽ ያልሆኑ ነገሮችም አሉት፡፡

በተለይ በብሔራዊ ደረጃ የሚሰጠው በወረቀትና በኦንላይን መሆኑን በራሱ ተማሪዎች ላይ ውዝግብ እንዳይፈጥር ሥጋት እንዳላቸው የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጇ፣ አሠራሩም አዲስ ነገር በመሆኑ ዝግጅት ምን ያህል ተደርጎበታል የሚለው በራሱ በወላጆች ላይ ጥያቄ መፍጠሩን አብራርተዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ በጉዳዩ ላይ ከወላጆች ጋር ውይይት ማድረጉን ገልጸው፣ በውይይቱ ጊዜም ግማሽ ያህል ወላጆች አሠራሩን ሲደግፉ ግማሾቹ ደግሞ ጉዳዩን እንዳልተቀበሉት ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር የግል ትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማቶችን እንድታዘጋጁ ባለው መሠረት ትምህርት ቤቱ ዝግጅት ማድረጉን ሥራ አስኪያጇ፣ መንግሥት እንዲህ ዓይነት አሠራር ሲከተል ቀደም ብሎ በተለያዩ ፈተናዎች ሙከራ ማድረግ ነበረበት ብለዋል፡፡

በግል ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ላፕቶፕ እንዲያዘጋጁ እንደተነገራቸው ገልጸው፣ በኦንላይን የሚፈተኑት የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች በተመረጡ ከተሞች መሆኑ ወላጆችን ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

ከዝግጅት አኳያ የትምህርት ሚኒስቴር በትክክለኛው መንገድ አስቦበታል የሚለው ብዙዎችን ጥርጣሬ ውስጥ እንደከተተ ጠቅሰው፣ የግል ትምህርት ቤቶች ሚኒስቴሩ ያስቀመጠውን አሠራር ከተከተሉ ፈታኝ ተመድቦላቸው ፈተናውን እንደሚያከናውኑ እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡

በርካታ የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች የተባሉትን ግብዓት ለማቅረብ እንደማይቸገሩ፣ ነገር ግን ወላጆች የፈተናው ሁኔታ በዚህ መንገድ ሲሰጥ አዲስ ስለሆነባቸው ግርታ እንደፈጠረባቸው አክለዋል፡፡

የአጠቃላይ የትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ ጉዳዩን በተመለከተ ሙሉ መረጃ መስጠት የሚችለው፣ የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና አገልግሎት መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዋ ከሚኒስቴሩ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ እንደገለጹት በኦንላይን የሚሰጠውን ፈተና በተሻለ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡ ወላጆች ስለፈተናው የተሻለ አረዳድና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ልጆቻቸውን እንዲደግፉና በራስ መተማመን ወደ ፈተናው ሊገቡ የሚችሉበትን ዕድል ሊፈጥር እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

በተለይ ፈተናውን እንዲሰጥባቸው በተመረጡ ከተሞች ፈተናውን በኦንላይን የሚወስዱ የዚህ ዓመት የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ከወዲሁ እንዲዘጋጁ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...