Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የሜሪትና የደመወዝ ቦርድ የሚያቋቁም ረቂቅ አዋጅ ቀረበ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የሜሪትና የደመወዝ ቦርድ የሚያቋቁም ረቂቅ አዋጅ ቀረበ

ቀን:

  • ረቂቁ የመንግሥት ተቋማት ሥራን በሦስተኛ ወገን እንዲያከናውኑ ይፈቅዳል

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰብሳቢነት የሚመሩት የሜሪትና የደመወዝ ቦርድን የሚያቋቁም ድንጋጌ ያካተተ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡

በ2010 ዓ.ም. የወጣውን የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅን በመሻር እንደ አዲስ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ፣ ችግሮችን በመፍታት የመንግሥትን የመፈጸም ብቃት የሚያጎለብት፣ የዜጎችን ፍላጎት የሚያረካ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ መሆኑን፣ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ ለፓርላማው ባደረጉት ማብራሪያ አስረድተዋል፡፡

የመንግሥት ሠራተኞችን ስብጥር ግምት ውስጥ የማስገባት፣ የደመወዝ ጭማሪ፣ እርከን፣ ክፍያና ጥቅማ ጥቅም፣ ማትጊያና የማበረታቻ ሥርዓት፣ የሠራተኞች ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ፣ ሥልጠና አሰጣጥ፣ የሥራ ሥምሪት፣ እንዲሁም ነፃና ገለልተኛ ተቋም መገንባትን የተለመ ረቂቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

በ160 አንቀጾች ተዋቅሮ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ፣ በሚያቋቁመው የሜሪትና የደመወዝ ቦርድ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከዘጠኝ በላይ አባላት እንደሚኖሩት ተደንግጓል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾም ምክትል ሰብሳቢ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር፣ የገንዘብ ሚኒስትር፣ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ከሚተገብሩ ተቋማት ሁለት ተለዋጭ አባላት፣ የኢትዮጵያ ስታስትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር፣ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር፣ እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱ በስብሰባው የሚመደቡ ሌሎች አባላት እንደሚኖሩት በረቂቁ ተመላክቷል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ሜሪት ማለት ብቃቱ የተረጋገጠ አዲስ ወይም በሥራ ላይ ያለ የመንግሥት ሠራተኛ ግልጽ፣ ነፃና ገለልተኛ በሆነ አሠራር በውድድርና አብላጫ ውጤትን መሠረት በማድረግ በአንድ የሥራ መደብ ሠራተኛ የሚቀጠርበት፣ ወይም በደረጃ ዕድገትና በሙያ መሰላል የሚያድግበት ወይም የሚደለደልበት የአሠራር ሥርዓት መሆኑ ተደንግጓል፡፡

ቦርዱ በመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር የአፈጻጸም ሥርዓት ግንባር ቀደም የሆኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የመንግሥት ሠራተኞች፣ የዓመታዊ አገልጋይነት ቀን ሽልማት ሥርዓት እንዲኖር የማድረግ ሥልጣን አለው፡፡

በተመሳሳይ መንግሥታዊ አገልግሎትን ለመስጠት በሕግ የተቋቋመና ከመንግሥት በሚመደብ በጀት በሚተዳደር የመንግሥት መሥሪያ ቤት የሚሠሩ ሠራተኞች ደመወዝ፣ በአገር አቀፍ ስኬል መሠረት የተዘጋጀ መሆኑን ያረጋግጣል ተብሏል፡፡

 የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ፣ የደመወዝ ጭማሪ፣ የክፍያና ጥቅማ ጥቅም፣ የማትጊያ ወይም ማበረታቻ ጥናትን ተመልክቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረብ ያለበትን የሲቪል ሰርቪስ የውሳኔ ሐሳብ የማረጋገጥ ሥልጣንም አለው፡፡

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞች ከተሰማሩበት ሙያ መደብ አንፃር መከፈል ያለባቸውን ተስማሚ፣ ተመጣጣኝ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም የተመለከተ የኮሚሽኑ የውሳኔ ሐሳብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ማቅረብና በመንግሥት የተዘጋጀውን አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ሥራዎች በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በአግባቡ መተግበሩን በመቆጣጠር በመከታተል እንደሚያስፈጽም ተደንግጓል፡፡

በረቂቅ አዋጁ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንደ አማራጭ ከግል አስቀጣሪዎች ጋር ሥራዎችን ለሦስተኛ ወገን በውል አስተላልፎ ማሠራት እንዲችሉ፣ ለኮሚሽኑ በየጊዜው ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸው በረቂቁ ተጠቅሷል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ አሠራር የሕግ መሠረት ያልነበረው በመሆኑ ያለውን ችግር እንዲፈታ ጥልቅ ጥናት ተደርጎበትና መመርያ ወጥቶለት የሚተገበርበትን አሠራር ለመፍጠር፣ በረቂቁ አዋጅ መደንገግ አስፈላጊ መሆኑ ተብራርቷል፡፡

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የተወሰኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን በመምረጥ፣ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ዓላማ ያላቸውን ተሞክሮዎች ለመፈተሽና ፕሮግራሞችን ሊተገብር እንደሚችል በረቂቁ ተመልክቷል፡፡

በዚህም በአዋጁ መሠረት የሚወጡ ደንቦችና መመርያዎች ላይ ከተደነገገው ሁኔታ የተለየ አካሄድ በመከተል፣ አዳዲስ የለውጥ አሠራር ሥርዓት በሥራ ላይ ለማዋልና ለመዘርጋት የሙከራ ትግበራ ሊያደርግ እንደሚችል በረቂቁ ተደንግጓል፡፡

ረቂቁ በመንግሥት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ተደራሽና ፈጣን ለማድረግ በዕለት ተዕለት የሚተገበሩ ተግባራትንና ተገልጋይ የሚበዛበትን አገልግሎት በጥናት ላይ ተመሥርቶ፣ በግልና በመንግሥት ልማት ድርቶች የሚያሠራበትን ሥርዓት ማጠናከር አለበት ይላል፡፡

የመንግሥት መሥሪያ ቤት ከኮሚሽኑ ፈቃድ በማግኘት የሕዝብን ጥቅም በማይጎዳና በግልጽ ተለይቶ በተወሰነ የሥራ መደብ ወይም ሥራ በአዋጁና በሌላ አግባብነት ባለው ሕግ መሠረት በውል፣ በሊዝ ወይም በአጋርነት ስምምነት መሠረት ለግል ወይም ለመንግሥት ልማት ድርጅት በውል በማሸጋገር እንዲሠራ ማድረግ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ሥራ የሚቀበለው ተቋም በሥራ አመራር ኢንስቲትዩት የተሰጠ የብቃት ማረጋገጫ ያለው የግል ወይም የመንግሥት ተቋም መሆን እንዳለበት በረቂቁ ውስጥ ሠፍሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...