Friday, May 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከጦርነት ጦስ ያወጡ እጆች

ከጦርነት ጦስ ያወጡ እጆች

ቀን:

‹‹የጦርነት ጥሩ፣ የሰላም መጥፎ የለውም›› ይባላል፡፡ ጦርነት በሰው ልጆችም ሆነ በአጠቃላይ በተፈጥሮ ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ ይህ ነው ተብሎ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ጦርነት ብዙ አስከፊ ገጾች አሉት፡፡ ከሰው ልጆች ሞት፣ አካል መጉደል፣ የንብረት ውድመትና ከቀዬ መፈናቀል ባሻገር ሥነ ልቦናዊ ጠባሳው በዋዛ ታክመው የሚድኑት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ በሰሜኑ አካባቢ የተካሄደው ጦርነት ለዚህ ዋቢ ምስክር ነው፡፡

በጦርነቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሲሞቱ፣ ብዙዎችም ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ አረጋውያን ያለጧሪ ቀርተዋል፣ ልጃገረዶችና ሴቶች ተደፍረዋል፣ ንብረት ወድሟል፣ በርካታ ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፣ በመጠለያ ጣቢያዎችም የዕለት ዕርዳታ ጠባቂ ለመሆን የተገደዱ ብዙዎች ናቸው፡፡

በጦርነቱ ከተጎዱ አካባቢዎች መካከል የሰሜን ወሎ ዞን በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት አንዱ ነው፡፡

- Advertisement -

አቶ ሀብታሙ ደጉ በዋድላ ወረዳ፣ ጋሸና ቀበሌ፣ ‹‹የአጤውኃ›› አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ጦርነቱ፣ በይበልጥ ከጎዳቸው ሥፍራዎች መካከል አካባቢው አንዱና ተጠቃሹ ነው፡፡

በአካባቢው የሚኖሩ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ብዙዎች ሞተዋል፣ ቆስለዋል፡፡ በርካታ መኖሪያ ቤቶችም ወድመዋል፡፡ ቤትና ንብረታቸው ከወደመባቸውና ከተቃጠለባቸው ነዋሪዎች መካከል ወደ 700 የሚጠጉት ‹‹ጨንገር ገብርኤል›› በተባለ ዋሻ ለወራት ተጠልለው ቆይተዋል፡፡

እንደ አቶ ሀብታሙ፣ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውንና በዋሻ ተጠልለው የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ በተደረገው ጥረት የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

በጋሸና ‹አጤ ውኃ›› አካባቢ ቤታቸው የወደመ፣ የተቃጠለባቸውንና በዋሻ ይኖሩ የነበሩትን ነዋሪዎች ቤታቸውን መልሶ በመገንባት፣ ወደ ቀድሞ ኑሯቸው እንዲመለሱ በማድረግ በኩል አስተዋጽኦ ከነበራቸው ግለሰቦች መካከል በአሜሪካ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጥበበ እሸቱ አንዱ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

አቶ ሀብታሙ እንደሚናገሩት፣ በአካባቢው በጦርነቱ ወድመው ከነበሩት ቤቶች ውስጥ 147 ያህሉን አቶ ጥበበ ሠርተው በግንቦት 2015 ዓ.ም. ለነዋሪዎች አስረክበዋል፡፡ በዚህም ‹‹ጨንገር/ገብርኤል ዋሻ›› ይኖሩ የነበሩ የአካባቢው ሰዎች ወደ ቤታቸው ሊመለሱ ችለዋል፡፡ በተጨማሪም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰበትን ‹‹አጣጥ ሥላሴ ገብርኤል›› ቤተ ክርስቲያንን እንደ አዲስ አስገንብተዋል፡፡

ሌላው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ወርቁ ቢተው እንደተናገሩት፣ በዋድላ ወረዳ 26 ቀበሌዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ቀበሌዎች ‹‹ጋሸና›› እና ‹‹መላይ›› የተባሉት በሰሜኑ ጦርነት እጅግ ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸው ናቸው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ቤቶችና ለኅብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ መሠረተ ልማቶች ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚቻል ደረጃ ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡ ነዋሪዎችም ጦርነቱን ሸሽተው በዋሻ ተጠልለው ቆይተዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት በጦርነቱ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስና የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲተባበሩ ባደረገው ጥሪ መሠረት ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦች የአቅማቸውን ድጋፍ አድርገዋል፡፡

አቶ ወርቁ እንደሚናገሩት፣ በወቅቱ በተደረገው ጦርነት ቤት ንብረታቸው ወድሞ ዋሻ ለተጠለሉ ከ700 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች አቶ ጥበቡ ያሠሩዋቸውን ቤቶች ተረክበዋል፡፡ ነዋሪውም ከዋሻ ሕይወት ወጥቶ ወደ ቀዬው ሊመለስ ችሏል፡፡ የጋሸናና የአካባቢው ማኅበረሰብም በችግሩ ወቅት የደረሱለትን ግለሰቦችና ተቋማት ውለታ መቼም የሚዘነጋው አይደለም ብለዋል፡፡

በሪልስቴት መስክ የተሰማሩት አቶ ጥበበ እንደተናገሩት፣ በሰሜኑ ጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም በሚቻልበት ደረጃ የክልሉ መንግሥት ያደረገውን ጥሪ ተቀብለው በጋሸናና አካባቢው የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ተንቀሳቅሰዋል፡፡

‹‹መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ ሰምቼ ወደ ሥፍራው ሳቀና አብዛኞቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ቤታቸው በጦርነቱ ምክንያት ፈርሶና ተቃጥሎ በዋሻ ተጠልለው ነበር፡፡ ስለሆነም እነዚህ ወገኖች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ለማስቻል የግድ ቤታቸው መሠራት ስለነበረበት ከወረዳና ከቀበሌ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር በ1.5 ሚሊዮን ብር ከ140 በላይ ቤቶችን ሠርቼ ለማስረከብ ችያለሁ፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡

‹‹በጎ ሥራ ከልጅነቴ ያደኩበት ነው፡፡ አቅም በፈቀደ መጠን ወገንን መደገፍ የህሊና እረፍት ነው፤›› የሚሉት አቶ ጥበበ፣ ለነዋሪዎች ቤታቸውን ሠርተው ከመስጠት ባሻገር አቅም ለሌላቸው ግለሰቦች በግና ፍየል ገዝተው እንዲያረቡ የገንዘብ ድጋፍ አበርክተዋል፡፡

የ2016 ዓ.ም. የትንሳዔ በዓልን ምክንያት በማድረግ ‹‹በመቄዶኒያ የአረጋውያን መርጃ ማዕከል ለ7,500 አረጋውያን የምሳ ግብዣ ያደረጉት ግለሰቡ፣ ከአንድ መቶ በላይ ለሚሆኑ አረጋውያን ብርድልብስና ጫማ ገዝተው ሰጥተዋል፡፡

እንደ አቶ ጥበቡ፣ በቀጣይ በትግራይ ክልል በጦርነቱ የተጎዱና የተፈናቀሉ አካባቢዎችን በመጎብኘት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዕቅድ ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው፡፡

በባህርዳር ከተማ በሦስት ቢሊዮን ብር ለመገንባት አቅደው የጀመሩትና በአካባቢው በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ የተቋረጠውን ዘመናዊ የሪዞርት ግንባታ በማጠናቀቅ ከተማዋ ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ እንዲኖራት ለማስቻል እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ