Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በመንግሥትና በግል ተቋማት ከውጭ የገቡ 900 ሺሕ የውኃ ፓምፖች የተፈለገውን ያህል አገልግሎት አልሰጡም ተባለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ፓምፖቹ አርሶ አደሮቹ ጋ እንደደረሱ ወዲያውኑ ይበላሻሉ››

ውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

በተለያዩ ጊዜያት ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው በመንግሥትና በግል ተቋማት ለመስኖ ልማት እንዲውሉ ከውጭ የገቡ 900 ሺሕ የውኃ ፓምፖች፣ በተፈለገው ልክ አገልግሎት መስጠት አለመቻላቸውን ኤስኤንቪ የተሰኘ ድርጅት አስታወቀ፡፡

ድርጀቱ ይህንን የገለጸው ጀፀሐይ ኃይል የሚሠሩ ፓምፖችን በመጠቀም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግና የአርሶ አደሩን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን በተመለከተ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዓርብ ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ውይይት ሲያደርግ ነው፡፡

የውይይት መነሻ ጽሑፉ ያቀረቡት የኤስኤንቪ ኢትዮጵያ የልማት ድርጅት  የሴፍ ፕሮጀክት የቴክኒመ ባለሙያ አቶ ዓለማየሁ ዘለቀ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ የመስኖ ውኃ ፓምፖችን ጠቀሜታ ለአርሶ አደሮች ለማስተዋወቅ ድርጀቱ ፕሮጀክት ቀርፆ እየሠራ ነው፡፡

በመንግሥትም ሆነ በግል ተቋማት በነዳጅ ወይም በናፍጣ የሚሠሩ በርካታ የውኃ ፓምፖች በተለያዩ ጊዜያት አገር ውስጥ ገብተው ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ቢሆኑም፣ አርሶ አደሮች ስለውኃ ፓምፕ በቂ ዕውቀት ስለሌላቸው በቂ አገልግሎት ሳይሰጡ ተበላሽተው እንደሚቀመጡ ገልጸዋል፡፡

በተለይም ከከተማ ወጣ ያሉ ገጠራማ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች የውኃ ፓምፖችን ከግል ተቋማት ወይም ከመንግሥት በድጎማ መልክ ቢያገኙም፣ በአብዛኛው እንደማይጠቀሙባቸው አስረድተዋል፡፡

አርሶ አደሮች ከዕውቀት ባለፈ የውኃ ፓምፖቹን ለመጠቀም ነዳጅ ወይም ናፍጣ ለመግዛት ረዥም ርቀት ስለሚጓዙ መጠቀም እንደማይፈልጉ ገልጸው፣ ብዙ ጊዜ በመስኖ ልማት የሚጠቀሙት ከተማ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አማራ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ለመስኖ ልማት ምቹ ቢሆኑም፣ በክልሎቹ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ስለሚያስፈልጉና ለአርሶ አደሮች አቅም ብቻ የሚተው ባለመሆኑ በዘርፉ የተፈለገውን ያህል መጠቀም አለመቻሉን አብራርተዋል፡፡

አንድ አርሶ አደር በፀሐይ ኃይል የሚሠራ ፓምፕ ከተተከለ ረዥም ጊዜ መጠቀም እንደሚቻል ገልጸው፣ ነገር ግን ይህን ሶላር ፓምፕ በአንድ ጊዜ ለመትከል ከፍተኛ ወጪ ስለሚጠይቅ፣ አብዛኛዎቹ አርሶ አደሮች መጠቀም እንደማይፈልጉ ጠቁመዋል፡፡

በተለይ መንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት አንድ የውኃ ፓምፕ ከውጭ ሲያስገቡ ከ400 እስከ 500 ሺሕ ብር እንደሚያወጡ፣ ለአርሶ አደሩ ሲደርስ ደግሞ አርሶ አደሩ ከዚያ በላይ ወጪ አውጥቶ ሊገዛ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮች ከወለድ ነፃ የሆነ ብድር ተመቻችቶላቸው በፀሐይ ኃይል ፓምፕ መትከል ቢችሉ፣ የመስኖ ልማትን ማሳደግ እንደሚቻል ጠቅሰው፣ ከውጭ የገባው የውኃ ፓምፕና የባለሙያ ቁጥር ሲታይ ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ስላለው፣ ብዙ ጊዜ ከውጭ የሚገቡ የውኃ ፓምፖች ሲበላሹ ያላግባብ ይባክናሉ ብለዋል፡፡

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ወልዱ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በርካታ የኢነርጂ ሀብት ያላት አገር ብትሆንም እስካሁን ድረስ በዘመናዊ መንገድ መጠቀም አልተቻለም፡፡

እ.ኤ.አ. በ2030 በኢትዮጵያ የሚገኙ 65 በመቶ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ኃይል እንዲያገኙ እንደሚደረግ፣ 35 በመቶ ደግሞ ከተለያዩ የኢነርጂ አማራጮች እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ገጠራማ አካባቢዎች 201 አነስተኛ የፀሐይ ማመንጫ ጣቢያዎች ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር እየተገነቡ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ጣቢያዎቹም ተገንብተው ሲጠናቀቁ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት 900 ሺሕ ከውጭ የገቡ የውኃ ፓምፖች እንዳሉ፣ ነገር ግን ፓምፖቹ አርሶ አደሮች ዘንድ ከደረሱ በኋላ ወዲያ እንደሚበላሹ ተናግረዋል፡፡

የገጠር ማኅበረሰብ ክፍሎች የባዮ ጋዝና ሶላር ቴክኖሎጂዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ ከልማት ባንክ ብድር እንዲመቻችላቸው እየተደረገ መሆኑን፣ በዚህም በርካታ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ አክለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ከክልሎች ጋር በመሆን 51 በመቶ ማኅበረሰብ ክፍል በባዮ ጋዝ ልማትና በፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን መደረጉን፣ ወደፊት በ500 ሚሊዮን ዶላር የሚገነቡ 201 አነስተኛ የፀሐይ ማመንጫ ጣቢያዎች ሲጠናቀቁ የተሻለ ዕድል መፍጠር ይቻላል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች