Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አማዞንን ጨምሮ ጉግልና አፕል የተጨማሪ ዕሴት ታክስ እንዲመዘገቡ የሚያስገድድ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ እንደ አማዞን፣ ጉግል ፕሌይና አፕል የመሳሰሉ የኤሌክትሮኒክ ግብይት የሚያከናውኑ ኩባንያዎች ለተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ፡፡ 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት የተመለከተውና ለዝርዝር ዕይታ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመራው የተጨማሪ እሴት ታክስ ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ፣ እንደ የሌሎችን ምርቶች ለገበያ የሚያቀርቡ የውጭ ኩባንያዎች እንደ ጉግል ፕሌይና አፕል ስቶር በመሳሰሉ ሥርዓቶች አማካይነት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚያከናውኑት ግብይት ለተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያ መመዝገብ እንዳለባቸው ይደነግጋል። 

በረቂቅ አዋጁ እንደተመለከተው፣ ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ የባንክ ሒሳብ መክፈት አለባቸው፡፡ ባንክም ከሒሳባቸው ላይ ታክሱን ቀንሶ ያስቀራል፡፡ ኩባንያዎቹ በማናቸውም ምክንያት ያልተመዘገቡ ከሆነ፣ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ከሩቅ የሚሰጥ አገልግሎት የሚያገኝ ለታክሱ ያልተመዘገበ በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ሰው መመዝገብ፣ ታክሱን ራሱ ከሚከፈለው ገንዘብ ላይ በማስላት መክፈል እንዳለበት የሚደነግጉ አንቀጾች በረቂቁ ተካተዋል፡፡

የአዋጁን መሻሻል አስፈላጊነት ለምክር ቤቱ ገለጻ ያደረጉት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ፣ ‹‹አዋጁ ከወጣ ወዲህ የኤሌክትሮኒክ ግብይትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙ አዳዲስ ዕሳቤዎችን በአገሪቱ የሕግ ማዕቀፎች ውስጥ ማካተት አስፈላጊ በመሆኑ ነው፤›› ብለዋል። 

ረቂቅ አዋጁ ሲፀድቅ ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት በ1994 ዓ.ም. የወጣውንና በ2001 ዓ.ም.፣ እንዲሁም በ2011 ዓ.ም. ማሻሻያዎች የተደረጉበትን አዋጅ እንደሚሽር ተመላክቷል። ረቂቁ ካካተታቸው ማሻሻያዎች መካከል ለፋይናንስ ሥርዓቱ ተሰጥቶ የነበረው ከታክስ ነፃ የመሆን መብት አንዱ ነው። በዚህም ለፋይናንስ ሥርዓቱ ተሰጥቶ የነበረው ከታክስ ነፃ የመሆን መብት፣ ተቋሙን ሳይሆን የአገልግሎቱን ባህሪ እንዲመለከት በማድርግ ብድር ከመስጠት፣ ከመሰብሰብ፣ ከተቀማጭ ገንዘብ፣ ከአክሲዮን፣ ከቦንድ፣ ከሌሎች የዋስትና ሰነዶች ከመገበያየት፣ የኢንቨስትመንት ፈንድ ከማስተዳደርና የጡረታ ፈንድ ከማቋቋም ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች ብቻ ከታክሱ ነፃ እንደሚሆኑ ደንግጓል። 

ከዚህ ውጪ የፋይናንስ ተቋማት በተወሰነ ክፍያ (ኮሚሽንና የአገልግሎት ክፍያ) የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ከታክሱ ነፃ ከተደረጉት መካከል እንዳይካተቱ መደረጋቸው ተመላክቷል። ለዚህ ማሻሻያ በምክንያትነት የቀረበው አብዛኞቹ አገልግሎቶች ከታክስ ነፃ የመሆን መብት ከተሰጠበት ዓላማ ጋር የማይገናኙ በመሆናቸው፣ ለይቶ መዘርዘርና ከዚያ ውጪ ያሉት ደግሞ ታክስ እንዲከፈልባቸው ማድረግ ተገቢ በመሆኑ ነው ሲል አስቀምጧል። 

በተጨማሪም ባለሦስት እግር ተሽከርካሪን ሳይጨምር ከስምንት መቀመጫ በታች ያላቸው ተሽከርካሪዎች ተጨማሪ እሴት ታክስ እንደሚከፍሉ የተደነገገ ሲሆን፣ ከሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ውጪ ድጋፍ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑ ተገልጿል።

ከሕዝብ ትራንስፖርት ውጪ ለሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎቶች እንዲህ ዓይነቱን ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ባለመሆኑ፣ ለትራንስፖርት አገልግሎት የተሰጠው ከታክሱ ነፃ የመሆን መብት ባለ ሦስት እግርን ሳይጨምር ከስምንት መቀመጫ በታች ያላቸውን ሌሎች ተሽከርካሪዎች እንዳይመለከት ተደርጓል፡፡ 

አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ወጪ ለመቀነስ በማሰብ ከታክሱ ነፃ ተደርገው የነበሩ የኤሌክትሪክና የውኃ አቅርቦት፣ የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያ ከሚወሰን በታች የኤሌክትሪክና የውኃ ፍጆታ ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲከፍሉ በረቂቁ ተመልክቷል።

ማሻሻያ ማድረግ ያስፈለገው ኤሌክትሪክና ውኃ በብዛት የሚጠቀመው የመክፈል አቅም ያለው የኅብረተሰብ ክፍል በመሆኑ፣ የተሰጠው መብት ይበልጥ ተጠቃሚ የሆነውም ይህ የኅብረተሰብ ክፍል ስለሆነ ነው ተብሎ በረቂቁ ተገልጿል፡፡ 

ከግለሰቦች ታክስ ለመሰብሰብ የገቢዎች ሚኒስቴር በየአካባቢው መዋቅር ስለሌለው ክልሎች ታክሱን እየሰበሰቡ እንዲጠቀሙበት ውክልና ሰጥቶ እንደነበር፣ አዲስ በሚሻሻለው ረቂቅ የተጨማሪ እሴት ታክስ በፌዴራል መንግሥት እንደሚተዳደር የተላለፈው ውሳኔ በትክክል እንዲሠራበትና የገቢዎች ሚኒስቴር ቅርንጫፎች በሌሉባቸው አካባቢዎች የክልል የገቢዎች ቢሮዎች በግልጽ የውክልና አሠራር እንዲከናወኑ ማድረግ የሚያስችል አንቀጽ በረቂቁ ተካቷል፡፡

ለማሻሻያው ምክንያት የሆነውም ከግለሰቦች የሚሰበሰበው ታክስ በክልሎች ተሰብስቦ ጥቅም ላይ መዋሉ በግብዓት ላይ የተከፈለውን ታክስ በማቀናነስ ረገድ ችግር ስለሚታይበት፣ በፍትሐዊነት ረገድ ለቅሬታ ምንጭ መሆኑ በረቂቁ ውስጥ ሠፍሯል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች