Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

ቀን:

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና ጫና እያደረገብን ነው የሚል ተቃውሞ እያቀረቡ ነው፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት በሰኔ 2013 ዓ.ም. በተካሄደው 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ከ547 የሕዝብ ተወካዮች ምርጫ ክልሎች ውስጥ በ436 የምርጫ ክልሎች ምርጫ የተካሄደ ሲሆን፣ በመጪው ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ደግሞ ያለፈው ምርጫ ባልተካሄደባቸው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በሶማሌ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በአፋር ክልሎች ይካሄዳል፡፡

በአሁኑ ምርጫ ከሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) አንዱ ነው፡፡ ቦዴፓን ወክለው በዚህ ምርጫ ከሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች መካከል የፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ አባል መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ፈተናዎች እያጋጠሙን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

አዳራሽ ከመከልከል በተጨማሪ፣ ‹‹የብልፅግና ካድሬዎች በየቀበሌው እየገቡ ብልፅግናን ለማይመርጡ ካርድ አትስጡ የሚል ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ፤›› ብለዋል፡፡ ይህንን ችግር ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቃቸውንም አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የቅስቀሳ ማስታወቂያዎችንና ባነሮችን መቅደድ የመሳሰሉ ጫናዎች ፓርቲያቸው እየገጠመው መሆኑን የተናገሩት መብራቱ (ዶ/ር)፣ ‹‹በብልፅግና የሚመራው መንግሥት በድባጤ ወረዳ አዳራሽ እንዲፈቀድ በደብዳቤ ቢጠየቅም፣ አልሰጥም ብሎ በመከልከሉ ዛፍ ሥር ሆነን ስብሰባ እያካሄድን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ብልፅግናን ካልመረጣችሁ ማዳበሪያ አንሰጥም፣ ግብዓት አንሰጥም የሚሉ ማስፈራሪያዎችና ማሸማቀቅና ማዋከብን ጨምሮ እናስራችኋለን የሚል ዛቻ እየገጠመን ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ 99 የክልል ምርጫ መቀመጫዎች በዚህኛው ምርጫ የሚካሄድባቸው 71 የክልል ምክር ቤትና ስድስት የፓርላማ መቀመጫዎች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስተዳደር በጻፈው ደብዳቤ፣ ከዚህ ቀደም ፓርቲዎቹ የሕዝብን የጋራ ሀብት መጠቀም እንደሚችሉ በተመለከተ ያስተላለፈውን ሰርኩላር ባለመቀበል፣ ቦዴፓ በቡለንና በድባጤ ምርጫ ክልሎች አዳራሽ መከልከሉን ከፓርቲው አቤቱታ እንደደረሰው አስታውቆ ነበር፡፡ ቦርዱ በደብዳቤው ፓርቲው ለምርጫ ዝግጅት አዳራሾችን እንዲጠቀም ድጋፍ እንዲደረግለት፣ በተዋረድ ለሚመለከታቸው አካላት እንዲያሳውቅ ሲል ማሳሰቢያ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ ቦርዱ ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ለብልፅግና ፓርቲ በጻፈው ደብዳቤ፣ በቡለን ምርጫ ክልል ሥር በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች፣ የቡለን ወረዳ የብልፅግና አመራሮችና ካድሬዎች፣ በየምርጫ ጣቢያው እየተገኙ ካርድ እንዳይወስዱ ዛቻና ማስፈራሪያ እያደረሱባቸው መሆኑን ቦዴፓ እንደገለጸለት አስታውቋል፡፡

በመሆኑም ብልፅግና ፓርቲ የቀረበውን ቅሬታ በማጣራት ምላሽ እንዲያቀርብና ድርጊቱ ተፈጽሞ ከሆነ መሰል ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ፣ በፓርቲው ጽሕፈት ቤት በኩል በተዋረድ ምርጫ በሚደረግባቸው አካባቢዎች ሙሉ መረጃው እንዲተላለፍ ቦርዱ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገሃስ ሙሐመድ፣ ክልሉ በቅርቡ ከጦርነት የወጣ በመሆኑ ችግሩ ዘርፈ ብዙ ቢሆንም፣ ሥራቸውን እያከናወኑ መሆናቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ከመንግሥት አካላት የሚመጣው እንቅፋት ብዙ ነው የሚሉት አቶ ገሃስ፣ በአንዳንድ ቦታዎች የዴሞክራሲ ሥርዓት እያሉ የሚያወሩት የገዥው ፓርቲ ሰዎች የቃሉን ትርጉም በውሉ አያውቁትም ብለዋል፡፡

‹‹በዚህ በኩል ስለዴሞክራሲ ያወራሉ፣ በዚያኛው ዘወር ብለን ለምርጫ እንወዳደራለን ስንል ፍላጎት የላቸውም፣ እኛን ማየት አይፈልጉም፤›› በማለት፣ ‹‹የስብሰባ አዳራሽ ቢጠየቁ እንደማይሰጡ እናውቃለን፣ ነገር ግን ግርግር ላለመፍጠር በየዛፉ ሥር ነው ስብሳባ የምናደርገው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ለመወዳደር እኩል ሜዳ አግኝተን አናውቅም፣ አሁንም እናገኛለን ብለን አንገምትም፡፡ ይህንን ለመገመት መጀመሪያ ሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ዴሞክራሲ የሚለውን ቃል በተግባር ምን እንደሆነ ማወቅ አለባቸው፤›› የሚሉት አቶ ገሃስ፣ ‹‹እያየን ያለው ሁኔታ እየባሰ እንጂ እየተሻሻለ አይደለም እኛም ግን እንታገላለን፤›› ብለዋል፡፡

በሶማሌ ክልል የሚወዳደረው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) መሪ አቶ አብዱራህማን መሃዲ፣ የምርጫ ዝግጅታቸውን በተመለከተ ለሪፖርተር እንደነገሩት፣ ‹‹ከዚህ በፊት በነበረው ምርጫ እንዳየነው ይህ ምርጫ ምንም ተስፋ የለውም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አሁንም የምርጫ ተወካዮቻችን ጉዳት እየደረሰባቸው ነው፣ መንግሥታዊ አስተዳደሩን የተቆጣጠሩት የገዥው ፓርቲ ሰዎች እኛን ማየት አይፈልጉም፤›› ብለው፣ ‹‹በዚህ ምርጫ የምንሳተፈው ለልምድ እንጂ ወንበር እናገኛለን በሚል ተስፋ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትና እናት ፓርቲ ከሁለት ሳምንት በፊት በሰጡት መግለጫ፣ አገር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ከመሆኗና በተለያዩ አካባቢዎች ካለው የፀጥታ ሁኔታ አኳያ ምርጫ ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታዎች እንደሌሉ በመጥቀስ፣ አስቻይ ሁኔታዎች እስኪፈጠሩ ምርጫው እንዲዘገይ ለቦርዱ በደብዳቤ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ቦርዱ ያቀረቡትን ጥያቄ ከግንዛቤ በማስገባት፣ የተጠየቀውን ማስተካከያ ማድረግ ባለመቻሉ፣ በተጠቀሰው ቀሪና ድጋሚ ምርጫ እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...