Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትዛሬም ኧረ በሕግ!

ዛሬም ኧረ በሕግ!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣ እንደነገሩም ሆነ ለአንደበት ወግ ያህል ታስቦ፣ ተከብሮ ነግሦ የዋለው የፕሬስ ነፃነት ቀን፣ ዛሬም እንደ እንደ ሁልጊዜው መነጋገሪያ ጉዳያችን ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት የሁልጊዜም፣ በተለይም ለዴሞክራሲ በሚታገሉ ወደ ዴሞክራሲ እንሸጋገር በሚሉ አገሮችና ሕዝቦች ውስጥ የሁሉምና የአገር ሁሉ የሆድ ቁርጠት ሆኖ የሚታይበት ምክንያት በመብቶች መካከል መበላለጥ ስላለ፣ አንዱ መብት ከሌላው የሚልቅ ስለሆነ አይደለም፡፡ በመብቶች መካከል መበላለጥ የለም ቢባልም የፕሬስ ነፃነት ግን በራሱ በዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶች ሥርዓት መሠረት የመብቶች ሁሉ የማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡ ‹‹መጀመሪያ የመቀመጫዬን›› ያለችው የዝንጀሮዋ ታሪክና ምሳሌ ይህንን በደንብ ያስረዳል፡፡ ዝንጀሮ መጀመሪያ የመቀመጫዬን እሾህ አውጡልኝ ያለችው ከመላ የሠራ አካሏ ውስጥ/መካከል መቀመጫዋን አብልጣ፣ ወይም እሱ በልጦባት፣ ወይም የክሱ ሥቃይ ብሶባት አይደለም፡፡ መጀመሪያ መቀመጫዋ ውስጥ የተሰገሰጉትን ካወጡላት፣ ሌላው የሰውነቷ አካል ውስጥ መውጣት ያለበትን እሾህ ሁሉ እሷም እያገዘች ስለምታወጣው ነው፡፡

ይህንን አገራችንም ውስጥ በዝንጀሮ ተረትና ምሳሌ አማካይነት የሚታወቀውን ጥበብ ነው በተለያዩ ዓለም የሚገኙ፣ በተለያየ ዘመን የኖሩ፣ የተለያየ ርዕዮተ ዓለም ጭምር ያላቸው የታወቁ ሰዎች ያሉትና ለጥቅስ የበቃ አባባል የሆነው፡፡ ለምሳሌ፣

- Advertisement -

‹‹Our liberty depends on the freedom of the press, and that can not be limited without being lost.››

Thomas Jefferson

‹‹The Mahpix, the indespensable condition of nearly every other form of freedom

Justice Cardogo

‹‹The inevitable general staff of all liberties, the only effective guardian of every other right.››

Kare Marx  ያሉት፡፡   

ይህን የመሰለ ሁሉም የተመድ የራሱ የሰብዓዊ መብቶች ‹‹ሕግና ፍትሕ›› ጥምር የሚያምኑበት የሚመኩበት እውነትና እምነት ግን አጣማጆች አሉ፡፡ ያንኑ ያህል እንደ ነፃነቱ ከሰማይ ከምድር የከበደ ኃላፊነት አለበት፡፡ የፕሬስ ነፃነት ግዴታና ኃላፊነት አለበት፡፡ ኃላፊነቱና ግዴታውም ይህንን ሸክም ተመቻችቶ መያዝ የሚያስችል ጨዋነት ይጠይቃል፡፡ በተለይም ነፃነቱ የተጻፈበትን የተደነገገበትን ሕገ መንግሥት ይሁን ሌላ ዓይነት ሕግ ተፈጻሚነት አሰነካክሎ ከኖረ አድራጊ ፈጣሪነት፣ ሕግ ገዥ ወደ ሆነበት ዴሞክራሲ በሚደረግ ሽግግር/ለውጥ ውስጥ የሚገኝ አገር ሚዲያ፣ ጋዜጠኛ ከፍተኛ ጥንቃቄ ብልኃት የሚፈልግ ትግል ውስጥ መኖሩን/መሆኑን ማወቅ አለበት፡፡ ከነፃነቱ ይበልጥ ነፃነቱን አቅፎና ደግፎ ዘላቂ ህልውና ለሚሰጠው ለዴሞክራሲ መደላደል መትጋት አለባቸው፡፡

ሰላሳ አንድ ዓመት የሞላው ዓለም አቀፋዊው የፕሬስ ነፃነት ቀን አመጣጥ ከኢትዮጵያ የነፃ ፕሬስ ትግል ታሪክና ሒደት ጋር የአንድ ዘመን ‹አብሮ አደጎች›/ተጓዦች ናቸው ወይም ነበሩ፡፡ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንን ፀንሶ አምጦ የወለደው ሚያዝያ 1983 ዓ.ም. የታወጀው የዊንድሆክ ዲክላሬሽን ነው፡፡ ዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንን አንድ ብሎ ማክበር የጀመረው ይህን የዊንድሆክ (ናሚቢያ) ዲክላሬሽን መነሻ አድርጎ የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 1993 በሰጠው ውሳኔ መሠረት ነው፡፡ ቀኑና ወሩ ሜይ ውስጥ የሆነበትም ምክንያት ‹‹The Windhoek Declaration for the Development of a Free, Independent and Pluralistic Press›› የተባለውን አቋም ያወጀው ስብሰባ ናሚቢያ ዊንድሆክ የተካሄደው ከ29 አፕሪል እስከ 3 ሜይ የ1991 ዓ.ም. በመሆኑ ነው፡፡ ለማስታወስ ያህል ከሚያዝያ 21 ቀን እስከ ሚያዝያ 25 ቀን የ1983 ዓ.ም. በተካሄደው የአፍሪካውያን የናሚያ ስብሰባ ላይ ተሳታፊ ጋዜጠኛ ሊኖራት የማትታሰበው ኢትዮጵያ ገና፣ ነገር ግን የመጨረሻው የደርግ አስተዳደር ውስጥ ነበረች፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን ለአሥራ ሰባት ዓመታት ሲገዛ የቆየው የወታደራዊ አምባገነን መንግሥት መገርሰስ የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩንና መንግሥቱን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንደ አዲስ ለመገንባት የሚችልበትን ዕድል የከፈተ ታሪካዊ ወቅት በመሆኑ…›› የተባለው በተለይም፣ ‹‹… ሰብዓዊ መብቶች ያላንዳች ገደብ ሙሉ በሙሉ ተከብረዋል…›› ተብሎ በሽግግሩ ወቅት ቻርተር የታወጀው ገና ሐምሌ 1983 ነው፡፡ ከጥቅምት 21 ቀን 1985 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናው የፕሬስ ነፃነት አዋጅም በሕግ ፕሬስ ነፃ ነው ብሎ አወጀ፡፡ ቅድሚያ ምርመራና ማናቸውም ሌላ ተመሳሳይ ገደብ ተከልክሏል አለ፡፡ የኢትዮጵያውያንን በፕሬስ ሥራ የመሰማራት መብት አወቀ፡፡ መረጃ የማግኘት ነፃነት አወጀ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ‹‹የፕሬስ ውጤቶችን ይዘት ሕጋዊነት›› የማረጋገጥ ሕጋዊነት የጋዜጠኛው፣ የአሳታሚው ብቻ አደረገ፡፡

ይህ ሕግ ከመውጣቱ በፊት ጭምር መጀመሪያ እንደ አሸን የፈላው፣ ከዚያም ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ቦግ ብሎ እስከ ጋዜጣ አዟሪ ድረስ የወረደ የሥራ ዕድል ፈጥሮ የነበረው፣ ነገር ግን ከዴሞክራሲ ግንባታ ጋር አልተዋወቅ ያለው፣ መልሶም ነፍስ ሳይዘራ ለብዙ ጊዜ የቆየው ጋዜጠኝነት/አሳታሚ የሙያ ሥራ የሚያጎናፅፈው ነፃነት፣ ኃላፊነትንና ዕውቀትን ይጠይቃል፡፡ የፕሬስ ነፃነት የነፃነቶች ሁሉ ፊት አውራሪ ነገር በተነሳ ቁጥር ሁልጊዜም ሊጨንቀን ሊጠበን የሚገባው ይህ ዴሞክራሲን የማደላደል፣ ዕውቀትን የመገንባት፣ ሥነ ምግባራዊ ጋዜጠኝነትን (ባለሙያነትን) የነፃቱና የሙያው የእግር መንገድና የዓይን ብርሃን ማድረግ ይሻል፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያው ሥነ ምግባር የአመለካከት አድልኦን በአሸናፊና ክፍት በሆነ አቋምና ገለልተኛ በሆነ ስሜት መቅረብ፣ መመርመርና መተርጎም ነው፡፡ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎችና በየአገሩ ሕገ መንግሥት መተማመኛ የተሰጠው (የአንቀጽ 29 በመላው ዓለም ደግሞ የአንቀጽ 19 መብት) የአመለካከት ሐሳብን በነፃ የመናገርና የመግለጽ መብት፣ ማንኛውም ሰው ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል ይላል፡፡ የሙያው ሥነ ምግባርና ነፃነቱ የሚያሸክመው ኃላፊነትና ጨዋነት ደግሞ ክፍት በሆነ፣ በሌላ አመለካከት ባልተዘጋ አዕምሮ፣ የአመለካከት አድልኦን ባሸነፈ አዕምሮ፣ ገለልተኛ በሆነ ስሜት መስማትን፣ መቅረብን፣ መመርመርንና መተርጎምን ይጠይቃል፡፡ የፕሬስ ነፃነት በተነሳ ቁጥር ነፃነቱን እናክብር፣ እናስከብር ባልን ቁጥር፣ ስለነፃነቱ በተቆረቆርን፣ ተቆረቆርን ባልን ቁጥር ሆድ ቁርጠታችን መሆን ያለበት ይህ ነው፡፡ ዴሞክራሲን እያደላደልን የዴሞክራሲን መደላደል እያገዝን ነው ወይ? ነፃነቱ የሚፈልገው ኃላፊነትና ጨዋነት እያሟላን ነው ወይ?

የዘንድሮው 31ኛው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ደግሞ መሪ ቃሉን የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ አድርጎታል፡፡ ሁሉም መሪ ቃሎች የዓመቱ በዓል የሚከበርበት የተለየ ‹ልብስ› ዓይነት ባይሆንም፣ በተለይም የኢንቫይሮመንት ጉዳይ ከዋናው ጉዳይ በላይ ሆድ የሚቆርጥ ነው፡፡ የምድራችን ለሕይወት፣ ለሰው ልጅ ህልውና ምቹ ሆኖ መቀጠል አደጋ ላይ ከወደቀ ቆይቷል፡፡ ይህ አደጋ የሰው ልጅ አኗኗሩን እንዲያርቅ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ካወጀና የጣር ጩኸት መሰማት ከጀመረ ብዙ ጊዜ ቢሆነውም፣ ሰው ግን እንደ አገሩ ኃያልነትና ‹ጥጋብ› አኗኗሩን ማረም እሺ አላለም፡፡ የዘንድሮ የፕሬስ ነፃነት ቀን ሚዲያውን፣ ጋዜጠኝነትን ይህም ሥራ የእናንተ ነው እያለ ነው፡፡ ተፈጥሮ ያለ ሰው መኖር ትችላለች፣ ሰው ግን ያለ ተፈጥሮ መኖር አይችልም፡፡ ሰው ተፈጥሮን አደጋ ላይ እየጣለ የምድርን ጤናማ ሆኖ፣ ለሕይወት ምቹ ሆኖ መቀጠልን እየተፈታተነና አደጋ ላይ እየጣለ ነው፡፡ ሚዲያው ይህን እውነት የዓመት አንድ ቀን ተረኛ ወሬ ሳይሆን የዘወትር አደራው አድርጎ ይህን ሀቅ መናገር፣ ይህን እውነት መለፈፍ አለበት፡፡ እውነቱን በመናገሩም የሚመሽበትና ‹‹የመሸበት ማደር›› የሚባል አደጋ የለበትም፡፡ ይልቅስ አደጋው ጉዳዩን አድበስብሶ ዝም ማለት ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ አገራችን ውስጥ በዚህ በኢንቫይሮመንት ዘርፍ ያተኮረ የሚዲያ ማኅበር እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ የተቋቋመው በ1997/98 አካባቢ እንደሆነ የሚጠቁሙ መረጃዎችን ከየቦታው አይቻለሁ፡፡ ማኅበሩ ግን በአፍላ የሕይወት ዘመኑ የነበረው ዜና ዛሬ የለም፡፡ ከናካቴውም ድምፁ ከጠፋ በጣም ቆይቷል፡፡ የዘንድሮው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ደግሞ ‹‹ጋዜጠኝነትና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት አሁን በምንገኝበት ዓለማዊ ኢንቫይሮመንታዊ ቀውስ ዓውድ›› የሚል መሪ ቃል ይዞ አክብሩኝ ሲል፣ ይህ የጋዜጠኞች ማኅበር ዋናው ባለጉዳይ የክብረ በዓሉ ግንባር ቀደም መሪ ምልክት መሆኑ ቀርቶ ጭራሽ ‹‹ድራሹ›› ሲጠፋ ምንድነው ብዬ ጠየቅሁ፡፡ የተረጋገጠ ነገር ባላገኝም ጉዳዩ ይበልጥ መጣራት መጠናት ያለበት ቢሆንም፣ የሚታመኑና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ማኅበሩም ውስጥ ንቁ ተሳታፊ የነበሩ ወዳጆች እንደነገሩኝ ግን አሁን በሕይወት ያለ ማኅበር አይደለም፡፡ የዚህ ምክንያት በወቅቱ የነበረው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ የ2001 ዓ.ም. ሕግና እሱን ለማስፈጸም የውጡ መመርያዎች ሰለባ ሆኖ አላሠራው ብሎ፣ በአብዛኛው ወጪውን የሚሸፍነው የውጭ ዕርዳታ በመሆኑ እንደሆነ ይነገራል፡፡ መጣራት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ሕገ መንግሥቱ በሚደነግገው መሠረት ለማንኛውም ዓላማ የመደራጀት መብት የማንኛውም ሰው፣ የማንኛውም ሙያ ጭምር ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት፣ የመደራጀት መብት የትኛውም ቦታ የትኛውም ሙያ ውስጥ ሲያጥርና ሲያጣጥር አደጋ ላይ ሲወደቅ ጉዳዬ ብሎ መታገል አለበት፡፡ የኢንቫይሮመንታል ጋዜጠኞች ማኅበር ምን ሆነ ብለን የምናነሳውም፣ የተጣራና የተረጋገጠ ምላሽ ያስፈልገዋል የሚባለውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ ግን (ይህን ጉዳይ አጋጣሚ ፈልጎ ከማንሳት የበለጠ አሳፋሪ ነገር አለመኖሩን ከማመንና ከግለ ሂስ ጋር) ኢንቫይሮመንት የዓለም አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን፣ ከኑክሌር መሣሪያ ሥጋትና ኮቪድን ከመሳሰሉ በሽታዎች ሥጋት ጋር የኢንቫይሮመንቱ አደጋ ላይ መውደቅ ሌላው በሰው ልጅ ላይ ያንዣበበ አደጋ ነው፡፡ ተደጋግሞ እንደተገለጸው የምድራችን ለሕይወት ምቹ ሆኖ መቀጠል መተማመኛ ያጣ፣ የሰው ልጅ የፈጠረው ሥልጣኔ ራሱ የጥፋቱ የዕልቂት መሣሪያና ምክንያት እየሆነ ነው ተብሎ ከታወጀ ቆይቷል፡፡ ከዚህ የበለጠ መጀመሪያ የመቀመጫዬን የሚባል ቀዳሚ ነገር አለ ወይ! መልስ ሊሰጠው የሚገባ ጥያቄ ነው፡፡ ሌላም በዚህ አጋጣሚ መነገር ያለበት ጉዳይ አለ፡፡ የአገራችን የኢንቫይሮመንት ሕግ፣ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን ከማፅደቅና የአገር ሕግ አካል ከማድረግ ጋር መልካም አጀማመርና ይዘት ያለው እንደግ  ተመንደግ የሚባል፣ በተግባርና በአፈጻጸም እየተፈተሸ ሊዳብር የሚገባውና በርታ ግፋ ገና ነው የሚባል ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የአገሪቱ የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር ሕግ፣ ከመነሻው ከሚገርም መንደርደሪያ ይነሳል፡፡ ‹‹አንዳንድ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ጥረቶች ልማቱን የሚቀለብስ ጎጂ አካባቢያዊ ተፅዕኖ ሊያስከትሉ የሚችሉ በመሆናቸው፣ በአጠቃላይ አካባቢን መጠበቅ፣ በተለይም የሰውን ጤንነትና በጎ ሁኔታ፣ እንዲሁም የህያዋንን ደኅንነትና የተፈጥሮን ሥነ ውበት ማቆየት የሁሉም ተግባርና ኃላፊነት በመሆኑ…›› ብሎ ይጀምራል፡፡ ከዚህ ላይ በመነሳት ደጋግመን የምናነሳውን የምድራችንን ለሕይወት ምቹ ሆኖ መቀጠልን አደጋ ላይ የጣለውን የአካባቢን ብክለት ቁጥጥርን ይዘረጋል፡፡ ለዚህ ዓላማ ከሌሎች መካከል ለምሳሌ ‹‹በካይ›› እና ‹‹ብክለት››ን ይተረጉማል፡፡ በካይ ማለት ፈሳሽ፣ ጠጣር፣ ወይም ጋዝ የሆነ በቀጥተኛ ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ

ሀ) ያረፈበትን የአካባቢ ክፍል ጥራት በመለወጥ ጠቀሜታ የመስጠት አቅሙን የሚያጓድል ወይም፣

ለ) በሰው ጤና ወይም በሌላው ሕያዋን ላይ ጉዳት የሚያደርስ ወይም ሊያደርስ የሚችል መርዝን፣ በሽታን፣ ክርፋታን፣ ጨረርን፣ ድምፅን፣ ንዝረትን፣ ሙቀትን ወይም ሌላ ክስተቶችን የሚያመነጭ ማንኛውም ነገር ነው ይላል፡፡

ብክለት ማለት ደግሞ በሕግ የተደነገገን ግዴታ ማዕቀብ ወይም ገደብ ጥሶ የማንኛውንም አካባቢ ክፍል ቁሳዊ፣ ጨረራዊ ሙቀታዊ፣ ንጥረ ነገራዊ፣ ሥነ ሕይወታዊ፣ ወይም ሌላ ባህሪን በመለወጥ የተፈጠረ በሰው ጤና ወይም በጎነት ወይም ደግሞ በሌሎች ህያዋን ላይ አደገኛ የሆነ ወይም አደገኛ ሊሆን የሚችል ሁኔታ ነው ይላል፡፡ በዚህ መሠረት ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የብክለት ቁጥጥርን ሥርዓት ይዘረጋል፡፡ ስለአደገኛ ቆሻሻ፣ ኬሚካልና ጨረር አመንጪ ቁስ፣ ስለከተማ ቆሻሻ አያያዝ ይደነግጋል፡፡ በዚህ ውስጥ ይበልጥ የሚገርመው በሕጉ የተቋቋመው የመክሰስ መብት ይዘት ነው፡፡ በዚህ መሠረት አካባቢያዊ ጉዳይ በሚመለከት ረገድ፣ ምድራችን ለሕይወት ምቹ ሆነ የመቀጠሏን ነገር በተመለከተ ማንም ሰው፣ አንተ ደግሞ ምን አገባህ ሳይባል የመክሰስ መብት አለው፡፡ የመክሰስ መብት የሚደነግገው የሕጉ አንቀጽ 11፣

1) ነገሩ የሚመለከተው መሆኑን ማስረዳት ሳይጠበቅበት ማንኛውም ሰው በአካባቢ ላይ ጉዳት አድርሶ ወይም ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ተግባር እየፈጸመ ነው በሚለው በማንኛውም ሰው ላይ ለባለሥልጣኑ (ለአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ወይም ለሚመለከተው የክልል የአካባቢና የተፈጥሮ ሀብትና ጥበቃ) ቅሬታ የማቅረብ መብት አለው፡፡

2) ባለሥልጣኑ ወይም የሚመለከተው የክልል የአካባቢ ጥበቃ መሥሪያ ቤት በሰላሳ ቀናት ውስጥ ውሳኔ ካልሰጠ ወይም ቅሬታ አቅራቢው በወሰነው ካልተስማማ፣ ውሳኔው ከተሰጠበት ወይም የሚሰጥበት የጊዜ ገደብ ካለፈበት ቀን አንስቶ በስልሳ ቀናት ውስጥ በፍርድ ቤት ክስ መመሥረት ይችላል፡፡ እና የኢንቫይሮመንት ጉዳይ፣ ደግሞ አንተ ማን ነህ? ምንህ ተነካ? የማይባልበት ሁሉምና ማንም ሰው ተነስቶ ያገባኛል ባይነቱን በተግባር የሚያረጋግጥበት የምድራችን ለሕይወት ምቹና ጤናማ ሆኖ የመቀጠል ጉዳይ ነው፡፡ ይህን በመሰለ ጉዳይ ሌላው ቀርቶ ዜግነትን እንኳን በማይጠየቅ፣ ኢትዮጵያዊ ነህ ወይ የሚባል ጥያቄ በማያስከትል የኢንቫይሮመንት የአገር፣ የዓለምና የኃላፊነታችን ጉዳይ ላይ ነበረ የተባለው የጋዜጠኞች ማኅበር አለ? የሚለው ጥያቄ መልስ ቢያጣ ቢያንስ ቢያንስ በጣም ይገርማል፡፡ ለክርክር፣ ለእሰጥ አገባ ጉዳይ ሳይሆን ለሚዲያ ሚና፣ ለአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ሲባል መልስ ሊሰጠው የሚገባው ጥያቄ ነው፡፡

በዚህ የኢንቫይሮመንት ዘርፍ ውስጥ ከሕገ መንግሥቱ የሚጀምርና በዚህም የሚቃኝ ሕግ አለ፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 44 በመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ዝርዝር ውስጥ የአካባቢ ደኅንነት መብትን (Environmental Right) ይደነግጋል፡፡

  • ሁሉም ሰዎች ንፁህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት አላቸው፡፡
  • መንግሥት በሚያካሂዳቸው ፕሮግራሞች ምክንያት የተፈናቀሉ ወይም ኑሮአቸው የተነካባቸው ሰዎች ሁሉ በመንግሥት በቂ ዕርዳታ ወደ ሌላ አካባቢ መዘዋወርን ጨምሮ ተመጣጣኝ የሆነ የገንዘብ ወይም ሌላ አማራጭ ማካካሻ የማግኘት መብት አላቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ አሥር የብሔራዊ ፖሊሲ መርሆዎችና ዓላማዎች ዝርዝር የአካባቢ ደኅንነት ጥበቃ ዓላማዎችንም ያካትታል፡፡ እነዚህ ዓላማዎች፣

1) መንግሥት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንፁህና ጤናማ አካባቢ እንዲኖረው የመጣር ኃላፊነት አለበት፡፡

2) ማንኛውም የኢኮኖሚ ልማት ዕርምጃ የአካባቢውን ደኅንነት የሚያናጋ መሆን አለበት፡፡

3) የሕዝብን የአካባቢ ደኅንነት የሚመለከት ፖሊሲና ፕሮግራም በሚነድፍበትና ሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ የሚመለከተው ሕዝብ ሁሉ ሐሳቡን እንዲገልጽ መደረግ አለበት፡፡

4) መንግሥትና ዜጎች አካባቢያቸውን የመንከባከብ ግዴታ አለባቸው ይላሉ፡፡

በእነዚህ ድንጋዎች ላይ የአንቀጽ 44 የአካባቢ ደኅንነት መብትና የአንቀጽ 92 የአካባቢ ደኅንነት ጥበቃና ዓላማዎች ድንጋጌዎች የሚገኙበት ምዕራፎች ምሽግ ያደረጉትን የሕገ መንግሥቱን ፍጥርጥርና መዋቅር ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ከእነዚህ የመብትና የዓላማ/መርህ ድንጋጌዎች ጋር የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 13/2 እና የአንቀጽ 85/1 ከቁጥር ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ሁለቱም አንቀጾች የእያንዳንዱ ምዕራፍ (የምዕራፍ ሦስት የመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች የምዕራፍ አሥር የፖሊሲ መርሆዎችና ዓላማዎችም ምዕራፍ) መግቢያዎች ናቸው፡፡ ይህን ሁሉ የምዘረዝረውና እዩልኝ ስሙልኝ የምለው ኢንቫይሮመንትና የፕሬስ ነፃነትን ዛሬ ‹‹ድንገት›› 2024 የዓለም አቀፉ የፕሬስ ነፃነት ቀን ላይ ‹‹መንገድ›› ላይ የተገናኙ ሳይሆን፣ ሲጀመር አብሮ ተጓዦች፣ ተጓዳኞች መሆናቸውን፣ በማኅበር መደራጀትና የፕሬስ ነፃነት መብት ለየቅል ሳይሆኑ አንዱ ለሌላው ግፊት እየሰጡ የሚፋፉ የሚተጋገዙ መሆናቸውን፣ ይልቁንም ቀደም ሲል እንደተባለው መጀመሪያ የመቀመጫዬን ማለት የጋዜጠኞች የሚዲያው የጥበብ መጀመሪያ መሆኑን ለመጠቆም ነው፡፡

ሐሳብን በነፃ የመግለጽና የፕሬስ ነፃነት የሁሉም መብትና ነፃነቶች፣ የመብትና የነፃነቶቻችን ሁሉ ፊታውራሪና ዘብ ጠባቂ ነው ብለናል፡፡ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ማንም የሚለግሳቸው፣ የሚሰጣቸው አይደሉም፡፡ በሰውነታችን፣ ሰው በመሆናችን ብቻ የምናገኛቸው ናቸውም እንላለን፡፡ በዚህ ረገድ የሚሰጥም የሚቀበልም የለም ማለት ሕግና ሥርዓት አያስፈልግም ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም እነዚህ መብቶችና ነፃነቶች የሕግና የሥርዓት መተማመኛና ጥበቃ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ መብቶቻችንን ከአንድ ወይም ሌላ መንግሥት መልካም ፈቃድ፣ ከእርጥባን በዘለለና ከጉልበተኛ/አመፀኛ ጥቃት ነፃ በሆነ ደረጃ መኖር ላይ እንድንደርስ፣ ይህንንም ማፅናት እንድንችል ሕግና ሥርዓት መንገንባት፣ እዚህ ውስጥ መታገል ይገባናል፡፡ ሁልጊዜምና ምንጊዜም ኧረ በሕግ የምንለውም ለዚሁ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...