Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከተገነባ ዘጠኝ ዓመታትን ያስቆጠረውና ተዘግቶ የሚገኘው የቦንጋ ብሔራዊ የቡና ሙዚየም የምክር ቤት...

ከተገነባ ዘጠኝ ዓመታትን ያስቆጠረውና ተዘግቶ የሚገኘው የቦንጋ ብሔራዊ የቡና ሙዚየም የምክር ቤት አባሉን አስቆጣ

ቀን:

የከፋን ሕዝብ ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ቆጭቶ ገብረ እየሱስ፣ በ2000 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ በ2007 ዓ.ም. ግንባታው የተጠናቀቀውና ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ያለአገልግሎት ተዘግቶ የሚገኘው ‹‹የቦንጋ ብሔራዊ የቡና ሙዚየም›› ጉዳይ በሚመለከት ቁጣቸውን ገለጹ፡፡

አባሉ ከቦንጋ ብሔራዊ ቡና ሙዚየም ጋር በተገናኘ ጥያቄ አለኝ ሲሉ አፈ ጉባዔው ታገሰ ጫፎ ‹‹ተነስቷል›› ብለው ለማቋረጥ ሲሞክሩ ‹‹የከፋ ሕዝብ መስማት ስላለበት ከመነሻው ታሪክ ጀምሮ ለዚህ ቤት ማብራራት አለብኝ፡፡ አይሰማም ካላችሁም ልተወው እችላለሁ፡፡››

‹‹የከፋን ሕዝብ ወክዬ ይኼን ጉዳይ እንዳብራራ ዕድሉ ይሰጠኝ›› በመጨረሻ አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ‹‹ቀጥል›› ካሉ በኋላ አቶ ቆጭቶ ቀጠሉ፡፡ ይህ ብሔራዊ ሙዚየም የከፋን የቡና መገኛነት ታሳቢ በማድረግ በሚሊኒየም መግቢያ በ2000 ዓ.ም. እንዲሠራ ዕድሉ ተሰጠ፡፡ በ2000 ዓ.ም. የወቅቱ ፕሬዚዳንት ነፍስሄር ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የመሠረት ድንጋይ አስቀመጡ፡፡ ግንባታው ተጠናቆ በ2007 ዓ.ም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተገኙበት ተመረቀ፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ ሐሳብ እየተወለደ ነው፡፡ ታሪክ ወደፊት እንጂ እንዴት ወደኋላ ይሄዳል? ይህ ሙዚየም ከተመረቀ በኋላ እስከዛሬ ለዘጠኝ ዓመት ተዳፍኖ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ ይህም የከፋን ሕዝብ በከፍተኛ ቁጭትና ምሬት ውስጥ ያስገባ አጀንዳ ነው፡፡ ከዚህ ተነስተን እኛም አቋም እንይዛለን፡፡ የእኛ ምርት ተቀባይነት ባላገኘበት ሁኔታ አብሮ ለመቀጠል እንቸገራለን፡፡ እኛ እዚህ ምክር ቤት ከገባንበት ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ጊዜያት የሕዝብ ውክልና ስንወስድ ለእርሶ (ለ/ወሮ ናሲሴ ጫሊ) መሥሪያ ቤት ለቱሪዝም ሚኒስቴር አምስት ጊዜ በደብዳቤ ጥያቄ አቅርበናል፡፡ ጥያቄው ግን ተቆርጦ እየወጣ ነው ያለው፡፡ በጣም ነው የማዝነው፡፡ የዛሬ ዓመት የደቡብ ምዕራብ ክልል ሪፖርት እዚህ ቤት ሲቀርብ፣ ይህንን ጉዳይ ስናነሳ ምላሽ ሳይሰጡን ነው የወጡት፡፡ እርስዎም እየተባበሩ ነው፡፡ ምን ማለት ነው? የአንድ ኢትዮጵያ ሕዝቦች አካል ከሆንን በጋራ በእኩልነት ልታስተባብሩንና ልትመሩን ይገባል፡፡ የከፋ ሕዝብ ይኼን ጉዳይ አይቀበልም፡፡ እኔም እንደ ከፋ ሕዝብ ተወካይ አልቀበልም፡፡ የራሳችንን አቋም የምንይዝበት ጉዳይ መሆኑን እንድታውቁት፡፡ ቡና በዓለም የተገኘው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከፋ ዞን ዴቻ ወረዳ ማክራ ቀበሌ ‹‹ቡን›› በተባለ መንደር ነው፡፡ ይኼንን አስምራችሁ እንድትይዙት እንፈልጋለን፡፡ በጫና ውስጥ ሕዝቡ ታፍኖ የሚቀጥልበት ሁኔታ ስለሌለ እንድታውቁትና እንድትይዙት እፈልጋለሁ፤››

የቱሪዝም ሚኒስትሯ ናሲሴ ጫሊ በሰጡት ምላሽ የቱሪዝም ሚኒስቴር የተሰጠው ኃላፊነት ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ማስተዋወቅና መሸጥ ነው፡፡ ከዚያም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች እንዲገኙ ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያን እንደ አገር ነው የሰው ዘር መገኛ ብለን የምናስተዋውቀው፡፡ ቡናን በተመለከተ የቡና መገኛ ሰንሰለት (Coffee Belt) አለ፡፡ የቡና መገኛ ብለን የምናስተዋውቀው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከፋን፣ ጂማንና ሌሎችም አካባቢዎች ነው፡፡ ስናስተዋውቅ ኢትዮጵያን ነው እንደ ቡና መገኛ የምናስተዋውቀው፡፡ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት (National Consensus) ላይ መድረስ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ነው፡፡ ይህንን ለመፍታት ለቱሪዝም ሚኒስቴር የተሰጠ ሥልጣን የለም፡፡ የቱሪዝም ሚኒስቴር በአገሪቱ የሚገነቡ ሙዚየሞች ስታንዳርድ ጠብቀው እንዲሠሩ ያደርጋል፡፡ ድጋፍ ለማንኛውም ሙዚየም እናደርጋለለን፡፡ ያልተፈቱትን ችግሮች በምን መልኩ መፍታት ይቻላል ለሚለው ጥያቄ ጥናት ያስፈልጋል፡፡ እንደ አገር ያንን ጥያቄ በጥናት ላይ በመመርኮዝ የምንመልስ ይሆናል፡፡ አሁን ባለው ግን ኢትዮጵያን የቡና መገኛ ብለን ነው የምናስተዋውቀው፡፡ ልዩ ቦታውን (Specific) አንጠቅስም፡፡ ከዚያ በተረፈ ያሉት ጉዳዮች በብሔራዊ መግባባት መፈታት አለባቸው፡፡ እኛ ጥናቱን አድርገን ለሚመለከተው አካል እናቀርባለን፡፡ ውሳኔ እንዳገኘ ድጋፋችንን የምንሰጥ ይሆናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...