Wednesday, June 12, 2024

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት ከበፊት ጀምሮ ውስብስብ ከመሆኑ የተነሳ፣ ሞቅና ቀዝቀዝ የሚለውም በተለያዩ ሁነቶች ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ሁለቱ አገሮች ዘርፈ ብዙ የሆነው ውስብስብ ግንኙነታቸው ዲፕሎማሲን፣ ኢኮኖሚንና ጂኦ ፖለቲካን ያካተተ ስለሆነ አሜሪካ ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ እንደ ሁነኛ አጋሯ ታያታለች ይባላል፡፡ በሌላ በኩል የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብቶችና የብሔር ጠቀስ ውጥረቶች ደግሞ ንትርክ አዘል ናቸው፡፡ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ የፖሊሲ ንግግር የሚያንፀባርቀውም፣ አገራቸው ቅድሚያ ለምትሰጣቸውና ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ እንደሆነ ነጋሪ አያሻም፡፡ ለዚህም ሲባል ሰላም፣ ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች ሁሌም ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣቸዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡

መንግሥት የአምባሳደሩን ንግግር በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደ መግባትና ለተቀናቃኞቹ ዕውቅና እንደ መስጠት ወስዶ መረር ያለ መግለጫ ሲያወጣና ሉዓላዊነትን እንደ መዳፈር ሲቆጥረው፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ወይም መካረር ሊፈጥር ይችላል፡፡ ከልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ጋር እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት ሊታከልበት ይገባል፡፡ የአምባሳደሩ ንግግር ምናልባትም የአገር ውስጥ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር የሕዝብ አስተያየትን በማዛባት፣ ሊኖር የሚገባውን ንግግር ወይም ክርክር ሌላ ገጽታ በማላበስ፣ እንዲሁም የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችን በማነሳሳት ችግር ሊፈጥር እንደሚችል መንግሥት ሊያስብ ይችላል፡፡ ከአገር ቤት አልፎም በአፍሪካ ቀንድም ጭምር አሉታዊ ነገር ሊያስከትል እንደሚችል ሥጋት ይኖራል፡፡ አንድ ነገር መረሳት የሌለበት ግን በአምባሳደሩ አንደበት የተነገረው የአሜሪካ መንግሥት አቋም እንደሆነ መገንዘብ ነው፡፡

በዚህ ላይ በመመሥረት መንግሥት ቁጣ ያዘለ መግለጫው እንዳለ ሆኖ፣ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ገንቢ ውይይት ማድረግን ተመራጭ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ የዲፕሎማሲው ገጽታ መቼ እንደሚቀየርና ምን ዓይነት ዓውድ እንደሚይዝ ለመገመት አዳጋች በሆነበት በዚህ ጊዜ፣ ብልኃትና ብልጠትን አማራጭ አድርጎ መንቀሳቀስ ተመራጭ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁለቱን ወገኖች በሚያሳስቧቸው ጉዳዮች ላይ ግልጽ የግንኙነት ዘዴ መመሥረት ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም የጋራ ዕይታዎች እንዲኖሩ የሚያስችሉ ዓውዶችን በመፍጠር፣ መፍትሔዎችን ለማፈላለግ የሚረዱ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት በዚህ የፖሊሲ ንግግር ያስተላልፈው መልዕክት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ለኢትዮጵያ የሚኖረው ፋይዳና የወደፊት ጥቅም ቢሊካ ይመረጣል፡፡ አሜሪካ ሁሌም ጥቅሟን ለማስከበር የምትሄድበት ርቀት ከብዙ አገሮች ጋር ቢያላትማትም፣ አገሮቹ ግን አቅማቸውን እየመዘኑ ነው ግንኙነታቸውን ጠበቅ አድርገው የሚይዙት፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ከበፊት ጀምሮ እስካሁን እንደ ችግር የሚነሱ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ዋናው መሠረታዊ በሚባሉት ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ራስን አለመቻል ነው፡፡ ለኢኮኖሚ ጥገኝነት የተጋለጠ አገር የለጋሾቹ ሽንቆጣም ሆነ ግልምጫ አይቀርለትም፡፡ ኢትዮጵያም በርካታ የተፈጥሮና የሰው ኃይል ፀጋዎች እያሏት ለውጭ ተፅዕኖ የተጋለጠች ናት፡፡ ውስጣዊ ፖለቲካው የፈጠረው ሽኩቻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰበት፣ ኢትዮጵያውያንን በዓለም የምፅዋት ጠባቂነት ተርታ በግንባር ቀደምነት በማሠለፍ ተወዳዳሪ የለውም፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን ልዩነቶቻቸውን በሠለጠነ መንገድ ፈር አስይዘው ይህንን መርገምት መቀየር ሲገባቸው፣ አሁንም ከዚያ አሳዛኝ አረንቋ ውስጥ መውጣት ተስኗቸው የሕዝባችን ሰቆቃ የበለጠ እየጨመረ ነው፡፡ በሰከነ መንገድ ተነጋግረው ዘለቄታዊ ሰላም በመፍጠር ኢትዮጵያን ሀብታም የማድረጊያ ሥልቶችን በጋራ ቢነድፉ፣ ይህችን የመሰለች አገር የድህነት መጫወቻ አትሆንም ነበር፡፡

ሌላው መቼም ቢሆን መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ለሕግ የበላይነት መሰጠት ያለበት ክብር ነው፡፡ አገርን ከሚያስተዳድረው መንግሥት ጀምሮ የፖለቲካ ኃይሎችና የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ፣ ለሕግ የበላይነት መስፈን የራሳቸውን ሚና ካልተጫወቱ በስተቀር ችግሮች ተባብሰው ይቀጥላሉ፡፡ ሕግ ሲከበር ከጉልበት መፈታተሽ ይልቅ ተቀምጦ መነጋገር ባህል ይሆናል፡፡ ሕግና ሥርዓት ሲኖር ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ቦታ አይኖራቸውም፡፡ በሕግ የበላይነት መተዳደር የሚበጀው ለግጭት የሚያነሳሱ ሁሉንም ልዩነቶች ወደ ጠረጴዛ ውይይት ለማምጣት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሳይከበር ሲቀር እንዳሻ የመሆን ፍላጎት ያይልና ሁሉም በየአቅጣጫው ጦር ነቅናቂ ይሆናል፡፡ ጦር ነቅናቂነት እየበዛና ትርምሱ እየተስፋፋ ሲቀጥል፣ ለውጭ ጣልቃ ገብነት የሚጋብዙ ሥጋቶች ይፈጠራሉ፡፡ ዲፕሎማሲውም ሆነ ሌላው ጉዳይ ሁሉ አመኔታ እያጣ መላተም የዘወትር ሥራ ይሆናል፡፡

መንግሥት አሜሪካም ሆነች የአውሮፓ ኅብረት፣ ወይም ሌሎች የመብት ተቋማት መግለጫ ባወጡ ቁጥር መልስ ከመሰጣጠት ይልቅ ቤቱን ጥርት አድርጎ ቢያፀዳ ይበጀዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና የአገር ጉዳይ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር አሳታፊና አካታች ንግግርና ድርድር እንዲጀመር ጥርጊያውን ማመቻቸት፣ አሠራሩ ግልጽና ተጠያቂነት እንዳለበት በተግባር ማሳየት፣ ለንግግር ነፃነትና ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ተገቢውን ዋስትና መስጠት፣ የተለየ ሐሳብና ዕይታ ያላቸው ወገኖችን ለማስተናገድ ቁርጠኝነት ማሳየትና የመሳሰሉት ላይ ቢያተኩር ይመረጣል፡፡ በተቃውሞው ጎራ ያሉትም ከአፈንጋጭነት ይልቅ ሰላማዊውን መንገድ ለመከተል ፈቃደኝነት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን አሸናፊ የማይኖርበት ትንቅንቅ ትርፉ ድቀት እንደሆነ ረጅሙ የታሪክ ጉዞ ያስረዳል፡፡ ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት እንዳይጎድለው ቢደረግ የምታተርፈው አገር ናት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...

የ‹‹ክብር ዶክትሬት›› ዲግሪ ጉዳይ

በንጉሥ ወዳጅነው ‹‹የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ግልጽ የሆነ መመርያ እስኪወጣ ድረስ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...

ከግጭት አዙሪት ውስጥ የሚወጣው በሰጥቶ መቀበል መርህ ነው!

የኢትዮጵያን ሰላም፣ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ማዕከል በማድረግ መነጋገር ሲቻል ለጠብ የሚጋብዙ ምክንያቶች አይኖሩም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚደረጉ ክንውኖች በሙሉ ከጥፋት የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ...