Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜና‹‹ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው እንዳይመለሱ የሚያደርጉ ችግሮችን መፍታት የፌዴራል መንግሥቱ ኃላፊነት ነው›› ...

‹‹ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው እንዳይመለሱ የሚያደርጉ ችግሮችን መፍታት የፌዴራል መንግሥቱ ኃላፊነት ነው›› ሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት

ቀን:

በአብረሃም ተክሌ

በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል በተደረሰው የጋራ ስምምነት ማዕቀፍ መሠረት፣ ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው እንዳይመለሱ የሚያደርጉ ችግሮችን መፍታት የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ አካላት ኃላፊነት መሆኑን፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደ አስታወቁ፡፡   

ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይህንን የተናገሩት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ግንቦት 11 2016 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ሲሆን፣ በመግለጫቸው ሁለቱም ወገኖች የተስማሙባቸው ጉዳዮች እንዳሉና በተደረሰው ስምምነት መሠረት የጋራ ማስፈጸሚያ ዕቅድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

የተዘጋጀው ዕቅድም የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ አካላት ተግባር ሕገወጥ አስተዳደርን ማፍረስ፣ ሕገወጥ የታጠቁ ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ወደ ቦታቸው መመለስን በዋናነት የያዘ ነው፡፡

ሌተና ጄኔራል ታደሰ ወቅታዊ ጋዜጣዊ መግለጫው የሚሰጥበትን ምክንያት ሲገልጹ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ሚያዚያ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሰጠው ይፋዊ መግለጫና ከትግራይ ክልል ጦርነት ጋር በተያያዘ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስና በኃይል የተያዙ ቦታዎችን አመላለስ በሚመለከት በአፍሪካ ኅብረት ፓናል ታዛቢዎች ባሉበት በተደረገው ስምምነት ላይ በተደረሱና ባልተደረሱ ጉዳዮች ላይ በሒደት ለመፍታት ተስማምተዋል፡፡ በወቅቱ በተደረሰው የማስፈጸሚያ ዕቅድ መሠረት እስካሁን ምን እንደተሠራና ምን ለመሥራት እንደታሰበ ለመግለጽ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ዕቅዱን የመፈጸምም ሆነ የማስፈጸም ኃላፊነት የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ አካላት ንደነበር ገልጸው፣ በተላለፈው የፖለቲካ ውሳኔ መሠረት ዕቅዱን ለመተግበር የትግራይ ክልል የፀጥታ አካላት ኃላፊነት እንደተሰጣቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡

‹‹በፖለቲካ ውሳኔ በተደራዳሪዎች መካከል ስምምነት ተደርሷል፡፡ የፕሪቶሪያ ውሳኔን መሠረት በማድረግ አተገባበሩ ላይ ያሉ ሁኔታዎች ተገምግመው ችግሮችን በመፍታት በተሟላ መንገድ ለመተግበር አጠቃላይ የሆነ ስምምነት ተደርሷል፡፡ በሦስትዮሽ ኮሚቴ ማለትም የአማራ ክልል፣ የትግራይ ክልልና የፌዴራል መንግሥትን ያካተተ ስምምነት ነው የተደረሰው፤›› ብለዋል፡፡               

‹‹የተፈናቀሉት ዜጎች ወደ ቤታቸው እንደሚመለሱ ጥርጥር የለውም፤›› ባሉበት መግለጫቸው፣ የስምምነቱ ትግበራ በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት ተፈናቃዮች የዘንድሮው ክረምት ከመድረሱ በፊት ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ እየተሠራ እንደሆነ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተፈናቃዮቹን በማዘጋጀት የፀጥታ አካላትን አስተባብሮ መሥራት እንደሚጠበቅበትም ጨምረው ገልጸዋል።

‹‹በዘንድሮ ክረምት ተፈናቃዮቹ ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ እየሠራን ሲሆን፣ በስምምነቱ ማዕቀፍ መሠረትም የተፈናቀሉ ወገኖቻችን በእርግጠኝነት ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፤›› ብለዋል፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቱ በመቀጠል በመሠረታዊነት ወደ ነበሩበት የሚመለሱት ከቀዬአቸውና ከቤታቸው የተፈናቀሉት ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አብዛኞቹን የመለየት ሥራ እንደተጠናቀቀና ለጊዜው አድራሻቸው ያልተገኙ ቢኖሩም አመላለሳቸውን በሚመለከት በተዘጋጀው ዕቅድ መሠረት መዘጋጀታቸውን ጨምረው አስረድተዋል፡፡ ጄኔራሉ በተጨማሪ የክልሉ ኃይሎች ካሉበት ቦታ የሚወጡበትን መንገድና እንዴት መውጣት እንዳለባቸው የሚከናወነው ሥራ እንዳለቀም ገልጸዋል፡፡

‹‹በእኛ በኩል የማስፈጸሚያ ዕቅዱ ተግባራዊነት ላይ እንቅፋት የሚሆኑትን ነገሮች በሙሉ አስተካክለን ጨርሰናል፤›› ብለዋል፡፡    

በጊዜ ሰሌዳው መሠረት የማስፈጸሚያ ዕቅዱን ለማከናወን መዘግየቶች እንዳሉ የጠቀሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሕገወጥ ሆኖ የተመሠረተውን አስተዳደርና ታጣቂ ኃይል የማፍረስ፣ እንዲሁም ፀጥታ የማስፈንና ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራ የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ አካላት ተልዕኮ ሆኖ ሳለ፣ እሰካሁን ድረስ ግን ከፌዴራል መንግሥት የፀጥታ አካላት በኩል የተከናወነ ሥራ የለም ብለዋል፡፡

‹‹ስምምነት እንደ ማንኛውም ስምምነት የአተገባበር እንቅፋቶች ቢኖሩትም፣ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት አድርገን ነው ዕቅድ ያወጣነው፡፡ አሁን ተመልሶ ዕቅዱን መተግበርና ችግሮቹ ይቃለላሉ የሚል ግምት ነው ያለን፡፡ ችግሮቹን የማቃለል ሥራ ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ስለዚህ የፌዴራል መንግሥት እነዚህን ችግሮች እንቅፋት እንዳይሆኑ የመፍታት ኃላፊነት አለበት፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተና ጄኔራል ታደሰ ሚያዚያ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ፣ ግንቦት 30 እና ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ቀነ ገደብ ማድረጋቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡ በአዲሱ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የቀድሞ ታጣቂዎችን ሙሉ በሙሉ ትጥቅ የማስፈታት፣ የትግራይ ክልልን ከጦርነት በፊት የነበሩትን ወሰኖች መልሶ የማቋቋምና ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተፈናቃዮችን ወደ ቤታቸው የመመለስ ሥራ ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ እንደሚቀረው ጨምረው መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...