Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየድህነት ቅነሳ ሥራ ወቅታዊና ሳይንሳዊ መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ

የድህነት ቅነሳ ሥራ ወቅታዊና ሳይንሳዊ መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ

ቀን:

በኢትዮጵያ በድህነት ምጣኔ ቅነሳ ላይ የሚከናወኑ ሥራዎች ከተለመደው ባህላዊ ዘዴ ተላቀው፣ በሳይንሳዊ ጥናቶች መደገፍ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ኦክስፎርድ ፖሊሲ ማኔጅመንት የተሰኘውና በእንግሊዝ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ከአሥርት ዓመታት በፊት የተመሠረተው ተቋም፣ ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ድህነትን የተመለከቱ መረጃዎችና ሳይንሳዊ የምርምር ውጤቶችን መደገፍ ላይ ያተኮረ ውይይት ማክሰኞ ግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡

በእንግሊዝ መንግሥት የሚደገፈው ተቋም ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ላይ ትኩረት አድርጎ ድህነትና ማኅበራዊ ጥበቃን የተመለከቱ ጥናቶችን ለሚያካሂዱ አካላት ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን፣ በመጪው ሐምሌ 2016 ዓ.ም. በድህነት ቅነሳ ላይ ለሚሠሩ የአገር በቀል አጥኚዎችና ተመራማሪዎች የሚያደርገውን ድጋፍ ይፋ እንደሚያደርግ፣ የኦክስፎርድ ፖሊሲ ማኔጅመንት የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ሚካኤል አድነው ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

አጥኚዎች በድህነት ቅነሳ ላይ የሚያደርጉትን የምርምር ውጤት ለቀጣይ ፖሊሲ ግብዓት እንዲሆን ታስቦ የሚዘጋጅ ነው ብለዋል፡፡

በመድረኩ በድህነት ላይ የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች ጊዜውንና ጥራቱን በጠበቀ መንገድ ማደራጀት ለመንግሥት የወደፊት አገራዊ ዕቅዶች አፈጻጸም ክትትልና ግልጽነት ወሳኝ ስለመሆናቸው የተናገሩት፣ በዓለም ባንክ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያ ሴዛር ካንቾ ናቸው፡፡

የዜጎች ወቅታዊ የአኗኗር ሁኔታ፣ እያገኙ ያሉት አገልግሎት፣ የሚፈልጉት የሥራ ዓይነት፣ የተዘረጋላቸውን የመሠረተ ልማት ጨምሮ በአጠቃላይ ዘርፈ ብዙ ፍላጎታቸውን በመመልከትና የችግሩን መጠን በመረዳት የምርምር ሥራዎችን ማከናወን የድህነትን ሁኔታ በግልጽ ማሳየት ያስችላል ብለዋል፡፡

የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የነበሩ የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ አጠቃላይ አገራዊ የድህነት ምጣኔ ሪፖርት በመጪው አንድ ወር ውስጥ ይፋ እንደሚያደርግ አክለው ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተመራማሪ አምዲሳ ተሾመ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በድህነት ላይ የሚደረጉ ጥናቶችና የሚሰበሰቡ መረጃዎች ሊዋሀዱና ሊቀናጁ እንደሚገባ እንዲሁም በቀጣይ ለሚፈለጉ ሥራዎች ዋነኛ መሣሪያ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪ የድህነት ምጣኔን የመሳሰሉ ትልልቅ አገርን የተመለከቱ ጥናቶች ትንተና ብሔራዊ በሆነ ስታንዳርድ ውጤቱ ጥያቄ በማያስነሳ መንገድ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በተቋቋመ ገለልተኛ ካውንስልና በራሱ ባለሙያዎች ተደግፎ መሥራት የወደፊት ሥጋቶችን ይቀንሳል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ድህነት እንደቀነሰ ሲነገር መለኪያው ገቢ ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑን የተናገሩት ባለሙያው፣ ድህነትን የሚመለከቱ በርካታ ዘርፎችን አካቶ ጥናት ቢካሄድ ኖሮ ግን ቢያንስ 86 በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በእነዚህ ዘርፈ ብዙ መለኪያዎች በተለይም በትምህርት፣ በጤና፣ በውኃ፣ በፀጥታና በበርካታ መስኮች አካትቶ ለማየት ከተሞከረ ድህነቱ የከፋ እንደሚሆን፣ ይሁን እንጂ አሁን እንደሚሰማው ድህነት ቀንሷል ሲባል የዜጎችን ገቢ መሠረት ብቻ ያደረገ ከሆነ ሊያስኬድ ይችላል ብለዋል፡፡

በሰቆጣ ቃልኪዳን የፌዴራል ፕሮግራም ከፍተኛ ፕሮግራም ማኔጀር ሲሳይ ሲናሞ (ዶ/ር)፣ በድህነት ምክንያት ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናት የቀነጨሩ ናቸው ብለዋል፡፡

በሕፃናት ላይ መሥራት ካልተቻለና በተለይም በሕፃናት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ላይ ድህነት ምን ይመስላል የሚል የግብዓት ሰነድ ቀርቦ ችግሩ ካልተጠና፣ በየመድረኩ ድህነት ላይ ያተኮረ ስብሰባ ማካሄድ ፋይዳ የለውም በማለት ገልጸዋል፡፡

በመቀንጨር ምክንያት በየዓመቱ 55 ቢሊዮን ብር አገሪቱ እንደምታጣ አብራርተው የሕፃናት ሞት፣ የአምራች ኃይል መጥፋትና የድህነት አዙሪት ከመቀንጨር የሚመጣ አደጋ ነው ብለዋል፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ አማካሪና በኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ መምህር አበበ ሽመልስ (ፕሮፌሰር)፣ ድህነት የኢኮኖሚ ሥርዓቱ በቂ የሆነ ምርት ባለማግኘቱ የመጣ ነው ብለዋል፡፡ በምርት እጥረት ምክንያት በዚህ ጊዜ ችግርተኛ የሚባለው ሰው ጠዋት ለሥራ ወጥቶ ማታ ቤቱ የሚገባ መሆኑን በመግለጽ፣ ‹‹ይህ የሚያሳዝን ጉዳይ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የኢኮኖሚ አማካሪው እንደ መፍትሔ መወሰድ ያለበት የሚሉት ድህነት ውስጥ የሚያስገቡ ጉዳዮችን በተገቢው መንገድ መለየት፣ ከዚያም ከድህነቱ ወደ ተሻለ ሕይወት ለመሸጋገር የሚያስችሉ መሠረታዊ ጥናቶች ተከናውነው አስፈላጊ የፖሊሲ ዝግጅቶችን የማድረግ አስፈላጊነት አክለዋል፡፡

‹‹በአንዳንድ ቦታ ዕርቃኑን የወጣ ድህነት አለ፤›› ያሉት አበበ (ፕሮፌሰር)፣ አለመታደል ሆኖ የሽግግር ፖለቲካውና ጦርነቱ ድህነትን እየፈለፈሉት መሆናቸውን፣  በእዚህ ምክንያት ወደፊት የሄደውን ኢኮኖሚ ወደኋላ እየመለሱት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሚወጡ ፖሊሲዎች በተሟላ ሰነድና በጠንካራ መረጃ የተመረኮዙ እንዲሆኑ ፍላጎቶች መኖራቸውን የገለጹት ደግሞ፣ የእንግሊዝ ኪንግስ ኮሌጅ መሞህሯ ኤማንዳ ሌንሃርዶት ናቸው፡፡

የመረጃ አሰባሰቡ ባህላዊ ከሆነውና ከተለመደው አሠራር በተለየ መንገድ ሊታገዝ ይገባል ብለዋል፡፡ አንድ ጥናት የፖሊሲ ምንጭና መነሻ መሆን ካለበት ከተለመደውና የሆነ ቦታ ሄዶ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ አድርጎ ከሚደረግ ጥናት በተጨማሪ፣ ፈጣን በሆነ መንገድ ውሳኔ ለመስጠት የሚረዱ የምርምር ሥራዎችን በተለይም የሳተላይት ምልክቶችን፣ የሞባይል ኢንተርኔት ዳታና መሰል ዘመናዊ መሣሪያዎች መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ሳምንታዊ፣ ወርኃዊና እንደ አስፈላጊነቱ መረጃዎችን ከትላልቅ አገራዊ ጥናቶች በተጨማሪ ሥራ ላይ በማዋል፣ የድህነት ምጣኔን በመለየት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውንና አደጋ ውስጥ ያሉ ዜጎችን በቀላሉ መድረስ ያስችላል ብለዋል፡፡

በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የፖሊሲ አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ አስፋው፣ አሁን በሥራ ላይ ያለውና በመንግሥት ደረጃ የሚታወቀው አገራዊ የድህነት ምጣኔ አመላካች ጥናት በ2008 ዓ.ም. የተሠራ መሆኑንና ከዚያ ወዲህ የተከናወነ ጥናት አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...